Saturday, 22 June 2013 11:39

አህመድ ሴኩቱሬ የኢምፔሪያሊዝም ውጋት!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

        “ፓርቲው የህዝቡ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ የፓርቲው”

             የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል፤ ጊኒ ከሌሎች የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከነበሩ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተለይታ እቅዳቸውን በመቃወም ነፃነቷን በመምረጧና መሪዋ አህመድ ሴኩቱሬም ባደባባይ ክብራቸውን በማዋረድ ለፈጸሙት ድፍረት ተገቢ ነው ብለው የወሰዱት በተለያዩ የመንግስትና የግል የስራ መስኮች ተሰማርተው የነበሩትን ፈረንሳውያን ከጊኒ የማስወጣት የበቀል እርምጃ አለንጋው የጊኒና የሴኩቱሬን ጀርባ ሰምበር በሰምበር እንዳደረገውና ህመሙም ክፉኛ እንደቆጠቆጣቸው በሚገባ ተገንዝበውት ነበር፡፡ እናም ጊኒም ሆነ መሪው ሴኩቱሬ የበቀሉ አለንጋ የፈጠራቸውን ከፍተኛ የህመም ስሜት መቋቋም ስለማይችሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ “አባታችን ፓፓ ደጎል ወይ ! ሳናውቅ በስህተት አውቀንም በድፍረት በሰራነው ስህተት እጅግ በጣም ስላስቀየምንዎት ፤በተለምዶው ፈረንሳዊ የአባትነት ቸርና ሩህሩህ ልብዎ እባክህ ይቅር ይበሉን፤ ከዚህ በኋላ እንዲህ ያለ ድፍረት በፍፁም አይለምደንም! መጀን ለእርሶና ለታላቋ ፈረንሳይ አገዛዝ!” በማለት ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡

ከዚያም ያወጁትን ነፃነት በመቀልበስ ይመሰረታል የተባለው የፍራንኮ - አፍሪካ ኮሚኒቲ አባል በመሆን፣ በፈረንሳይ አገዛዝ ስር ለመኖር ይወስናሉ ብለው በእርግጠኛነት ጠብቀዋቸው ነበር፡፡ ለፕሬዝዳንት አህመድ ሴኩቱሬ ግን ይህ የሚሞከር ሳይሆን ጭራሽኑ የሚታሰብ ነገር አልነበረም፡፡ ያጋጠማቸው ፈርጀ ብዙና ውስብስብ ችግሮች ከፍተው ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆኑ በውስጣቸው የተፈጠረው ስጋት ልባቸውን በጭንቀት ሊያቆመው ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን በህዝባቸውም ሆነ እንደ ቀንደኛ ጠላት በሚቆጥሯቸው ፈረንሳዊያን ዘንድ ተሸናፊና ተንበርካኪ መስለው ለመታየት ፈፅሞ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይህ ችግርና ፈተና ጊዜያዊ እንደሆነና መፍትሄ እንደሚያፈላልጉለት ለህዝባቸው ቃላቸውን መስጠታቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎም ለጎረቤቶቻቸው ሀገራት መሪዎች የድረሱልኝ የእርዳታ ጥሪያቸውን አቀረቡ፡፡ ይሁን እንጂ እህ ብሎ የሰማቸው አልነበረም፡፡ ሁሉም “ስራህ ያውጣህ! እዚያው በፀበልህ እንደ ፍጥርጥርህ!” በማለት ጥሪያቸውን ጆሮ ዳባ ልበስ አለባቸው፡፡ የድረሱልኝ የእርዳታ ጥሪው በቀጥታ ባይደርሳቸውም ጉዳዩን በወሬ ወሬ ሰምተው አስር ጋናውያን መምህራንና አስር ነርሶችን የላኩላቸው ቀድሞውኑም “ግንባር ቀደሙ የትግል ጓዴ” እያሉ የሚጠሩዋቸውና በጣም የሚያደንቋቸው የጋናው ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ብቻ ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሱ ከእለት ወደ እለት እየከፋ እጅግ አደገኛ አቅጣጫን መከተል ሲጀምር፣ በጐረቤቶቻቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት “አይንህን ላፈር” ተብለው የተገለሉት ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ ፊታቸውን ወደ ምዕራብ አለም ማዞር እንደማያዋጣ አልጠፋቸውም፡፡ መያዣ መጨበጫ በሌለው ሁኔታ ምስቅልቅሉ የወጣው የጊኒ ሁኔታ የጊኒውያኑን የዕለት ተዕለት ህይወት ፈታኝ ቢያደርግባቸውም የነፃነታቸው አባት መሪያቸው ሴኩቱሬ፤ ቃል በገባላቸው መሰረት ችግራቸውን ባፋጣኝ እንደሚፈታላቸው በመተማመን በከፍተኛ ትዕግስት በተስፋ ጠብቀዋቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ግን ያደረጉት ጥረት “የቅኝ ገዢዎች ቡችሎች” ያሉዋቸው የጎረቤት ሀገሮች መሪዎች ባደረሱባቸው መገለልና ፈረንሳይ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆነችበት የምዕራቡ ኢምፔሪያሊዝም ነፃነታቸውን መልሶ ለመቀማት በፈፀሙባቸው “ታላቁ ሴራ” ሳቢያ እንዳልተሳካላቸው ለህዝባቸው ይፋ አደረጉ፡፡ በመጨረሻም ፈረንሳይና የምዕራቡን አለም “የኢምፔሪያሊዝም አድርሆት ሀይል” በሚል ክፉኛ ካወገዙ በሁዋላ፣ ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ህብረትና ሌሎች ሶሻሊስት ሀገራት አዞሩ፡፡ ህዝባቸውን በኮናክሪ የነፃነት አደባባይ ከሰበሰቡ በሁዋላም እንዲህ ሲሉ ንግግር አደረጉላቸው፡- “ቅኝ ገዢው የፈረንሳይ መንግስትና የምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም ነፃነታችንን ዳግመኛ ለመቀማት በማሰብ፣ በፈፀሙብን ሴራ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የቅኝ ገዥዎችና የኢምፔሪያሊዝም ቡችላ በሆኑ አድሀሪ መንግስታት በአራቱም ማዕዘን ዙሪያችንን ተከበናል፡፡

ስለዚህ የተጋረጠብን አደጋ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ነፃነታችንንና ሉአላዊነታችንን ከምዕራብ ቅኝ ገዢዎች ግዙፍ መንጋጋ ውስጥ በትግላችን መንጭቀን እንዳወጣነው ሁሉ አሁን የገጠመንን ችግርም አምርረን በመታገል እንወጣዋለን፡፡ ልብ አድርጉ ይህ ችግር የገጠመን በባርነት ለመኖር አሻፈረኝ ስላልንና ጦርነት ስር ሆነን በምቾትና በድሎት ለመኖር ፈቃደኞች ስላልሆንን ብቻ ነው፤ እኛ ጊኒያውያን በባርነት ውስጥ ከሚገኝ ምቾት ይልቅ ነፃነታችንን ተጎናፅፈን በድህነት ለመኖር የመረጥን ነፃነት ወዳድ ታጋይ ህዝቦች እንደሆንን መቼም ቢሆን እንዳትዘነጉ፡፡ ከቅኝ ገዢዎችና ከኢምፔሪያሊዝም እግር ስር እስክንበረከክ ድረስ እስከ እድሜ ልካችን እንደማይተኙልን እንዳትረሱ፡፡” ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁም፤ “ሞት ለቅኝ ገዢዎች! ሞት ለምዕራብ ኢምፔሪያሊዝምና አድርሆት ሀይላት! የጊኒ ነፃነት ለዘላለም ይኑር!” በማለት መፈክር አሰሙ፡፡ ህዝቡም መፈክሮቹን አብሮአቸው ካሰማ በሁዋላ፣ “ቪቫ ቱሬ”፣ “ቪቫ ቱሬ” እያለ በከፍተኛ ድምፅ በመጮህ ለእሳቸው ያለውን ፍቅር ገለፀላቸው፡፡

ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ በሶቪየት ህብረትና በሌሎች የምስራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ሀገራት ይፋ ያልተገለፀ የሁለት ሳምንት ጉብኝት አድርገው ተመለሱ፡፡ እግራቸው የሀገራቸውን ምድር መርገጡን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ የምስራቅ አውሮፓ የአስተዳደር ባለሙያዎች፤ ዶክተሮች፣ ነርሶችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች፤ ኢንጅነሮች፣ ቴክኒሻኖችና መምህራኖች ወደ ጊኒ ጎረፉ፡፡ ቀኑ ቀንን እየገፋ ወደ ፊት በተጓዘ ቁጥርም ከቁጥጥር ውጪ ወደ መሆን ተቃርቦ የነበረው ምስቅልቅል ሁኔታ ቀስ በቀስ ወጥ መስመር እየያዘ መሄድ ጀመረ፡፡ የጊኒን ሁኔታ በጥሞና ይከታተሉ የነበሩ የአፍሪካና የተለያዩ ሀገራት ህዝቦች ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬን “ለቅኝ አገዛዝና ለምዕራብ የአድህሮት ሀይላት ያልተበገረ ጀግና!” ሲሉ አወደሷቸው፡፡ ድፍን ጊኒያውያን ደግሞ “አይበገሬው የነፃነት አባታችን! ካንተ ቀድመን እኛ እንሙትልህ!” በማለት ዳር እስከዳር እልል አሉላቸው፡፡ ከምስራቅ አውሮፓ የመጡት ባለሙያዎች የፈረንሳይን ባለሙያዎች መውጣት ተከትሎ የተፈጠረውን ከፍተኛ ምስቅልቅ ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይችሉም ካሁን አሁን ፈነዳ ሲባል የነበረውን የጊኒን ልብ በመጠኑም ቢሆን ተግ ማድረግ መቻላቸውን የተረዱት ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ፤ ወዲያውኑ የወሰዱት እርምጃ የሴኩቱሬና የሴኩቱሬ ብቻ የሆነ የአመራር ስርአትን መዘርጋት ነበር፡፡

እናም በቢሮአቸው ውስጥ በልዩ ረዳትነት ሲያገለግሏቸው የነበሩትን አራት የሩማኒያ የፓርቲና የመንግስት አስተዳደር ባለሙያዎች፣ በሻይ ዕረፍት ሰአት ወደ ቢሮአቸው ጠርተው ሻይ ጋበዟቸውና በተሰባበረ እንግሊዘኛ እንዲህ ብለው ጠየቋቸው፡- “ሰማችሁ ጓዶች! ታላቁ የሩማኒያ ህዝባዊ አብዮት በኮሚዩኒስት ፓርቲው ጠንካራ አመራር የምዕራብ አድርሆት ሀይላት የደቀኑበትን በርካታና ውስብስብ ችግሮችን ተቋቁሞ አመርቂ ድሎችን እንደተቀናጀ ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ የጥንካሬው ምንጭ ከቶ ምንድን ነው?” እነሱም የስላቪክ ቋንቋ ቃና ባደላበት አነጋገር እንዲህ በማለት መለሱላቸው፡- “ጓድ ሊቀመንበር! ታላቁ የሩማኒያ አብዮት በኮሚኒስት ፓርቲው ጠንካራ አመራር የተቀናጀውን በርካታ አንፀባራቂ ድሎች መረዳት መቻልዎት የሚያረጋግጠው አንድ ታላቅ ቁምነገር፣ ምን ያህል አርቆ አሳቢና ባለብሩህ አዕምሮ መሆንዎን ነው፡፡ የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ጓድ ኒኮላይ ቻውቸስኮም የላቀ አርቆ አሳቢና የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ናቸው፡፡

ታላላቅ አብዮተኞች ተመሳሳይ ባህሪ እንዳላቸው ይህ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ጓድ ሊቀመንበር! የሩማኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ ለታላላቅ ድሎች የበቃበት የጥንካሬው ምንጭ በዋናነት የአመራሩ ጥንካሬና ህዝባዊ መሰረቱ ነው፡፡ ፓርቲው የህዝብ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ የፓርቲው ነው፡፡ “የሩማኒያ ህዝብ ከኮሚኒስት ፓርቲው በቀር ሌላ ፓርቲ ያልፈለገበት ምክንያት የምዕራብ አድርሆት ሀይላት እንደሚያስወሩት የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በመቃወም ሳይሆን በዚህ የተነሳ ብቻ ነው፡፡ ፓርቲው የህዝብ ፓርቲ በመሆኑ ህዝቡ ምን እንደሚያስፈልገው፣ ምን አይነት ሀሳብ ማሰብና ምን አይነት ውሳኔ መወሰን እንዳለበት አስቀድሞ በማሰብ ይወስንለታል፡፡ የኮሚኒስት ፓርቲው ምን አይነት የትግል መስመርና አቅጣጫ መከተል እንዳለባት የሚወስኑ የፖሊት ቢሮና የማዕከላዊ ኮሚቴ አሉት፡፡ የእነዚህ ሁለት ኮሚቴዎች ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተርና የህይወት እስትንፋስ ደግሞ ጓድ ዋና ፀሃፊ ኒኮላይ ቻውቸስኮ ብቻ ናቸው፡፡ በቃ ምስጢሩ ይሄው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምንም ነገር የለም ጓድ ሊቀመንበር ሴኩቱሬ!” ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ እንደዋዛ ለጠየቁት ጥያቄ ያገኙት መልስ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ከሩማንያ ረዳቶቻቸው ያገኙት ምክር የወደፊት የአመራር መስመርና አቅጣጫ የጠቆማቸው ነበር፡፡

ሴኩቱሬ ረዳቶቻቸው የሰጧቸውን ይህንን ምክር ለቀናት ቢሮአቸውን ዘግተው ለብቻቸው ሲያወጡና ሲያወርዱ ከቆዩ በሁዋላ፣ የጊኒና የህዝቦቿን ቀጣይ እጣፈንታ የወሰኑበትን የአመራር ስርዓታቸውን የዘረጉበትን አራት ወሳኝና ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውሳኔዎችን በመወሰን በተግባር ለመተርጎም ባጭር ታጥቀው ተነሱ፡፡ ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ ካሳለፏቸው አራት ውሳኔዎች ውስጥ የመጀመሪያው “የምዕራባዊያንንን የኢምፔሪያሊዝምና የኮሎኒያሊዝም የአድህሮት ሀይላት በምዕራብ አፍሪካ ሳያሰልሱ መዋጋት” የሚለው ነው፡፡ ይህንን ውሳኔአቸውን በተመለከተ በተደጋጋሚ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ሴኩቱሬ፤ የሰጡት መልስ፤ ግንባር ቀደም የአፍሪካ ፀረ ኮሚዩኒዝም ትግል መሪ እንደመሆናቸው መጠን ያላቸውን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት የወሰኑት ውሳኔ እንደሆነ በማስመሰል ነበር፡፡ ግን ትክክለኛው ምክንያታቸው ይህ አልነበረም፡፡ የዚህ ውሳኔ ኢላማ አሜሪካ ወይንም እንግሊዝ አልነበሩም፡፡

ፈረንሳይና ፈረንሳይ ብቻ እንጂ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ጊኒ ነፃነቷን ለመጎናጸፍ በወሰደችው እርምጃ የተነሳ በተለያዩ መንግስታዊና የግል የሙያ መስክ ተሰማርተው ጊኒን እንደሃገር ቀጥ አድርገው አቁመው ይዘዋት የነበሩትን በሺ የሚቆጠሩ ፈረንሳዊያንን በማስወጣት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ሻርል ደጐል የወሰዱት የበቃል እርምጃ ያደሠረባቸው ጉዳት ህመሙ ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ከምስራቅ አውሮፓ የተላኩላቸው ባለሙያዎች ተፈጥሮ የነበረውን እጅግ አደገኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል ከሞላ ጐደል ቢቀርፉላቸውም የጀርባቸው ላይ ቁስል ገና በወጉ አላጠገገም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም በፈረንሳይና በፕሬዚዳንት ደጐል ላይ የቋጠሩት ቂም በቀል እየተንከተከተና አንዳንዴም እየገነፈለ እረፍት ይነሳቸው የነበረው በየእለቱ ነበር፡፡ ለፕሬዚዳት ሴኩቱሬ በቀል ማለት ልክ እንደ ዝናብ ማለት ነበር፡፡ ዝናብ ሲዘንብ ደግሞ የአንድን ቤት ጣራ ብቻ ለይቶ አይመታም፡፡

ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ፈረንሳይና ፕሬዚዳንቷን ሻርል ደጐልን መልሰው ለመበቀል በእጅጉ ቋምጠው ነበር፡፡ ይህን የበቀል ጥማቸውን ለማርካትም ፕሬዚዳንት ደጐል ከፅንስ እስከ ውልደቱ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑበትን የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲን ለማፍረስ ይህ ቀረሽ የማይባል ዙሪያ መለስ የፖለቲካ ትግልና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈቱ፡፡ ዝሆን የፈለገውን ያህል ከሲታ ቢሆን በሚኖርበት ጫካ ውስጥ ከሱ የበለጠ ግዙፍ እንስሳ እንደ ሌለ በሚገባ ያውቃል ይባላል፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም በጊኒ ብቻ ሳይሆን በምዕራብ አፍሪካ ደን ውስጥ ያሉት ዝሆን እርሳቸው እንደሆኑ ለፈረንሳይና ለፕሬዚዳንት ደጐል ለማሳየት የምድሩን ድንጋይ ሁሉ ገለበጡት፡፡

በፊት የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ቡችሎች እያሉ ይዘልፏቸው የነበሩትን የሴኔጋሉን መሪ ሊዎፖልድ ሴዳር ሴንጐርንና፣ የኮትዲቯሩን መሪ ፌሊክስ ሁፌት ቧኘን ሳይቀር በወዳጅነት በመጋበዝ፣ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ህዝቦች የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲን በማፍረስ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ ትግላቸውን እንዲያጧጡፉ ጥሪያቸውን አቀረቡ፡፡ የፈረንሳይ ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ከተቋረጠብን ምኑን ከምን ልናደርገው ነው በሚል ሲጨነቁና ሲጠበቡ ለነበሩት የምዕራብ አፍሪካ ግንባር ቀደም ፖለቲከኞች “ፍርሀት መቼውንምና በየትኛውም ቦታ ቢሆን ሞትን አስቀርቶት አያውቅም” አሏቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ እንኳን ሌሎቹ ፈረንሳውያን ራሳቸውም እንኳ እስኪያንቃቸው ድረስ የጀመሩትን ፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ትግልና ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አጠናክረው ገፉበት፡፡

እንዲህ ሆኖም ግን ፈረንሳውያንና ፕሬዚዳንታቸው የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን የፀረ-ፈረንሳይ ዘመቻ በቀላሉ እንደማይሳካ በመተማመን ዘና ብለው ነበር፡፡ ክፉኛ መሳሳታቸውን ያወቁት 1960 ዓ.ም በባተ በሁለተኛው ወር የፈረንሳይ አፍሪካዊ የበኩር ልጅ በመባል የሚታወቁት የሴኔጋሉ መሪ ሴንጐር፤ ሀገራቸውንና ያኔ ሱዳን ተብላ የምትጠራውን ማሊን በፌዴሬሽን አዋህደው፣ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ደጐል፤ በሀገራቸው እጅ በምርጥ የፈረንሳይ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ ተቀማጥለው ያደጉትና በኋላም የፈረንሳይ ካቢኔ አባል ሚኒስትር የነበሩት ቀንደኛው አፍቃሬ ፈረንሳይ ሴዳር ሴንጐር ያቀረቡት የነፃነት ጥያቄ የፈጠረባቸው ግርምትና ድንጋጤ ገና ሳይለቃቸው ሌላ ሁኔታ ተከትሎ መጣባቸው፡፡ በአቢጃንና በኮናክሪ ሁለት ጊዜ በሚስጥር በመገናኘት ለረጅም ሰአታት ከፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ ጋር ሚስጢራዊ ውይይት አድርገዋል እየተባለ ውስጥ ውስጡን ሲታሙ የነበሩትና የፍራንኮ-አፍሪካ ኮሙኒቲ መመስረቻ የፈረንሳይ አምስተኛው ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ግንባር ቀደም አርቃቂ የነበሩት “ባለ ጥቁር ቆዳ ፈረንሳዊው” የኮትዲቯሩ መሪ ሁፌት ባኘም የሀገራቸውን የነፃነት ጥያቄ በይፋ ለፈረንሳይ መንግስት አቀረቡ፡፡ ካሜሩንና ቶጐም፣ ሴኔጋልንና ኮትዲቯርን ተከትለው የነፃነት ጥያቄአቸውን አቀረቡ፡፡

አዲስ ፀረ-ፈረንሳይ የነፃነት እንቅስቅሴ በምዕራብ አፍሪካ በፍጥነት መቀጣጠል ጀመረ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትም እንደ ካሜሩንና ቶጐ የፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ትግላቸውን እንዲያፋፍሙና የነፃነት ጥያቄአቸውን እንዲያቀርቡ በመገፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ ትግላቸውንና ቅስቀሳቸውን አፋፋሙ፡፡ የተፈጠረው ሁኔታና ጊዜው ለፈረንሳይና ለፕሬዚዳንት ደጐል አዲስና አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሀገራቱ ያቀረቡትን የነፃነት ጥያቄ በእሽታ ከማስተናገድ በቀር አፍነው ሊያስቀሩት የሚችሉበትም ሆነ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን በድጋሚ የሚበቀሉበት አቅም ጨርሶ አልነበራቸውም፡፡ እናም አንጋፋ ምኒስትሮቻቸውን ስነስርአቱን እንዲከታተሉ የፈረንሳይ ወኪል አድርገው በመላክ ለካሜሩንና ለቶጐ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ፈቀዱ፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተቀጣጠለው የነፃነት ትግልና የፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ የፀረ-ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ቅስቀሳ ግን በቀላሉ የሚገታ አልነበረም፡፡ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እስከ ሞሪታኒያ፤ ከሴኔጋል እስከ ቻድ በመላ የምዕራብ አፍራካ ሀገራት፣ የነፃነት ትግሉ ዳር እስከ ዳር መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ይህም በምዕራብ አፍሪካ ተዘርግቶ ለበርካታ ዘመናት የዘለቀው የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ፀሀይ እንደጠለቀችና ግብአተ መሬቱ በእጅጉ እንደታቀረበ የሚያመለክት የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ ደወል ሆነ፡፡

የ1960 ዓ.ም ነሀሴ ወር አሀዱ ብሎ ግም ካለበት ጀምሮ በቀጣዮቹ ሀያ ቀናቶች ብቻ ዘጠኝ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ወጡ፡፡ ምኒስትሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ያሉበት የፈረንሳይ ልኡካን ቡድንም በቤኒን፣ ኒዠር፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጐ ብራዛቪል፣ ጋቦንና ሴኔጋል የፈረንሳይ የቅኝ አገዛዝ ባንዲራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲወርድ በእማኝነት ለመታዘብ በየእለቱ ከአንዱ ከተማ ወደሌላኛው ቀልባቸውን አጥተው ሲዋከቡ ከረሙ፡፡ በዚሁ አመት የመስከረምና የጥቅምት ወራትም ማሊና ሞሪታንያ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ በመላቀቅ ነፃነታቸውን አወጁ፡፡ የበቀል ጥማቸው የረካውና አንጀታቸው ቅቤ የጠጣው ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ በልባቸውም ቢሆን ፕሬዚዳንት ደጐልን “እኔ ሴኩቱሬ እንዲህ ነኝ! የልቤን ሰራሁልህ!” ማለታቸው አልቀረም፡፡ በአፍሪካና በምስራቁ አለምም የፀረ ኢምፔሪያሊዝምና ኮሎኒያሊዝም ጀግና ታጋይ በመባል በዝና ላይ ዝና ደረቡ፡፡ በሀገራቸዉ ውስጥም ጊኒያውያን “ቆራጡ መሪያችን! የኢምፔሪያሊዝም ውጋት! የኮሎኒያሊዝም መጋኛ!” በማለት በእልልታና በሆታ ጨፈሩላቸው፡፡ የመጀመሪያው እቅዳቸው በተሳካ ሁኔታ እንደተከናወነ እርግጠኛ የሆኑት ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም ሌላ ጊዜ አላጠፉም፡፡ ወደ ሁለተኛው እቅዳቸው ተሸጋገሩ፡፡ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲን የህዝቡ ፓርቲ፣ ህዝቡንም የፓርቲው ማድረግ፡፡ ይህን እቅዳቸውን ለማሳካትም ከዚህ የሚከተሉትን ድርጊቶች ፈፀሙ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለን፡፡ እንመለስበታለን፡፡

Read 4495 times