Saturday, 15 June 2013 12:00

ልቤን፤ “እባክህ እንዲህ አይነት ሙዚቃ እፈልጋለሁ” ስለው ይሰጠኛል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“ዘፈኖቼ ህፃናትን የሚያሳድጉ ናቸው” - ጃ ሉድ

የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኙ ጃ ሉድ፤ በዳግማይ ትንሳኤ እለት በላፍቶ ሞል “ድግስ ቁጥር ሁለት” የተሰኘ ኮንሠርት ለማቅረብ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀና ትኬት ተሸጦ ካለቀ በኋላ ድንገተኛ የመውደቅ አደጋ ደርሶበት ኮንሰርቱ መሰረዙ ይታወሳል፡፡ መውደቁ ካደረሰበት የጤና መታወክ ካገገመ በኋላ ግን በተለያዩ የውጭ አገራት ተዘዋውሮ ኮንሰርቶችን በማቅረብ የዛሬ ሳምንት ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ምሽትም በተሰረዘው ኮንሰርት ምትክ “ድግስ ቁጥር ሁለት”ን በላፍቶ ሞል አቅርቧል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ድምፃዊውን ከኮንሰርቱ በፊት አግኝታው ስለውጭ አገር ኮንሰርቱ፣ ስለአዘፋፈን ስልቱ፣ በኮንሰርቱ መሠረዝ ስለደረሠው ኪሳራና ሌሎች ጉዳዮች አነጋግራዋለች፡፡ እንደ ዘፈኖቹ ዘና የሚያደርገውን ጭውውት እንድታነቡት ተጋብዛችኋል፡፡

 

የት የት ነበር የሙዚቃ ድግስ ስታቀርብ የቆየኸው?
ምን እባክሽ እኔ እኮ አላውቃቸውም… አንዱ ስዊዘርላንድ ነው፤ የመጨረሻውን አሪፍ እና የሚያምር የሙዚቃ ጊዜ ያሳለፍኩት ስዊዲን ነበር፡፡ ከዛ በፊት እንግሊዝ ነበርኩኝ፡፡ ለነገሩ እንግሊዝን ከበፊት ጀምሮ አውቃታለሁ፡፡ ግን ምን አለፋሽ… ስንገበገብ ሄጄ ስንገበገብ መጣሁ፡፡
እንዴት?
የዚህ አገር አየር እዚያ የለማ! እስካሁን የረገጥኩበት ቦታ የኢትዮጵያ አየር የለም፡፡
አየሩ ብቻ ነው ያልተመቸህ ወይስ ሌላም ነገር አለ?
አየሩ ነው፤ ብቻ ኢትዮጵያን ስለቃት የሆነ የሆነ ነገር እሆናለሁ፡፡ አይደላኝም፡፡ ነገር ግን ስራዬን በቆንጆ ሁኔታ ሰርቻለሁ፡፡
ኮንሠርትህን ያሳረግኸው ስውዲን ላይ ነው፡፡ የሠው አቀባበል እንዴት ነበር?
ኦ! የስውዲኑ በጣም ያምራል፤ ከምነግርሽ በላይ አሪፍ ነበር!
ስለተሠረዘው ኮንሠርትህ ብናወራስ?
ይቻላል! ምን ገዶኝ …
አወዳደቅህ እንዴት ነበር? ምን አጋጠመህ?
አወዳደቄ ትንሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ድንጋጤውን የበለጠ ያደረገው የኔ መውደቅና መታመም ሳይሆን የሠዎች መጉላላት አስጨንቆኝ ስለነበር ነው፡፡ ነገር ግን ችግሬ አሳማኝ ነበር፤ አሁን እንደምታይው እየደረቀልኝ ነው (ጉልበቱ ላይ ያለውን በመድረቅ ላይ ያለ ቁስል ሱሪውን ሰብስቦ እያሳየኝ) አወዳደቄ ከቤቴ ጋር ተጋጭቼ ነው፡፡ ቤቱ አዲስ ስለነበር ደረጃ የረገጥኩ መስሎኝ መሬት ረገጥኩ፡፡ እግሬና ጆሮዬ ጋ በጣም ተጐድቼ ነበር። በተለይ የጆሮዬ አናቴን አናጋብኝና አዕምሮህ ላይ ችግር ይፈጥራል ሲሉኝ በሲቲ ስካን ታይቼ ምንም ችግር እንደ ሌለው ተነገረኝ፤ ግን ምቱ ሀይለኛ ስለነበር ለኮንሰርቱ መድረስ አልቻልኩም፡፡ ሀይለኛ ህመም ስለነበረው ማለቴ ነው፡፡
ምናልባት ዓውደ ዓመት ስለነበረ ትንሽ መጠጥ ቀማምሰህ ይሆን እንዴ?
አ…ይ… ነው ብለሽ ነው?
በተሠረዘው ኮንሠርት ብዙ ኪሳራ መድረሱን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ነው?
ኪሣራው እኔ ነኝ፡፡ የእኔ መታመም ነው ኪሳራው፡፡ ባይሰረዝና ብጫወት ጥሩ ነበር፡፡ የእኔ ዘፈኖች ህፃናትን የሚያሳድጉ ናቸው፡፡ የህፃናትን አዕምሮ የሚያቆሽሽ ዘፈን አልሰራም፡፡ ህፃናትን አሳድጋለሁ፤ በዚህ ትርፋማ ነኝ፡፡ የእኔ መውደቅና መታመም እንጂ የብር ኪሳራ የለም፡፡
እንደሰማሁት ከሆነ ከኮንሰርቱ መሰረዝ ጋር በተያያዘ ወደ 700ሺህ ብር ኪሳራ ደርሷል፡፡ ይሄ እንደ ኪሳራ አይቆጠርም?
እሱ እኔን አያገባኝም …
የአንተ ብር የለበትም ማለት ነው?
እርግጥ የእኔም ብር አለበት፣ አዘጋጆቹ ከሚያወጡት ግማሹን አወጣለሁ፡፡ ቢጂአይም በርካታ ገንዘብ አውጥቷል፡፡ ነገር ግን ቢጂአይ ባወጣው ገንዘብ ሳይቆጭ፣ ፕሮሞሽናችንን በማድነቅ የዛሬውንም ኮንሠርት አጋራችን ሆኖ እየሠራ ነው፡፡ ከዛ በተረፈ ስለ ኪሣራ ስናወራ አሁንም ኪሣራው እኔ ነበርኩኝ፡፡ አሁን ጤናዬ ተመልሶ ድኛለሁ፤ ስለዚህ ምንም ኪሣራ የሚባል ነገር የለም፡፡
ቅድም ህፃናትን አሳድጋለሁ ብለኸኛል… እስቲ አብራራልኝ?
ምን ማለት ነው… ሁሌም የህፃናትን አዕምሮ በበጐ መልኩ የሚያንፁና የሚያሳድጉ ነገሮችን ነው የምዘፍነው፡፡ ዘፈኖቼ ለበጐ ስራ የተሠጡ፣ አስታራቂና አቀራራቢ ናቸው፡፡ የምስራች አብሣሪም ናቸው፡፡ እናም ይሄ ነገር ወደፊት ለአርት ሥራ የሚዘጋጁ ህፃናትን የሚያሳድግና ጥሩ አመለካከት እንዲይዙ ይረዳቸዋል ለማለት ነው፡፡ አየሽ ህፃናት ሁልጊዜ “አንጀቴን በላሽው” የሚል ዘፈን እየሠሙ ከሚያድጉ ስለ ፍቅር፣ ስለ ባህል፣ ስለ ጤናማ ግንኙነት እየሠሙ ቢያድጉ መልካም ነው። ለምሣሌ እኔ ያደግሁበት አስተዳደግና አሁን ልጆች እያደጉ ያሉበት መንገድ አንድ አይደለም ብዬ ነው፡፡
አለባበስህን የተመለከተ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ጥለት ያላቸው ልብሶችን ራስህ ዲዛይን እያደረግህ እንጂ የተዘጋጁ ልብሶችን አትለብስም ይባላል፡፡ ይሄ ከምን የመጣ ነው? መቼ ነው የጀመርከው?
አሁንም የምታይው አለባበስ ያልሽው አይነት ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከማሸርጣቸው ልብሶች በሙሉ የአገሬ ልብሶች ናቸው፡፡ ይሄን መቼ ጀመርክ ላልሽው በጣም ቆይቷል ነው መልሴ፡፡ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ አልበም ከማውጣቴ በፊት ማለቴ ነው፡፡
ነጭ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ ካልሆነ የትኛውንም አይነት ሽፍን ጫማ ቆዳም ይሁን ስኒከር አታደርግም። ቤትህ ውስጥ ጥልፍልፍ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ በገፍ ይገኛል ይባላል፡፡ ለምንድን ነው?
ደስ የሚለኝ እንደዛው ነው፤ ጐንበስ ስል ነጭ ሆኖ ሳየው ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎቹን አይነት ጫማዎች አላውቃቸውም፤ ማወቅም አልፈልግም፡፡
የተለየ ምክንያት አለህ?
እኔ እንጃ! ይሄ ጫማ ልቤን ይዞብኛል (በዕለቱም ነጩን ጥልፍልፍ የጠፍር ጫማና ነጭ ካልሲ ተጫምቷል) ጐንበስ ስል ንፃቱ ለአይኔ ካልማረከኝ ትንሽ ጭንቅላቴን ይይዝብኛል፡፡ የእኔ ጭንቅላት ከተያዘ የሌላውም መያዙ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ሌላውን አልደፍረውም፡፡
ስለ አዲሶቹና በአልበምህ ውስጥ ስላልተካተቱት አምስት ዘፈኖችህ እናውራ?
እንዴ? አምስት ዘፈን ዘፍኛለሁ እንዴ? እኔ እኮ ዘፈኖቼን አላውቃቸውም፡፡
“ኩሉን ማንኳለሽ”፣ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ድግስ” የተሠኙትን ዘፈኖች ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ አልበምህ ላይ የሉም…
ኦ! አዎ ልክ ነሽ “ዳጐስ”፣ “ድግስ”፣ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ኩሉን ማንኳለሽ”፣ እና “ባቲ” የተሠኙ አዳዲስ እና የሚያማምሩ ሥራዎች ሠርቼያለሁ፡፡
ባህላዊና የሠርግ ዘፈኖችን ወደ ሬጌ ስልት ማምጣት አይከብድም?
በጣም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን የኔ ጭንቅላት ሙዚቃ ውስጥ ስለተነከረ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀለል እያለኝ መጥቷል። መጀመርያ አካባቢ ወደ ሬጌ ስልት መቀየር ትንሽ ያሰለቻል፤ ነገር ግን እኔ መሰልቸት ስለማላውቅ ስልቱን አገኘሁት፡፡ አሁን “እባክህ እንዲህ አይነት ሙዚቃ እፈልጋለሁ” ብዬ ልቤን እጠይቃለሁ፤ ልቤ ይሠጠኛል፡፡ በነገርሽ ላይ ሬጌ ላይ ግጥም ይከብዳል፡፡ ሬጌን ለመዝፈን ግጥም ነው ዋናው ነገር፡፡ ስለዚህ ግጥም ስፈልግ መንገድ ላይ ያገኘኋቸው ሀሳቦች ናቸው የሠርጉን የባህሉን ወደ ሬጌ እንዳመጣቸው ያደረገኝ፡፡ በፊት በፊት የሬጌ ግጥም የትግል ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ እናም ብዙ ጊዜ ድርቅ ያሉ ግጥሞች ይሆኑብኛል፡፡ አሁን ግን ቀስ በቀስ እየተፍታታልኝ፣ በአጫጭር ግጥሞች ሀሣብ መግለፅ ጀምሬያለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ ከአስር ዓመት በኋላ የመጣ ነገር ነው፡፡
እንዳልከው ሬጌ አብዮተኛ የሙዚቃ ስልት ነው። ከደከሙበት ከጣሩበት ግን የፍቅርም የባህልም መግለጫ ይሆናል እያልክ ነው?
በሚገባ! እኔ አሁን ይህን እያደረግሁ ነው። ለምሣሌ “ታዲያስ አዲስ”፣ “ኩሉን ማን ኳለሽ” የተሠኙት ዘፈኖች ባህልንም ፍቅርንም የሚገልፁ ዘፈኖች ናቸው።
እስቲ ስለ ባህሪህ ንገረኝ… ቁጡ ነህ? ተጫዋች? ወይስ…
ስትቆጪኝ እቆጣለሁ፤ ስታጫውቺኝ እጫወታለሁ፡፡ እንደ አንቺ ተፈጥሮ የምጓዝ ነኝ፡፡ ተፈጥሮ እንደምትሆነው ነው የምሆነው ማለት ነው፡፡
እንደምሠማው ከሆነ ጃ ሉድ ትንሽ የባህሪ ችግር አለው፣ ከማናጀሮቹ ጋር እየተጣላ በተደጋጋሚ ማናጀር ቀይሯል፣ ከአቀናባሪው ከካሙዙና ከፕሮድዩሠሩ ታደለ ሮባም ጋር ሠላም አይደለም ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ከታደለም ከካሙዙም ጋር አልተጣላንም፡፡ ባለፈው አሜሪካ ስሄድም ሸኝተውኛል፡፡ ታደለ ሮባ አሁንም ወዳጄ ነው፡፡ እንዳልኩሽ ባለፈው አሜሪካ ስሄድ ከካሙዙ ጋር መጥተው ሸኝተውኛል፡፡ ከአሜሪካ ስመለስ ግን ታደለ ሮባ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም፡፡ ካሙዙም ቢሆን አሁን ወደ አሜሪካ ሊሄድ ነው፡፡ እኔም በቅርቡ ስለምሄድ እዛው እንገናኛለን፡፡ ሁለተኛ አልበማችንን እዛ ልንጀምር ነው፡፡
ረዘም ላለ ጊዜ ልትቆይ ነዋ?
እኔ እመላለሣለሁ እንጂ ከአንድ ወር በላይ በየትኛውም አለም ከኢትዮጵያ ውጭ መቆየት አልችልም፡፡ አሁን መመላለስ እችላለሁ፤ ዓለም የኔ ናት፡፡ እንደ በፊቱ አይቸግረኝም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ረጅም ጊዜ ስቆይ ጤንነት አይሰማኝም። በክርስቲያኑ ፋሲካም፣ በሙስሊሙ የረመዳን ፆም ፍቺ (ኢድአልፈጥር) ጊዜም ከኢትዮጵያ ውጭ መሆን አልችልም፡፡ በጣም ደስ አይለኝም፤ ስለዚህ እመላለሳለሁ፡፡
እንደ በፊቱ አይቸግረኝም ስትል ምን ማለትህ ነው?
በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ዓለም ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ አሁን መሄድ መምጣት ለምጃለሁ ለማለት ነው። እርግጥ አሁን አሜሪካ የምሄደው ለስራ ስለምጠራ ነው እንጂ እዛ ለመኖርና ሌላው ስለሄደ መሄድ አለብኝ ብዬ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከማናጀር ጋር ተጣላ፣ ከአቀናባሪ ተጋጨ፣ ፕሮዱዩሠሩን አኩርፎታል የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሁሉም ጋር ሠላም ነኝ፣ እንደዛም ከሆነ ተበዳይ እኔ ነኝ፡፡ ነገር ግን አልበደሉኝም አልበደልኳቸውም፤ በእኔ ላይ የሚወራው ውሸት ነው፤ እንግዲህ አሉባልታ የሚወራበት ሌላ ጃ ሉድ ካለ አላውቅም፡፡
ከሬጌ ሙዚቃ እና ከህይወት ዘይቤያቸው (Style) ጋር ተያይዞ የሚነሳው የአደንዛዥ ዕፅ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ሠዎች ጃ ሉድን ከዕፅ ጋር አገናኝተው ሲያነሱት ይደመጣል፣ የባለፈውን ኮንሠርት ያሠረዘህን አወዳደቅም ሀሺሽ ከመውሠድ ጋር ያገናኙት አልጠፉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?
በፈጠረሽ ተይው፡፡ ምንም ነገር የለም! ይህንን ነገር ተይው፡፡ አሁን ህዝቡ በዚህ መልኩ እኔን መቃኘት የለበትም፡፡ እውነት ለመናገር ይህንን ነገር ላድርገው ብል አደርገዋለሁ፣ መብቴ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ነገር የለም፡፡ እውነቴን ነው የምልሽ የለሁበትም!
ሰዎች ቀጠን ማለትህንና የኪሎህን ነገር እያዩ ምግብ በደንብ አይበላም፣ ከምግብ ጋር ያለው ዝምድና የጠበቀ አይደለም ይላሉ፡፡ ለምንድን ነው በደንብ የማትመገበው?
እየውልሽ… ሰዎች ሁሉ ምግብ አይመገብም እያሉ ብዙ ሳልመገብ ቀረሁ፡፡ ይመገባል ቢሉኝ ኖሮ ብዙ እመገብ ነበር፡፡ ምክንያቱም “እሹ ይሰጣችኋል” ነው የሚለው መፅሀፉ፡፡ አሁን ብዙ ይመገባል እያሉ ቢያበረታቱኝና ብመገብ ደስ ይለኛል፡፡
ከ”መሀሪ ብራዘርስ” ባንድ ጋር ምን ያህል ተጣጥማችኋል?
“መሀሪ ብራዘርስ” በጣም ፍቅር የሆኑና ለሙያው ራሣቸውን የሠጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ አሜሪካም፣ አውሮፓም በአጠቃላይ እዚህም ያለውን ኮንሠርት ከእነሱ ጋር ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ለእኔ በጣም ተስማምተውኛል፡፡ እርግጥ አሜሪካ “ዛዮን” ባንዶች አሉ፡፡ እዚህ ያለውን ከመሀሪ ብራዘርስ ጋር ነው የምሠራው፡፡ አውሮፓና አፍሪካ አገር ካሉ ፕሮሞተሮች ጋር ትንሽ ጉዳዮች አሉኝ፡፡ እነሱን ካስማማሁኝ “መሀሪ ብራዘርስ” ከእኔ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ይቆያሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በጣም ጥሩ ልጆች ናቸው፤ ፍቅር የሆኑ ወንድማማቾች ናቸው። እንዲህ አይነት ወንድማማችነት ውስጥ ተካትቼ ለረጅም ጊዜ ብኖር ደስ ይለኛል፡፡

 

Read 7831 times