Saturday, 29 June 2013 09:32

የአዳኙና የተጓዡ ማስታወሻ

Written by  ሰለሞን አበበ ቸኮል
Rate this item
(2 votes)

“የሀገራችን ታሪክ የሚያተኩረው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደካማ ጐኖች በመተወን፣ ሥልጣን ላይ የሚወጡትንና ሥልጣናቸውን የሚያደላድሉትን በማሳቅ በማሞገስ ወይም በማንቋሸሽና በመርገም ላይ ነው፡፡ ይላል ተርጓሚው ዑስማን ሐሰን፡፡ ከዚህም የተነሣ ታሪክን በተመለከተ የተለያዩ አስተሳሰቦች በኢትዮጵያውያን ላይ ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ ታሪክን አሽቀንጥሮ መጣል፣ በታሪክ ውስጥ አልፈው የመጡትን ትውፊቶችን ጭምር መጣል ወይም መሳት ወይም ያለመፈለግ አዝማሚያ…በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ አረዳድ እና በተለያየ እውቀት (መረጃ) ይዞ መኖር፤ ከነዚህም ሌሎች ዓይነቶች የሚሆኑ ሞልተው በሚገኙበት ዓለም ውስጥ የወደቅን ሕዝብ የመሆናችንን ሐቅ ልብ አንለው ይሆናል እንጂ የማይታይስ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለውን ሁኔታ የተመለከተው የሥነ ማኀበረሰብ መምሕር ዑስማን ሐሰን (ኤም ኤ) ከልብ የታሰበበትን የታዋቂውን ዊልፍሬድ ቴሲጀር የጉዞ ማስታወሻዎች ወደ አማርኛ መልሶ ሰሞኑን አውጥቷል፡፡

“ሀገረ ሀበሻና የሰገሌው አብዮት” ተብለው በአሥራ አንድ ምዕራፎች የቀረቡት የዊልፍሬድ ቴሲጀር ሥራዎች በአማርኛ መቅረባቸው ብቻውን አንድ ትልቅ ነገር ሲሆን፤ ተርጓሚው የጨመራቸው “መግቢያ” እና “ማጠቃለያ” የተባሉት ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ ቁብ ያላቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ሃያኛው መቶ በኢትዮጵያውያን አንድ ተብሎ መቆጠር በጀመረበት ዘመን ላይ የቴሲጀር አባት የእንግሊዝ ሌጋሲዮን አዲስ “እንደራሴ” ሆነው ስለተሾሙ፣ ከጥቂት ወራት በፊት ካገቧት ባለቤታቸው ጋር በምሥራቅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡ ከድሬዳዋ ወደ ሐረር በማምራት ሃሮማያ ላይ ከነጓዛቸው እንዲያርፉ ያደረጓቸው የወቅቱ የሐረርጌ ገዥ ባልቻ አባ ነፍሶ በክብር ተቀብለው በአጀብ ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው፡፡ በከብት ወር ፈጅተው አዲስ አበባ ገቡ ያን ጊዜ በሌጋሲዮኑ ግቢ (የዛሬው እንግሊዝ ኤምባሲ ግቢ) ውስጥ መደዳ ተሰልፈው የሚታዩ ሰፋፊ ጐጆ ቤቶች ብቻ ነበሩበት፡፡ ከነዚያ “ክብር ና የሣር ክዳን” ከነበራቸው ጐጆዎች በአንዱ የአምባሳደሩ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው፣ ተጓዡና አዳኙ እንዲሁም የመጽሐፉ ፀሐፊ የሆነው ዊልፍሬድ ቴሲገር ተወለደ።

“በሀበሻ ሀገር የተወለድሁ የመጀመሪያው አውሮፓዊ” መሆኑን ሳይቀር ለይቶ ማየት የቻለው ቴሲገር ጀብድን ወዳድ ሆኖ ያደገ ነበር፡፡ ጭካኔን፣ ሁከትን፣ የተተረማመስን ነገር የመውደዱን ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ በልጅነቱ የተመለከታቸውን የሰገሌ ዘመቻን፣ ከሰገሌ መልስ በጃንሜዳ ከአባቱ ጋር ተገኝቶ ያየው የግዳይ መጣል ሥርዓት የመሳሰሉትን ምክንያት ያድርገው እንጂ አባትየው ገና በልጅነቱ ጀምሮ ወደ ጫካ እየሰወዱት በወፎችና በሌሎች እንስሳት ላይ አነጣጥሮ እንዲተኩስ እያደረጉና በትላልቅ አውሬ አደናቸው ሁሉ እያስከተሉ ያሳደጉት ከመሆኑ ጭምር የመጣበት ነበር፡፡ በቤተሰቡ ታሪክና ታላቅነት ኩራትና ይሰማቸው የነበሩት አባቱ፤ ከአያት ቅድመ አያታቸው ጀምሮ እየተረኩላቸው ያደጉም ነበሩ፡፡ ቅድመ አያቱ የእንግሊዝ ፓርላማ ቻንስለር ነበሩ፣ አያቱ በታወቁት የዓለም ዐውደ ግንባሮች የተካፈሉ ጄኔራል ሲሆኑ በክሬምያ እና በመቅደላው ላይ ተካፍለዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት በመጣው የእንግሊዝ ጦር ውስጥ ከናፒዩር ቀጥለው አዛዥ ነበሩ፡፡ እነዚህን ሁሉ በምዕራፍ አንድ ያስተዋውቃል፡፡

በምዕራፍ ሁለት፤ ቴሲገር የኢትዮጵያን አጠቃላይ ታሪክ ሊዳስስ ሞክሯል፡፡ ማንኛውም አንባቢ የሚጠብቃቸው ከተለመዱትና ከታወቁት የኢትዮጵያ “ሂስትሪ” መሠረቶች ሌላ ምንም መጠበቅ የለበትም፡፡ ይህ “ሂስትሪ” ከሚያውቃቸው ሰዎች መካከል ዑለንዶርፍ የቴሲገርን መጽሐፍ ከመታተሙ በፊት የተመለከተውና የአርትዖት ሥራም የሠራበት መሆኑን አስቀድሞ በመግቢያው ስለገለጸ ብዙም የተለየ ነገር አንጠብቅም፡፡ በትምሕርት ቤቱ፣ በየዩኒቨርሲቲው፣ በየመጽሐፉ፣ በቱሪስት መምሪያውና በኛ ባለሥልጣኖች እንዲሁም የቋንቋ፣ የጐሣና የጐጥ ፖለቲካ ሊቃናት ጭንቅላት ውስጥ ተመስገው የኖሩ የታሪክ እውቀቶች፣ ሐሳቦችና ግንዛቤዎች ናቸው የቀረቡት፡፡ “ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ሀገረ ሀበሻ ቀይ ባሕርን ተሻግረው (የገቡ ሰዎች) ሥልጣኔን ወደ ኢትዮጵያ አስገቡ፤ ክርስትና በፍሬምናጦስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ገባ፤ ፍሬምናጦስ ቀድሞ ጣዖትን አምላኪ የነበረውን “ኢዛናን ክርስትና አነሳው” “ለብዙ መቶ አመታት በአክሱሞች ቁጥጥር አስተዳደር ውስጥ ሳይገቡ የኖሩት የአገው ሕዝቦች ለአመጽ (ተነሳስተው) የአክሱምን ንጉሣዊ አስተዳደር (ወጉት)፡፡ (ገጽ 39) “እነዚህ የደቡብ አገዎች ክርስትናን የተቀበሉት ከዮዲት ዘመነ መንግሥት በኋላ ነበር፤ የዛጉዌ ሥርወመንግሥትን (?) መመሥረት የቻሉት ክርስትናን ከተቀበሉበት ዘመን (ከዮዲት ዘ.መ) ወዲህ ነው ወዘተ እያለ ይቀጥላል “ሰሎሞናዊ፣ “ዛጉዌዋዊ” የተባሉ “ሥርወመንግስታት” (ራሱን “ሥርወመንግስት የሚለውም”) ዓይነት የታሪካችን ስሞችንና ቃሎች መቸም እንኳን በቴሲገር ጽሑፍ በሮማ ልዑካን የተሠራውን ታሪክ ጠብተው ባደጉ የታሪክ ምሑራኖቻችንም ቢሆን ያልታየ ጉዳይ ነው፡፡

ራሱ ቴሲጀር የጨመራቸው የሚመስሉ አዳዲስ እይታዎችና ጥቆማዎችም እናገኛለን፡፡ “አፄ ምኒልክ በእንጦጦ እስከነገሱበት አመት ድረስ ሁሉም (ነገሥታት) የሚቀቡባት ሥፍራ አክሱም ነበረች፤” ይላል፡፡ ብዙም ሩቅ ሳይጓዝ የገዛ አያቱ የጄኔራል ናፒየር ጦር ምክትል የጦር አዛዥ ሆነው የዘመቱበትን የቴዎድሮስ ሥርዓተ መንግሥት የት እንደተፈፀመለትና የተቀባው የት እንደነበር ቢያውቅ እንዲያ ባልጻፈ ነበር፡፡ ሌሎች የታሪክ መጽሐፎችም አፄ ሰርፀድንግልንና አፄ ዘርዓ ያዕቆብን በንግሥ ሥርዓት ጉዳይ ወደ አክሱም መሄዳቸውን የተለየ አድርገው የሚጠቅሱላቸው ሁሎችም በአክሱም ባለመቀባታቸው ነበር፡፡ ፍሬምናጦስ በሮም ግዛተ አፄ የኢትዮጵያ እንደራሴ ሆኖ እንደነበርም ቴሲገር ጽፏል፡፡ ከየት እንዳገኘው ለማወቅ ይቸግራል፡፡ እሱማ ሩፊኖስን ይጠራል፡፡ ሩፊኖስ ግን በጭራሽ እንዲህ ያለ ጥቆማ አልጻፈም፡፡ ሩፊኖስ የፍሬምናጦስ ወንድም የነገረውን ሃቅ እንዳለ ቢጽፍም በብዙ ፀሐፊዎች የቀረቡ፤ “የተበረዘ፣ የተከለሰ” ከሚባለውም በላይ የሆኑ ልዩ ልዩ ሥራዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ከነዚያ ዓይነቱም ቢሆን ግን እንዲህ ያለው ነገር አይገኝም፡፡ ደግሞም ፍሬምናጦስ ለጉብኝት ሔዶ ሳለ፣ በዚያው አትናቴዎስን አግኝቶት፣ ጳጳስነትን ሾሞት ወደ ኢትዮጵያ እንደላከውም ያስነብባል። አፄ ሱስንዮስ፣ “ያልሰማህ ስማ፣ የሰማህ አሰማ ይህንን እምነት የሰጠናችሁ መልካሙን አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ተገደሉ፡፡

ለምሣሌ ጁሊየስ፣ ገብርኤል፣ ተክለጊዮርጊስ፣ ሠርፀ ክርስቶስ እና አሁን ደግሞ እነዚህ ገበሬዎች። ለነዚህ ምክንያቶች ስንል የአባቶቻችሁን እምነት መልሰንላችኋል ደስ ይበላችሁ” ብለው አዋጅ ካስነገሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተገደሉ” ይላል፡፡ አፄ ሱስንዮስ በግድያ ነበር የሞቱት? አዲስ ነገር ይሆናል፡፡ አወጁት ተብሎ የተገለፀውም አዲስ ነገር ይሆናል፡፡ የቀረበው ቃል ያልተጻፈ አይደለም አይባልም፡፡ ለብዙዎች አዲስ ነገር ሊሆን ቢችልም ምናልባት የመገደሉም ነገር ይህን ዓዋጅ ለመጻፍና ለማስጻፍ በቻሉት በኩል የሚተረክ ይሆናል፡፡ የዜሲገርን መጽሐፍ በልዩ ጥንቃቄ ማንበብ የሚገባበት ምክንያት እንዲህ አንድ ሁለቱን መጠቃቀስ በጀመርንለት የምዕራፍ 2 “የሀገረ ሀበሻ ታሪክ” ብሎ ባቀረበው ላይ ብቻ አይሆንም፡፡ ማራኪ እና ብዙ መረጃዎችንና ዕውቀቶችን በምናገኝባቸው በተቀሩት ምዕራፎችም ውስጥ አልፎ አልፎ የተሰገሰጉ አይጠፉም፡፡ ባየውና በተመለከተው ነገር እየተነሳ የሚጨምራቸው አንዳንድ መበጠር የሚገባቸው ጉዳዮች አሉት፡፡ የቴሲገርም ሆነ የሌሎች ሥራዎች እንዲህ የመቅረባቸው አንድ ፋይዳም እነዚህንም እሚገልጡ መሆናቸው ነው፡፡

ቴሲገርን የሚወድዱትና የሚፈልጉበት ምክንያቶች ግን የጉዞና የጉብኝት ማስታወሻዎቹ ናቸው፡፡ ተራ ነገሮችን ቁምነገር አድርጐ ስለሚያቀርብ ለማንበብም ይማርካሉ፡፡ ትናንሽ መሰለው ሊታዩ የሚችሉ ነገር ግን ጥሩ የታሪክ ምሥክርነት ያላቸው መረጃዎችና እውቀቶችም ይገኝባቸዋል፡፡ ምንሊክ “ድሀው ሕዝቤ” እያሉ በሕመም አልጋ ላይ በዋሉበት ጊዜ ያለቅሱ እንደነበር፣ በኬንያ ሰሜናዊ ግዛት የቀሩ ሁለት የኦሮሞ ጐሣዎችን “ሕዝቤ” ብለውና በስማቸው እየጠሩ በመነጠላቸው ሲንገበገቡ መኖራቸውን የመሰለውን ታሪክ ከየት ልናገኝ እንችል ነበር? በሰገሌ ጦርነት ጊዜ ራስ ተፈሪ የሁለት ዓመት ተመንፈቅ የነበረውን ልጃቸውን (በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን) በቀይ አንቀልባ አሳዝለው፣ ዣንጥላ አስጠልተው ይዘው ወደ እንግሊዝ አምባሳደር (ወደ ጸሓፊው አባት) ወስደው በአደራ እንዲቀመጥላቸው ማድረጋቸው የመሰለውንም እናገኛለን፡፡ “ብዙ አውሮፓውያን የሀበሻን ቄሶች ያልተማሩ፣ አጉል እምነት አምላኪዎችና በዓለማዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ሲናገሩ ሰምቼ ነበር፡፡ ላሊበላ፣ እምረ ሀና (ይምርሐነ ሊል ነው ይምርሐነ ክርስቶስ፡፡) በነበርኩበት ጊዜ ግን ይህንን አባባል እውነት ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

ቄሶቹ በሥርዓታቸው፣ በደግነታቸውና በአዛኝነታቸው የሀበሻ ትልልቅ ሰዎች መገለጫዎች ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡” ቴሲገር በስተደቡብ በኩል ባደረገው ጉዞ ከየትኛውም የአውሮፓና የአሜሪካ የመጡ ሚሲዮናውያን በእንግድነት እያረፈባቸው ቢያልፍም፣ “ለእኔ በጣም ደግና እንግዳ ተቀባይ ቢሆኑም በነዚያ ቦታዎች መገኘቴ ግን አበሳጭቶኝ ነበር” ይላል፡፡ (ገጽ 61) በላሊበላ እርሱ ጉብኝት ሲያደርግ ከወልድያ በበቅሎ በሁለት ቀን ውስጥ በድምሩ የ15 ሰዓታት ጉዞ በማድረግ ገብቶ፣ ከአዲስ አበባ በአውሮፕላን እዚያ ድረስ ጐብኝዎችን እየወሰዱ ሊያስጐበኟቸው መታቀዱን ሰምቻለሁ ብሎ በዚያ ያዘነ መሆኑን ገልጿል (ገጽ 158) በ1948 በደቡብ ያደረገው ጉዞ ጫማውን እስኪቀደድ ድረስ አብቅቶት በጨንቻ፣ ኮንስና ተልተሌ አድርጐ ሜጋ ላይ ያለ የእንግሊዝ ቆንሲል ወደ ሞያሌው ወስዶት፣ በዚያው የነበረው የእንግሊዞች ወኪል ጆርጅ ዌብ ነበር ጫማው እንዲጠገንና አንድ ሰንደል ጫማ እንዲሰራለት ያደረገው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሰሜን አቅጣጫ የሶማሌዎችንና የጉጂዎችን ሀገር ጐብኝቶ በሀገረማርያም አድርጐ ዲላ በመድረስ፣ በአውቶቡስ ሻሸመኔ፣ ከዚያም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ የሞያሌው ጆርጅ ዌብ ጫማው ተቀድዶ ለመጀመሪያ ቀን ያየው እለት የነገረውን አስፍሯል፡፡ “ትናንት ሳይህ ልቤ [ክው ነበር] ያለው፡፡ ድሃ የሆነ እንግሊዛዊ ቼክ ሊለምነኝ የመጣ ነበር የመሰለኝ፡፡” ከዚህ ጉዞው ተመልሶ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ ካርቱም ነበር የሄደው፡፡ በዚህ ዘመን ነበር ሱዳን ነፃ የወጣችው፡፡

ስለ ሱዳናውያንም ሲጽፍ፣ “ምናልባትም ከአፍሪካውያን ሁሉ በጣም የሚወደዱና ደግ የሆኑ ሰዎች” ብሎ ያደንቃቸዋል” ከሦስት ዓመት በኋላም እንደገና ለጉብኝት ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ አሁን ደግሞ የአባይን ሸለቆ በመከተል ጣና ፣ ጐንደር፣ ሰሜን ተራሮች ከዚያ ላሊበላን በድጋሚ ተመልክቷል። መቅደላን፣ ከዚያ ወደ ሸዋ ገብቶ አንኮበርንና በልጅነቱ ጀምሮ ተቀርጾበት የቀረው ጦርነት የተካሄደበትን ሰገሌን ጐብኝቶ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ የሰገሌው “ግርግር” ተብሎ የሚጠራው፣ ከአዲስ አበባ 96 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኝ ዓውደ ግንባር ላይ ከወሎው ንጉሥ ሚካኤል ጋር የተደረገውን ጦርነት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጋር ምን ያህል ይገናኛል? “ምን ያህል” ቀርቶ ምን ዓይነት ግንኙነት እንደሚኖረውስ ማን ይገምታል? እርግጥ ነው በሀገር ውስጥ ካሉ ጀርመናውያንና ቱርካውያን ጋር ልጅ ኢያሱ ያደርጉት የነበረውን ግንኙነት ጠቆም በማድረግ የኢያሱ ወገኖች የሚያይሉበት ሊሆን እንደሚችል እና ሌሎች ስስ የሆኑ ዓለምአቀፋዊ መነካኪያዎችን ለማውጣትና ለመግለጽ የተቻለባቸው የታሪክ ጽሑፎች አናጣም ይሆናል። ነገር ግን በሰገሌው ጦርነት ለልጃቸው ለኢያሱ ሥልጣን ማጣት የተነሱት ንጉሥ ሚካኤል ቢያሸንፉ ከጀርመኖችና እና ከቱርኮች ጋር ለተፋጠጡት እንግሊዝና ፈረንሳይም እንደ አንድ ሽንፈት ይቆጠር እንደነበር ምንኛ ታስቦ ይሆን! ተርጓሚው መምሕር ዑስማን ሐሰን “የሰገሌው አብዮት” በማለት የትርጉም ሥራው ከፊል ርእስ ማድረጉ ጥያቄ ይፈጥርና ለምን እንዲያ እንዳለው ለማወቅ ያጓጓ ይሆናል፡፡ እኔም መጽሐፉን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁ ጊዜ እንዲሁ አስቤ ነበር ለማየት የፈለግኹት፡፡

ከማንበብ በፊትም ሆነ እያነበብኩት፣ ካነበብሁትም በኋላ ለምን እንዲያ እንደተባለ ለማወቅ ራሱን ተርጓሚውን ማግኘት እንዳለብኝ አስቤ ነበር፡፡ በመግቢያው ላይ ራሱ ቴሲገር “አብዮት” ብሎ እንደጠራው የተገለፀውም ሆነ፣ ቴሲገር ምዕራፎች (ገጽ 53) ከርእሱ ጀምሮ “የሰገሌው አብዮት” ማለቱና በውስጡም፣ በዚያው ወቅት ከእንግሊዝ ለጋሲዮን ወደ ውጭ የሚወጡ ሪፖርቶችም ሆኑ ሌሎች ወረቀቶች ያን “ግርግር” ተብሎ በኛ ዘንድ እንዲጠራ የተደረገውን ጦርነት “አብዮት” ብሎት እንደነበር መረዳቱም ቢሆን ጥያቄውን አያጠፋውም - ከተርጓሚው ራስ ያወርደው እንደሆን እንጂ፡፡ ተርጓሚው የሶሺዮሎጂው ምሑርና መምሕር ዑስማን ሐሰንም ቢሆን “መጀመሪያ ላይ እንዳልተዋጠለት ይገልጻል፡፡ “በኋላ ላይ ግን ወድጄዋለሁ” አለኝ፡፡ ለዚህም ያስከትል የነበረውን ለውጥ በማጤን እንደነበርም ጨምሮ አስረድቶኛል። የተርጓሚው መግቢያና ማጠናቀቂያ በ214 ገጾች ክትት ተደርገው ደቀቅ ባሉ የፊደል መጠናት የቀረቡልን ጽሑፎች በሙሉ የታዋቂው ተጓዥና አዳኝ የዊልፍሬድ ቴሊገር ሥራዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የመጽሐፉን ዓይነት ለየት እንዲል ብቻ ሳይሆን፣ ጠቀሜታውንም ጨመር የሚያደርገው የተርጓሚው የራሱ ሥራዎች መሠመራቸውም ላይ ነው፡፡

“መግቢያ” እና “ማጠቃለያ” ተብለው የቀረቡ ምሑራዊ እይታዎችና ሙያዊ የጥናት ወረቀቶች አከል የሆኑ ሁለት ምንባባትም 51 ገጾችን ይዘዋል፡፡ ምናልባት ለምን አስፈለጉ ማለቱ ይቀድምብን ይሆናል፡፡ በተለይ “መግቢያ (ከተርጓሚው)” ተብሎ 22 ገጾች ማቅረቡን በመጀመሪያ እኔ ብቻ ሳልሆን ቀድመው ማንበብ የቻሉ ሌሎችም ጠቁመውኛል። እኔም ልክ እንደ ልብ ወለድ መጽሐፍ ያን ዘልዬ በሁለት ገጾች ከቀረበችው የቴሲጀር መግቢያ ጀምሬ ነበር ማንበቤን የቀጠልኹት - በኋላ እመለስበታለሁ ብዬ፡፡ ያን መግቢያ ሳነብብ ግን ሶሺዮሎጂስቱ ዑስማን ከሥነ ማኅበረሰብ ምሑርነቱ አኳያም ታሪክን በእንደምን ያለ አቀራረብ መመልከት እንደሚገባን፣ የትርጉም ሥራውን ለመተርጐም ወይም ለማቅረብም የተነሳሳበትንና ቁም ነገር አድርጐ የተመለከተበትን ግንዛቤውን የሚገልጽልን፤ ራሱን የቻለ እጅግ ሰፊ እና ከበድ ያለ ጉዳይን ነው በዚህ “መግቢያ” ብሎ በጠራው ጽሑፍ ያቀረበው። እንዲያውም፣ ከበጉ ሥጋ ቆዳው በልጦ የሚገኝበት ይመስለንና ለምን ለብቻ አያቀርበውም ወደ ማለት ወሰድ ሊያደርገን የሚችል ይኾናል፣ ግን በጉን ያለ ቆዳው ወይም ያለ ሥጋው በግ ብለን አንይዘውም፡፡ በዚያ መግቢያው በሥነ ማኅበረሰባዊ ኅልዮት ግንዛቤና እውቀት የተተነተነ ታሪክን በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን የተባልን ዛሬ የዕለት ተዕለት ጉዳያችን ለመኾን ያበቃንን የሀገራችንን የቀድሞ ዘመን ታሪኮቻችንን እንደምን አድርገን እንደያዝነው እና እንዴት መያዝ እንደሚገባ በቅንነት ያለ ስስት ያለውን መስጠቱን እናያለን፡፡

ማኅበረ ፖለቲካዊ ጥሪቶችን” ለጋራ ጥቅማችንና እድገታችን ልናውል እንደሚገባ፤ ያንንም ወድደን ሳይሆን ያለ ምርጫ መቀበል ያለብን መኾኑን፤ ከዚያ ተነስተን ያንን እንደሚገባው ራሳችንን በማስገባት አዎንታዊ ጉዞ መቀጠል እንዳለብን ነው ያ ጥናት አከል ጽሑፍ ሲጨመቅ ጠብ የሚያደርግልን፡፡ ለአብነት እጠቅስለታለሁ፡- “… በእያንዳንዳችን አቅምና ቁጥጥር ስር የሚኖሩት ብቸኞቹ ነገሮች የአባቶቻችንን ውርስና ቅርሶች እምነት መቀበልና (መቀጠል) ብቻ ነው። ለሀገራዊ ማንነት መሠረታዊ መነሻዎች በአግባቡ ለመገንዘብ ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ማከናወን ይኖርብናል፡- አንድ፣ ያለ ፈቃዳችን ማቀበል፤ ሁለት፣ የተቀበልነውን ፈቅደን መቀጠል፡፡ (ገጽ 13) አንዲቷን እንደ ምርቃት እንጨምር፡- “ማንኛውም የጋራ ማንነት እውን እንዲሆን ተመሳሳይና ወጥ የኾነ አስተሳሰብ (እንዲኹም) ትርጉም ያለው ምልክት (አርማ) ያስፈልገናል፡፡” (ገጽ 18) እንዲህ ያለ ቃለ ምዕዳን የመሣሰሉ አናቅጽ ብቻ አይደሉም “መግቢያ” ብሎ ተርጓሚው ባቀረበው የራሱ ሥራ ያቀረበው፡፡ እነዚህን ለማምጣት ያስቻሉ ነባራዊ ኹኔታዎችንና ሙያዊ ሀቲቶችን በማቅረብና በምሑራዊ ሥራዎች በማስደገፍ የሚገልጻቸውን በመጨመር እንጂ፡፡ “ማጠናቀቂያው” ላይ ጥያቄ አይኖርም።

ከዋናው ሥራ ቀጥሎ የቀረበ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ታሪክ ከውጭም ኾነ ከሀገር ውስጥ የታሪክ ምሑራንና ጸሐፊዎች በመቅዳት ወይም በመተርጐም ለማቅረብ ሲፈለግ ብዙ የሚያንገበግቡ ነገሮች ይገጥሙና እነዚያን እንዴት ነው ማድረግ የምንችለው? ጸሐፊው ያለውን ቀይረን፣ ለውጠን፣ አርመን ሌላ ጉዳይ ይኾናል፡፡ እንዳለ ማቅረቡም ሌላ ችግር ነው፡፡ እንዳለ አለማቅረቡም ቢሆን ይበልጥ አጉዳይ ይኾናል፡፡ ዑስማን ቴሲገርን ተርጉሞ ያላንዳች ጣልቃ ገብነት የራሱን በራሱ ገጾች ካቀረበለት በኋላ፣ በዚህ ታሪካዊ እና የጉዞ ማስታወሻው ውስጥ ያሉትን ሳንካዎች፣ አጉል የሆኑ አረዳዶችና የተሳሳቱ ጥቆማዎችን በመነቃቀስ በመጨረሻዎቹ ገጾቹ አቅርቧል፡፡ በዚያውም፣ አስቀድሞ በመግቢያው ወደ አለፉ ታሪካችን እንዴት ባለ አቀራረብ መጠጋት እንደሚቻል ያላንዳች ምርጫ የምንቀበላቸውን ተቀብለን እንዴት እንደምናጤንም በተግባር ለአብነት ያህል ማቅረብ የቻለባቸው ገጾችም ናቸው፡፡ ይህን የዑስማንን ሥራ አስቀድሞ ከምናውቃቸው ወደ አማርኛ ተመልሰው ከቀረቡልን ታሪክና ታሪክ ቀመስ ሥራዎች ለየት ያለ ቦታ የምንሰጠውና ቁብ ያለው አድርገን ለማሰብ የሚያስችለንም እነዚህ ሁለቱ የተርጓሚው ሥራዎች የተጨመሩበትም መሆኑ ላይ ነው፡፡

Read 3801 times Last modified on Saturday, 29 June 2013 10:02