Print this page
Saturday, 15 June 2013 11:46

እማይነትበዉ ስዉር-ስፌት

Written by  አብደላ ዕዝራ abdiezra@yahoo.com
Rate this item
(4 votes)

ክፍል ሁለት፥ በጥሞና ስለአራት ግጥሞች

፩ ሀገርህ ናት በቃ ! 

አያሌ ገጣሚያን ሀገር ስትፈካ፣ ሀገር ስትፋቅ፣ ገሃድ ሲገጣጠብ ወይም ሲያብረቀርቅ ግለሰቡ እኔ ምን አገባኝ የመሰለ ገለልተኝነት እንዳይጠናወተዉ ተቀኝተዋል:: ስለ አገር ያልፃፈ የአማርኛ ገጣሚ የለም:: ብዙዎቹ በፍቅር በናፍቆት፣ ጥቂቶቹ እየረገሟት፤ እንደ ወዳጅም እንደ ደመኛም:: ሆድ የባሰዉ፣ ያቄመ፣ ተገፍትሮ ዉስጡ ያመረቀዘ ለሱ <ሀገር> ምኑ ናት ? ያምፅ ይሆናል ወይም ይስለመለማል:: አገር ሲባል ግዑዙ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ፣ ባህሉ፣ ዕምነቱ፣ ወዳጅና ዘመድ ... ይጠራራሉ:: ስብሐት በ <አምስት ስድስት ሰባት> አጭር ልቦለዱ የገለፀዉ በርሱፈቃድ <... ሰሞኑን ስለ ክርስቶስ ስቅለት ትሰማላችሁ:: ግን ማነዉ ሰዉ ሆኖ ያልተሰቀለ? ማነዉ በልጁ ለቅሶ ያልተቸነከረ? ማነዉ በሚስቱ ሞት ያልተቀበረ? ... ከነልጆቹ ረሃብ ሲከታትፈዉ ለሀገርም ለስቅለትም ህሊናዉ ይሻክራል::

እንግዲህ ባለቅኔ የት ሆኖ? ገጠመኙ ምን ቋጥሮ ፃፈ ? የግጥሙ ተናጋሪ personna ንቃተ ህሊናዉ እንደነገሩ ነዉ ወይስ ተመስጧል ? ዘመነኛ ሂስ ፅሑፍን እንጂ የወቅቱን መንፈስና የባለቅኔዉን ግለታሪክ ማሰስ አያደፋፍርም:: ነቢይ ከአማርኛ ገጣሚያን የሚለየዉ አንድ-ሁለት ሳይሆን፣ በአገር ጉዳይ ከሃያ ግጥሞች በላይ መቀኘቱ ነዉ:: የኛ ሰዉ በአሜሪካ መፅሐፍ ልዩ ጣዕሙ ስለ አገር ቤት ትዝታ፣ ኑሮ፣ ህልም ... እያጠለለ ገፆቹ ርሰዉ ስላፈሰሱም ነዉ::
ግለሰብ እትብቱንና ስሩን የተቀማ ተንሳፋፊ እንዳይሆን ይሰጋል:: ሥነቃሉም <አገር አላት ይበሉኝ፣ ማህደረ ማርያም ቅበሩኝ> ሲል የስፍራ፣ የማንነት ጥያቄ ከአፈር ጋር ይቦካል:: ነቢይ “ባገር የመሸ ቀን፣ ሰዉ አገር አይነጋ // ማብቃቱ ታወቀኝ ሲደርስ አፈሯጋ” እንዳለዉ ነዉ:: ሰለሞን ደሬሳ በዘበተ እልፊቱ መግቢያ፣ ከጠፉበት ብዙ ግጥሞች < ... ሆዴን የምትበላኝ አንዲት በኤርትራ ነፃነት ማግስት የፃፍኳት ወለሎ ብቻ ናት::
...ታሪክን ለማበጠር የማትሞክር፣ አርበኝነት የማይጐድላት፣ ጀግና የማይፅፋት፣ የግል ሀዘኔ የተጫናት ወለሎ ብቻ ናት::> ብሏል፤ አገርም ፀፀትም ተሸራርበዋል:: በድሉ ዋቅጅራ በኤርትራ መገንጠል ማግስት <ለካስ መሬት እግር አለዉ!> እያለ በግጥሙ ተመስጧል:: [ፍካት ናፋቂዎች፥ 45]
“እንደ አላቂ ብጣሽ ጨርቅ፣ መርፌ ላይጠቃቅመዉ / እንደ ባልና ሚስት ጠብ፣ ገመና ላያግደዉ / አይሄድም ሲሉት ይሄዳል፤ ቅርብ ነዉ ሲሉት ይርቃል፤ ለካስ መሬት እግር አለዉ::” ብድግ ብሎ የሚኮበልል ስፍራ ያስደነግጣል:: ከመንደሩም ተፈናቅሎ ሀገሩ ዉስጥ ሌላ ቦታ የሚሰፍር ከባዕድ አገር የተሰደደ ይመስለዋል:: የቆሌ፣ የአድባር ዛፍ፣ የታቦት... ቁርኝት ነዉ::
ወጣት ገጣሚያን በሀገር ጉዳይ ዕምቅና ዉስብስብ መሆን ይደፍራሉ:: በዕዉቀቱ ሥዩም <የመፅዋተኛዉ አገር> በማለት ህሊናን ይቦጫጭራል:: “አገር ድንኳን ትሁን /ጠቅልዬ የማዝላት/ ስገፋ እንድነቅላት /ስረጋ እንድተክላት::” እንደ ሁኔታዉ የሚኮሩባት አሊያም የሚሸሽጓት ሀገር:: ኑረዲን ዒሳም በተነበበ ቁጥር ቀንበጥ ፍካሬ የሚለግስ ግጥም ተቀኝቷል:: “አንድ ትልቅ ሃገር፣ በትንሽ መንደር ላይ / ተጣጥፎ ተኝቶ / ሲጨናነቅ አየሁ፣ ለእግሮቹ መዘርግያ / ሽራፊ ቦታ አጥቶ::” አገርን ትንሽ ስፍራ ዉስጥ ማስጨነቅ ሳይበቃ <የክፉ ዘመን ህልም> በማለት ዋሲሁን በላይ አመረረ:: “አገሬን / ኮሮጆ ከትቼ / በምስማር መትቼ / ከቆጥ ላይ ሰቀልኋት፣ /ነግቶ ስፈልጋት/ መርዝ በበሉ አይጦች /ተበልታ አገኘኋት!” እንደ ፅላት ታቦት ዉስጥ መደላደል ያለበት ሀገር፣ ከጨርቅ ከቁርበት በሚስሰፋ የሆነ ዕቃ የሚቋጠርበት ኮሮጆ ዉስጥ ተሸብልሎ ጉድ ሆነ:: የሚያሳምም ርዕስና ግጥም ነዉ::
ነቢይ አገርን ከስደት፣ ከባይተዋርነትና ከናፍቆት እየነከረ ያስተዉላል:: ሆድ የባሰዉ ወይም ሩቅ አላሚ ቢሰደድ ሌጣዉን አይደለም፤ ትዝታዉን፣ ልጅነቱን፣ ፍቅርና ጥላቻዉን ከዉስጡ አምቆ ነዉ የተጓዘዉ - የነተበ ዘባተሎ ይመስል አወላልቆ አይሄድም:: ላለማስታወስ፣ በሌላ ጉዳይ መጠመድ ቢሞክር ትናንቱ ድቅን ይልበታል:: “ኧረ አንድ በሉት በበለስ፣ ይሄ የአገሬ አፈር ደሞ / ኋላ ረገጥከኝ እንዳይል፣ አጉል መንገዴ ላይ ቆሞ” ነቢይ በሁለት ሀይል እየተጐተተ፣ ስደት ቢደላዉም አገሩ እያባነነዉ ስለተሰቀቀ ግለሰብ ተቀኝቷል:: ማን ያስጥለዉ፣ ማን እንዲቀናዉ ይዘክረዉ? ለንባብ የተቀነበበዉ ግጥም “አገርህ ናት በቃ !” ቁጥር ሁለት ነዉ:: በቁጥር አንድ ጠበኞችን ይገላግላል:: “ይቺዉ ናት ዓለምህ፤ ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ // ልቧን አታዉልቃት አትጨቅጭቃት በቃ / አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረህ ንቃ” ቁጥር ሁለት ረቀቅ ይላል፤ መገላገል ሳይሆን መሳተፍ፣ ለጋራ የግልን መጋረድ፣ ትንሳኤን ማጣደፍ ይመስላል:: በሶስት አንጓ ሊከፈል የበቃ ግጥም ነዉ::

አንዳንዴ፤
አንጐሌን እንደዣንጥላ አጥፌ
አገሬን በወግ ሰልችቼ፣ ፍቅሯን ከልቤ አጠንፍፌ
ወደሷ የሚያደርሱኝን፣ መንገዶቼን ሁሉ አጥሬ
ሌላ ሌላ አገር አያለሁ::
አንድም አገሩን ገፍትሮ ባህር ለመሻገር የተነሳሳ፣ አንድም ለሀገር ያባዉን በጐ ስሜት ሆን-ብሎ ለማስተባበል የሚጣጣር፣ አንድም እርግጠኛ ለመሆን የሚታክት ሄደ-ቀረ የምንለዉ ተናጋሪ ጥርጣሬዉን ይናዘዛል:: < አንዳንዴ > ማለቱ ግን ሀገርን ቸል በሎ ለመራመድ የሰርክ ግፊት እንዳልሆነ ይጦቅማል፤ በአመዛኙ ዕርቅ ላይ ነዉ ወይም አላቄመም:: ማሰሮ ዘቅዝቆ የአገር ፍቅሩን ያፈሰሰ መስሎታል:: ይህ አንጓ የተናጋሪዉን መደናገር፣ በዕዉኑ ራሱን ከአገሩ እየጋረደ ለመገለል፣ በደመነፍሱ ግን ሰለቸዉ እንጂ አልተበደለምና መስቀለኛ መንገድ ላይ ዉል ጠፋዉ:: ሆኖም ቆዳዉ ስስ አይደለም:: ስንት የጋለ የእምባ ጠብታ ፈገግታን ያገነፍላል? ጥማት የሚያጋልጠዉ የምንጭ አሰሳ መሰለ:: ገና የሚጤን እሚያማክሩት ከልብ ዉስጥ የተሰነቀረ አንዳች ነገር ቀርቷል:: <ተስፋ ያልቆረጠ መነኩሴ ምናኔ ሲሄድ ሴቲቱን ይሰናበታል> የመሰለ ማቅማማት ነዉ:: ለመሄድም ለመቅረትም አንድ ድርጊት መከሰት አለበት::

አገሬ ግን፤ ...... እንደጌታ የስቅለት ቀን
በአራት አቅጣጫ ተወጥራ
እመስቀል ላይ ተቸንክራ
ጣሯን ቁልቁል በማሰማት
ነገዋን በእኔ ለማየት
“ላማ ሰበቅታኒ ?” አለችኝ - “ለማን ተዉከኝ በዚህ ሰዓት ?”
ፊቴን መልሼ አየኋት::
የምር ሆነ፤ አገር ልጆቿን ትማጠናለች:: ይህ ምስል ግን - የጌታ ስቃይና ሕማማት - ክህደትንም ያስታዉሳል፤ አሳልፈዉ የሰጡትን:: የአገር ትንሣኤ እንደ ጌታ ትንሣኤ የተረጋገጠ መሰለ:: <ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ ?> አምላክ ትልቁን አምላክ ሲማፀን አያዎነቱ ፈተና ነዉ:: ከመጥበብ ይልቅ የሚሰፋ ክፍተት አይነት:: ደራሽነቱ ቅፅበታዊ፣ ያኔዉኑ ግን አይደለም:: ሰለሞን ደሬሳ ስለ አንድ ግጥሙ ሲተች ለአገር ምላሽ ወድያዉነትን አደመቀ:: አገር፣ ጠላት ድንበሯን በጉልበት ከሰበረ ታቃስታለች:: አዳል ተሰማ ሰራዊት አስከትለዉ ወሰን ጥሶ የመጣዉን የደርቡሽ ጦር ግንባር ለግንባር ገጥመዉ ኑሮ፤ ድል መመታት መጣ:: ሀበሻ ግልብጥ ብሎ ሲሸሽ ... ተገኝ ወርቄ የሚባል ስመ-ጥር የጐጃም ፈረሰኛ በግር የምትሸሸዉን የዛለች አረሆ በፈረስ ሲያልፋት <አዙር ተገኝ በንጉሥ ሞት> ብትለዉ ፋታ አልሰጥ ብለዉ ከነበሩት ደርቡሾች ጥቂቶቹን ገድሎ ዘፋኟን አፈናጠጣት:: ፈረሰኞቹም <አዳልን አናስበላም> በማለት አሸናፊዉን ደርቡሽ የድል ሰዓቱን አስረገሙት:: [ልጅነት፥ 77]
የጌታ መስቀል ላይ መቸንከር ለሀገር ተምሳሌት፣ ፅልመትም ተስፋም ነዉ:: ነጋ ጠባ ሽሽት ላይ ያለ ግለሰብ፣ እግዜር በየቦታዉ የሚያሯሩጠዉ ከመሰለዉስ? በደረሰበት በደል ሳቢያ ጀርባዉን ለጌታ የሰጠ፣ ጌታን ለሀገር አይታመንም ካለስ ? ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሚተርከዉ አለዉ:: ሁለት ባሎቻቸዉ የሞቱባቸዉ ሴቶች ነበሩ:: አንዷ ባለወገን የሁለት ልጆች እናት፣ ሌላዋ የአንድ ልጅ እናትና የቸገራት:: በሽታ ገብቶ የመንደር ልጆች ታመሙ:: ባለወገን ልጆቿ ዳኑ፤ ድሃዋ ግን ልጇ ሞተ:: <...የጐንደር ሴቶች ሳይማሩ የተማሩ ናቸዉና እናት እንዲህ ብላ አለቀሰች “ሁለቱን ታማለህ አንዱን ትገድላለህ፣ / የሴት ልጅ ነህና ፍርድ ወዴት ታዉቃለህ ?” [የልቅሶ ዜማ ግጥም፥ 11ኛዉ] እንዲህ ምርር ያላት እንስት የጌታ ምስል አይመጣላትም:: በአራት አቅጣጫ መወጠሩ አይገባትም:: ቅን ካልሆነች የሩቁን አታጤንም:: የነቢይ ግጥም ተናጋሪ ግን የሀገሩን ማጣጣር አድምጦ መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ ነዉ::

ሩቁን የአንጐሌን ዣንጥላ፣ መልሼ ዘረጋሁላት
አፈሯን ጠርጌ ቁጭ አልኩ፣ ትንሣዔዋን ላልምላት!!
ይች ናት አገሬ ማለት
ሞታ እስከምትነሳ፣ ተኝታ እስከምትነቃ
አገሬ እችዉ ናት በቃ !!
የተበረከተዉም - ለአገሬና ለህልሜ- ነዉ:: ተናጋሪዉ ከራሱ ጋር የሞገተበት ያልተንዛዛ ተራኪ ግጥም ነዉ:: ሀገርን ከጐህ እስከ ጐህ ከመዉቀስ፣ በአገር ከመሸማቀቅ ማለምና መጠበቅ የተመረጠበት ነዉ:: ሌላዉ ቢቀር <አፈሯን መጥረግ> አሀዱ ተግባር ነዉ:: ግጥሙም የተጠነጠነበት ምስል ተራ ስቃይና ጩኸት ሳይሆን ሀያሉ ጌታ - እንድ አገር - የራደበት ነዉ:: ለዚህም ነዉ ተናጋሪዉ “ቁጭ” ብሎ እንዳይቀር የሚያሰጋዉ:: የደበበ ሰይፉ <ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ> ያስታዉሰናል፤ ሀገር ተርቦ ለአንድ ቁና ጤፍ ብድር፣ ባዶ ተልኮ ሌጣዉን የተመለሰ የተጨማደደ አቁማዳ። ከባዶ አቁማዳ የሚዛቅ የሀገር ፍቅር፤ ይህ የአገር ጥሪ ከግለሰብ ኩርፍያ የላቀ የመጠቀ ነዉ:: ነቢይ ተኝታ አትቀርም-ትነቃለች የመሰለ ተስፋ ነዉ ያከረረዉ:: ባዕድ ጠላት አገራችንን ከገላመጣት ህዝብ አይጠብቅም፤ ይዘምታል:: የእርስ በርስ ትንቅንቅና ጠብ፣ አገርና የአገር ልጅ መኮራረፍ ግን የተለመደ ነዉ:: በብዙ ምክንያት ባህር መሻገር፣ ከመንደር መራቅ አለ:: ሥነቃልም ይህንን ዕዉነታ ይቀባበላል:: “እኔ መሄዴ ነዉ ሄድኩልሽ ከሀገር / ሰፌዱም እንቅቡም ጠምዶኛል በነገር” ከተሰደዱ በኋላ ነዉ ልብ ዉስጥ ያንቀላፋዉ ሀገር ተቀስቅሶ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለዉ:: አገር ላማ ሰበቅታኒ ብላ ስትማፀን ብድግ ብሎ የሚሸሽ ግን ወጨት ሰባሪ ነዉ:: <የግልብጥ ሩጫ> ይለዋል ነብይ::

ይገርማል ...
ስንት አይነት ችኩል ሰዉ አለ
መሮጥ መንደርደሩን በቀር፣ መድረሻዉን ያልታደለ::
ለአገር ማቃሰት፣ መነሳሳት እንጂ ጀርባ መስጠት ማስተዛዘቡን በዉብ ምስሎች ያደነደነ ግጥም ነዉ::

፪ ነገሩ ገብቶኛል [ ስዉር-ስፌት ፥ 85 ]
ጠዋት ቤትሽ መጣሁ
አንቺ ግን የለሽም፤ በተስኪያን ሄደሻል::
ያዉ፤ የገላገልሽዉ
የጉደሩ ጠርሙስ ባዶዉን ተኝቷል::
ስትንፈራገጪ ድንገት የረገጥሺዉ
ብርጭቆ ተሰብሮ፣ ወለሉን ሞልቶታል::
ብርድልብስሽ የለም -
እንደአድፋጭ - ዉሽማ፣ አልጋሽ ሥር መሽጓል::
አንሶላሽ ከፍቶታል -
በሌሊቱ አበሳ ሽንሽን ቀሚስ መስሏል::
ግድየለሽም ፍቅሬ ነገሩ ገብቶኛል
በህልምሽ ከኔ ጋር፣ ተቃቅፈሽ አድረሻል::
እኔ አኩርፌሽ ብዬ፣ ጅሉ ልቤ ወልቋል::

አይ የልብሽ ጉዱ !
ዕምነትን መሻሩ፣ ልማድን መካዱ
ለብቻ እንዳደረ፣ ደሞ እንደጨዋ ልብ፣ በተስክያን መሄዱ::
አይ የልብሽ ጉዱ !
ያፈቅራታል፣ ግን ተቀይሟት ብቻዉን ከቤቱ አደረ:: እስክታባብለዉ አልጠበቀም፤ ማለዳ ከቤቷ ቢመጣ ጉድ ሆነ:: ሌሊት የጦፈ የተረማመሰ ወሲብ የተጐዘጐዘበት አልጋ ጠበቀዉ:: አምሮት እያቃሰተ ከህይወት ጣፋጭ ጣዕም እንዴት ይላቀቅ ? የተወራጩበት ሌሊት ሌጣዉን አልነጋም፤ የተራረፈዉን ፍራሽ ላይ በታትኖ ነዉ የሄደዉ:: ይህን ግጥም ደረጀ በላይነህ ቃኝቶታል <በዚህ ግጥም አልጋ እንደ መፅሐፍ ተገልጦ ይነበባል፤ ይተረካል... ከህይወት ፍቅርን ገልብጦ እንደጥጥ ሲከምረዉ ጉድ ነዉ::> [ ብሌን ቁ5 ፥ 37 ] ይህ ግጥም የተጨረማመተ ታሪክ ሸሽጓል:: ገጣሚዉ ለአፍታ ከተናጋሪዉ ጋር አገጣጥሞን ገሸሽ ይላል:: አይኖቹን እንደ ካሜራ እያዟዟረ የፍቅረኛዉን መኝታ ክፍል ይታዘባል:: ትናንት ምን አጣላቸዉ ? በጧት ምን ፍለጋ ከቤቷ ሰተት አለ ? የሴቷ ፅላሎት ረበበ እንጂ ድምፅዋ አይሰማም:: ከወንዱ አንፃር ነዉ የተቀረፀዉ:: ሆኖም ገጣሚዉ በሚመስጥ ምስል ያነዘራቸዉ ስንኞች ሌላ ሌላም ይናገራሉ:: በሩ የወላለቀበት ግጥም ሳይሆን ተጨማሪ ስዉር ጓዳ አለዉ::
ከመኝታ ክፍል ትዕይንት ይልቅ እጅጉን የሚመስጥ ተናጋሪዉ ነዉ:: አልጋ ስር ሳይቀር ያሰሰዉን ዕዉነታ ይክዳል፣ ወደ ዉስጡ ሊያፈገፍግ፣ ሊኮራመት መሆኑ ያስታዉቃል:: እሷ በሌለችበት እየተናገረ፣ ያየዉን እንደፈለገዉ ነዉ የተረጐመዉ:: አንድ አይኑ ያስተዉላል፤ ሁለተኛዉ በአሳብ ይቃብዛል:: የሌላ ወንድ ጠረንና አሻራ ፍለጋ የተኛችበትን አልጋና ዉስጥ ልብሷን በአይኖቹ ይሄድባቸዋል:: ራሱን ያፅናናል፤ “በህልምሽ ከኔ ጋር፣ ተቃቅፈሽ አድረሻል” እያለ:: ተናጋሪዉን ማመን ይቻላል ወይ ? የተደረገዉን፣ የተፈፀመዉን ሳይሆን እሱ ስሜቱን ለማስከን የልቡን ሸሽጐ የአንደበቱን ያወጋ ይመስላል:: መኝታ ክፍሏን ሳታስተካክል ምን አጣድፎ አስወጣት ? አፍቃሪዉ ክህደቷን ለምን አለዘበዉ ? ይህን ክፍተት አንባቢዉ እንዲሞላዉ ነዉ የተተወዉ:: ነቢይ ግጥሙን አለወትሮዉ በመንቶ ነዉ የቀረፀዉ፤ ስንኞች እየተቀባበሉ ግጥሙን አይዘልቁም:: በሁለት በሁለት አንድ ትዕይንት እየላጡ አረፍ፣ ሰከን፣ ቀጥ ይላሉ - የተናጋሪዉን ማቃሰት እያረገቡ:: ተራ በተራ ብርሃን የሚዞርበት የአልጋ ጠርዝ የሚቋጨዉ በከፊል የተናጋሪዉን ሥነልቦናና የዋህነትን አቀጣጥሎ ነዉ:: ገጣሚዉ - በዕዉን ያጡትን በሕልም ለሚያገኙ - ብሎ ግጥሙን ስለአበረከተ የተናጋሪዉን ድምዳሜ አድምቆ ይሆናል እንጂ፣ ገለጣዉ ከማታ ድርጊት የተረፈን ዕዉነታ፣ በፍቅርና በወሲብ መካከል ያለዉን የሀይል ልዩነት ሳያድበሰበስ ይጦቅማል::
በቃል ግጥም የተጠቀሰዉ የእንስቷ ስጋዊ ፍትወት አልተገደበም “ወየዉ ባደረገኝ የደጅህን ሰርዶ / አህያህ በበላኝ ጐራርዶ ጐራርዶ”:: አንዳንዴ እንስት የሚመዘምዛት የወሲብ ረሃብ ይሰፍርባታል፤ ወንዱ ደግሞ እንደነገሩ ሊሆን ይችላል:: ደምሴ ፅጌ በፍለጋ ልቦለድ የቀረፃት ቅድስት፣ እንዳለጌታ የወሲብ ጥሟን የተቀኘላት የዛጐል ልቦለድ ዕሌኒ ይታወሳሉ:: ወሲባዊ ጥሪዋን የግጥሙ ተናጋሪ ያጤነዉ ይመስላል:: አፈቀራት እንጂ የዕዉነታዉ ስቃይ እንዳለ ነዉ፤ ከሌላ መቅበጧን ማስተባበሉ አዝግሞ እንዲጓዝ አግዞታል:: “እምነትን መሻሩ፣ ልማድን መካዱ / ለብቻ እንዳደረ፣ ደሞ እንደ ጨዋ ልብ፣ በተስክያን መሄዱ” ሲል ለገሃድ እንጂ ለህልም እንዳልሆነ ልቦናዉ ያዉቃል:: የበድሉ ዋቅጅራን ባለ አንድ መንቶ ጥልቅ ግጥም ያስታዉሰናል::

እኔ ምኑን ተጐዳሁ፣ ላንቺ ይብላኝልሽ እንጂ
እንደ መንፈስ ዉስጤ ሳኖርሽ፣አካል ሆነሽ ስትሄጂ

ግጥሙ ዉስጠቱ የተጋረደ ግርማነት ያጠላበት ነዉ:: እሱ እንደ መንፈስ እየሸበለላት፣ እሷ ከስዕሉ ሸራ ወርዳ ርቃዉ ትሄዳለች:: መመለክን የመሰለ ፍቅር ሳይሆን፣ መተሻሸትና የአካል ግለት እርቧት ከሆነስ ?
<ነገሩ ገብቶኛል> ግጥም ሲጤን አፍቃሪዉ ከመኝታ ክፍል ያየዉን በደረቁ አልገለጠም:፡ ከዉስጡ፣ ከታህተንቃቱ - subconcious - የሸፋፈነዉ የሚላወስ ጉዳይ እያፈተለከ በምስል ይከሰታል:: በመተሻሸት ሽንሽን ቀሚስ የመሰለ አንሶላ፣ እንደ አድፋጭ ዉሽማ አልጋ ሥር የመሸገ ብርድ ልብስ ... ገላዋን ባዕድ እንደሚጋራዉ ነግረዉታል:: እሱም ከአካሏ የሚቀስመዉን ላለመነፈግ ይመስላል የሚያስተባብለዉ:: ገመና፣ ምስጢር እንዲሆንለት ነዉ ገሀዱን በህልም የሚመነዝረዉ:: <የየጁ ቄስ ቅኔዉ ቢጐድልበት፣ ቀረርቶ ሞላበት> አይነት ግን አይደለም፣ ተናጋሪዉ ሆን ብሎ ነዉ የደበቀዉ:: <ትንፋሽሽ አይራቀኝ አቦ !> የሚለዉ የነቢይ ግጥም ተናጋሪና ይህ የፍቅረኛዉን አልጋ የሚበረብር አፍቃሪ አንድ ናቸዉ:: በሩቅ መሆንን መርጠዋል::

ሲበርደኝ
ወደ አንቺ እደዉላለሁ
ድምፅሽ ዳር ቁጭ ብዬ
እንደሳት እሞቃለሁ::
የፍቅርና የወሲብ ጣዕም እንደ ግለሰቡ ይበላለጣል:: የከአድማስ ባሻገር አበራ ወርቁ - ባህር ማዶ ተምሮ የጨመተዉ - እንኳን፣ ሉሊት የከዳችዉ መስሎት የአልቤርጐ በር በርግዶ ሌላ ሴት በጥይት ገድሏል:: ነገር የገባዉ አፍቃሪ ግን ክህደቷን አስተባብሎ እንዳትፈርጥበት ያዝላታል:: እንደ አላል - አላል የተጫነዉን ጭነት ለማስተካከል፣ በላዩ ላይ የሚደረብ ተጨማሪ ጭነት ነዉ፣ አለበለዚያ ይሰናከላል:: ክህደቷን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመዉ ሣይሆን የተለማመደዉ ይመስላል:: ይልቅስ የተጐዳችው እንስቷ ናት:: ሲያከንፋት ያደረ የወሲብ እርካታ ትዝታዉ ሳይተን፣ ፍቅረኛዋ በህልምሽ እኔን አቅፈሽ አድረሻል ቢላት ትሸማቀቃለች:: ወይም ለክህደቷ ንሰሃ ልትገባ ጧፍና ዘቢብ ዘግና ቤተክርስትያን ሄደች፤ እንዳይታወቅባት ትሳላለች የመሰለ አንድምታዉን ብታጤን ሊሰቅቃት ይችላል:: ለአንድ አጭር እድሜ በሱም ዉስጥ ላለዉ ዉስን ትኩስነት መኖር፣ ሊያላትም ይችላል:: ወንድ በፍቅር ለፈዘዘላት እንስት እያቃሰተ፣ እየተደናቀፈ ማዝገም መምረጡን ነዉ ነቢይ የተቀኘዉ:: ድሮም ቢሆን በጨሌና በገንፎ የምትከበር የሴት አምላክ አቴቴ ናት::

፫ ብቸኝነት የተደሰተበት ቀን [ ስዉር-ስፌት ፥ 113]
ጐዶሎ ... የቡና ብርጭቆ
ግማሽ የነደደች ክብሪት
ግማሽ የጨሰች ሲጋራ
አሽትሬ ከቁሩ ጋራ::
ቡና የደረቀባት ማንኪያ::
ጉስቁልቁል ያለ ሰዉዬ፣ ኑሮ እንደሸሚዝ ያለቀበት::

ሰዉዬዉ፤
ከነሃሳቡ፣
ከነሰባራ ኮከቡ፤
ባንዳች ስሜት ያላንዳች ቃል
ከብቸኝነት ይጫወታል::

ቆየ ቆየና ግና፤

ሲጋራዋን ስቦ ስቦ፣ ከምሬት ጋር ወረወራት
በጥቁር ያለቀ ጫማ፣ ወለሉ ላይ ደፈጠጣት
አጅሬ ብቸኝነትም፣ ጮቤ ረገጠ ክልቡ ፍንድቅድቅ አለ በሀሴት
ባደባባይ ግዳይ ጣለ፣ አ.ን.. ድ ጠላት ወደቀለት !
ግለሰብ ሲያዉጠነጥን፣ሲቀፈዉ ወይም በሆነ ጉዳይ ከታወከ ተለይቶ ለብቻዉ መነጠልን ይመርጣል:: ነቢይ የብቸኝነት መብት ይለዋል:: በሀገር ልብስ ደምቀዉ ለረበሹት አዛዉንትና ግለ-ነፃነት ላጡ የተቀኘዉ ነዉ:: “ስጡኝ አንድ ጥጋት / አንዳንዴ የማርፍበት / እንደ ዕዉነት የምትሞቅ / እንደ ዉበት ደማቅ” [ ጥቁር ነጭ ግራጫ ፥ 31] በስዉር-ስፌት ስብስቡ “ዘላለምን ካፍታ አባርቆ / ብቸኝነት ዉስጥ ጠልቆ / ... በብቻ ዓለም ተንደላቆ” እያለ ለብቸኛ ህይወት ፌሽታ ተቀኝቷል:: የግጥሙ ርዕስ <አንዳንዴ> ነዉና ግለሰብ ቆይቶ ከሌሎች ጋር ተቀላቅሎ እንደ ወትሮው ህይወቱ በየእድሩ ትቀነጠባለች:: ሰዎች መካከል ሆኖ ብቸኝነት ከተሰማዉ ግን ጠነን ጐብደደ ይላል:: እዉስጡ በተጠነሰሰ ስጋት፣ ኩርፍያና ጥርጣሬ ከጀማዉ ባለመግጠሙ ባይተዋርነት እንደ ታማኝ ዉሻ ይከተለዋል:: መሬት ቢንቀጠቀጥ ዐይነስዉር ወዴት እንደሚሮጥ አያሳስበዉም:: ሳንወለድ የተቀባነዉ የህይወት ቅድመ ትርጓሜ የለምና ሳርተር እንዳለዉ <ሌላዉ ሰዉ ነዉ ገሃነም > በመሰለ የህልዉናነት ጭንቀት - existential anguish - የተሸበለለ ብቸኛም አለ:: ከዮፍታሄ “አይኔን ሰዉ አማረዉ ...” ጀምሮ ስለብቸኝነት የአማርኛ ገጣሚያን ተቀኝተዋል:: ሎሬት ፀጋዬ “ለየብቻዉ በመገንጠል // ተደባብቆ ሲብሰለሰል / ጉድም አይደል ? ድንቅም አይደል ?” እያለ ለብቸኞች - ለፍቅር ጦስ የተንገበገበዉ ያክል ባይጠልቅም - ተቀኝቷል:: [ እሳት ወይ አበባ ፥ 191] በዕዉቀቱ ስዩም በ<የባይተዋር ገድል> ያለአጋር ለቀረ ግለሰብ ዘምሯል:: “በሌሊት ወፍ ምትክ፣ ክንፍ ያወጣ ሌሊት፣ ጐጆህን ሲዞረዉ // መንሳፈፍ ይቅር፣ መስጠም ያቅተዋል ሰዉ ? / ሲያሰኝህ ዕድልህ / ያኔ ይጀምራል፣ የባይተዋር ገድልህ” ራስን እስከማጥፋት እንደ ደነበረ በሬ የሚያሯሩጥ፣ የሚገፈትር ብቸኝነት አለ:: [ ስብስብ ግጥሞች ፥ 72 ] እነሰለሞን ደሬሳ፣ ደበበ ሰይፉ... ተቀኝተዋል:: ብሩክ ገ/መድህን ይህን ለብቻ የመኮራመትን ሰቆቃ በ<ያኔ ነዉ ብቻ> ግጥሙ ተደምሞበታል:: “እንደምድረበዳ ቁልቋል፣ ብቸኝነት ሲገጥ / ከሰዉ በታች ዉሎ እያማጠ ሲያጥጥ / ያኔ ነዉ ብቻ / ሚታጣለት አቻ” [ ድርድር ፥ 19 ] በብዙ የፅሁፍና የቃል ግጥም የተገበረለት ብቸኝነት ምን ቢተርፈዉ ነዉ ነቢይ በተራዉ የተቀኘለት ?
የነቢይ ግጥም <ብቸኝነት የተደሰተበት ቀን> በምኑ ከሌሎች ተለየ ? ነቢይ ካሜራዉን ተሸክሞ ነዉ ብቸኛዉን ፍለጋ በየጉራንጉሩ የሮጠዉ:: እንደሌላዉ ለማተት፣ ያዉጠነጠነዉን ለመፍተል ብቻ ሳይሆን ባይተዋር ሲንቀሳቀስ እንዲጤንና አንባቢ ያሻዉን እንዲያክልበት በአንደምታ የተወረረ ግጥም ተቀኝቷል:: ግጥሙ የሚጀምረዉ ግማሽ በተረፈ፣ በተነካካ ቡናና ሲጋራ ነዉ:: የሚያምር ሳይሆን የቆሸሸ ጠረጴዛ ታክኮ፣ ከቁሳቁስ ጋር <ጉስቁልቁል ያለ ሰዉዬ> ተደባልቆ ተቀረፀ:: ካሜራዉ ሽፋኑን ሳይሆን የግለሰቡን ዉስጣዊ ሰቆቃ ለመግለብ አደፈጠ:: የግጥሙ አቀራረፅ በግዑዝ ቁስ እና በህይወት ንዝረት ይዋልላል፤ በሚዳበስና በማይዳበሰዉ:: ሲቋጭ ግን ዕልልታ የጋረደዉ ለቅሶና የመፈራረስ ድል የመሰለ አያዎነት ተጨናንቀዉበታል:: የብቸኛዉ ሰዉ እንቅስቃሴ ለመዉደቅ ነዉ ወይስ ለአዲስ ጉዞ መንገዳገድ ነዉ የሚለዉ አሻሚነት እንዳለ ሆኖ:: የግጥሙ አንጓ አቀራረፅ ያልተለመደ ነዉ:: አንድ ሀረግ “ቆየ ቆየና ግና፣” ሙሉ አንጓን ወክሎ የብቸኛዉ ጠባብ ተስፋ “ቡና የደረቀባት ማንኪያ” የመሰለ ሀቅ ይፈናጠርበታል:: የተናጋሪዉ ድምፀት ከገለልተኛ ወደ ተቆርቋሪ ብሎም የተደናገረ ደስታና ዕሪታ ዝብርቅርቅነት የዋጠዉ ልክ እንደ ብቸኛዉ ነፍስ ተርበትብቷል:: የአንጓዉ ክፍተት ዝም፣ ቀጥ ማለትን ይጠይቃል - መገጣጠምን የተጋፉ ስንኞች:: ነቢይ በዚህና በተነበበዉ < ነገሩ ገብቶኛል > ግጥም እንደተስተዋለዉ ለኪነዉበት የመዘርዘር ቅንያዊነት ይጠቀማል:: ማለትም እየመረጠ አልጋን እንደ መፅሄት ሲገላለጥ፣ ከባይተዋሩ ጠረጴዛ እንደ ካርታ እየሳበ ጆከሩን ሲያፈላልግ ይወስድ ይወስድና ከሆነ ሥነልቦናዊ አልያም ህይወታዊ ግድግዳ ያላትማል - ክህደትና ብቸኝነት የሚያካክል::
የሆነ ብሶት አለ:: መቆዘሙ፣ አካባቢዉን መዘንጋቱ፣ ጀማምሮ መተዉ፣ ጉስቁልናዉና እዉስጡ የሚፈላ ኑሯዊ ሀዘን፣ እጦት የመሰለ በሌላዉ አለመጤን፣ ችላ መባልም አለ:: ነፍሱ ዉስጥ የሰመጠ ሀዘን፣ የሚያደናግር ትዝታን የመሰለ፣ ከዕድሜዉ የረገፉ ብኩን ቀናትን ማስታወስ አይነት የመሸገበት እንቅስቃሴ አለ - ገጣሚዉ ሊያወረዛዉ፣ ሊያለሳልሰዉ ቢሞክርም:: ልክ ሰዐሊ መስፍን ሀብተማርያም በነፃ ግጥሙ እንዳወሳሰበዉ “የሚስጥሬን አበባዎች ዝምታዬ ዉስጥ ቀበርኳቸዉ /በስለዉም ሀዘን ሆኑ” መጐዳት አልያም ለከበባ እጅ አለመስጠት የመሰለ ህይወት:: በአካባቢያችን ለምደናቸዉ ልብ ባንልም ነቢይ የተቀኘለት በብቸኝነት የተተበተበ ይኖራል:: አለማየሁ ገላጋይ በ<ኩርቢቷ> አጭር ልቦለዱ ሰዎች መካከል ሆና ብቸኝነት የቆረፈዳት ወጣት እናት ስሏል:: ድንገት የሞተዉ ባሏ ቤቱንና ንብረቱን በእናት አባቱ ስም ስላስመዘገበ ለወለደችለት ልጅ ብላ ሁሉን ነገር ተነፍጋ፣ ተቸግራ ዝምታን ለምዳ አለማምዳም እንደጥላ ያለኮሽታ ትንቀሳቀሳለች:: ህፃን ልጇም ታዘበቻት <እዚህ አያቶቼ ግቢ ዉስጥ የኖረችዉ በመንፈስ ህልዉና ነዉ ማለት እችላለሁ:: ስትሄድ ኮቴዋ አይሰማም:: ለዚህ ዓለም ሙቀትና ቅዝቃዜ ምንም አይነት ምላሽ ስትሰጥ አይታይም:: አትስቅም፣ አታለቅስም:: ሆዷ ተከፍቶ ስትበላና ስትጠጣ አጋጥሞኝ አያዉቅም::> [ኩርቢት ፥ 53] ብቸኝነት የመጠጣት እናት አንድ ጠዋት ብድግ ብላ ጠፋች:: ነቢይ በዕምቅ አጭር ግጥም ዉጭና ዉስጥ እያጤነ የተቀኘለት ገፀባህርይ ሲንቀሳቀስ የአንድምታ ጨረሮች አፈነገጡ:: “ከነሃሳቡ / ከነሰባራ ኮከቡ” የቆዘመዉ፣ ልብሱ ብቻ ሳይሆን “ኑሮ እንደሸሚዝ ያለቀበት” ብድግ አለ:: የማጋትን ሲጋራ እግሩ ስር አልጣላትም፤ ከምሬት ጋር ወረወራት እንጂ:: እወረወረበት ድረስ ሄዶ ባለቀ ጫማዉ ወለሉ ላይ ደፈጠጣት:: ይህ ለምን አስፈለገ፣ ድርጊቱስ ምንን ይጦቅማል ?
በትርፍራፊ የተከበበዉ፣ የቀናቱ ኮከቡ የተሰበረዉና ዉጫዊ መልኩ አለባበሱ የተንገላታ፣ ምን በመሰለ አሳብ ነዉ የተዘፈዘፈዉ ? እንደቸገረዉ፣ ቁሳዊ ህይወቱ እንደጐደለዉ ያስታዉቃል:: ግን ከጀማዉ አግልሎ ያስቆዘመዉ አልተገለጠም:: መንቀሳቀስ ሲጀምርና
ሲጋራዉን ሲደፈጥጥ “አጅሬ ብቸኝነትም፣ ጮቤ ረገጠ ከልቡ ፍንድቅድቅ አለ በሀሴት / ባደባባይ ግዳይ ጣለ፣ አ.ን.. ድ ጠላት ወደቀለት !” ይህ ብቸኛ ግለሰብ < አ.ን.. ድ> የሚለዉ ቃል እንደ ሸክላ ከሶስት ቦታ ስለተሰነጠቀበት መፍረሱን አደመቀዉ:: ጭራሽ ራሱን አለመሳቱ፣ በቡና በሲጋራ መጠመዱ እንደመዘናጋት ስለሆነ ብቸኝነት ጮቤ የረገጠዉ ከነዚህ ጥቃቅን የእስትንፋስ ምልክቶች ብቸኛዉ የተላቀቀ መስሎት ነዉ:: ሆኖም የእንቅስቃሴዉ ጥንካሬ፣ ምሬቱ የመንገዳገድ ብሎም የማገገም፣ ከጉዳቱ የማሸለት ተስፋም ነዉ:: ነቢይ ቀቢፀ ተስፋነትን በግጥሞቹ አያባብልም:: ይህን የመሰለ ጨለማነት <ላምባዲናም የለኝ... > በሚለዉ ግጥም ከትንሽ ፍንጣቂ፣ ከሴት የፈገግታ ብልጭታ ተስፋ አያጣም:: “የሰባራ ኑሮ ሰባራ ኮከብም፣ ሙሉ ዕድሏ በርቶ / በጥርሷ ብርሃን፣ ብርሃን ተወልዶ፣ ብርሃን አፍርቶ” እያለ ነዉ ማንሰራራት እንደሚቻል፣ ጨለማ እንደሚረታ የተቀኘዉ:: ዕዉቋ ባለቅኔ Anne Sexton < ግጥም ህዋሳትን ማሸበር አለበት፤ የአንባቢን ስሜት እስከ ማደፍረስ> ላለችዉ ይህ ግጥም ወካይ ነዉ:: ተነቦ አይዘነጋም፤ ይኮሰኩሳል::

፬ ከሞት ጋር ተቃጥረን [ ስዉር-ስፌት ፥ 114]
ከሞት ጋር ተቃጥረን፣ የቆራጥ ቀጠሮ
ካምናም ብሶበታል ዘገየ ዘንድሮ::
ወትሮም እንዲህ ነዉ የአበሻ ቀጠሮ !!

ሞት ለካ አበሻ ነዉ ?!
ግና ምን ሆኖ ነዉ ?
እንዴት ቢንቀኝ ነዉ ?
እንዴት ቢፈራኝ ነዉ ?
መንገዱ ረዘመ ወይ መንገዱ ጠፋዉ ?
የህይወትን አጥር፣ ዳር ዳሩን ይዞራል !
ዕድሜን ደጅ ይጠናል::

ሞትም እንደሰዉ ልጅ ቀን ይጐድልበታል ?
በለስ የቀናት ለት
ህይወት እንደዚህ ናት
ሞትን መገነዣ፣ ስዉር ስፌት አላት !!
ሞትን መቅጠር፣ ለምንስ ቀረ ብሎ መብሰክሰክ መነሻዉ ምንድነዉ ? በኮሽታ የምትበረግግ ነፍስ የቤተክህነት እንጂ የመቃብር መረዋ አያረጋጋትም:: ስለ ድኅረሞት ህይወት የተሰበከዉ፣ ለመንደራችን የቋጠርነዉን ፍቅር ሊያስጥለን እንደማይችል ስብሀት በአጭር ልቦለዱ ቀርጾታል:: አጋፋሪ እንደሻዉ ከሞት ለማፈትለክ ሲባዝኑ አቡነ ተክለሃይማኖት <ወደ ሰማይ ቤት ልዉሰድህ> ቢሉት እንደ ቃርሚያ ቆጥራችሁ ናቁኝ በማለት አዲሳባ መመለስን ይመርጣሉ:: የመኖር ጣዕም እንዲሉ:: ሰዉ እድሜዉን ጨርሶ ከነምርኩዙ እመቃብር አፋፍ ቢደርስ ፣አፈሩን ገለባ እንዲያደርግለት እንሸኘዋለን:: ገና አቅምና ዕድሜ ተርፎት ድንገት በሞት ሲነጠቅ እንሸማቀቃለን:: በተለይም ዓላማ አንግቦ ለተበደሉት የሚተጋ ከሆነ:: አንድ ለህዝብ ጥሪ ዱር የገባ ጀግና ፣ የወሎ ሰዉ በድብቅ እየቀለበዉ ፣ ጐህ እንዲቀድ አብረዉት ህልም ይፈትሉ ነበር:: ረሀብ ገብቶ ትንሽ ትልቁን ፈጀዉ:: ህዝብ እጅ አጠረዉ፤ ጀግናዉም ብሩክ ጠኔ ገደለዉ:: ቅኔ አዋቂ “ብሩኬ ሞተ አሉ ቋጥኝ ተጭኖበት / ገደሉን ሲቧጥጥ አገልግል ጠፍቶበት” በማለት የማይዳሰስ ሀዉልት አዋቀረለት፤ ለሌላ ፋኖ አሻገረዉ:: ታድያ ነቢይ እንደ ተቀኘዉ ምን ሲኮን ነው ሞትን ቀጠሮ አክብረን የምንጠብቀዉ ? ሞትን በጉጉት መጠበቅ በዝቶ መሽቀዳደምም አለ:: <የሰዉ ህይወት፥ በበረሃ ዉስጥ ሲጓዝ ዉሃ የጠማዉ ሰዉ፥ ራቅ ብሎ ከወደፊቱ ኩሬ እንደሚታየዉ ዐይነት፥ የቀን ቅዠት ነዉ ... በበኩሌ ከመሆን አለመሆንን እመርጣለሁ:: > [አንድ ለአምስት ፥ 303] አስፋዉ ዳምጤ የገለፁት የሥነልቦና ምሁር ወንድይራድ ልጥ ልጦ ገምዶ በአፍላ ዕድሜዉ ዛፍ ላይ የገዛ ህይወቱን አሳለፈ:: አንባቢ ስለ ግል ህይወቱ ለማዉጠንጠን ይገደዳል:: ነቢይ ለበዐሉ ግርማ ባበረከተዉ ግጥም

ይሄ ምን አማርኛ ነዉ፣ ፌዙ ለጆሮ የከፋ
ምን ያለስ ልብስ ሰፊ ነዉ፣ ሞትን በልኬ እሚሰፋ ?
ሞት ከአረጋዊ ቢያረጅም፣ ከሰዉ የባሰ ክፉ ነዉ
በተለይ ደራሲ ሲያገኝ፣ ሲስገበገብ ለብቻዉ ነዉ > በማለት ተመስጧል::
ሞት እርጅና አድፋፍሮት ከሰዉ ጋር ብርድ ልብስ ቢናጠቅ አያስደንቅም:: ዕድሜ እየፈራረሰ አጥንት ከረገበ፣ ህልዉና ከቀረፈፈ ማንን ይለማመጣሉ ? የመኖር ሸክም የሰበረዉ ወይም አንዳች ህልዉናዊ ጭንቀት የቀፈደደዉ ሞትን ይመኛል:: ለዚህ እንግልት በሥነቃል የተዘረፈ ቅኔ አለ “ሞት ይቅር ይላሉ ቢቀር አልወድም / ድንጋዩም አፍሩም ከሰዉ ፊት አይከብድም” ተብሏል:: የደበበ ሰይፉ ግጥም <ለምን ሞተ ቢሉ> ይታወሳል:: ነቢይ ግን “መንገዱ ረዘመ ወይ፣ መንገዱ ጠፋዉ ?” ሲል ዘመቻ ሄዶ ያልተመለሰን አባወራ ነቅቶ የመጠበቅ ጉጉት ቢመስልም ነፍስ ገዳይ በመዘግየቱ መታወክን ምን ቀሰቀሰዉ ? በአንፃሩ ደግሞ እንደ አጋፋሪ እየጋለበ ከሞት የሚሸሸ አለ:: መሸሸ ሳይበቃ፣ አፈታሪክ ተዋናይ የሚባል አዋቂ ሞትን ለሰባት አመት መገደቡን ያወጋል:: ተዋናይ በጐጃም የነበረ ፈላስፋ፣ ታላቅ ሊቅ፣ ቅኔን የፈጠረ ባህረ ምስጢሩን ዋኝቶ የመረመረ መሆኑን ተነግሮለታል:: በዕዉቀቱ ስዩም ለሰባት አመት ተዋናይ ሞትን መገዘቱ ርዑየትን በመፃረሩ ይበልጥ ለጐደጐደዉ ህልም አደላ:: “ተዋናይ ስለምን እግዜርን ይከሳል / ሞት አንዴ ይመጣል! ሕልም ይመላለሳል / መቃብርን ደፍኖ ሞትን በቁም አስሮ / ሰዉ ነፍሱን ይቀብራል ? ሕልሞቹን ቆፍሮ” [ስብስብ ግጥሞች ፥ 103] ነቢይ <ከሞት ጋር ተቃጥረን> ግጥሙን ያበረከተዉ - ለፍትጉና ለህቡዐን ህይወት - ነዉ:: አብርክቶቱ ዳር የተረሳ ትራፊ ሳይሆን የሚነዝር ምስጢር የቆጠበ ስንኝ ነዉ:: ፍትጉ ድሮ በጐህ መፅሄት ይሳተፍ የነበረ - ምናልባትም የብዕር ስም - ሲሆን፣ ህቡዐን ህይወት ለመራራ ህዝባዊ ትግል፣ ለአላማ ህይወቱን ለመማገድ ላላቅማማዉ ንቁ ወጣት ጥቆማ ነዉ:: ይህ ጥቆማ የሞትን አዉድና እሴት አበለፀገ::
ግጥሙ ሲዋቀር ሶስትዮሽ አዝሎ ነዉ:: ከሞት ጋር ቆራጥ ቀጠሮ፥ ሞት ዕድሜን ደጅ መጥናቱ እና ህይወት በለስ ሲቀናት :: የተናጋሪዉ ድምፀት በህይወት ሳይሆን በሞት ላይ መቀለድን መዝናናትን፣ የአበሻ ቀጠሮ ይመስል ለጊዜ ቁብ መንፈግን ታክኮ አይደብትም:: በጥልቀት ሲጤን ህይወት ሞትን ድል የሚነሳት ዝም ብሎ በመኖር አይደለም:: ተራ ሰዎች ተስፋና ደስታ እንዳይነፈጉ ስንዳክር፣ በጥሞና ሲመሽና ሲነጋ ብቻ ነዉ:: ነቢይ በሌላ ግጥሙ እንዳለዉ “በጥላ በጣዩ ረክቶ በጥሞና ለሚኖረዉ / እያንዳንዱ ማታና ቀን፣ የራሱ ዘላለም ነዉ” ይህን ዘላለም ከአንድ ዕለት መዝምዞ ለመታደስ ወኔ ይጠይቃል:: እያንዳንዷን ቀን ለተንገላቱት በመላተም እንደሚቆላ ተልባ፣ ብርሃን ከደሳሳ ጐጆ ማፈናጠር፣ በዕንባ የረጠቡ አይኖች ስቀዉ ደስታቸዉ ሲጋባብን ለነሱ ድል “ሞትም እንደሰዉ ልጅ ቀን ይጐድልበታል ?” እየተባለ ያጣድፋል:: ሀዲስ ዓለማየሁ የገለፁት በዛብህ፣ የስዕለት ልጅ ስለሆነ የእናቱን ቃልኪዳን አክብሮ ታቦት ለማገልገል ማፈግፈግ አለበት:: በዛብህ አይነ ጥላዉ ተገልጦ እንደ ነፃ ሰዉ መኖር ቢያልምም፣ የእናትና አባት ፍላጐት ከማመፅ አገደዉ:: <በመሄድና በመመለስ አዉታር ተወጥሮ> በደመ ነፍሱ ሞታቸዉን ሳይመኝ አልቀረም:: የሁለቱንም ሞት ካረዱት በኋላ እንደምንም አለቃቅሶ <... ቀለለዉ፤ ... ደስ አለዉ:: ... ወደሁዋላ የሚጐትተዉ ነገር ሣይኖር ... የፈለገዉን አይነት ህይወት መኖር ይችላል ... ወቃሽ ከሳሽ ሳይፈራ> [ ፍቅር እስከ መቃብር ፥ 63 ] በሌላዉ ሞት ምክንያት ህይወቱ ነፃ ወጣች:: ይህን ለመሰለ የሞት ቀጠሮ “ካምናም ብሶበታል ዘገየ ዘንድሮ” እያለ የሌላዉን ሞት እንደ በዛብህ ለሚቋምጥ አይደለም ነቢይ የተቀኘዉ:: የበዛብህ እንደ ተረት ነዉ፤ ለራስ ጉዳይ በትንሹ በትንሹ መሸራረፍ:: ነብይ ገዋ ሰዉ የሚለዉ አይነት “ብዙ ሰዉ ባለበት አገር፣ ብዙ ባዶ ይታየኛል”:: ይህን ብርቅ ህይወት ለተጐዱት አርነት መማገድ፣ ራስንና ዕድሜን አሳልፎ መስጠት፣ ለወሰነ ጀግና ነዉ የተቀኘዉ:: በድሉ ዋቅጅራ ከደብረ ማርቆስ እስር ቤት በቀይ ሽብር ሊገደል ስሙ ስለተጠራ “ከእሱ በቀር / ያቺን የህይወትና ሞት ድንበር” ማንም ለማይጋራዉ ወጣት እንደ ዘመረዉ አይነት:: [ፍካት ናፋቂዎች ፥ 63 ]
<ከሞት ጋር ተቃጥረን> ለቀዘዘ ህይወት ሳይሆን ሌሎችን ከእንግልት ለማስጣል መስዋዕት ለሚጠይቅ ኅላዌ ነዉ የተገጠመዉ:: <እስረኛዋና የሰጠመችዉ ፀሐይ > ገፅ 137፣ <እስርቤትና ጊዜ > ገፅ 138፣ ግጥሞች የክትና የአዘቦት ህይወትና ሞት ይደፍቃሉ:: ቀጠሮ አክብሮ ይመጣል የተባለዉ ሞት “የህይወትን አጥር፣ ዳር ዳሩን ይዞራል ! / ዕድሜን ደጅ ይጠናል::” ተብሎ እስኪናቅ ድረስ ተሰለቀበት:: ሆኖም ለህዝብ ጥሪ ሳያቅማማ ያመፀዉ፣ አያሌ ፈተናን አሸንፎ እንደ ትዝብት የተናደዉን ትናንት ሲያጤን፣ አሁንም በመተንፈሱ ለኑሮ ረቂቅ ፍቅር ያጥወለዉለዋል:: “በለስ የቀናት ለት / ህይወት እንደዚህ ናት / ሞትን መገነዣ፣ ስዉር ስፌት አላት !!” ነቢይ ለግጥሞቹ ስብስብ የመረጠዉ ርዕስ
(ስዉር-ስፌት) በዚህ ግጥም መዉጫ፣ ከግማሽ ስንኝ ዉስጥ የተወሸቀ ዕንቁ ነዉ - እንደ ሽንኩርት ተልጦ የማያልቅ:: ስለ ህይወትና ሞት የዕድሜና የገጠመኝ ጨመቅ ማጠንፈፍ በቂ ነዉ::

ጊዜ እንደ ፀጥታኮ ነዉ፣ ላፍታ አይታሰርም ከቶ
ሰዉ እንኳንስ ጊዜን ሊያስር፣ ሊኖር ጊዜ የት አግኝቶ
በማለት ነቢይ የጊዜ አሸናፊነትና የእስር ቤት መናድን አብስሯል:: ማንንም ከማታዉቅበት ከተማ ብትኖር፣ በርህ በተደጋጋሚ ሲንኳኳ ተነስተህ ለመክፈት ፍላጐት ከሌለህ ? ከፈራረሰ ጐጆ የሚያገለግል መስኮት ከተረፈህ በቂ ነዉ ወይ ? በየህይወትህ ምዕራፍ የምትዳብሰዉ ስዉር-ስፌት ዘወትር ያስፈልግሃል::
ይቀጥላል

Read 5423 times