Saturday, 29 June 2013 10:58

ቆራጡ አብዮታዊ መሪ አህመድ ሴኩቱሬ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(1 Vote)

“ተቃዋሚዎች ከከባድ ቁስል የባሰ የሚያሳምሙ እከኮች ናቸው”

     የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን አስደናቂ የማደራጀት ችሎታ አሳንሼ አቀርባለሁ አሊያም እተቻለሁ ብሎ የሚነሳ ማንም ሰው እንኳን በምድረ ጊኒ ይቅርና በፈረንሳይ ውስጥም ቢሆን እህ ብሎ የሚያዳምጠው ሰው ማግኘት መቻሉ በጣም ያጠራጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ሰውየው ያላቸው የማደራጀት ችሎታ እንዴት ያለ እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት ካስፈለገ የጊኒን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ከተራና እዚህ ግባ ከማይባል የሰራተኛ ማህበርነት አንስተው እንዴት ወዳለ ጠንካራና መሠረተ ሰፊ ፓርቲነት እንደቀየሩት መመልከት ብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡ በ1957 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ከምክር ቤቱ ስልሳ መቀመጫዎች ሀምሳ ስድስቱን ጠራርጐ የወሰደበት ዋነኛው ምስጢር፣ ያኔ የሰላሳ አምስት አመት ጐልማሳ የነበሩት አህመድ ሴኩቱሬ፣ ይህ ቀረሽ የማይባል የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ከፍተኛ ችሎታ ነበር፡፡ ይህንን ከፍተኛ የማደራጀት ችሎታቸውን በመጠቀምም የፓርቲውን መዋቅር ከመደበኛው የመንግስት መዋቅር እኩል ከከፍተኛው አካል እስከ ዝቅተኛው የቀበሌ አካል ድረስ ወርዶ እንዲዘረጋ አደረጉ፡፡

ከመደበኛው የመንግስት የአስተዳደር አካል በበለጠ ስልጣንና ሀላፊነት ለፓርቲው በመስጠት፣ የህዝቡ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከፓርቲው ጋር በቀጥታ እንዲቆራኝ አደረጉ፡፡ መደበኛ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል መሆንን በቅድሚያ ግዴታነት አስቀመጡ፡፡ ከአንድ የካቢኔ ምኒስትር ይልቅ ለምኒስትር መስሪያ ቤቱ የፓርቲው መሠረታዊ ድርጅት ፀሀፊ የበለጠ አይነት ስልጣን አጐናፀፉት፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ፓርቲያቸውን በዚህ አይነት ካዋቀሩ በኋላ ግንባር ቀደም ካድሬዎቻቸውን ሰበሰቡና እንዲህ በማለት የስራ መመሪያ ሰጧቸው፡- “ጓዶች! በጫካው ውስጥ ዝሆኖች እንደሌሉ ከታወቀ ጐሾች ዝሆን ነን ማለታቸው እንደማይቀር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ስለዚህ ለፓርቲያችን ተቃዋሚዎች ወይም የፓርቲያችን አባላት ላልሆኑት ሁሉ ዝሆኖች እናንተ መሆናችሁን በሚገባና በግልጽ ማሳየት አለባችሁ፡፡ ምርጫ ያለው ሰው ምንጊዜም ቢሆን ችግር ሊፈጥር እንደሚችል መዘንጋት የለባችሁም፡፡ እናም ሰዎች ከፓርቲያችን ውጪ ሌላ ምርጫ እንዳይኖራቸው ማድረግ አለባችሁ” ቤተመንግስታቸው የሚገኝበት የሰሜን ምዕራብ ኮናክሪ አንዱ የቀበሌ መስተዳድር ለፓርቲው አባላት ባዘጋጀው የንቃተ ህሊና ማዳበሪያ ስብሰባ ላይ ድንገት ከች ያሉት ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ፤ ስለ ጊኒ አብዮትና “የምዕራቡ የአድህሮት ሀይላት የጊኒኒ አብዮት ለመቀልበስ” ስለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ረጅም ንግግርና ሰፊ ገለጻ ካደረጉ በኋላ፣ በመጨረሻ ለተሰበሰበው ህዝብ አንድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

“ጓዶች! እስስት ታውቃላችሁ?” ህዝቡ በአንድ ድምጽ ጮክ ብሎ “አዎ!” በማለት መለሰላቸው፡፡ “እስስት የሚታወቅበት ተፈጥሮው ምን እንደሆነስ ታውቃላችሁ?” ህዝቡ እንደ መጀመሪያው ጥያቄ በአንድ ላይ ሳይሆን እንዲሁ እንደ መሰለው ሲመልስ፣ የቀበሌው ግንባር ቀደም ወይም ጠርናፊ የሆነው ካድሬ ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ሁለት እጆቹን በማንሳት፣ ህዝቡን ፀጥ ካሰኘ በኋላ “ቆራጡ መሪያችን ጓድ ሊቀመንበር! እስስት ከሌላው እንስሳት ተለይቶ የሚታወቅበት ልዩ ተፈጥሮው ከአካባቢው ጋር ለመመሳሰል ቀለሙን መለዋወጥ መቻሉ ነው! እናሸንፋለን!” በማለት ህዝቡን ወክሎ መልስ ሰጠ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ መልሱ እንዳረካቸው ለመግለጽ ችምችም ብለው የተተከሉትንና ልዩ ንጣት ያላቸውን የሚያምሩ ጥርሶቻቸው ከዳር እስከ ዳር እስኪታዩ ድረስ ፈገግ ብለው አንድ ሶስቴ ያህል ካጨበጨቡ በኋላ “ይሄውላችሁ ጓዶች!” የጠንካራውና የመሪ ፓርቲያችን አባላት እንደመሆናችሁ መጠን ፓርቲያችንንና አብዮታችንን ከተቃዋሚዎችና ከአድሀሪያን ሀይሎች ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ሁልጊዜም ይጠበቅባችኋል።

ይህን አብዮታዊ ሀላፊነት በድል ለመወጣት ደግሞ እስስት መሆን የግድ ይጠበቅባችኋል። በምትኖሩበት ቦታ ሁሉ እንደ እስስት እየተንቀሳቀሳችሁ፣ የፓርቲያችንንና የአብዮታችንን ጠላቶች እያጋለጣችሁ መመንጠር አለባችሁ!” አሉዋቸው፡፡ የተሰበሰበው ህዝብም የግራ እጁን ወደ ላይ በማውጣት “የፓርቲያችንና የአብዮታችን ጠላቶች ይወድማሉ! እናሽንፋለን!” በማለት መቼም ቢሆን ቸል የማይባለውን የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ መቀበሉን አረጋገጠ፡፡ የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ባለስልጣኖችና መሪ ግንባር ቀደም ካድሬዎች፣ በየካቲት ወር 1960 ዓ.ም የተላለፈውን የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ቀጭን ትዕዛዝ በተራቸው እስከ ዝቅተኛው ቀበሌ የሚገኙ ጊኒያውያን በስራ ላይ እንዲያውሉት የመንግስትና የፓርቲውን መዋቅር በመጠቀም የቅርብ ቁጥጥር ማድረግ ጀመሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲን የህዝቡ ፓርቲ፣ ህዝቡንም የፓርቲው ለማድረግ ያደረጉት እንቅስቃሴ፣ በአንድ እጅ ጣቶች በሚቆጠሩ ወራት ብቻ ያስገኘላቸው ውጤት በእጅጉ አርክቷቸዋል፡፡

መደበኛ የሆኑ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ይቅርና ከሰፈር ቦኖ ውሀ ለመቅዳት እንኳ ያለ ፓርቲ አባልነት የሚቻል ባለመሆኑ የፓርቲውን የአባልነት መታወቂያ ካርድ ለማግኘት ጊኒያውያን ሙሉ የወር ገቢያቸውን በየደረጃው ላሉ የፓርቲ ፀሀፊዎችና መሪ ካድሬዎች ጉቦ ከመስጠት ጀምሮ የማያደርጉት ጥረት አልነበረም፡፡ “ልክ እንደ እስስት መንቀሳቀስ አለባችሁ” የተባለውን የፕሬዚዳንቱን ቀጭን ትዕዛዝ በተግባር ለመፈፀምም የፓርቲው አባላት የስራ ባልደረቦቻቸውን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን፣ ጐረቤቶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሳይቀር ጠቅላላ የየእለት እንቅስቃሴአቸውን እየተከታተሉ ለጠርናፊ ካድሬዎቻቸው የየእለቱን ሪፖርት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ቀድሞውኑም አነስተኛና የተበታተኑ የነበሩት የጊኒ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በጊኒ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ይበልጡኑ ለእግር መትከያ የሚሆን ቦታ እንኳ ማግኘት አቃታቸው፡፡ ይህንን ብሶታቸውን በማሰማትም ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስዱ በይፋ ጠየቁ፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሰጡት ምላሽም ቅልብጭ ያለና ፈጣን ነበር፡፡ “የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ በ1957 ብሔራዊ ምርጫ ማግስት ያቀረበላችሁን ታላቅ አብዮታዊ ግብዣ ንቃችሁ ትታችሁታል፡፡ ያ ትልቅ እድል መቸም እንደማይመለስ ሆኖ አልፏል፡፡

ያኔም ሆነ ዛሬ እናንተ የመረጣችሁትና የፈለጋችሁት የፀረ-አብዮተኞች በተለይ ደግሞ የምዕራብ አድህሮት ሀይላት አንጋች መሆንን ነው፡፡ ዛሬ እኛ ፍየሎች እናንተ ደግሞ ነብሮች ናችሁ፡፡ ታዲያ ፍየሎች ከነብር መንጋ ጋር ሲኖሩ ያያችሁት ከመቼ ወዲህ ነው?” በማለት ነበር ፕሬዚዳንቱ ለተቃዋሚዎች የመለሱላቸው፡፡ በ1957 ዓ.ም በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ፣ የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ከስልሳ የምክር ቤት መቀመጫዎች ሀምሳ ሰባቱን ማሸነፉ በጊኒ የምርጫ ቦርድ በይፋ እንደተረጋገጠ፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ሴኩቱሬ ሶስት መቀመጫዎችን ብቻ ላሸነፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፓርቲዎቻቸውን በመተው የእሳቸው ፓርቲ አባላት እንዲሆኑ ጠይቀዋቸውና ይፋ ግብዣ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ መቸም የማይመለሰው ትልቅ እድል ያሉትም ይህን ግብዣቸውን ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን አንዳንዶቹ ነፃነታቸውን ጠብቀው በተቃዋሚነት ለመቀጠል በመምረጥ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወግና ስርአት ባለው ሁኔታ ቦታችንና ሚናችን ታውቆ ባይሆን ውህደት እንፈጽም እንጂ እንዲያው ዝም ብለን ፓርቲዎቻችንን አፈራርሰን እንዴት የዲሞክራቲክ ፓርቲው ተራ አባላት እንሆናለን በማለት የፕሬዚዳንቱን ግብዣ ውድቅ አደረጉት፡፡

ከዚህ በሁዋላ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ጥቂት ጊዜ ያጠፉበት አብይ ጉዳይ ተክለ-ሰብዕናቸውን መገንባት ላይ ነበር፡፡ ይህንን እቅዳቸውን ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ እንደ ፓርቲያቸው መዋቅርና ግንባር ቀደም ካድሬዎቻቸው በሚገባ ያገለገላቸው ፈጽሞ አልነበረም፡፡ “ቆራጡ አብዮታዊ መሪ! ታላቁ የአፍሪካ ልጅ! የኢምፔሪያሊዝ ውጋት! የቅኝ አገዛዝ መጋኛ! የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መቅሰፍት! የአብዮታዊ ሳይንሶች ዶክተር!” የሚሉትን ስያሜዎች ተጨንቆና ተጠቦ በማውጣት ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬን የሰየማቸው ፓርቲያቸው ነበር፡፡ ስያሜዎቻቸውን በህዝቡ ዘንድ ያሰረፁትና ሌሎች ተጓዳኝ የተክለ-ሰብዕና ግንባታ ስራዎችን በከፍተኛ ብቃትና አብዮታዊ መንፈስ ቀን ከሌት ላይ ታች ብለው ያስፈጸሙት ደግሞ በየደረጃው ያሉ መሪ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ እናም ታዲያ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በየትኛውም ቦታና አጋጣሚ ሁሉ በእርሻም ሆነ በምህንድስና፣ በፍልስፍናም ሆነ በእግር ኳስ በማንኛውም አይነት የእውቀት ዘርፍ አቻ የለሽና ታላቅ ምሁር እንደሆነ ተደርገው ይቀርቡ ነበር፡፡

አባባ ጃንሆይ በተለያየ ጊዜ ያደረጓቸውን ንግግሮች አካቶ የያዘ “ፍሬ ከናፍር ዘ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ፣ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ” የሚል ባለ ብዙ ቅፅ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም በተለያየ ጊዜ ያደረጉትን ንግግርና የጊኒን አብዮትና የአፍሪካን እድገት በማስመልከት የሰጧቸውን ገለፃዎች ያካተተ ባለ ሀያ ሶስት ቅፅ መጽሀፍ አሳትመው በጥሞና እንዲያነቡት ከትዕዛዝ ጋር ለህዝባቸው እንዲሠራጭ አድርገዋል፡፡ እነዚህን የፕሬዚዳንቱን መጽሀፍት በማንበብ በኩል ከተራው ህዝብ ይልቅ ተማሪዎች ያለባቸው ሀላፊነት በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ በተለይ ከአንደኛ ደረጃ በላይ ያሉ ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል ለመዘዋወር የሚሠጣቸውን ፈተና ማለፍና ከሀያ ሶስቱ ቅጾች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ መጽሀፍት በቃል ሸምድዶ መያዝ ብቻ አይበቃም፡፡ ፕሬዚዳንቱ የጊኒን የፀረ-ቅኝ አገዛዛ ትግልና የምዕራባውያን የአድህሮት ሀይሎችን ሴራ “ያጋለጡበትን” የተለያዩ እጅግ በጣም ረጃጅም አብዮታዊ ግጥሞችን ሸምድዶ በቃል ማነብነብ መቻልም የግድ ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ይህንን የተክለ-ሰብዕና ግንባታ እንደማይፈልጉ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ “ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ እንጂ እኔማ አንድ ተራ ግለሰብ እኮ ነኝ!” ይሉ ነበር፡፡ ይህ አባባላቸው ግን ፈጽሞ ውሸት ነበር፡፡ እንዴት ቢባል ጉዳዩን ከጀርባ ሆነው የሚያስተባብሩትና የሚመሩት እርሳቸው ስለነበሩ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ የተክለ ሰብዕና ግንባታ እንቅስቃሴ ለፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ተራ ዝና ለመገንባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አልነበረም። በርካቶች የሰላ ትችት ያቀርቡባቸው እንደነበረው በአፍሪካ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግልና በጊኒ ድህረ-ነፃነት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና፣ ኢኮኖሚያዊ ህይወት ውስጥ አብዛኛውን የታሪክ ምዕራፍ በዋናነት ሞልቶ ለመያዝ ከነበራቸው ይህ ነው የማይባል ፍላጐት በመነሳት ብቻ የተደረገም አልነበረም፡፡ ለእሳቸው ጉዳዩ ከዚህ ያለፈ ፋይዳ ነበረው፡፡ ራሳቸውን የፓርቲው እስትንፋስ ለማድረግ የነደፉትን ዋናውን እቅዳቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ፈጣንና ቀላል ለማድረግ የመረጡት ስትራተጂ ተክለ ሰብዕናቸውን መገንባት ነበር፡፡

እንዳሰቡትም ከፍ ያለ ውጤት አስገኝቶላቸዋል፡፡ “የሁሉም አብዮታዊ ሳይንሶች ዶክተር” የተባሉት ሴኩቱሬ፤ በፓርቲው የፖሊት ቢሮም ሆነ የማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንኳን ንግግራቸው ይቅርና የአይን ጥቅሻቸውና የእጅ እንቅስቃሴአቸው ሳይቀር እንደዋና መመሪያ ተደርጐ ተቆጠረ፡፡ እሳቸው ያቀረቡትን ማናቸውም አይነት ንግግር ገለፃ ወይም አስተያየት ደግፎ ከማጨበጨብ በቀር የድጋፉም ቢሆን ተጨማሪ አስተያየት መስጠት እንደ ከባድ ወንጀል መታየት ቀጠለ፡፡ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ለቢሮ ጽዳት የሚያገለግል መጥረጊያ እንደመግዛት ያለ እጅግ ተራ ውሳኔም ቢሆን ያለ እሳቸው እውቅናና ፈቃድ መወሰን እንደ ፀረ አብዮተኛ አስቆጥሮ በቀጥታ ወህኒ ማስወርወር ጀመረ፡፡ በፓርቲውም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የፈለገው አይነት ስልጣን ምንጭ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬና እሳቸው ብቻ ሆኑ፡፡ የእሳቸውን ሞገስ ያገኙት ከተራው እስከ ከፍተኛው የምኒስትርነትና የፓርቲ ፀሐፊነት ስልጣን ሲሾሙ፣ ያላገኙት ደግሞ ከስልጣናቸው ይባረራሉ፡፡

በማናቸውም አይነት የህግ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በህዝቡ ስምና ለህዝቡ ጥቅም በሚል የራሳቸውን ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ለምን ብሎ ደፍሮ የሚጠይቃቸው የለም፡፡ እሳቸው በሁሉም የእውቀት ዘርፍ ከሁሉም የላቁ ምሁር ናቸዋ! በዚህ አይነት ጊኒ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣች በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ የፓርቲያቸውና የመንግስታቸው እስትንፋስ ብቻ ሳይሆን የጊኒና የህዝቦቿን የእለት ተእለት ህይወት የሚወስኑ አዛዥና ናዛዥ የሌላቸው ብቸኛው ሰው ሆኑ፡፡ ጊኒም፤ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ብቸኛው ተዋናይ ሌሎች ደግሞ ለእርሳቸው ክብር አጨብጫቢ፣ በእሳቸው ሙዚቃ ብቻ ጨፋሪ የሆኑበት የአንድ ሰው ትርኢት መድረክ ሆና ራሷን አገኘችው፡፡ ተፈጥሮ ሙሉ ልግስናዋን ለጊኒ አሳይታለች። ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በአለምአቀፍ ደረጃ የሚጠቀስ እጅግ ከፍተኛ የብረትና የቦክሳይት ማዕድናት ክምችት አድላታለች፡፡ በዚህ የተነሳ ጊኒ በቀላሉ ለማደግ ከፍተኛ እድል ነበራት፡፡ የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ግን ያንን ከፍተኛ እድል “ላም አለኝ በሰማይ” ሆኖ እንዲቀር አደረገባት፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ጊኒን ከፈረንሳይ ተጽእኖ ለማላቀቅና ስራ ፈጣሪ የሆነ ልዩ ጉልሃን (elit) ቡድን እንዳይፈጠር ለመከላከል በሚል ሁሉንም የኢኮኖሚ ሴክተሮች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን አደረጉ፡፡

ግለሰብ ነጋዴዎችን ከሃዲ ፀረ አብዮተኛና የኢምፔሪያሊዝም ቡችሎች ብለው በአደባባይ አወገዟቸው፡፡ ይባስ ብለውም የመንግስት ፋብሪካዎችንና እርሻዎችን በፓርቲው ካድሬዎች እንዲመሩ አደረጉ፡፡ እነሱም ከፓርቲ ካድሬነት ውጪ ምንም አይነት የስራ አመራር ችሎታና እውቀት ስላልነበራቸው ውጤቱ አደገኛ ውድቀት ብቻ ሆነ፡፡ ፕሬዚዳንት ሲኩቱሬ የኢኮኖሚ ፖሊሲያቸውን ውድቀት በ”ምዕራብ አድህሮት ሃይሎች ታላቅ ሴራ” የተከሰተ እንደሆነ በድርቅና አመካኙ፡፡ ይግረማችሁ በሚል አይነትም በ1977 ዓ.ም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጊኒያውያን የእለት ተዕለት ህይወት የተመሰረተበትን የአካባቢና የጉልት ገበያዎች እንዲነሱ፣ ገበሬዎችም ምርቶቻቸውን ለመንግስት የገበያ ድርጅት (እኛ እንደነበረን እርሻ ሰብል ገበያ ድርጅት አይነት) ብቻ እንዲሸጡ የሚያስገድድ መመሪያ አወጡ፡፡ ይህ መመሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጊኒያውያንን ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ ከተተው፡፡ በዚህ መመሪያ የተነሳ የቤታቸው ሌማት ክው ብሎ የደረቀባቸው የሰፈር ጉልት ሻጭ ሴቶች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት ወደ ቤተመንግስት አመሩ። እዚያ ሲደርሱ የጠበቃቸው ግን ችግራቸውን የሚያዳምጥ ፕሬዚዳንት ሳይሆን የቤተመንግስቱ ጠባቂ የክብር ዘበኛ ጦር ጥይት ነበር፡፡

የፓርቲው ልሳን የሆነው “ሆሮያ” የተሰኘው ጋዜጣ፣ በርካታ ሰልፈኞች የተገደሉበትን ይህን የተቃውሞ እንቅስቃሴ “በአብዮትና በፀረ አብዮት መካከል የሚደረግ ትግል ነው” በማለት አስረዳ፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም በበኩላቸው፤ አድማውን “የአምስተኛ ረድፈኞች ሴራ ነው” በማለት ካወገዙ በኋላ፣ ህዝቡ ተራራውን ሳይወጡ የተንጣለለውን የእርሻ መስክ ማየት እንደማይቻል መገንዘብ እንዳለበት ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ የሆነ ሆኖ ከፍተኛ አዘቅት ውስጥ በገባው ኢኮኖሚ የተነሳ ጊኒን ሙሉ በሙሉ ከመንኮታኮት በጊዜው የታደጋት በውጭ ኩባንያዎች እየተመራ እንዲቆይ ልዩ ፍቃድ በተቸረው የቦክሳይትና የብረት ማዕድን ሽያጭ ባገኘችው ገቢ ብቻ ነበር። ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በሶሻሊስት ርዕዮተአለም እየተመሩ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በጊኒ እንዲኖር ጥሬአለሁ በማለት አዘውትረው ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ይህን ቢሉም በተግባር ያደረጉት ግን ድህነትን ለመላው ጊኒያውያን ማካፈል ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በፖለቲካውም መስክ ያሳዩት አመራር ከኢኮኖሚ አመራራቸው በእጅጉ የከፋና ለምን “ቆራጡ አብዮታዊ መሪያችን” እንደተባሉ በትክክል የሚያሳይ ነበር፡፡

ከ1957 እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ በነበሩት ጊዜያት ተቃዋሚዎችን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ የነበራቸው አቋም ፓርቲዎቻቸውን እየተው የሳቸውን ፓርቲ በተራ አባልነት እንዲቀላቀሉ መጋበዝና መጐትጐት ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም መግቢያ ላይ ግን “እንግዲህ ሁለታችንም (ራሳቸውንና ተቃዋሚዎችን) የቤቱ አባወራ ከሆንን ግመሎችን ታዲያ ማን ሊመራቸው ነው?” ማለት አመጡ፡፡ ነገርየው በአንድ ቤት ሁለት አባወራ አይኖርም ለማለት ብቻ ሳይሆን በአንድ ሀገርም ሁለት መሪ ሊኖር አይችልም ብሎ ለመናገር ነው፡፡ ቀጠሉና ደግሞ “ከከባድ ቁስል ይልቅ ለመቋቋም የሚከብድ ሀይለኛ ህመም የሚፈጥረው እከክ ነው!” ማለት ጀመሩ፡፡ የፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ አባባል ሰምና ወርቅ ያለው ቅኔ አልነበረም፡፡ ተቃዋሚዎች ከከባድ ቁስል የባሰ የሚያሳምሙ እከኮች ናቸው ማለታቸው ነበር፡፡ በሌላም በኩል ፕሬዚዳንቱ ለተቃዋሚዎች ምን አይነት ድግስ እየደገሱላቸው እንደሆነ በግልጽ የሚያመላክት ነበር፡፡

እናም እከክ ያሏቸውን ተቃዋሚዎችንና ሌሎች “ፀረ - አብዮተኞችን” ከጊኒ የፖለቲካ መድረክ ጨርሶ ለማስወገድ ከሰው አፍ የማያስገባ ሰበብ ለመፍጠር እያሰላሰሉ በነበረበት ወቅት ድንገት አንድ “መልካም” አጋጣሚ ደጃቸው ድረስ ከች አለላቸው። በ1960 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በምዕራብ የአድህሮት ሃይሎችና የነሱ ቡችላ በሆኑ የጊኒ አብዮት ጠላቶች የተቀነባበረ ነው የተባለ የግድያና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ በሙከራው ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት የሃምሳ አለቆችን ጨምሮ ወደ አስር የሚጠጉ የክብር ዘበኛ ጦር አባላት የሆኑ ወታደሮች እዚያው ቤተመንግስቱ ውስጥ ተረሸኑ፡፡ ይህ በሆነ በማግስቱ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በኮናክሪ አደባባይ ያደረጉት ንግግር፤ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም በ1967 ዓ.ም የደርጉ ሊቀመንበር የነበሩትን ጀነራል ተፈሪ በንቲንና ሌሎች ተቀናቃኞቻቸውን ቤተመንግስት ውስጥ ከረሸኑ በኋላ በአብዮት አደባባይ ያደረጉትን ንግግር የሚያስታውስ ነበር፡፡

“የምዕራብ የአድህሮት ሃይሎች ወኪል በሆኑ ከሀዲ ፀረ አብዮተኞች የተቃጣው የአብዮት ቅልበሳ ሴራ በሀቀኛ የአብዮቱ ልጆች ተበጣጥሶ ከሽፏል። የጊኒ አብዮተኞች ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ይሸጋገራሉ፤ የኢምፔሪያሊዝም ቅጥረኛ የሆኑ ፀረ አብዮተኞችን ከገቡበት እየገቡ የእጃቸውን ይሰጧቸዋል!” በማለት ፕሬዚዳንቱ በአደባባዩ ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር አደረጉ፡፡ ይህ ንግግራቸውም በጊኒ የድህረ ነፃነት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የጨለማው ዘመን መጀመሩን የሚያበስር ንግግር ሆኖ ተመዘገበ፡፡ የዘፈቀደ እስር፣ የይስሙላ ፍርድ፣ የአደባባይ ርሸናና አሰቃቂ ግርፋት የእለት ተዕለት ክንውን ሆነ፡፡ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው የዚህ አሰቃቂ እርምጃ ዋነኛ ሰለባዎች ሆኑ፡፡ የደመወዝ ጭማሪ የጠየቁ መምህራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ጋር እንዲፎካከሩ እጩዋቸውን ያቀረቡ ነጋዴዎች ታስረው ለሳምንታት በአስከፊ ሁኔታ በግርፋት ሲሰቃዩ ከከረሙ በኋላ በአደባባይ ተረሸኑ፡፡ በ1970 ዓ.ም ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ድንገት በቴሌቪዥን ብቅ አሉና “የኢምፔሪያሊዝምና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ቡችሎች የሆኑ አምስተኛ ረድፈኞች፤ በፓርቲያችንና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከታች እንደተሰገሰጉ ተደርሶባቸዋል” በማለት መግለጫ ሰጡ፡፡

ከሶስት ቀናት በኋላም በመቶ የሚቆጠሩ ምኒስትሮች፣ የገዥው የጊኒ ዲሞክራቲክ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎችና አምባሳደሮች በቁጥጥር ስር ውለው በከፍተኛው አብዮታዊ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በቴሌቪዥን ታዩ። አንዳቸውም ጠበቃ አቁመው ለመከራከርም ሆነ የህግ የምክር አገልግሎት ለማግኘት ይቅርና የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት እድል አላገኙም። በጥይት እንዲደበደቡ ከተወሰነባቸው ሌላ በስቅላት እንዲቀጡ የተበየነባቸው ሃምሳ ስምንት ባለስልጣኖች በኮናክሪ አደባባይ ሲሰቀሉ ሂደቱን በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሁኔታውን የገለፀው “በኮናክሪ የአብዮት አደባባይ አሁን አንድ አሪፍ የካርኒቫል ትርኢት በመካሄድ ላይ ይገኛል” በማለት ነበር፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ከፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ጋር ያላቸው ቅርበትና ወዳጅነት ዋስ ጠበቃ ይሆነናል ብለው ተማምነው ነበር፡፡ ይህ እምነታቸው ግን ባዶና ከንቱ ቀቢፀ ተስፋ ብቻ ነበር። “የአብዮታዊው መሪ አብዮታዊ ሰይፍ” ለቅርብ ወዳጅነት ቅንጣት ታክል ቁብ የሌለው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ በጥይት አስደብድበው ወይም በስቅላት ካስገደሏቸውና የሞት ቅጣቱ ቢቀርላቸውም በወህኒ ቤት እድሜ ልካቸውን እየማቀቁ እንዲኖሩ በእስራት ከቀጧቸው ባለስልጣኖች ውስጥ ሀምሳዎቹ የቅርብ የትግል አጋርና ወዳጃቸው የነበሩ ምኒስትሮች ናቸው፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ጊኒ ካፈራቻቸው ድንቅ ዲፕሎማቶች አንዱ የሆኑትና አቶ ክፍሌ ወዳጆን ተከትለው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ዲያሎ ቴሊ ይገኙበታል፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬ ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ተጠናውቷቸው ሌት ተቀን ሲያባንናቸው የኖረው ክፉ መንፈስ የጊኒን አብዮት ለመቀልበስ “የምዕራባውያን አድህሮት ሃይሎችና የሀገር ውስጥ ቡችሎቻቸው ሴራ” ነው አሉ፡፡ ለምሳሌ በ1972 ዓ.ም በመላው ጊኒ የመድሀኒት እጥረት ተከሰተና ጉዳዩ ተነገራቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሴኩቱሬም በቴሌቪዥን ቀረቡና በጊኒ የተከሰተው የመድሃኒት እጥረት የተፈጠረው የኢምፔሪያሊዝም ቅጥረኞች የሆኑ ሃኪሞች የአብዮቱን ገጽታ ለማበላሸት ሆን ብለው በሸረቡት ሴራ መሆኑን ተናገሩ፡፡ በ1973 ዓ.ም በጊኒ አንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ሲነገራቸው ወረርሽኙ የተከሰተው በፀረ - አብዮተኞች ሴራ እንደሆነና ይህንን ታላቅ የፀረ አብዮተኞች ሴራ ህዝቡ በንቃት በመከታተል እንዲያከሽፈው ጥሪያቸውን አቀረቡ፡፡ በ1976 ዓ.ም ደግሞ ለአፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ለፍፃሜ ደርሶ የነበረው የጊኒ ብሔራዊ ቡድን የተሸነፈው፣ ፀረ አብዮተኞች በጐነጐኑት ሴራ እንደሆነ በይፋ አስታወቁ፡፡

ይህን በመሰለው የቆራጡ አብዮታዊ መሪ አህመድ ሴኩቱሬ፤ አገዛዝ ስር የወደቁት ጊኒያውያን ቀስ በቀስ በባርነት ከሚገኝ የድሎት ኑሮ ይልቅ ነፃነታችንን ተጐናጽፈን በድህነት ብንኖር ይሻለናል ያሉበትን ጊዜ በሹክሹክታ መራገም ጀመሩ፡፡ ይህን በማለታችሁ ተሳስታችኋል ብሎ የሚፈርድባቸው የለም፡፡ ያጡት ነፃነታቸውንም ምቾታቸውንም ነበርና፡፡ ይሁን እንጂ አንሾካሹከው ብቻ ፀጥ አላሉም፡፡ ከጠቅላላ ቁጥራቸው አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ጊኒያውያን የቆራጡ አብዮታዊ መሪን የብረት ክንድ ለማምለጥ ወደ ጐረቤት አገሮች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዱ፡፡

Read 5261 times