Saturday, 29 June 2013 11:01

ጽንስ ወደ ድንጋይነት ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

“አንድ ጥያቄ አለኝ..... በሚል ጽሁፋቸውን የጀመሩ አንድ አንባቢ የሚከተለውን ብለዋል። ..... እኔን የሚገርመኝ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። እርግዝና ተፈጠረ...እሰይ...ልጅ ላገኝ ነው...ብሎ ምስጋና ለፈጣሪ ሲያቀርቡ የቆዩ ባልና ሚስት...እርግዝናው በትክክለኛው ቦታ አይደለም ...ይልቁንም በሆድእቃ ውስጥ ነው ሲባሉ ...ምን ይሰማቸው ይሆን? መቼም ሁሉም ነገር እንደምንም የማይቆጠርበት አጋጣሚ ብዙ ነውና...አ.አ.ይ ...ምንም አይደለም...እንኩዋንም እሱዋን ለቀቃት ... ወደሚለው እሳቤ ይገባል። እርግጥ ነው ...ሴትየዋ ብትተርፍ እንደገናም ልጅ መውለድ ትችላለች፡፡ ሁኔታው ግን እጅግ ያሳስባል...” ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለንባብ በቀረበው ከማህጸን ውጭ እርግዝና በመነሳት ሌሎች ጥያቄዎችም ደርሰውናል፡፡ ሶስት ጥያቄዎችን ያዘለው እና በድህረገጻችን የደረሰን መልእክት እን ዲህ ይላል፡፡ “በቅድሚያ ከማህጸን ውጭ እርግዝናን በተመለከተ ላወጣችሁት ጽሁፍ በጣም አመሰግ ናለሁ፡፡ ችግሩ በእኔም ቤት ተከስቶ ስለነበር በተመስጦ አንብቤዋለሁ፡፡

የእኔ ሚስት የ27/አመት እድሜ ያላት ስትሆን የአንድ ልጅ እናት ናት፡፡ ልጃችን የ3/ አመት እድሜ ሲይዝ ሌላ ልጅ ተረገዘ፡፡ ባላሰብነው መንገድ ሚስ በድንገት ታመመች...ለካስ እርግዝናው ከማህጸን ውጭ ነበር፡፡ ወደህክምናው ስትቀርብ ሐኪሙ የነገረን ጽንሱ ያረፈው በዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ስለሆነ ቱቦውም ጭምር ይወገዳል የሚል ነበር። ወደፊት ልጅ ስለመውለድ መቻልዋ ስንጠይ ቀውም መውለድ እንደምትችል ነግሮናል፡፡ ነገር ግን የእኔ ጥያቄ... የዘር ማስተላለፊያ ቱቦን ማስወገድ ሌላ የአካል ጉድለትን አያመጣምን? በአንድ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ብቻ ልጅ መውለድ ይቻላልን? በስንት አመት ልዩነት ነው ማርገዝ የምትችለው?...የሚል ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በብራስ የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር አቅርበን የሰጡን መልስ ከማህጸን ውጪ እርግዝና የተከሰተበት የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ መወገዱ ትክክል እንደሆነና በአንድ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ አማካኝነትም ልጅ ማርገዝ እንደሚቻል ነው።

የጊዜውም ጉዳይ እንደፈለጉት እንጂ በዚህ ጊዜ የሚል ገደብ እንደሌለው ነግረውናል፡፡ ነገር ግን ምናልባት አሁንም በቀረው የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ላይ ከማህጸን ውጭ እርግዝና ከተከሰተና እሱም ከወጣ ልጅ ማርገዝ የሚባለው ነገር የሚቋረጥ ይሆናል ብለዋል፡፡ ...በቀጣይ የምናስነብባችሁ የአንዲት ሴትን የቅርብ ቀናት ገጠመኝ ነው፡፡ ሴትየዋ ከ5-6 ወር የሚገመት እርጉዝ ነች፡፡ ሕመም እንደሚሰማት ለሐኪሞች ገልጻ ምርመራ ትጀምራለች። በመጀመሪያው ቀን ምርመራ የልጁዋ የልብ ምት እንደሚሰማ ገልጸውላት በሚቀጥለው ቀን እንድትመለስ ትደረጋለች፡፡ በቀጣዩ ቀን ግን የልጁዋ የልብ ምት አይሰማም ነበር፡፡ ስለዚህ ልጁ በሕይወት ስለሌለ ይወለድ ተብሎ የምጥ መርፌ ተሰጣት፡፡ ቢጠበቅ... ቢጠበቅ ምጥ አልመ ጣም፡፡ ከዚያ በሁዋላ ሴትየዋ ከነበረችበት ሆስፒታል በመውጣት ወደካዲስኮ አጠቃላይ ሆስፒ ታል ትሄዳለች፡፡

ታሪኩዋን በማስረዳትዋም ወደአልትራ ሳውንድ ምርመራ ስትላክ በማህጸንዋ ውስጥ ምንም ነገር የሌለ እና ባዶ መሆኑን ውጤቱ ያሳያል፡፡ በዚህ ጊዜ ጥርጣሬ በማሳደሩ እንደገና ወደ ባለሙያው ከታሪኩዋ ጋር ትላካለች፡፡ በዚህ ጊዜ እርግዝናው በሆድ እቃዋ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ምርመራው ግልጽ አደርጎታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው ሴትየዋን በኦፕ ራሲዮን ያዋለዱዋት ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን እንደሚሉት የሆድ እቃ ውስጥ እርግዝና ከማህጸን ውጭ እርግዝናዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ከብዙ በጥቂቱ የሚገኝ ነው፡፡ በአብዛኛው የሆድ እቃ ውስጥ እርግዝና የእን ግዴ ልጁ የሚገናኘው በሆድ ስር ወይንም በእንግሊዝኛው omentum በሚባለው ክፍል እንዲ ሁም በትንሹ ወይንም በትልቁ የአንጀት ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ማህጸንን የሚመግቡ ትላልቅ የደም ስሮች ላይ ወይንም ከማህጸን የሁዋለኛው ክፍል እንዲሁም ጉበት ፣ ቆሽት የሚባሉ የሰውነት የውስጥ አካላት ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ የእንግዴ ልጅ የሚያገኘው የደም ስርጭት ጥሩ በሆነ ቁጥር እስከ ዘጠኝ ወርም ድረስ የማደግ እድል የሚኖረው ሲሆን የደም ዝውውሩ ባነሰ ቁጥር ግን ህይወቱን የማጣት እድሉ እየሰፋ ይመጣል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን በመቀጠል እንደተናገሩትም ሕክምናዋን በሌላ ሆስታፒል ጀምራ በመሀከል ወደካዲስኮ የመጣችው ሴት በእድሜዋ ከሰላሳ አመት በላይ ስትሆን እሱዋ እንደ ምትናገረው ከዚህ በፊት ዘጠኝ ወር ደርሶ ከምጥ ጋር በተያያዘ ችግር የሞተ ልጅ ወልዳለች፡፡ በመቀጠልም በነበራት የእርግዝና ታሪክ ወደ ሁለት ጊዜ አስወርዶአታል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ አራተኛው እርግዝና ደግሞ ከማህጸን ውጭ ሆኖአል፡፡ ሴትየዋ ቀደም ሲል በታከመችበት ሆስፒታል እርግዝናው እንዲቋረጥ ከተነገራት በሁዋላ የምጥ መርፌ ተሰጥቶአት ልጁ ሊወለድ አለመቻሉ አንዱ ለጥርጣሬያችን ምክንያት ነበር፡፡

ምክንያቱም ልጁ በህይወት እስከሌለ ድረስ የምጥ መርፌው እንዲወለድ ሊያደርገው ይገባ ነበርና ነው፡፡ ነገር ግን ልጁ በማህጸን ውስጥ ስላልነበረ የማማጫ መርፌው በምንም ምክንያት ልጁ እንዲወለድ ማድረግ አልቻለም፡፡ በአል ትራሳውንድ ምርመራው ሲደረግ የታየው በሆድእቃዋ ውስጥ ፈሳሽ መኖሩ ነው፡፡ ያ ፈሳሽ ደግሞ እየደማች እንደሆነ ከግምት የሚገባ ነበር፡፡ ስለዚህ ኦፕራሲዮን እንድትደረግ ከባለጉዳዮቹ ጋር በተደረገ ስምምነት የሆድ እቃዋ ሲከፈት ልጁን ማግኘት አስቸጋሪ አልነበረም። ሕይወት ባይኖረውም ከነሽፋኑ እንዲወጣ ተደርጎአል፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝና በሆድ እቃ ውስጥ ሲፈጠር የእንግዴ ልጁ የሚያርፍበት ውስን ቦታ እንደሌለው ከላይ ተገልጾአል፡፡ ስለዚህም የዚህችን ሴት ልጅ ካወጡ በሁዋላ ቀጣዩ ስራ የእ ንግዴ ልጁ የት እንዳለ መፈለግ ነበር፡፡ በእርግጥ እርግዝናው በሆድ እቃ ውስጥ እስከሆነ ድረስ የሚመረጠው የእንግዴ ልጁን በዚያው መተውና ጊዜውን ጠብቆ ቀስ በቀስ እንዲወገድ ማድረግ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን የተፈጠረበት ቦታ አመቺነትም የሚወሰደውን እርምጃ ይወስነዋል፡፡

የዚህች ሴት ሆድ እቃ ውስጥ የእንግዴ ልጁ ያረፈው ከማህጸን የውጭ ግድግዳ እና ከሁዋላው እንዲሁም ትልቁን ደንዳኔ ጭምር ተጣብቆ ነው። እርግዝናው እድሜው ከአምስት ወር እስከ ስድስት ወር ድረስ ስለሆነው የእንግዴ ልጁ ሰፋ ያለ ቦታ ይዞ ነው የተገኘው፡፡ የእንግዴ ልጁን ማውጣት ግድ ስለነበር በከፍተኛ ጥንቃቄ ለማውጣት ተሞክሮአል፡፡ በእርግጥም ከፍተኛ መድማት ስለነበር ያንን ለማቆም ተገቢው ጥረት ተደርጎ ሴትየዋ በሰላም ወደቤትዋ ገብታለች፡፡ በሆድ እቃ ውስጥ በሚኖረው እርግዝና የእንግዴ ልጁን ማውጣት የሚያስቸግረው በተለይም በትላልቅ የደም ቧንቧዎች ላይ ተጣብቆ የሚገኝ ከሆነ እና ሊያስከትል የሚችለውን የደም መፍሰስ ማስቆም ስለማይቻል ነው፡፡ ስለዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገጥምበት ጊዜ መድሀኒት እየወሰደች የእንግዴ ልጁ ቀስ በቀስ እየሞተ በራሱ ጊዜ እንዲወጣ መጠበቅ ግድ ይሆናል፡፡ ግን በዚህም ወቅት የሚፈጠር ችግር የለም ማለት አይቻልም፡፡

አንዳንድ ጊዜ የእንግዴ ልጁ በሰውነት ውስጥ በመቅረቱ እዛው በስብሶ መግል የማጠራቀም ወይንም ፌስቱላ የሚባለውን ሕመም ሊፈጥር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በተለይም አንጀት ላይ ከሆነ አንጀት ተበስቶ ሰገራንም የመቆጣጠር ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከማህጸን ውጭ በሆድ እቃ ውስጥ የተፈጠረው እርግዝና መቀጠል ባለመቻሉ ሕይወቱ ሲያልፍ በሆድ እቃ ውስጥ በሌሎች አካላት ላይ የሚያስከትለው ችግር የለም ወይ ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር የወንድወሰን በለጠ ሲመልሱ፡- .....የሆድ ውስጥ እርግዝና ካለ የሚመከረው በፍጥነት ማከም ወይንም በኦፕራሲዮን ማውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜው ደርሶ ሊወለድ የሚችለው ከብዙ በጥቂቱ ስለሆነና የመወ ለጃ ጊዜው እስኪደርስ ሳይጠብቅ ለህልፈት የሚዳረገው ግን ብዙ ስለሆነ አስቀድሞውኑ መፍ ትሔ መስጠት ሰለሚገባ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከማህጸን ውጭ የሚፈጠሩ እርግዝናዎች የአፈጣጠር ወይንም የክሮሞዞም ችግር ሊኖራቸው እንደሚችል ብዙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሌላው ችግር በማህጸን ውስጥ እንደተረገዘ ልጅ የሽርት ውሀ በበቂ ስለማይኖረው የሴትየዋ አንጀት ወይንም ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የልጁን ቅርጽ ይቀይሩታል፡፡ ስለዚህ ልጁ የእግሩ ...የእጁ...ወዘተ የአስተዳደግ ቅርጽ ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ጭንቅላቱ የተጣመመ ሊሆን ይችላል፡፡ ከልጁም ባሻገር እናትየውም በተለይም አንጀትዋ ላይ ከሆነ የአንጀት መዘጋት ...በዚያም ምክንያት የሆድ ማበጥ ሊያስከትልባት ይችላል።

ከዚህም በላይ መጥፎ የሚሆነው የእንግዴ ልጁ ሆዳቸው ውስጥ ተላቆ ደም በመድማት እናቶች ሾክ ውስጥ የሚገቡ መሆኑ ነው፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝና በተለይም በሆድ እቃ ውስጥ ከሆነ ይደግ ተብሎ ቢተው እንኩዋን የሚያስከትለው ችግር አስከፊ ስለሆነ በጊዜ መታከም ይገባዋል ብለዋል ዶ/ር ወንድወሰን በለጠ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡ ማንኛዋም እናት የወር አበባዋ መቅረቱን ካረጋገጠችበት እለት ጀምሮ ወደሕክምና በመቅረብ የጽንሱንም ሆነ የእራስዋን ጤንነት መከታተል ይገባታል፡፡ ለዚህ ታሪክ መነሻ የሆነችው እናት ከጸነሰች ጀምሮ ምንም ክትትል ባለማድረጉዋ በስተመጨረሻ ጽንሱ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ትንሽ ግራ አጋቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ጽንሱ ከማደጉ በፊት የእናትየውን ጤንነት በተሙዋላ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ይቻላል፡፡ በጊዜው አስፈላጊው ሕክምና ሳይሰጥ በሆድ እቃ ውስጥ እያደገ ከሄደ ግን ... ሆድ ውስጥ መግል የመጠራቀም፣ አንጀት የመታጠፍ፣ አንጀት የመበሳት፣ የመድማት ...ወዘተ ችግርን ሊያስትል ይችላል፡፡ ከማህጸን ውጭ የሆድ እቃ ውስጥ እርግዝና ያለበት ቦታ በቂ ስፋት ያለው ከሆነ ጽንሱ ሕይወቱን ቢያጣም እንኩዋን ምንም ችግር ሳያመጣ ወይንም ሕመም ሳይሰማ ዝም ብሎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ከአስር እና ከሀያ አመት በሁዋላ ሴቶች በሆድ እብጠት ችግር ምክንያት ለሕክምና ይመጣሉ፡፡ በምርመራ የሚገኘው ውጤት ጽንሱ ወደ ድንጋይነት ተለውጦ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ካልሽየም ከሰውነት ወደ እርግዝናው በመሄድ ስለሚጠራቀም ነው፡፡ ስለዚህም ሴቶች ከማርገዛቸው በፊት ጀምሮ የወር አበባቸው በቀረ ማግስት የእርግዝና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል የሚል ምክር ለግሰዋል ዶ/ር የወንድወሰን በለጠ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻ ሊስት፡፡

Read 8730 times