አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በተመረጡ 26 አካባቢዎች በተሰባሰቡ 3000 ህፃናት ላይ የተደረገውን ጥናት አስመልክቶ የጥናቱ ዋና አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ሲናገሩ፤ ጥናቱ በህፃናቱ ጤና፣ የዕድገት ደረጃና የትምህርት አቀባበል ችሎታ ላይ ትኩረት አድርጐ መካሄዱንና በአማካይ ደረጃ ካሉ የኢትዮጵያ ቤተሰቦች ጋር ሲነፃፀሩ የባሰ ድሃ በሚባሉና የምግብ እጥረት ባለባቸው ዝናብ አጠር አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ ህፃናት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቡድኑ በህፃናት ላይ የሚያደርገውን ጥናት የጀመረው በ1993 ዓ.ም ሲሆን ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አስራ ስድስት ወር የሆናቸው 1ሺ999 ህፃናትና ዕድሜያቸው ከ7.5 እስከ 8.5 ዓመት ድረስ የሆናቸው 1000 ህፃናትን አካቷል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የጥናት ዳሰሳ ላይ ከነበሩት ህፃናት መካከል 78 ያህሉ ለ3ኛው ዙር የዳሰሳ ጥናት ለመድረስ ሣይችሉ ቀርተዋል፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የተለያዩ በሽታዎች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ማጣት እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡ በህፃናቱ ላይ በመጀመሪያው ዙር የተደረገው ጥናት በ3ኛው ዙር ላይ ያሳየውን መሻሻል አስመልክቶ ረዳት ፕሮፌሰር ጣሰው ሲናገሩ፤ ለእድሜያቸው የሚመጥን ቁመት ላይ ባለመድረስ ክፉኛ የተጠቁ ህፃናት ቀላል የማይባል መሻሻልን አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ህፃናቱ ወደፊት ተገቢውን ዕድገት እንዲያሳዩ አልሚ ምግቦችን ከወዲሁ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩም ከከተሞች ይልቅ በገጠር ከፍተኛ ሆኖ ታይቷል፡፡ ጥናቱ በተደረገባቸው አካባቢዎች በሀብት ደረጃ፣ ፍጆታና ድህነት፣ የአገልግሎቶች ተደራሽነት፣ ጤናና አልሚ ምግብ እጥረት፣ የትምህርት አቅርቦት፣ የህፃናት ሥራና የጊዜ አጠቃቀም እንዲሁም የግል ደህንነት ላይ ህፃናቱ ያሉበትን ደረጃ ለማየት ተሞክሯል፡፡ “ያንግ ላይቭስ” በኢትዮጵያ፣ በህንድ፣ በፔሩና በቬትናም ውስጥ ባሉ ህፃናት የድህነት ተለዋዋጭ ገፅታ ላይ ምርምር በማካሄድ ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡