Saturday, 15 June 2013 12:12

በዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ጊዜ እየመጣ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(8 votes)

በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ዞን ለሚደረገው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ ለማለፍ ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካን በወሳኝ ግጥሚያ ሊገናኝ ነው፡፡ በ10 ምድቦች በሚደረገው የአፍሪካ የምድብ ማጣርያ በ5ኛ ዙር ግጥሚያዎች ሲቀጥል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ ደቡብ አፍሪካን የሚያሸንፍ ከሆነ 10 ቡድኖች ለሚሳተፉበት እና የአፍሪካን ተወካይ 5 ብሄራዊ ቡድኖች ለሚለየው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ ማለፉን ያረጋግጣል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በዚሁ ጨዋታ የኢትዮጵያን መሪነት በመንጠቅ ከምድብ 1 የሚያልፈው ቡድን በምድብ ማጣርያው የመጨረሻ 6ኛ ዙር ግጥሚያዎች እንዲወሰን ተስፋ ታደርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ ድል ካደረገ ምድብ 1 በመሪነት ማጠናቀቁን ከ6ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያዎች በፊት የሚያረጋግጥ ሲሆን ከሜዳው ውጭ ከሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ መርሃ ግብሩን ለመጨረስ ብቻ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ከሳምንት በፊት በምድብ 1 የ4ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያዎች ላይ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጭ ቦትስዋናን 2ለ1 በማሸፍ መሪነቷን ስታጠናክር፤ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ሳላሃዲን ሰኢድ እና ጌታነህ ከበደ ደግሞ በምድብ ማጣርያው የኮከብ ግብ አግቢዎች ደረጃ መሪነቱን ይዘዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በካሜሮኗ ከተማ ያውንዴ ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክን 3ለ0 በማሸነፍ በነገው ጨዋታ ኢትዮጵያን የምትፎካከርበትን ተስፋ አለምልማለለች፡፡

ከኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያዎች በፊት ኢትዮጵያ በምድቧ ባደረጋቻቸው 4 ጨዋታዎች 3 ድልና 1 አቻ ውጤት በማስመዝገብ በ10 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ ስትመራ ደቡብ አፍሪካ በ8 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ በ2ኛ ደረጃ ትከተላለች፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ በካሜሮን ያውንዴ ቆይታ ነበረው፡፡ ከትናንት በስቲያ በዱዋላ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ያደረጉት ባፋና ባፋናዎች ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ለነገው ጨዋታ ደግሞ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም የመጨረሻ ልምምድ ይሠራሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት ኢትዮጵያ ቦትስዋናን 2ለ1 ያሸነፈችበትን ጨዋታ ቪድዮ በትኩረት ሲያጠኑ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በነገው ጨዋታ ኢትዮጵያን ባልተጠበቀ ብቃት በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ሊነጥቅ እንደሚችል አንዳንድ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃናት ሁኔታውን በመሪ ርእስ በመግለፅ ቢዘግቡም ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ ኢትዮጵያ በሜዳዋ በከፍተኛ ብልጫ አሸንፋ ምድቡን በመሪነት ማጠናቀቋን እንደምታረጋግጥ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ጊዜው የኢትዮጵያ ሊሆን እንደሚችል በመገመት ትንተናቸውን አሰራጭተዋል፡፡

በነገው ጨዋታ ዙርያ ለአንባቢዎቹ የውጤት ግምት እንዲሰጡ እድል ሰጥቶ የውጤት ትንበያዎችን በድረገፁ ይፋ ያደረገው ጎል የአሸናፊነቱ እድል በሜዳዋ ለምትጫወተው ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ማጋደሉን አመልክቷል፡፡ በጎል ድረገፅ በቀረቡ 3 ዋና የውጤት ትንበያዎች መሰረት ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ0 እንደምታሸንፍ የገመቱ 33.9 በመቶ፤ 3ለ1 እንደምታሸንፍ የገመቱ 16.95 በመቶ እንዲሁም 2ለ1 እንደምታሸንፍ የገመቱ 15.25 በመቶ የድምፅ ድርሻ ወስደዋል፡፡ ከዓመት በፊት በምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ግጥሚያ ደቡብ አፍሪካ በሜዳዋ ሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም ኢትዮጵያን ባስተናገደችበት ወቅት ግጥሚያው 1ለ1 አቻ ተለያይተውበታል ይህ ውጤት ደቡብ አፍሪካ ለአራተኛ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የነበራትን ዓላማ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ከመሆኑም በላይ የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሃላፊዎችን ለውዝግብ ከመዳረጉም በላይ በወቅቱ የባፋና ባፋና አሰልጣኝ ለነበሩት ፒትሶ ሞሲማኔ መባረር መንስኤ እንደነበር ይታወሣል፡፡ በነገው ጨዋታ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በኢትዮጵያ ከተሸነፈ ምናልባትም ለ56 ዓመቱ አሰልጣኝ ጎርደን ሌጀሰንድ መባረር ምክንያት እንደሚሆን እየተገለፀም ነው፡፡

የባፋና ባፋና ተጨዋቾች ለወሳኙ ጨዋታ ስላደረጉት ዝግጅት እና ስለሚጠብቃቸው ፈተና ሰሞኑን ሲናገሩ የሰነበቱ ሲሆን ከእነሱም መካከከል አጥቂው ቶኬሎ ራንቲ እና አማካዩ ሲፍዌ ሻባላላ ይጠቀሳሉ፡፡ የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ቶኬሎ፤ ራንቲ በሰጠው አስተያየት‹ በወሳኙ ጨዋታ ላይ ማግኘት ያለብንን ውጤት ማንም ሊያስታውሰን ወይም በግፊት ሊያስረዳን አይገባም፡፡ ማሸነፍ የሚኖረውን ጠቀሜታ ሁላችንም ስለምናውቅ መነሳሳታችን አይቀርም› ሲል ተናግሯል፡፡ የነገውን ጨዋታ የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው ያለው አጥቂው ቶኬሎ ግጥሚያው የምንሰጥምበት ወይም የምንዋኝበት ነውም ብሏል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከ2 ዓመት በፊት ባስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ የውድደሩን የመክፈቻ ግብ ያስቆጠረው አማካዩ ሲፍዌ ሻባላላ በበኩሉ‹ የኢትዮጵያ ቡድን ካለው ወቅታዊ አቋምና በሜዳው ከመጫወቱ አንፃር የማይበገር ሊሆን ይችላል፡፡

በደጋፊያቸው ፊት በመጫወታቸው ከጨዋታው መጀመርያ ፊሽካ አንስቶ በከፍተኛ ወረራ ሊያጠቁን ይችላሉ፡፡ በዚህ ሳንሸበር ተረጋግተን ጨዋታውን ለመቆጣጠር በመትጋት የምንፈልገውን ውጤት ለማግኘት በህብረት እንሰራለን› ሲል አስተያየቱን ተናግሯል፡፡ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ የአፍሪካ ዞን የምድብ ማጣርያ ከዓመት በፊት ሲጀመር ስለምድብ 1 ብሄራዊ ቡድኖች ባቀረበው ትንተና ምድቡን በመሪነት ለማጠናቀቅ እድል ያላት ደቡብ አፍሪካ እንደሆነች ገልፆ ነበር ያልተጠበቀ ውጤት የምታስመዘግበው ቦትስዋና እንደሆነች ያመለከተው ድረገፁ የምድቡን አላፊ የሚወስነው ወሳኝ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና የሚያደርጉት ፍልሚያ እንደሆነም አብራርቶ ነበር፡፡

ከ1 ዓመት በኋላ የምድብ ማጣርያው ጉዞ በኋላ ግን የፊፋ ኦፊሴላዊ ድረገፅ እንደገመተው ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህን ግምት ፉርሽ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውጤታማነት ሲሆን ከምድቡ በመሪነት ለማለፍ ሰፊ እድል ከመያዙ ባሻገር የምድቡን አላፊ የሚወስነው ጨዋታ ነገ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ የሚገናኙበት ጨዋታ ሆኗል፡፡ በአፍሪካ ዞን በሚቀጥሉት የ5ኛ ዙር የምድብ ማጣርያዎች በምድብ 1 እንደምትገኘው ኢትዮጵያ ከመጨረሻው ዙር የምድብ ማጣርያ ግጥሚያ በፊት በየምድባቸው በመሪነት ለመጨረስ እድል ያላቸው ሶስት አገራት በምድብ 7 ግብፅ፤ በምድብ 2 ቱኒዚያ እና በምድብ 10 ሴኔጋል ናቸው፡፡ በተቀረ በምድብ 3 ኮትዲቯር ወይም ሞሮኮ፤ በምድብ 4 ጋና ወይም ዛምቢያ፤ በምድብ 5 ጋቦን ወይም ቦትስዋና፤ በምድብ 6 ናይጄርያ፤ በምድብ 8 አልጄርያ እንዲሁም በምድብ 9 ካሜሮን በመሪነት የምድብ ማጣርያውን ለማጠናቀቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ብራዚል ከዓመት በኋላ ለምታስተናግደው 20ኛው ዓለም ዋንጫ አፍሪካን ለመወከል እንደሚበቁ ግምት ካገኙ 5 ብሄራዊ ቡድኖች ደቡብ አፍሪካ ብዙ ግምት ያገኘች ነበረች፡፡

ከ10000 በላይ የውጤት ሁኔታዎችን በማገናዘብ እና በማስላት በአንድ ድረገፅ በቀረበ ትንበያ ደቡብ አፍሪካ ለዓለም ዋንጫው ያላት የማለፍ እድል 23.77 በመቶ ሲገመት ለኢትዮጵያ የተሰጠው ግምት ግን 5.8 በመቶ ነው፡፡ በሌላ በኩል አንድ የስፖርት ዘገባ በሰራው ግምታዊ ትንተና ወደ ዓለም ዋንጫው የሚያልፉ 5 ብሄራዊ ቡድኖችን ለመለየት በሚያስችለው የምድብ ማጣርያው በመሪነት ሊያልፉ የሚችሉትን 10 ብሄራዊ ቡድኖች ሲገምት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንንም አካትቷል፡፡ ይሄው ድረገፅ ለዓለም ዋንጫው የመጨረሻ ዙር የደርሶ መልስ ማጣርያ የሚያልፉ ቡድኖችን ዘርዝሮ ድልድሉ በሁለት ምድብ ሲከፍል በመጀመርያው በፊፋ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ኮትዲቯር፤ ናይጄርያ፤ አልጄርያ፤ ቱኒዚያ እና ዛምቢያን በሌላ ምድብ ደግሞ ካሜሮን፤ ግብፅ፤ ሴኔጋል፤ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምቷል፡፡

Read 5597 times