Saturday, 15 June 2013 12:15

አምባገነንነትን በነፃነት ትግል ውስጥ የደበቁ መሪ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

አፍሪካ የመጀመሪያውን የነፃነት ዳንሷን ትደንስ በነበረበት በ1960ዎቹ የመጀመሪያ አመታት ሴዳር ሴንጐር፣ ሁፌት ቧኘ፣ ክዋሜ ንክሩማህ፣ ጋማል አብደል ናስር፣ አህመድ ሴኩቱሬ፣ ሞዲቦ ኬታ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ጁልየስ ኔሬሬ፣ ካሙዙ ባንዳና የመሳሠሉ መሪዎች ነበሯት፡፡ መስራች አባቶችና የአፍሪካ የመጀመሪያው ትውልድ መሪዎች የሚል የተለየ መጠሪያ ያተረፉት እነዚህ መሪዎች ታላቅ ክብርና ዝና የተጐናፀፉ ነበሩ፡፡ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑትን የአፍሪካ ሀገራት ለበርካታ ዘመናት ሰጥለጥ አድርገውና አንበርክከው በቅኝነት ከገዙት ሁለት የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች አንዷ ፈረንሳይ ናት፡፡ “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል” ካልተባለ በስተቀር የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ዘይቤ “አመሳስለህ ግዛ (Assimilation) በመባል የሚታወቅና ዋነኛ የቅኝ አገዛዝ ተፎካካሪዋ ከነበረችው ከእንግሊዝ “የከፋፍለህ ግዛ” የቅኝ አገዛዝ ዘይቤ የተለየ ነበር፡፡

ፈረንሳይ በቅኝ አገዛዟ ስር የነበሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምዕራብ አፍሪካ ዜጐችን “አመሳስለህ ግዛ” በሚለው የአገዛዝ ዘይቤዋ አማካኝነት “እናንተ ጥቁር ሆናችሁ እንጂ ፈረንሳውያን ናችሁ እኮ! … ባለ ጥቁር ቆዳ ፈረንሳያውያን!” እያለች ታጃጅላቸው ነበር፡፡ በ1958 ዓ.ም የፈረንሳይ የአራተኛው ሪፐብሊክ መንግስት ፈርሶ ስልጣን እንደለቀቀ፣ በፕሬዚዳንት ሻርል ደጐል የሚመራው የአምስተኛው ሪፐብሊክ መንግስት ስልጣኑን ያዘ፡፡ አዲሱ የፕሬዚዳንት ደጐል መንግስትም በመላ አፍሪካ ቀስ በቀስ እየተቀጣጠለ የመጣውን የነፃነት ትግል የመጨረሻ መዳረሻውን በሚገባ በመገምገም፣ በምዕራብ አፍሪካ ያለውን የቅኝ ግዛት የበላይነትና ብሔራዊ ጥቅሙን ጠብቆ ለማቆየት ያስችለኛል ያለውን አዲስ አይነት ስልት ቀየሰ፡፡ በዚህም መሠረት የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ እንዲመሠረት የሚጠይቅ አንቀጽ የተካተተበትን አዲስ ህገ መንግስት ስልጣን በያዘበት አመት አርቅቆ አቀረበ፡፡

ይህንን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ደጐል፣ የፈረንሳይ ቅኝ የሆኑ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መስከረም 28 ቀን 1958 ዓ.ም በህገመንግስቱ ላይ ህዝበ-ውሳኔ በማካሄድ፣ የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ መመስረትን ይደግፉ አይደግፉ እንዲያሳውቁ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የፕሬዚዳንት ደጐል ትዕዛዝ የፈረንሳይ ቅኝ ለነበሩት በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ቀላል አልነበረም፡፡ ህዝበ-ውሳኔውም ተራ ህዝበ-ውሳኔ አይደለም፡፡ ፈረንሳይ ልትመሠርተው ያቀደችው የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ አባል ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት የሚፈቅደው የውስጥ አስተዳደር ነፃነትን ብቻ እንጂ የሚኖሩት በፈረንሳይ ሉአላዊነትና የበላይነት ስር በመሆን ነው፡፡ የዚህ ኮሙኒቲ አባል ለመሆን በጄ የማይልና የማይቀበል ሀገር ግን ነፃነቱን መጐናፀፍ ቢችልም ከፈረንሳይ መንግስት ሽራፊ ሳንቲም ማግኘት አይችልም፡፡

ፕሬዚዳንት ደጐል፤ በቅኝ አገዛዝ ሀገራቸው ለምታስተዳድራቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ያቀረቡት ምርጫ ከእነዚህ ሁለቱ አንዱን መምረጥ ነበር፡፡ ለፈረንሳይ መንግስት ባላቸው ታላቅ ከበሬታና ታማኝነት እንዲሁም የፈረንሳይን እርዳታ ላለማጣት ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጐት የተነሳ፣ በፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ስር ከነበሩትና ህዝበ ውሳኔውን መስከረም 28 ቀን 1958 ዓ.ም ካካሄዱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ አብዛኞቹ ህዝበ ውሳኔውን በመደገፍ፣ የአዲሱ የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ አባል ለመሆን ድምፃቸውን ሰጡ፡፡ “የፈረንሳይ እርዳታ ባፍንጫዬ ይውጣ! ነፃነት ወይም ሞት!” በሚል የፈረንሳይን ህገመንግስት በህዝበ ውሳኔ በመቃወም ነፃነቷን ለመጐናፀፍና ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ብቻዋን የቆመችው ምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር ጊኒ ነበረች፡፡ ከዚህ አቋምና ውሳኔ ጀርባ የነበሩት ግንባር ቀደም ታጋይ መሪ ደግሞ ጐልማሳው አህመድ ሴኩቱሬ ነበሩ፡፡

የጊኒ የነፃነት ትግልና የመጀመሪያው የጊኒ የድህረ ነፃነት መሪ የነበሩት አህመድ ሴኩቴሬ፤ በወቅቱ ከነበሩት የምዕራብ አፍሪካ የመጀመሪያው ትውልድ መሪዎች ጋር ሲወዳደሩ በአብዛኛው የተለዩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ፈረንሳይ “ባለጥቁር ቆዳ ፈረንሳዊ የበኩር ልጆች” እያለች በፍቅር ታንቆለጳጵሰውና በመንግስቷ ውስጥ የምኒስትርነት ማዕረግ አጐናጽፋቸው ከነበሩት ከሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ሴዳር ሴንጐርና ከኮትዲቯሩ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሁፌት ቧኘ ጋር የሚመሳሰሉ አልነበሩም፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ እንደ ሴንጐርና ሁፌት ቧኘ ከሀብታም ቤተሠብ የተወለዱና የታወቁ ቱጃር አልነበሩም፡፡ ይልቁንስ ብን ካለ መናጢ ደሀ ቤተሠብ የተገኙና የልጅነት እንዲሁም የአፍላ ጉርምስና ጊዜአቸውን በከፋ ድህነት ውሰጥ ያሳለፉ መሪ ነበሩ፡፡ ሴኩቱሬ እንደ ሴንጐርና ሁፌት ቧኘ በፈረንሳይና በሴኔጋል በሚገኙ ምርጥ የፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተማሩ ያደጉ ሰውም አልነበሩም፡፡ በአመለካከታቸውም ቢሆን “ባለ ጥቁሩ ቆዳ ፈረንሳዊ” የሚለውን የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ እምነትና አስተሳሠብ አጥብቀው የሚቃወሙ የለየላቸው የጊኒ ብሔርተኛና ፓን አፍሪካኒስት መሪ ነበሩ፡፡

በፖለቲካውም ረገድ ጠንካራ ፀረ ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ አቋም የነበራቸውና ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ በመላቀቅ፣ ነፃነታቸውን ለመጐናፀፍና ለኡላዊነታቸውን ለማስከበር የጣሩ መሪ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ፤ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድም ቢሆን ሴንጐርና ሁፌት ቧኘ በመጡበትና በአንፃራዊነት የተሻለና ደልዳላ በነበረው የአፍሪካ ልሂቃን ዝግ የፖለቲካ አለም አማካኝነት ሳይሆን ረጅም፣ ወጣ ገባና፣ አስቸጋሪ በነበረው የሰራተኛ ማህበራት ፖለቲካ በኩል ነበር፡፡ የጊኒን የሠራተኛ ማህበራት መሠረት በማድረግ የጊኒን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ጊዲፓ) ጠንካራ የህዝብ ንቅናቄ ፓርቲ እንዲሆን በሚገባ አስችለውታል፡፡ ይሄው ፓርቲያቸው በ1957 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ምርጫ፤ ከስልሳ መቀመጫዎች ሀምሳ አምስቱን እንዲያሸንፉ በማድረጋቸው፣ ገና በሰላሳ አምስት አመት የጐልማሳነት እድሜአቸው የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ችለዋል፡፡ የለየላቸው የክዋሜ ንክሩማህ አድናቂ የነበሩት ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ከፈረንሳይ የፍራንኮ አፍሪካ ኮሙኒቲ ይልቅ ለፓን አፍሪካን አንድነት መመስረት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙ መሪ ነበሩ፡፡

በዚህ አቋማቸው የተነሳም የፕሬዚዳንት ደጐልን እቅድ “አዲስ የንግድ ምልክት የተለጠፈበት የድሮ ያረጀ ሸቀጥ ነው” በማለት በሰላ ሂስ ይተቹና ይነቅፉ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ደጐል ያቀረቡትን ህገ መንግስት፣ የፈረንሳይ ቅኝ የሆኑ የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት በህዝበ ውሳኔ እንዲደግፍ ሲያደርጉት የነበረውን ቅስቀሳ አጠናቀው ነሀሴ 25 ቀን 1958 ዓ.ም የጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ ሲገቡ፣ ጠቅላይ ምኒስትር ሴኩቱሬ የተቀበሏቸው ከአየር ማረፊያው እስከ ቤተ መንግስቱ ድረስ ባለው ረጅም አውራ ጐዳና ግራና ቀኝ “ነፃነት! ነፃነት! ነፃነት ወይም ሞት!” እያሉ በከፍተኛ ድምጽ መፈክር የሚያሰሙ ጊኒያውያንን በማሰለፍ ነበር፡፡ ለፕሬዚዳንት ደጐል ክብር ተብሎ እድሜ ጠገብ በሆነው ነጩ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው ልዩ ስነስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የፈረንሳይን የቅኝ አገዛዝ ታሪክ እየዘረዘሩ፣ ጊኒ የፍራንኮ አፍሪካ ኮሙኒቲን ከመቀላቀሏ አስቀድሞ ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በመሉ ነፃ መሆን እንደምትሻ አቋማቸውን በማያሻማ ቋንቋ በግልጽ አሳወቁ፡፡ ቀጠሉናም ከፊትለፊታቸው የቀመጡትን የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ደጐልን በጣታቸው እያመለከቱ፣ በወቅቱ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ውስጥ በዋናነት ጐልቶ የሚጠቀሰውንና እሳቸውንም የግንባር ቀደም ፀረ ቅኝ አገዛዝና የነፃነት ታጋይ ክብር ያጐናፀፋቸውን ንግግር ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ሴኩቱሬ፣ በከፍተኛ ስሜት ተውጠው “እኛ ጊኒአውያን በባርነት ከሚገኝ ምቾትና ድሎት ይልቅ ነፃነታችንን ተጐናጽፈን ብንራብ ይሻለናል” በማለት ተናገሩ፡፡

ከፕሬዚዳንት ደጐልና አብረዋቸው ከነበሩት ረዳቶቻቸው በስተቀር በአዳራሹ የነበሩት ጊኒአውያን ከመቀመጫቸው በመነሳት በከፍተኛ የድጋፍ ስሜት ለደቂቃዎች ያልተቋረጠ ጭብጨባ አጨበጨቡላቸው፣ ጭብጨባው ጋብ እንዳለም ሴኩቱሬ ድምፃቸውን ከፍ አድርገውና የግራ እጃቸውን ጨብጠው ወደ ላይ በማንሳት “ነፃነት! ነፃነት! ነፃነታችንን አሁኑኑ! ነፃነት ወይም ሞት!” በማለት መፈክራቸውን በመደጋገም አሰሙ፡፡ የስብሰባው አዳራሽ በከፍተኛ የድጋፍ ጩኸትና ጭብጨባ በድጋሚ ለደቂቃዎች ተናወጠ፡፡ የሴኩቱሬን ንግግር በሬዲዮ ያዳመጡና በስሚ ስሚ የደረሳቸው ጊኒአውያን ከያሉበት በመሰባሰብ በአውራ ጐዳናዎች ላይ “ነፃነት! አሁኑኑ ነፃነት ወይም ሞት! ከባርነት ምቾት ይልቅ የነፃነት ረሀብ ይሻለናል!” እያሉ መፈክር በማሰማት፣ በተለይ ዋና ከተማዋን ኮናክሪን ቀውጢ አድርገዋት አመሹ፡፡ መስከረም 28 ቀን 1958 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔም ጊኒያውያን በጠቅላይ ምኒስትር አህመድ ሴኩቱሬ እየተመሩ ለፍራንኮ - አፍሪካ ኮሙኒቲ መመስረት ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፃቸውን ሰጡ፡፡

ይህን ካደረጉ አራት ቀናት በሁዋላም ጥቅምት ሁለት ቀን 1958 ዓ.ም አህመድ ሴኩቱሬ፣ ጊኒ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ መላቀቋንና ነፃና ሉአላዊ ሀገር መሆኗን ለመላው ህዝባቸው አወጁ፡፡ ይህ የነፃነት አዋጅ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አንድ ቀናት በመላ ጊኒ የሆነው ነገር ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ መላ ጊኒያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በያሉበት በነቂስ በመውጣት “ነፃነት ለዘለአለም ይኑር! ከዘለአለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት! ሴኩቱሬ ማለት ነፃነት ማለት ነው! ሴኩቱሬ የነፃነታችን አባት ነው! ሴኩቱሬ ለዘለአለም ይኑር!” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት አውራጐዳናዎችንና አደባባዮችን አጣበዋቸው ከረሙ፡፡ እነዚህ መፈክሮች በቀይ ቀለም የተፃፈባቸውን ባነሮች በዋና ዋና አደባባዮችና አውራ ጐዳናዎች ላይ ሰቀሉ፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠር የሴኩቱሬ ምስል ያለባቸው ካናቴራ፣ ሸሚዝና ቀሚሶች ህፃን አዋቂ ሳይለይ በድፍን ጊኒ መሠራጩት ቻለ፡፡ እነዚህን ልብሶች የለበሱ ጊኒያውያንም ለቀናት ሴኩቱሬንና ነፃነትን የሚያሞግሱ የትግልና የድል መዝሙሮችን በመዘመር ሲደንሱ ባጁ፡፡ በጠቅላይ ምኒስትር ሴኩቱሬ ንግግር እጅግ እንደተዋረዱና የፕሬዚዳንትነት ክብራቸው ክፉኛ እንደተነካ የቆጠሩትና ከአብዛኞቹ የፈረንሳይ ቅኝ ከነበሩ የምዕራብ አፍራካ ሀገራት ተለይታ ጊኒ ነፃነቷን በመምረጧ ልባቸው ሀይለኛ ቂም የቋጠረው የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጐል፣ የበቀል ቅጣታቸውን በሴኩቱሬና በጊኒ ላይ ማሳረፍ የጀመሩት አገሪቷ ነፃነቷን እንዳወጀች አንዲት ቀን እንኳ ሳይውሉና ሳያድሩ ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ደጐል በመጀመሪያው ቀን በወሰዱት እርምጃ፣ ፈረንሳይ ለጊኒ የምትሰጠው ሰብአዊና የልማት እርዳታ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን የሚገልጽ ባለ ሶስት መስመር ደብዳቤ በመፃፍ ሴኩቱሬ ለሚመሩት አዲሱ የጊኒ መንግስት አስታወቁ፡፡ በሁለተኛው ቀንም ፈረንሳውያን የመንግስት ሰራተኞች፣ ህዝብና ሀገር በመጠበቅ ላይ የነበሩ ፈረንሳውያን ፖሊሶችና ወታደሮች፣ እንዲሁም ለጊኒያውያን የህክምና የአገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ወታደራዊና ሲቪል ዶክተሮች፣ ነርሶችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ጊኒን ለቀው ባስቸኳይ እንዲወጡ አዘዙ፡፡ በሶስተኛው ቀን ደግሞ ፈረንሳውያን ኢንጅነሮች፣ ቴክኒሻኖች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ባስቸኳይ ጊኒን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ትዕዛዙን ተከትለውም ሶስት ሺ የሚሆኑ ፈረንሳውያን ባለሙያዎች በአንድ ቀን መሸከም የሚችሉትን ንብረት ተሸክመው፣ ያልቻሉትን ደግሞ ሰባብረው ጊኒን ለቀው ወጡ፡፡ እነዚህም ሆኑ እነዚህን ተከትለው በተከታታይ ጊኒን ለቀው የወጡት ፈረንሳውያን ባለሙያዎች አወጣጣቸው ሰላማዊና ጤነኛ አወጣጥ አልነበረም፡፡ በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት፣ የመንግስትን ፋይሎችና መዛግብቶችን ሰብስበው አቃጠሉ፡፡

የቢሮ ወንበርና ጠረጴዛዎችን ሰባበሩ፡፡ ስልኮችን ነቃቀሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫና ማስተላለፊያ ገመዶችን መነቃቀልና መበጣጠስ ብቻ ሳይሆን አምፑሎችን ሳይቀር አወላልቀው ወሰዱ፡፡ ሲቪልና የጦር ሀይሉ ዶክተሮችም አንዲት ቅንጣት ክኒን ሳትቀር የነበረውን መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በሙሉ ሙልጭ አድርገው ጭነው ወጡ፡፡ የፖሊስ አባሎችም ከሚሰሩባቸው የፖሊስ ጣቢያ ቢሮዎች ነቅለው መውሰድ ያልቻሉትን በሮችና መስኮቶችን እንዳልነበሩ አድርገው ሰባበሯቸው፡፡ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም በተለያየ መንግስታዊና የግል የስራ መስክ ተሠማርተው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፈረንሳውያን ጊኒን ለቀው ጥርግ አሉ፡፡ ከወር በኋላ ኮቴአቸው ያስነሳው አቧራ ገለል ሲል የፕሬዚዳንታቸውን ትዕዛዝ በመጣስ ጊኒን ለቀው ላለመውጣት በመወሰን በበጐ ፈቃደኝነት ለማገልገል በኮንናሪ ከተማ የተገኙ ማተባቸውን ያልበጠሱ ፈረንሳውያን አንድ መቶ ሀምሳ ብቻ ነበሩ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጐል የሰነዘሩት የበቀል ዱላ በጊኒ ህዝብ ላይ ያሳረፈው ቁስል ህመሙ አንጀት የሚያንሰፈስፍ ነበር፡፡ ጊኒ ፈረንሳዮቹ ጥለዋት ሲወጡ እነሱን ተክቶ የሚያገለግል የተማረና በወጉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ጨርሶ አልነበራትም፡፡

ፕሬዚዳንት ደጐል ይህን እርምጃ የወሰዱትም የጊኒን ጠቅላላ ሁኔታ በደንብ ስለሚያውቁት ነበር፡፡ እናም ፈረንሳዮቹ ከያሉበት ተጠራርተው ጊኒን ጥለው ውልቅ ሲሉ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶች በአንዴ ተቋረጡ፡፡ የህዝብ ፀጥታና ደህንነት ጥበቃ ቆመ፡፡ የጊኒ ድንበርም ያለ አንዳች ጥበቃ ወናውን ቀረ፡፡ ጊኒ ከቅኝ ግዛት ተላቃ ነፃነቷን መጐናፀፏና ሉአላዊ ሀገር መሆን መቻሏ የፈጠረባትን ደስታ በወጉ እንኳ አጣጥማ ሳትጨርስ ብርክ ያዛት፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ እንደነገሩ የተጠጋገነ አንድ የቆዳ ወንበርና ያረጀ ጠረጴዛ ብቻ ባለው ኦና ቢሮአቸው ውስጥ ከወዲያ ወዲህ እየተንጐራደዱ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አጡ፡፡ ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት ደጐልን ከቅስቀሳ ዘመቻቸው ሲመለሱ ና ብለው ጠርተው፣ አዳራሽ ሙሉ ሰው በተሰበሠበበት የሰላ ትችትና ወቀሳ በማውረድ እንዳስቀየሟቸው ቢያውቁም፣ በጊኒና በእርሳቸው ላይ ጨክነው ይህን የመሰለ እጅግ አስከፊ ቅጣት ይጥላሉ ብለው ጨርሰው አልገመቱም ነበር፡፡ ቀሪውን ሳምንት እንመለስበታለን፡፡

Read 4566 times