Saturday, 15 June 2013 12:05

የቀድሞው ኳስ ተጫዋች ስለዋልያዎቹና ስለነገው ግጥምያ ምን ይላል?

Written by 
Rate this item
(3 votes)
  • ኳሷን ማሸነፍ ማለት ለእያንዳንዷ ኳስ ትኩረት መስጠት ነው
  • አጥቂዎች አንድ እድል ሲያገኙ አንድ ጎል ለማግባት ማሰብ አለባቸው
  • አጥቂዎች ወደ ጎል የሚሞክሯቸውን ኳሶች መሬት አስይዘው ይምቱ
  • ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ማለት የአገር ገጽታን ሊቀይር የሚችል ነው


ኳስ ተጨዋች ነበር፡፡ ከ16 ዓመት በፊት በአርሰናል ተጠባባቂ ቡድን ውስጥ ለ6 ወራት የሙከራና የልምምድ ጊዜ አሳልፏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስም ተጨዋች ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያሬድ ተስፋዬ የተዋጣለት ነጋዴ ሆኗል፡፡ በመዝናኛ ዘርፉ ላይ የሚሰራው ያሬድ፤ የታዋቂው ፕላቲኒዬም የምሽት ክለብ ባለቤት ነው፡፡ ፕላቲኒዬም የፈርኒቸር ማምረቻ የሚባል ድርጅትም አለው፡፡ ቢቲ ትሬዲንግ በተሰኘ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አስመጭ ኩባንያ ውስጥም ከቤተሰቡ ጋር እንደሚሰራ ይናገራል፡፡ አሁን ያሬድ ወደ ስፖርቱ ለመመለስ አስቧል፡፡ ይህን ሃሳቡን በመደገፍም አብሮት የተማረው ጋዜጠኛ አማን ከበደ እያበረታታው እንደሆነም ይናገራል፡፡ “ካሳለፍኩት የተጫዋችነት ህይወት፣ ከነበረኝ ልምድና ተሞክሮ በመነሳት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የለውጥ ምዕራፍ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት እፈልጋለሁ” ይላል፡፡ በክለብ ማኔጅመንት፣ በተጨዋች ወኪልነት፣ በስፖንሰርሺፕና ማርኬቲንግ እንቅስቃሴዎች የመስራት እቅዶች አሉት፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደረሰበት የብቃት ደረጃ ለስፖርቱ ዕድገት የሚያግዙ ተግባራትን ለማከናወን መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የሚገልፀው ያሬድ፤ በተጫዋችነት ዘመኑ ሊያሳካው ይሻው የነበረውን ህልም በመጪው ትውልድ እውን ሆኖ ማየት ይፈልጋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማነት የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት መገለጫ እንደሆነም ያምናል፡፡ እኔ ከያሬድ ተስፋዬ ጋር ሰሞኑን ጭውውት ሳደርግ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሁሉ ወሬያቸው ነገ ብሄራዊ ቡድናችን ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ እንደሚሆን ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ያሬድ ተስፋዬም ያወጋኝ ስለዚሁ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ብሄራዊ ቡድኑ አባላትና ስለእግር ኳስና ስለነገው ግጥሚያ የተጨዋወትነውን እነሆ፡፡
ነገ ዋልያዎቹ ከባፋና ባፋና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ምን ትጠብቃለህ?
ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚደረገው ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ዋልያዎቹ በዚህ ግጥሚያ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሚገቡት ወደ ጦርነት ሜዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአገራቸውን ገፅታ የሚለውጡበት፣ የህዝባቸውን አንድነት የሚያጠናክሩበት፣ የኢትዮጵያውያን የዕድገት ተስፋ የሚያለመልሙበት ውጤት ነው የምጠብቀው፡፡
በነገው ጨዋታ የሚገኝ ውጤት እኮ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ያስችላል ማለት አይደለም፡፡ የነገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ቢወጣ እንኳን ቡድኑን ገና ሌላ ምእራፍ ይጠብቀዋል ፡፡ ከአፍሪካ 10 ሃያል ቡድኖች አንዱ ሆኖ ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው የደርሶ መልስ ጨዋታ ላይ ውጤት ማምጣት የዋልያዎቹ ፈተና ይሆናል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ወሳኝነት ታዲያ ምኑ ላይ ነው?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን አሸንፎ፣ ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ውድድር ከሚበቁ የአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን መብቃቱ ያጓጓል፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫ የሚያሳልፈው የ10 ብሄራዊ ቡድኖች የደርሶ መልስ ትንቅንቅ የነገውን ወሳኝ ፍልሚያ በድል በማጠናቀቅ የሚደረስበት ምእራፍ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ የነገውን ጨዋታ በድል ለመወጣት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ስለነገው ነው ማሰብ ያለበት፡፡ ቀጣዩ ጨዋታ ከማን ጋር እንደሚሆን በማናውቀው ጉዳይ ላይ ማሰብ የለብንም፡፡ የነገውን ማሸነፍ ዓለም ዋንጫ እንደመግባት እንዲቆጥሩት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ወሳኝ ምእራፍ አለ ብሎ መግባት ጥሩ አይሆንም፡፡ የነገውን ወሳኝ ጨዋታ አሸንፎ በማለፍ ነው ለመጨረሻው ምእራፍ የሚደረሰው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ተስፋ ተፈጥሮ መሸነፍ ማለት ለተጫዋቾቹም ሆነ ለስፖርት አፍቃሪው ሞራል የሚነካ ነው፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር 1ለ1 ከሜዳው ውጭ አቻ ወጥቶ የተመለሰ ቡድን፣ እዚህ አገሩ ላይ የሚሸነፍበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም፡፡
ዋልያዎቹ ለዚሁ ወሳኝ ጨዋታ ምን ማድረግ አለባቸው? በእርግጥ በደጋፊያቸው ፊት እንደመጫወታቸው ማሸነፍ እንደሚችሉ ለመገመት አይከብድም፡፡ ይሁንና የጨዋታው ወሳኝነት የሚፈጥረው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ደቡብ አፍሪካ በዚሁ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በከፍተኛ ፍላጎት ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ከሳምንት በፊት ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን 3ለ0 ማሸነፏም ስጋት መፍጠሩ አይቀርም ፡፡ አንተ እንደ ስፖርት አፍቃሪ፤ እንደ ቀድሞ ኳስ ተጨዋችነትህ እና ከነበረህ ልምድ አንፃር ምን ትላለህ?
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች እና አባላት ከፍተኛ የሞራል መነቃቃት እና ትኩረት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጨዋታው እያንዳንዷን ኳስ ለ90 ደቂቃዎች አሸንፈው መጫወት አለባቸው፡፡ ኳስ ከተነጠቁ መንጠቅ፣ ከነጠቁ ደግሞ ወደ ተግባር መለወጥ አለባቸው፡፡ እያንዳንዷን ኳስ ለማሸነፍ መፋለም አለባቸው፡፡ ኳሷን ማሸነፍ ማለት ለእያንዳንዷ ኳስ ትኩረት መስጠት ነው፡፡

በእያንዳንዷ ቅፅበት ያለውን ሁኔታ ሁሉም ተጨዋቾች እኩል ትኩረት በመስጠት ሙሉ 90 ደቂቃዎችን መጫወት አለባቸው፡፡ ዋልያዎቹ ጨዋታቸውን እዚህ አገራቸው እንደማድረጋቸው፤ ፊሽካ ከተነፋባት የመጀመርያዋ ደቂቃ አንስቶ ጫና ፈጥረው መጫወት አለባቸው፡፡ በሜዳቸው እየተጫወቱ መከላከል የለባቸውም፡፡ አገር ላይ መጫወት ያለው ጥቅም ለማግባት መጫወት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ቡድን ከኢትዮጵያ የምድቡን መሪነት ለመንጠቅ ከጅምሩ የሚጫወተው በማጥቃት ስለሚሆን፤ ያን በመከላከል ለማቆም መሞከር ለተደጋጋሚ ጥቃቶች ራስን ማጋለጥ ነው፡፡ ለማሸነፍ ማግባት አለብን፡፡ ለማግባት ደግሞ ማጥቃት አለብን፡፡ ዋልያዎቹ ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በምድቡ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ከሜዳው ውጭ ስለሚያደርገው ጨዋታ በፍፁም ማሰብ የለበትም፡፡ በነገው ጨዋታ ውጤቱን አሳምሮ ምድቡን በመሪነት ለመጨረስ መታሰብ አለበት፡፡ ማንም ተጨዋች ግጥሚያው የአገር ጉዳይ መሆኑን አምኖ መቶ በመቶ ብቃቱን ማሳየት አለበት፡፡ ይህን ለመወጣት የማይችል፤ በቂ እና የተሟላ ብቃት ለእለቱ ማበርከት እንደማይችል የሚያስብ ተጨዋች ካለ፣ ከእኔ ይልቅ እከሌ ቢገባ ይሻላል ብሎ በግልፅ ሃሳቡን ለአሰልጣኙ ማንፀባረቅ አለበት፡፡ ይህ ወሳኝ ምእራፍ የሙከራ ጊዜ አይደለም፡፡ ሜዳ የሚገቡ ተጨዋቾችም ያላቸውን ሙሉ ብቃት በመጠቀም፤ የላቀ የቡድን ስራ እና ቁርጠኝነት በማሳየት አስፈላጊውን ውጤት ለማስመዝገብ በልበሙሉነት መሰለፍ አለባቸው፡፡ ለብሔራዊ ቡድኑ ዋናው የስነልቦና ጥንካሬ የሚሆነው ለግጥሚያው በቂ ትኩረት ከማድረግ ባሻገር ለተጋጣሚው ቡድን ቀላል ግን ጠንቃቃ ግምት መስጠት ነው፡፡
ምንም አይነት ስህተት መሠራት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካን በሜዳዋ ገጥሞ 1ለ1 አቻ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በርግጥ በዚያ ጨዋታ የተገኘው ውጤት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስታድዬም ገብተው ለዋልያዎቹ የሰጡት ድጋፍ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ በነገው ጨዋታ ግን ዋልያዎቹ በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ይበልጥ የጨመረ ይሆናል፡፡ ሌላው ለዋልያዎቹ የስነልቦና ጥንካሬ የሚሆነው የሚያስመዘግቡት ውጤት ትልቅ የታሪክ ምእራፍ መሆኑን ማሰብ ነው፡፡ ሁሉም የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ከሰሞኑ ዝግጅታቸውም በላይ ዛሬ ልዩ ትኩረት እና በምክክር የተደገፈ የመጨረሻ ዝግጅት ያድርጉ፡፡ በቂ ልምምድ ሰርተውና ጥሩ እረፍት አድርገው ለነገው ፍልሚያ በተነቃቃ ስሜት፤ በጥሩ የአካል ብቃት እና ቅልጥፍና ተሳስበው በአገር ፍቅር ስሜት መስራት አለባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሸነፍ ይችል ዘንድ እንደ ተመልካች ምን አይነት ሃሳቦችን ትሰጣለህ?
ለማሸነፍ ከተፈለገ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን መተግበር አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ እነዚህ ተግባራዊ ሲደረጉ የማሸነፍ እድሉ 99 በመቶ ይሆናል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ማንኛውም ተጨዋች ያለበትን የስነልቦና ችግር ከአሰልጣኙ ጋር ከተወያየ እና በግልፅነት ከተመካከረ ለአገር የሚሆን ውጤት ያስገኛል፡፡ ሁለተኛ 90 ደቂቃዎቹን በሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ በመንቀሳቀስ ከተጫወተ ግጥሚያውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ይችላል፡፡ ሶስተኛ የቡድኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች የሚሰጧቸውን ያለቁ ኳሶች አማራጭ እንደሌለ በማሰብ ሌላ እድል አገኛለሁ በማለት ሳይዘናጉ፣ ከመጀመርያው ያገኟትን ኳስ ወደ ግብ መሬት አሲይዘው ከሞከሩ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አጥቂዎች ወደ ጎል የሚሞክሯቸውን ኳሶች መሬት አስይዘው ይምቱ የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
ከመረብ የመዋሃድ እድል ያላቸው ኳሶች መሬት ለመሬት የሚመቱ ናቸው፡፡ ወደ ላይ የሚነሳ ኳስ የመግባት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ አጥቂዎች አንድ እድል ሲያገኙ አንድ ጎል ለማግባት ማሰብ አለባቸው፡፡ ይህ አይነቱን ሙከራ ለሙሉ 90 ደቂቃዎች መቀጠል ደግሞ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካየኋቸው ለውጦች የመጀመሪያው የአጥቂዎች የአጨራረስ ብቃት ማደግ ነው፡፡ ዛሬ በብሔራዊ ቡድን ያሉ አጥቂዎች ጐል የማግባት ብቃታቸውና በቅጽበታዊ ውሳኔ ውጤት የማግኘት ክህሎታቸው ተለውጧል፡፡ በተለይ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አጥቂዎች ጐል የማስቆጠር ድፍረት ማዳበራቸው ጉልህ ለውጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውጤት እያማረ እና እየተለወጠ የመጣው የአጥቂዎች አጨራረስ ዕድገት በማሳየቱ ነው፡፡ ለዚህ የአጥቂዎች ውጤታማነት ፈር ቀዳጅነት ሚና የተጫወተው ሳላሃዲን ሰኢድ ነው፡፡ የእሱ የአጨራረስ ድፍረት እና በየግጥሚያዎቹ የሚያስቆጥራቸው ወሳኝ ጐሎች ብሔራዊ ቡድን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሌሎች በሱ መስመር የሚሰለፉ የቡድኑ ተጨዋቾችን በማነቃቃትም አርአያ ሆኗል፡፡
የነገው ጨዋታ በድል ተጠናቀቀ እንበል፤ ቀጣዩ ወሳኝ ምእራፍ ከዚያ በኋላ ይመጣል፡፡ አሁን ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደሚገልፁት፣ የኢትዮጵያ ጊዜ ሆኖ ብሄራዊ ቡድኑ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ቢያልፍ ስኬቱ ምን ትርጉም ይኖራዋል?
የማንም ተጨዋች፣ የየትኛውም እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ አገር ህልምና ተስፋ የዓለም ዋንጫን መሳተፍ ነው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ መቻል የእግር ኳሱን እድገት በአስደናቂ ሁኔታ የሚያፋጥነው ይሆናል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ሲያልፍ ለስፖርቱ ዕድገት በር ከፋች የሚሆኑ በርካታ እድሎች እና ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ካለፈ በኋላ በአገሪቱ በሚካሄደው የሊግ ውድድር ከፍተኛ የሆነ የፉክክር ደረጃ ይፈጠራል፡፡ ይህም ክለቦች በበቂ ሁኔታ ተደራጅተው እና በተጨዋቾች ስብስብ ተጠናክረው ወደ ውድድር የሚገቡበትን ሁኔታ ያነቃቃል፡፡ በየክለቡ ያሉ ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫ በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ ከፍተኛ ትጋትና ብቃት ማሳየታቸውም ሌላው ለውጥ ነው፡፡
ባለሀብቶች የአገሪቱ እግር ኳስ ለዓለም ዋንጫ በመብቃቱ በስፖርቱ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ፣ ክለቦችን በመግዛት እና በገንዘብ በመደገፍ ለመስራት በቀላሉ የሚነሳሱበትን ሁኔታም ይፈጥራል፡፡ ኩባንያዎች የተሰማሩባቸውን የኢንቨስትመንት መስኮች ለማስተዋወቅና ከስፖርቱ ለውጥ ጋር የንግድና የእድገት እንቅስቃሴያቸውን ለማስተሳሰር ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ ስታድዬሞችም በስፖርት አፍቃሪዎች መጥለቅለቃቸው አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል ህዝብ ወደ ስታድዬሞች የሚተመው በዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ተጨዋቾችን ለመመልከት ስለሚሆን ነው፡፡ የዓለም ዋንጫው ስኬት የመንግስትንም ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በአፋጣኝ እንዲያልቁም ያበረታታል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ውጤቱ መንግስትና ህዝብን በማገናኘት ለአገር ልማት እና እድገት በጋራ መተሳሰብ እና በበጎ ስሜት እንዲሰሩ ተፅእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ለዓለም ዋንጫ ማለፍ ማለት በውስጥም ሆነ በውጭ የአገርን ገጽታ ሊቀይር የሚችል ነው፡፡

Read 3546 times