Saturday, 29 June 2013 10:24

የማሸት ህክምና(ማሳጅ ቴራፒ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(10 votes)

እንዲህ እንደዛሬው አገልግሎቱ በአብዛኛው ለተለየ ዓላማና ተግባር እንዲውል ከመደረጉ በፊት የማሣጅ አገልግሎት (ህክምና) በአገራችን የተለመደና አዘውትሮ የሚከናወን ጉዳይ ነበር፡፡ የጥንት የአገራችን ሰዎች ጐንበስ ቀና ሲሉ የዋሉበት ሰውነታቸውን ከቤት ውስጥ ተንጦ በተዘጋጀ ለጋ የከብት ቅቤ በመታሸት እንዲፍታታና ሰውነታቸው ዘና እንዲል ማድረጉ የየዕለት ተግባራቸው ነበር፡፡ ነገስታቱ ሣይቀር የማሳጅ አገልግሎቱን አዘውትረው ይጠቀሙ እንደነበርና ለጦርነትም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች ከአገር አገር ይዘዋወሩ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ይህንኑ አገልግሎት የሚሰጧቸውን ሴቶች (የጭን ገረድ) ይዘው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡

የማሳጅ ህክምና ከ3ሺ ዓመታት በፊት በቻይና የተለመደ ጉዳይ ነበር፡፡ የተሳሰረና አልፍታታ ያለን ጡንቻ፣ ጥበባዊና ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ በማሸት እንዲፍታታ የማድረጉን ተግባር ቻይናዎቹ ተክነውበታል፡፡ የማሣጅ ቀጥተኛው ትርጓሜ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን በእጅ መዳፍ ማሸት የሚለው ሲሆን አስተሻሸቱ ለስላሳና ጠንከር ባለ መንገድ ሆኖ የራሱ ጥበባዊ ዘዴ ያለው ነው፡፡ የማሣጅ ህክምና የተለያዩ ጡንቻዎችንና የመገጣጠሚያ ጅማቶችን በማሻሸት እና ጫን ጫን በማድረግ አካልን ለማፍታታት እንዲሁም ጡንቻና መገጣጠሚያዎችን እንዲፍታቱ ለማድረግ የሚረዳ ዘዴ ነው፡፡ አንዳንድ የማሣጅ አይነቶች ከእጅ በተጨማሪ የተለያዩ መሳሪያዎችንና ሙቀትን ይፈልጋሉ፡፡ ጀርባ፣ ትከሻ፣ አንገት፣ የእግር ጡንቻ፣ ወገብ፣ በማሳጅ የሚዳሰሱ የአካል ክፍሎች ናቸው፡፡

ማሳጅ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዋንኛው በጡንቻና በመገጣጠሚያ አካባቢ የደም ዝውውርን ከፍ ማድረግና ከሰውነታችን የሚወጣውን ተረፈ ምርት (ቆሻሻ) በአግባቡ እንዲወገድ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰዎች ማሳጅን በተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀማሉ፡፡ ዘና ለማለት፣ ከጭንቀት ለመላቀቅ፣ ለስፖርት እንቅስቃሴ ለመዘጋጀት የተሳሰሩ ጡንቻዎችን ለማፍታታት፣ አሁን አሁን ደግሞ የወሲብ ፍላጐትን ለማነሳሳት ማሳጅን ይጠቀማሉ፡፡ የማሳጅ ህክምና በሙያው በሰለጠነ ሰው ካልተከናወነ እጅግ ለከፋ ጉዳትና ለሞት ሊዳረግ እንደሚችል የማሳጅ ቴራፒ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ደረጀ ይናገራል፡፡

ሙያው የራሱ የሆነ ጥበባዊ የአስተሻሸት ዘዴና ቅደም ተከተላዊ አሠራር ያለው በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ መሆኑንም ይገልፃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሰባ አምስት በላይ የማሳጅ አይነቶች መኖራቸውን የሚገልፀው የማሳጅ ቴራፒስቱ ዮሐንስ፤ ሁሉም የማሳጅ አይነቶች የየራሳቸው ባህርይና የአስተሻሸት ዘዴ እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡ ጥሩ ማሳጅ ፀጥታ በሰፈነበት፣ ብርሃን ባልበዛበት ሥፍራ እንደሚደረግ የሚገልፀው ባለሙያው፤ ሥራው በለስላሳ ሙዚቃ ታጅቦ ለእሽታው የሚያገለግሉ የተለያዩ አይነቶች ቅባቶችን በመጠቀም እንደሚከናወን ይገልፃል፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠውም በሙያው በሰለጠነ ሰው መሆን እንደሚገባውና ይህ ካልሆነ ግን ከአካል ጉዳት እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት ሊፈጥር እንደሚችል ይናገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በማሳጅ ሙያ ላይ ስልጠናን የሚሰጡ የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቆመው አቶ ዮሐንስ፤ እነዚህ ድርጅቶች ስልጠናውን የሚሰጡት በተገቢው መንገድና በሙያው በቂ ዕውቀት ባላቸው እንዲሁም ሙያውን ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ ሊያስተምሩ በሚችሉ ባለሙያዎች ነው ለማለት ግን እንደማያስደፍር ይገልፃል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው የማሳጅ አገልግሎት፣ ዛሬ ዛሬ ቀደም ሲል ከነበረው አገልግሎቱና አሠራሩ በተለየ መንገድ መከናወን ጀምሯል፡፡ በከተማዋ የማሳጅ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቤቶች ውስጥ ከመደበኛው የእሽታ አገልግሎት ውጪ ግማሽ ፓኬጅ እና ሙሉ ፓኬጅ በሚል መጠሪያ የሚሰጡት አገልግሎቶች እጅግ አስፈሪና አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን በሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ የተደረገውና በቅርቡ ይፋ የሆነው ጥናት ያመለክታል፡፡ ቢሮው በጉዳዩ ላይ በስፋት አደረግሁት ያለው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በከተማው ውስጥ ከሚገኙት የማሳጅ ቤቶች አብዛኛዎቹ ከማሳጅ አገልግሎት በተጨማሪ የወሲብ ገበያ ያደሩበታል፡፡ በማሳጅ ቤቱ ውስጥ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚመጡትን ሰዎች የሚያስተናግዱት “ባለሙያዎች” ከእሽታ (ከማሣጅ) ሙያ በተጨማሪ ጥሩ ቁመናና መልክ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አገልግሎቱን ከማሳጅ ቤቱ ውጪ በሆቴል፣ በመኖሪያ ቤትና በመኪናዎች ውስጥ ሁሉ ለማግኘት ለሚፈልጉ ደንበኞችም “ባለሙያዎቹ” እንደየሁኔታው አገልግሎቱን እንዲሰጡ ያደርጋል፡፡

ጥናቱ በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑና በተለያዩ ሥፍራዎች ከማሳጅ ቤቶች “ባለሙያዎችን” እየወሰዱ የሚጠቀሙ በርካታ ባለሃብቶች፣ ባለስልጣናትና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡ የማሳጅ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውም ትላልቅ ህንፃዎች፣ ሰፋ ያለ ግቢ ያላቸው ቤቶች፣ አፓርትማዎችና በከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች በሚገኙ ፎቆች ላይ የሚገኙ ቤቶች መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ ይህ ሁኔታ የማሳጅ ህክምናን ወደአላስፈላጊ መንገድ እንዲያመራና ህክምናው በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው እንዳይደርስ የሚያደርግ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ከሰባ አምስት በላይ የማሳጅ አይነቶች መኖራቸውን የሚናገረው የማሳጅ ቴራፒስቱ አቶ ዮሐንስ፤ በአገራችን የተለመዱት ግን እጅግ ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ ከእነዚሁ በአገራችን በስፋት ከተለመዱትና በበርካታ የማሳጅ አገልግሎት መስጫ ቤቶች ከሚዘወተሩት መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ስዊድሽ ማሳጅ ይህ የማሳጅ አይነት በአገራችን በስፋት የሚዘወተር የማሳጅ አይነት ሲሆን አሠራሩም ሰውነት ዘና እንዲል ለማድረግ ቅባትን በመጠቀም ረዘም ላለ ሰዓት ውጫዊ ሰውነትንና ጡንቻዎችን በዝግታ ማሸት ነው፡፡ የማሳጅ ባለሙያው ይህንን አይነት አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ደንበኛው ሰውነቱም ሆነ መንፈሱ ዘና እንዲል በማድረግ በዝግታ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡

ይህ የእሽታ ሕክምና በአግባቡ ከተደረገ ከብዙ በሽታዎች እፎይታን ለማስገኘትና ሰውነትንና ጡንቻዎችን ለማፍታታት ይረዳል፡፡ አሮማ ቴራፒ ይህ ቴራፒ የሚከናወነው በተለይ ከአዕምሮ ውጥረት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ላለባቸው ሰዎች ነው፡፡ ጥሩ ሽታ ባላቸው ቅባቶች በመጠቀምና ህመምተኛው ዘና እንዲል በማድረግ የሚከናወን እሽታ ነው፡፡ ይህንንም የማሳጅ ሕክምና በርካታ የማሳጅ ቤቶች ይጠቀሙበታል፡፡ ዲፓቲሹ ማሳጅ ይህ የማሳጅ አይነት ውስጣዊ በሆነው የጡንቻና የመገጣጠሚያ ክፍል ትኩረት አድርጐ የሚከናወን ሲሆን ባለሙያው በዝግታ የጡንቻ አወራረድንና የሰውነት ቅርጽን በመከተል እሽታውን ያከናውናል፡፡ ይህ አይነቱ ማሳጅ ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ የጡንቻ ህመምን፣ የሰውነት ቅርጽ መበላሸትና፣ የተወለጋገዱ የሰውነት አካላትን ለማስተካከልና ከጉዳት ለማገገም ይመረጣል፡፡ በአጠቃላይ የማሳጅ ሕክምና ሰውነትን ዘና ለማድረግ፣ የጡንቻ ውጥረትን ለማስወገድ፣ ጥሩ ስሜት ለመፍጠር፣ የሰውነት መሳሳብና መተጣጠፍን ለመጨመር፣ ድብርትንና ጭንቀትን ለማስወገድ፣ የደም ዝውውርን ለማቀላጠፍ፣ የወሲብ ስሜት እንዲጨምር ለማድረግ እንደሚረዳ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ይናገራሉ፡፡

የማሳጅ አገልግሎቱ በተገቢው ባለሙያና በትክክለኛው ቁሳቁሶች እየታገዘ ሊሰጥ ይገባዋል የሚሉት ባለሙያው፤ የመታሻ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የመደገፊያ ትራሶች፣ የእግር ማሳረፊያ፣ የአንገት ማንተራሻ፣ ልዩ ልዩ ቅባቶችና የኤሌክትሪክ ጡንቻ ማነቃቂያ መሳሪያዎች እንደሚያስፈልጉትም ይገልፃሉ፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ያለ ባለሙያና ትክክለኛ የማሳጅ ህክምና መስጫ መሣሪያ የሚከናወነው ማሳጅ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የጐላ መሆኑንም ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ የማሳጅ ህክምና ለሁሉም ሰው አስፈላጊና ተመራጭ ህክምና መሆኑን የሚገልፁት አቶ ዮሐንስ፤ ህክምውን መጠቀም እንደሌለባቸው የሚመከሩ ሰዎች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የደም መጓጐል ችግር ያለባቸው፣ ለቅባቶቹ አለርጂ የሚሆኑ ሰዎች፣ በቀላሉ የሚላላጥ ቆዳ ያላቸው፣ እርጉዞች፣ የአጥንት መሳሳት ችግርና ጠንከር ያለ ውስጣዊ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ህክምናውን ባይወስዱ እንደሚሻል ይገልፃሉ፡፡ የማሳጅ ህክምና ለበርካታ በሽታዎች እፎይታንና እረፍትን እንደሚሰጥ ሁሉ በአግባቡ ካልተከናወነም የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ ነውና ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ሲሉ ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡ በየአካባቢው በሚገኙ ማሳጅ ቤቶች ውስጥ ከሚገኙት ሠራተኞች መካከል ምን ያህሉ ሙያውን የተማሩና ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑ ናቸው የሚለውን ለማወቅ ግን ጥናት ያስፈልጋል፡፡

Read 9533 times Last modified on Saturday, 29 June 2013 10:28