Saturday, 13 July 2013 11:19

በመዲናችን ገጭተው የሚሰወሩ አሽከርካሪዎች ተበራክተዋል!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)
  • ገጭተው ከሚያመልጡት ውስጥ 90 በመቶው ይያዛሉ
  • ጥፋታቸው እንቅልፍ ሲነሳቸው እጃቸውን ለፖሊስ የሚሰጡ አሉ

ከሶስት ሳምንት በፊት ነው፡፡ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ አንድ ነጭ ቀለም ያለው ደብል ጋቢና ፒካፕ መኪና ከዮሐንስ ቤተክርስቲያን አቅጣጫ ወደ አስኮ መድሃኒያለም ይከንፋል፡፡ እኔ ደግሞ ከአልካን ዩኒቨርስቲ አቅጣጫ ወደ ራስ ደስታ ሆስፒታል መንገድ እያቋረጥኩ ነው፡፡ ይሄ ነጭ ፒክ አፕ በሠላም መስመሩን ይዞ እየተጓዘ የነበረን ወጣት መንገደኛ በሰከንዶች ልዩነት ውስጥ ከመኖር ወዳለመኖር ቀይሮት ሽምጥ ጋለበ፡፡ በድንጋጤ ጩኸቴን ለቀቅሁት፡፡ ራስ ደስታ ሆስፒታል አጠገብ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ አባላትና በአካባቢው ያሉ ሰዎች በአንዴ ተሰባሰቡ፡፡ ቆሞ ሲሄድ የነበረው ልጅ ድፍት ብሎ ቀረ፡፡ ትንፋሽ ቢኖረውም ከሞት የሚተርፍ አይመስልም ነበር፡፡ ወዲያው ፖሊሶችና ሌሎች ሰዎች የተገጨውን ወጣት ወደ ራስ ደስታ ሆስፒታል አስገቡት፡፡

ልጁ በነጋታው እሁድ ማታ ህይወቱ ማለፉን በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ሰምቻለሁ፡፡ መኪናውን ለመያዝ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የነበሩ ፖሊሶች ይሳካላቸው አይሳካላቸው ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ በሶስተኛው ቀን ሰኞ ሾላ ተብሎ በሚጠራውና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍ ብሎ በሚገኘው ሥፍራ አንድ መኪና አንድ ወጣት ገጭቶ ለማምለጥ ዚግዛግ ሲነዳ፣ በአካባቢው የላዳ ሹፌሮችና የህብረተሰቡ ጩኸት እንዲቆም የተደረገ ሲሆን ሹፌሩ ከልክ በላይ አልኮል ጠጥቶ ሲያሽከረክር እንደነበር የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ የተገጨው ወጣት ግን እንዳጋጣሚ አደጋው የከፋ ስላልነበር ህክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡

በዚሁ አመት ታህሳስ ወር ላይ ነው፡፡ በማለዳ ከሰሜን ሆቴል ወደ ሰሜን ማዘጋጃ ይበር የነበረ አንድ መኪና፣ ቤተክርስቲያን ለመሳለም ነጭ በነጭ ለብሰው አስፓልት ያቋርጡ የነበሩ አንዲት እናትን ሰማይ አድርሶ መሬት ላይ ካፈረጣቸው በኋላ በብርሃን ፍጥነት ተሰውሯል፡፡ እናቲቱ ግን አልተረፉም - እዚያው ጭጭ ብለው ቀሩ፡፡ ተሽከርካሪው ይያዝ አይያዝ አልታወቀም፡፡ ወ/ሪት ሳባ አለማየሁ የወንድሟን በመኪና አደጋ መሞት የሰማችው ለስራ በየሄደችበት ኩየት ሆና ነው፡፡ እናቷ አሁን በህይወት ባይኖሩም መኪናው ወንድሟን ገጭቶት እንዳመለጠ ለለቅሶ በመጣችበት ወቅት እንደነገሯት ገልፃለች፡፡ በግጭቱ ወንድሟ ብዙ ደም እንደፈሰሰው የተናገረችው ወ/ሪት ሳባ፣ ወደ ሆስፒታል የሚወስደው ቢያገኝ ኖሮ ሊተርፍ ይችል እንደነበር መስማቷን በፀፀት ገልፃልኛለች፡፡

በያዝነው አመት ጥቅምት ወር ውስጥ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በተለምዶ ቃሊቲ ገብርኤል በሚባለው አካባቢ፣ ጠዋት ላይ እናትና ልጅ አርሲ ሁሩታ ለመሄድ ወደ ቃሊቲ መነሀሪያ መንገድ ሲያቋርጡ፣ አንድ እንደነፋስ ይበር የነበረ መኪና ልጃቸውን ገጭቶ ያለ ጧሪ እንዳስቀራቸው ይናገራሉ፡፡ መኪናው ያዝ አይያዝ ግን የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፓርላማ አባል፣ ሰዎች ገጭተው እንዲያመልጡ የሚያነሳሳቸው ህጉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “የመኪና አደጋ ድንገት የሚፈጠር ክስተት ነው” ያሉት የፓርላማ አባሉ፣ አንድ ሰው በሠላም እያሽከረከረ እግረኛ መጥቶ ጥልቅ የሚልበት ጊዜ በርካታ መሆኑንና ህጉ ይህን ግምት ውስጥ ሳያስገባ፣ ሰው ገጨህ በሚል 15 ዓመት እንደሚታሰር ጠቁመው በዚህ ምክንያት ሰዎች ገጭተው እንሚያመልጡ ይናገራሉ፡፡ የፓርላማ አካሉ ይህን ይበሉ እንጂ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው መግደል ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ፀጋዬ ባልቻ ግን ሰዎች ገጭተው እንዲያመልጡ የሚያነሳሳቸው የገጨ ሰው 15 አመት ይታሰራል የሚል አጉል የሚናፈስና አስተሳሰብን የሚያዛባ ወሬ ስላለ ሰው ይህን ፍራቻ ገጭቶ ያመልጣል ይላሉ፡፡

ነገር ግን የገጨ ሰው ሁሉ 15 አመት እንደማይታሰርና በሂደትና በምርመራ ጉዳዩ እንደሚታይ ገልፀው ይህን ጉዳይ ለአሽከርካሪዎች ለማስተማር የሁሉንም አካል ጥረት እንደሚጠይቅ ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ግን ገጭቶ ለማምለጥ ምክንያቶች ያሏቸው ሃሳቦች ከፓርላማው አባል ይለያሉ፡፡ “አንድ ሰው ገጭቶ የሚያመልጠው መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም የሰው መኪና ተውሶ አሊያም መጠጥ ጠጥቶ ሲያሽከረክር አደጋ በሚያደርስበት ጊዜ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ገጭቶ ይሸሻል” ባይ ናቸው፡፡ የወንጀል ህጉ ገጭቶ በማምለጥ ዙሪያ ጥብቅ ነው የሚሉት ኮማንደሩ፣ የተፃፈው ህግ አንዳችም እንከን እንደሌለው ያብራራሉ፡፡ እንደውም ገጭቶ ማምለጥ ሁለቴ የመግደል ያህል እንደሚቆጠር ያክላሉ፡፡ “አደጋው በምንም መንገድ ይከሰት ነገር ግን የገጩትን ሰው መርዳት ሰብዓዊነት ነው” የሚሉት አቶ ግርማቸው አይናለም የተሰኙ የህግ ባለሙያ፣ አደጋው አንዴ ከተከሰተ በኋላ ሹፌሮች ተጐጂውን በመርዳት መትረፍ የሚችለውን ማትረፍ እየቻሉ መሄድ በተጐጂው ላይ ሞት መፍረድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

“ጊዜ ይወስዳል እንጂ ከህግ ፊት የሚሰወር የለም” የሚሉት አቶ ግርማቸው፣ የተጐዳን በመርዳት ግን ከህሊና ወቀሳ ከከባድ ቅጣትም መዳን ይቻላል ይላሉ፡፡ ሰውን መግጨት በቸልተኝነት ሰውን መግደል በሚለው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነስርዓት 543 ንዑስ ቁጥር አንድ ላይ የሚወድቅ መሆኑን የሚገልፁት የህግ ባለሙያው አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ ሰውን ገጭቶ ማምለጥ ደግሞ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነሥርዓቱ 543/2 መሠረት እንደሚከሰስ ያ_ረዳሉ፡፡ አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር ሁለት አሽከርካሪው ሀኪምና መሰል ሙያተኞች ከሆኑ በቸልተኝነት ሰውን መግደል በሚል ከአንድ አመት እስከ አምስት ዓመት እንደሚያስቀጣ የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ ይህ የሚሆነው በሙያው ልዩ ሃላፊነት ስላለበት መሆኑን ያብራራሉ፡፡ አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር አንድ ግን ምንም ሙያ የሌላቸው ተራ ሰዎች የሚያደርሱትን የቸልተኝነት ግድያ የሚመለከት ብቻ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር 3 የሚያርፈው ቅጣት፣ አንድ ባለሙያ (አሽከርካሪ) ግልጽ የሆኑ የትራፊክ ህጐችን ከጣሰ ለምሳሌ ዜብራ ላይ ከገጨ፣ ርቀት ባለመጠበቅ አደጋ ካደረሰ፣ ጠጥቶ ሲያሽከረክር ጉዳቱን ካደረሰ፣ አደንዛዥ ዕፅ ወስዶ ከሆነ--- እነዚህ ግልጽ የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች ስለሆኑ ቅጣቱ በአንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ እንደሚያርፍና ቅጣቱም ከአምስት እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰውን ገጭቶ ያመለጠ ሰው የትራፊክ ህግ ጣሰም አልጣሰ በማምለጡ ብቻ ሌላ ተጨማሪ ክስ እንደሚቀርብበትም የህግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ “አንቀጽ 575 በሁሉም ዜጋ ላይ ማለትም የተጐዳን ሰው እያየ ሳይረዳ በቀረ ሰው ላይ የተጣለ ነው” ያሉት የህግ ባለሙያው፣ በተለይ ሙያተኛ ሲሆን ቅጣቱ እንሚጨምር ይገልፃሉ፡፡

በዚህም ማንኛውም ዜጋ አደጋ የደረሰበትን ሰው ባለመርዳት እንደሚጠየቅ አብራርተው፣ ሙያተኛ ከሆነ ግን በአንቀጽ 575 ንዑስ አንቀጽ ሁለት እንደሚቀጣና ቅጣቱም እስከሁለት አመትና ተጨማሪም የገንዘብ ቅጣት አለው ይላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በተጨማሪ ሌላ አንቀጽ መከሰሱንና ሰውን ገጭቶ ማምለጥ ከፍተኛ ወንጀል እንደሆነ የሚያመለክት ነው ብለዋል - የህግ ባለሙያው አቶ ፍቃዱ ፀጋ፡፡ “የመኪና አደጋ በአሁኑ ጊዜ ጅምላ ጨራሽ የሚል ስያሜ ወጥቶለታል፣ አሳሳቢነቱም እስከዚህ ደርሷል” የሚሉት የማህበረሰብ ሠራተኛው አቶ ተበጀ ማንያዘዋል፣ ከሁሉም የከፋው ግን አደጋውን አድርሶ ማምለጥ ነው ይላሉ፡፡ በየጊዜው የሚሰማው እና አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የመኪና አደጋ በዜጐችም ላይ ሆነ በአገሪቱ ላይ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦናም ጭምር እንደሆነ የሚገልፁት ባለሙያው፣ ስነልቦናው የተጐዳ ማህበረሰብ ለምንም እንማይጠቅም ጠቁመው አንድ ሰው ሰውን ገጭቶ ሲያመልጥ ጀምሮ ከህሊናው ጋር በመጣላት ለባሰ ጥፋት ከመጋለጥና የስነ ልቦና ጫና እንደማያመልጥ ያሰምሩበታል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ኮማንደር ፋሲካ፣ ገጭተው ከሚያመልጡት 99 በመቶው እንደሚያዙ ገልፀው፣ አንዳንዶቹም ለጊዜው ይሰወሩ እንጂ ህሊናቸው እረፍት ሲነሳቸው “በዚህ ቀን በዚህ ሥፍራ ሰው ገጭቼ አምልጬ ነበረ፣ ግን እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም” በማለት ለፖሊስ እጃቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳ እጅ መስጠታቸው አግባብ ቢሆንም በገጩ ሰዓት ተጐጂውን የመርዳት ያህል እንደማይሆን ኮማንደሩ ይናገራሉ፡፡ በዚህ አመት ብቻ በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ 365 የሞት አደጋ የደረሰ ሲሆን 315ቱ መዝገቦች አጥፊው ታውቆ እልባት ቢያገኙም አርባ ስድስቱ ግን ገጭተው በመሰወር አጥፊያቸው ያልታወቀና አጥፊው ታውቆም የተሰወረ እንደሚገኙበት ዋና ኢንስፔክተር ፀጋዬ ባልቻ ጠቁመው አንዳንዶቹ ቢሰወሩም የታወቁና ማስረጃ ማሰባሰብ የሚቀራቸው በመሆኑ 46ቱ መዝገቦች እልባት አለማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አንድ መኪና ገጭቶ ሲያመልጥ በቅድሚያ ሊያዝ ስለሚገባው ምልክት ጠይቀናቸው ኢንስፔክተሩ ሲመልሱም አንድ ሰው ታርጋ ላይ ብቻ ካተኮረ ቁጥሩ ሊፋቅና ብሎን ሊያርፍበት ስለሚችል አንዳንዱ 3 ቁጥር ስምንት ሊመስል እንደሚችል የተናገሩት ኢንስፔክተሩ ከታርጋ በተጨማሪ የመኪናው ሞዴል፣ ቀለምና አጠቃላይ ሁኔታው መቃኘት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “ህዝቡ መረጃ የመስጠት መጠኑ ጨምሯል 315ቱን መዝገቦች እልባት የሰጠነው ከህዝቡ ጋር በመተባበር ነው” ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ፀጋዬ አሁንም የፖሊስ ኮሚሽኑን ስልክ በመጠቀም ወንጀለኞችን በጋራ መከላከል አለብን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Read 4323 times