Saturday, 20 July 2013 10:19

የመኪና አውላቂዎችና ተቀባዮች “የነገሱባት” ሱማሌ ተራ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

*ለሌቦቹ ሥጋት እስካልሆኑ ድረስ ንብረትዎትን ተደራድረው ይገዙታል
*ለፖሊስ የሚደረግ የስልክ ጥሪን የሚያውቁበት መላ ግርታን ፈጥሯል
*ከመኪናዎ የተሰረቀ እቃ ታርጋው ተፅፎበት እርስዎን ይጠብቃል
*በክረምት የመኪና እቃዎች ስርቆትና ገበያ ይደራል!

የልደታ ፍርድ ቤትን አጥር ታከው ከተኮለኮሉት መኪኖች መካከል ያቆማት ወያኔ ዲኤክስ መኪናው በአስተማማኝ ስፍራ ላይ በመሆኗ ስጋት አልገባውም፡፡ ለጥብቅና ስራው ወደዚህ ስፍራ አዘውትሮ በሚመላለስበት ጊዜ ሁሉ መኪናውን የሚያቆማት እዚሁ የተለመደ ቦታ ላይ ነው፡፡ የችሎት ቀጠሮውን ጨርሶ ሲወጣ፣ ሰዓቱ 4፡20 ይላል - ከረፋዱ፡፡ ከአንድ ደንበኛው ጋር ቀጠሮ ስለነበረው እየተቻኮለ ከፍርድ ቤቱ ግቢ ወጣና ወደ መኪናው አመራ፡፡ አካባቢው በወትሮው እንቅስቃሴ እንደ ደመቀ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰላም ይመስላል፡፡ የመኪናው የግራና የቀኝ መመልከቻ መስታወት (ስፖኪዮ) አለመኖሩን እንኳን ልብ ሳይል በሩን ከፈተው፡፡ ዳሽ ቦርዱ፣ የነዳጅ ጌጁ፣ የመኪናው ቴፕ፣ ስፒከር፣ የወንበር ትራሶች፣ የዝናብ መጥረጊያው… ወላልቆ ተወስዷል፡፡ ደነገጠ፡፡
የተቆለፈ መኪናውን ከፍቶ መግባቱን እርግጠኛ ነው፡፡ ግራ ገባው፡፡ “ሌላ መኪና ውስጥ ይሆን እንዴ የገባሁት?” ሲል ራሱን ተጠራጠረ፡፡ ከመኪናው ወርዶ ታርጋውን አየው - የራሱ ነው፡፡ በሰላም ከቤቱ ይዟት ወጥቶ ያቆማት መኪናው፣ በሰአታት ልዩነት ቀፎዋን የቀረችበት ምክንያት አልገለጥልህ አለው፡፡ ትንሽ ሲረጋጋ በመኪና ሽያጭ ሥራ ላይ ለተሰማራውና በጣም ለሚቀርበው ጓደኛው ደውሎ የሆነውን ሁሉ ነገረው፡፡ ጓደኛው ድርጊቱ የተፈመበትን ሰአትና ቦታ ጠይቆት፣ “ደውዬ ላጠያይቅና መልሼ እደውልልሀለሁ” ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ በአካባቢው ያገኛቸውን ሊስትሮዎች ስለጉዳዩ ቢጠይቃቸውም “ዓይናችንን ግንባር ያድርገው” ብለው እስከመማል ደረሱ፡፡
በዚህ መሀል ጓደኛው ደወለና ዕቃው ሊገኝ ይችላል የሚላቸው ቦታዎች ሁሉ አጠያይቆ “ገና አልገባም” እንደተባለ ነገረው፡፡ “የት ነው የሚገባው?” ጠበቃው ግራ ተጋብቷል፡፡ “ሱማሌ ተራ” አለው ጓደኛው፡፡ የመኪና ዕቃዎች በተሰረቁበት ቅፅበት ወደ ሱማሌ ተራ እንደሚሄዱና በቅናሽ ዋጋ ለባለንብረቱ ለራሱ ወይንም ለሌሎች ፈላጊዎች እንደሚሸጡ ገለፀለት፡፡

እሱም የጠፉበትን ዕቃዎች ለማግኘት ለጥቂት ሰአታት መታገስ እንደሚገባው አስረዳው፡፡ “ምን ማለት ነው? ሌባው ጊዜ አግኝቶ እስኪሰወር ወይም እስኪጠፋ ወይም ዕቃውን እስኪያሸሽ መጠበቅ አለብህ ነው የምትለኝ? ቶሎ ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ ይኖርብኛል ህግ ያወቀው ነገር ጥሩ ነው” አለ ጠበቃው፡፡ ጓደኛው በጠበቃው ምላሽ አልተደሰተም ግን ደግሞ የፈቀደውን ነገር እንዳያደርግ መከልከል አልፈለገም፡፡ ሆኖም የጠፉበትን ዕቃዎች ማግኘት የሚችለው ለፖሊስ በማመልከት ሳይሆን፣ ከሌቦቹ ጋር በመደራደር መሆኑን ነገረው፡፡ ይሄን ጊዜ ጠበቃው ሌላ ዘዴ አሰበ፡፡

ሌቦቹን በትእግስት በመጠባበቅ ለድርድሩ ሲያገኛቸው በፖሊስ ለማስያዝ ወሰነ፡፡ ለጓደኛውም በሃሳቡ መስማማቱንና በትእግስት መጠበቅ መምረጡን ገለፀለት፡፡
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ጓደኛው ደወለለትና፣ ሰዎቹ ደውለው ዕቃው ገብቷል እንዳሉት ነገረው፡፡ “ለድርድሩ ያመች ዘንድ ስልክ ቁጥርህን ልስጣቸው ወይ?” ብሎ ፈቃዱን ጠየቀው፡፡ ጠበቃው አላቅማማም፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በመስመር ስልክ ሞባይሉ ላይ ተደወለለትና፣ የመኪናው ታርጋ ተነገረው፡፡ አዎ ሲል አረጋገጠ፡፡ የጠፋበት ዕቃ በሙሉ መግባቱንና 3ሺህ ብር ይዞ 11 ሰዓት ላይ በኒን መስጊድ በራፍ ላይ እንዲገኝ ትዕዛዝ ደረሰው፡፡ ዕቃውን ከማግኘቱ በፊት ገንዘቡን ስፍራው ላይ ለሚጠብቀውና መጥቶ ለሚያናግረው ሰው መስጠት እንዳለበት ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጠው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ተግባር እፈፅማለሁ ብሎ ከሞከረ ግን ዕቃዎቹን እስከ መጨረሻው እንደማያገኝም ተነገረው፡፡
አሁን ለፖሊስ ለማመልከት በቂ መረጃ እንዳለው ጠበቃው ተማምኗል፡፡ ጉዳዩን ለፖሊስ ጣቢያ አመለከተና የተደወለበትን ቁጥር ለፖሊሶች ሰጠ፡፡ ፖሊሶቹ በቁጥሩ ለመደወል ሞከሩ፡፡ ግን ምላሽ የለም፡፡ ደዋዮቹ የተጠቀሙት የመንገድ ላይ ስልኮችን እንደሆነ ፖሊሶቹ ነገሩትና በጣም እየተገረመ የመርማሪ ፖሊሶቹን ቁጥር ተቀብሎ ወጣ፡፡
ልክ እግሩ ከጣቢያው እንደወጣ ስልኩ ጮኸ፡፡ ሌላ የመስመር ስልክ ጥሪ ነበር፡፡ ደዋዩ ቀደም ሲል ቀጭን ትእዛዝ የሰጠው ሰው መሆኑን በድምፁ ለይቶታል፡፡ ከስምምነታቸው ውጭ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት በማድረጉ፣ ለተጨማሪ ወጪ እንደዳረጋቸውና ይህንን ተጨማሪ ወጪ ለመሸፈን 2ሺ ብር በመጨመር፣ 5ሺህ ብር ይዞ በሰአቱ እንዲገኝ ተነገረው፡፡ ጠበቃው እጢው ዱብ አለ፡፡ “እንዴ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጌን ለማን ተናገርኩ?” ሲል ራሱን መመርመር ያዘ፡፡ ለማንም ትንፍሽ አላለም፡፡ ሌቦቹ ዝም ብለው ሊያስፈራሩት እየሞከሩ እንደሆነ አሰበ፡፡ ለሁሉም በቀጠሮው ቦታ ላይ በመገኘት ጉዱን ለማየት ጓጓ፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደውሎ፣ ሌቦቹ ሪፖርት ማድረጉን ማወቃቸውን ተናገረ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በተለመደው የመስመር ስልክ ጥሪ ተደረገለት፡፡ “ሃሎ” አለ ጠበቃው፡፡ በደጋሚ ሪፖርት ማድረጉ እጅግ እንዳናደደው በመግለፅ “ካንተ ጋር ድርድሬን አቋርጣለሁ፣ እቃህንም አታገኛትም” ሲል ደዋዩ አምባረቀ፡፡

አሁን ጠበቃው እጅግ ደንግጧል፡፡ ምንድነው እየተካሄደ ያለው? ማነው መደወሌን የሚነግራቸው? ግራ ቀኙን እየተገላመጠ የሰማው ሰው እንዳለ ፍለጋ ያዘ፡፡ ደዋዩ ስልኩን ከመዝጋቱ በፊት ግን “የመጨረሻ እድል ሰጥቼሀለሁ” ሲል የመገናኛ ቦታና ሰአቱን ቀይሮ ነገረው፡፡ ከ30 ደቂቃ በኋላ በላይ ተክሉ ኬክ ቤት አካባቢ ተባለ፡፡
አሁን ጠበቃው ወሰነ፡፡ ከ10 ሺ ብር በላይ ቢያወጣ እንኳን የማያገኛቸውን የመኪና ዕቃዎች ከሌባው ጋር ተደራድሮ መግዛቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ከዚህ በኋላ ለፖሊስ ማሳወቁ አስፈላጊ አለመሆኑን አምኗል፡፡ እናም መኪናውን አስነስቶ ወደተባለው ስፍራ ከነፈ፡፡ ገና መኪናውን ከማቆሙ አንድ ቀጭን ወጣት ወዳለበት መጥቶ ሰላም አለው፡፡ አካባቢው በዚህ ወጣት ግብረ አበሮች ቅኝት ወስጥ መሆኑን ጠበቃው ተገንዝቧል፡፡ “ዕቃው የታለ?” ጠየቀው ወጣቱን፡፡ ሂሳቡን በቅድሚያ መክፈል እንደሚገባውና “5ሺህ ብር ተቀበል” ተብሎ መላኩን ጭምር ነገረው፡፡ “ኧረ የለኝም፡፡ 3ሺህ ብር ብቻ ነው ያለኝ” ጠበቃው ተማፀነ፡፡
“እኔ አላውቅም፣ ተቀበል የተባልኩትን ብቻ ነው የምቀበልህ” አለው፡፡ “ኧረ ባክህ ደውልና ችግሬን አስረዳልኝ፣ ያለችኝ ይቺው ናት” ለመነው፡፡ እያቅማማ ደወለና፣ አለቆቹ አንዱን ሺህ ብር ቅናሽ እንዳደረጉለት ነገረው፡፡ ጠበቃው በዚህ ተስማማ፡፡ ግን ደግሞ ስጋት ገባው፡፡ ይህ ወጣት አራት ሺ ብሩን ተቀብሎኝ በዛው እብስ ቢልስ ሲል ተጠራጠረ፡፡ ለዚህ ችግር ግን የሱማሌ ተራዎቹ “ሰዎች” መፍትሄ አላቸው፡፡ ጠበቃው ገንዘቡን ቆጥሮ ለወጣቱ ሲሰጠው፣ ከበስተጀርባው ሌላ ወጣት የተሰረቁትን ዕቃዎች በሙሉ በኩርቱ ፌስታል ይዞ ቆሟል፡፡ በዛችው ቅፅበት ዕቃዎቹን አስረከበው፡፡ የመኪናው ታርጋ ቁጥር ኩርቱ ፌስታሉ ላይ ተፅፏል፡፡ ከፍቶ ማየት ፈራ፡፡ ዕቃውን የኋላ ወንበሩ ላይ ወርውሮ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ፡፡ ንዴት፣ እልህ፣ ግራ መጋባት --- ምስቅልቅል ስሜት ተጫጫነው፡፡ በአካባቢው ህገወጥነት ምን ያህል እንደነገሰ እያሰበ ነበር ሱማሌ ተራን ለቆ የወጣው፡፡
ይህ መሰሉ ታሪክ በሶማሌ ተራ የተለመደና የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ነው፡፡ የሶማሌ ተራ ህልውና የተመሠረተው ከየስፍራው እየተሰረቁ በሚመጡ የመኪና ዕቃዎች ሽያጭ ላይ ነው፡፡ አካባቢው በጠራራ ፀሃይ የመኪና ዕቃዎቻቸውን ተዘርፈው ለድርድር በሚመጡ፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆነባቸውን መኪና ለእርድ ለመሸጥ በሚያስማሙና የተሰረቀባቸውን መኪና ከመበታተኑ በፊት በነፍስ ለማትረፍ በሚጣደፉ ሰዎች የተጨናነቀ ነው፡፡ ሱማሌ ተራ የተመሰረተውም ሆነ ስያሜውን ያገኘው ቀደም ባሉት ዘመናት በአካባቢው በሚሰባሰቡና በሚገበያዩ የሱማሌ ክልል ነጋዴዎች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከበኒን መስጊድ ጀምሮ እስከ ተክለሃይማኖት አደባባይ፣ ጌሾ ግቢና አሜሪካን ጊቢን አካሎ የሚገኘው ይኸው አካባቢ፣ ቀስ በቀስ የንግድ ስፍራ በተለይም ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ የመኪና ዕቃዎች የሚሸጥበት ቦታ እየሆነ መጣ፡፡ ከአሮጌ መኪኖች የሚፈታቱ ዕቃዎችን በአነስተኛ ዋጋ ለመግዛት ብዙዎች ሱማሌ ተራን ይጐበኟት ጀመር፡፡ የአሮጌ ዕቃዎች ፈላጊው ቁጥር መበራከት በሽያጭ ሥራ ላይ ለተሰማሩት ነጋዴዎች ውጥረት ሆነባቸው፡፡ አቅርቦቱና ፍላጐቱ አልመጣጠን አለ፡፡ ይህንን ሁኔታ ልብ በለው የተገነዘቡት ከተፎዎቹ የሱማሌ ተራ ዕቃ አቅራቢዎች፣ የደንበኞቻቸውን ፍላጐት ለማሟላት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ፡፡ ከአሮጌ መኪና ዕቃዎች በተጨማሪ ከአዳዲስና ዘመናዊ መኪኖች ላይ እየተሰረቁ የሚመጡትን ዕቃዎች ከሌቦች ላይ በመግዛት ለሽያጭ ያውሉት ጀመር፡፡

የተሰረቁ ዕቃዎች ሽያጩ በድብቅ ይካሄድበት የነበረው ያ “ደግ ዘመን” አልፎ፣ ዛሬ በአደባባይ በጠራራ ፀሐይ የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎች በአደባባይ በግልፅና በድርድር የሚሸጥበት ጊዜ ላይ ተደረሰ፡፡ አካባቢው የራሱ ያልተፃፈ መተዳደሪያ ህግና መመሪያ ያለው፣ ህገወጦች የነገሱበት፣ በመኪና ሥርቆት የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተው የከበሩና ቢጠሯቸው የማይሰሙ “ባለሀብቶች” የሚገኙበት፣ ያቆሙት መኪና በጠራራ ፀሐይ ተፈታተው ዕቃዎቻቸው የተሰረቁባቸው ባለንብረቶች ከሌቦች ጋር በሰላማዊ ድርድር የተሰረቁ ዕቃዎቻቸውን የሚገዙበት ስፍራ ነው፡፡ በእርግጥ በሐቀኝነትና በህጋዊ መንገድ የሚገዟቸውን የወላለቁ የአሮጌ መኪና ዕቃዎች፣ በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚው የሚያቀርቡ ህጋዊ ነጋዴዎች ሱማሌ ተራ ፈፅሞ የሉም ማለት አይቻልም፡፡
የሱማሌ ተራ ሰዎች በተራ ሌብነት ወይም በጠራራ ፀሐይ ዘራፊነት ብቻ መፈረጁ “ፍትሃዊ” አይመስልም፡፡ እነሱ ከዚያም በላይ ናቸዋ፡፡ የራሳቸው ብቻ መግባቢያ ቋንቋና ምልክት ያላቸው፣ ፖሊስን ከሩቁ ማነፍነፍ የሚችል ልዩ አፍንጫ የተቸሩ፣ የሰረቁትን ንብረት ለባለቤቱ መልሶ የማስገዛት ልዩ ምትሃት የተካኑ “ጥበበኞች” ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎች ሳይወዱ በግድ ለሱማሌ ተራ ያልተፃፈ “ሕግ” ተገዝተው፣ የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎቻቸውን ከሌቦቻቸው ጋር ተደራድረው ገዝተው ይሄዳሉ፡፡ እንዴት? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች ሱማሌ ተራዎች ጋር አይሰሩም፡፡
እንዲህ እንደ አሁኑ በክረምት ወራት ላይ የሱማሌ ተራ ገበያ ይጧጧፋል፡፡

የተሰረቁ ዕቃዎቻቸውን ፍለጋ አካባቢውን የሚጐበኙ በርካታ “ደንበኞች” ባብዛኛው የመጡበትን አሳክተው ይመለሳሉ፡፡ “እንዴት ከህገወጦች ጋር እደራደራለሁ” በማለት ጉዳያቸውን ለፖሊስ ያመለከቱ ጥቂቶች ደግሞ በሱማሌ ተራዎቹ ሰዎች እልህ አስጨራሽ ቀጠሮ የማያገኙትን ዕቃ ጥበቃ ይባዝናሉ፡፡ የሶማሌ ተራዎቹ ሰዎች ፖሊስ የገባበትንና ክትትል ማድረግ የጀመረበትን ዕቃ ለባለቤቱ በፍፁም አይሸጡለትም፡፡ ድርድር ጀምረው ከነበረም አቋርጠው የዕቃዎቹን ደብዛ ያጠፉታል፡፡
ቴዎድሮስ አያሌው አዲሱ ገበያ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ አቁሞ የተሰረቀውን የመኪና ዕቃ ለማግኘት ሳምንታት የፈጀ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ ንብረቱ መሰረቁን እንዳወቀ ክትትል እንዲደረግለት ለፖሊስ አመለከተ፡፡ ዕቃህን እናገኝልሀልን በሚሉ ደላሎች አማካኝነት በየጊዜው በስልኩ ላይ እየተደወለ የዋጋ ድርድር ሲያደርግ ቢቆይም፣ ዕቃውን ፈፅሞ ማግኘት አልቻለም፡፡ “ሰዎቹ” ደውለውለት ካንተ ጋር “አበድን” ብለውታል፡፡
በሱማሌ ተራ ሌቦቹ (የመኪና አውላቂዎቹ) እና ዕቃ አቅራቢዎቹ (ሻጮቹ) አይተያዩም፡፡ በመሀል ያሉና ሁለቱን ተፈላላጊዎች የሚያገናኙ ደላሎች እንደ አሸን ናቸው፡፡ በዚሁ አካባቢ ያሉ አንዳንድ “ነጋዴዎች” ለመኪና ስርቆት ሥራው ስምሪት ሰጪዎችም ናቸው፡፡ ነጋዴዎቹ ከደንበኞቻቸው የሚቀርብላቸውን የመኪና ዕቃ (በሞዴልና በአይነት ይለያያል) ጥያቄ በቀጥታ በደላሎቹ በኩል ለሌቦቹ እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፡፡ የዲኤክስ ዳሽቦርድና ትራሶች፣ የፋይቭ ኤል ጌጅ፣ የኤክስኪዩቲቭ ስፖኪዮና ዝናብ መጥረጊያ…. ትእዛዙ በቀጥታ ይተላለፋል፡፡ ትእዛዝ ተቀባዩ “ዕቃ አቅራቢ” የተሰጠውን ትእዛዝ ተቀብሎ “ለሥራ” ይሰማራል፡፡ የተሰጠውን ትእዛዝ የሚያሟሉ መኪኖች የት አካባቢ እንደሚገኙ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ከአትላስ ሆቴል እስከ ቦሌ ድልድይ፣ ከሜክሲኮ እስከ ብሔራዊ፣ ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ፣ ከሰባራ ባቡር እስከ መድሃኒያለም ት/ቤት ከተማውን ያካልላል፡፡ የተፈለገው መኪና ከተገኘ፣ የተባለውን ዕቃ ለማግኘት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ይበቃሉ፡፡ በሰለጠነበት የመፈታታት ሙያው ዕቃዎቹን ፈታቶ በፌስታል ይከትና እብስ ነው፡፡ በዚህችው ቅፅበትም ዕቃዎቹን ይዞ ወደ ሱማሌ ተራ ይከንፋል፣ ምክንያቱም ዕቃውን አዘው የሚጠባበቁ ደንበኞች አሉና፡፡ አንዳንዴ መኪናዋን ከነነፍስዋ ሰርቆ እስከማምጣት የሚያደርስ ድርድር ሁሉ ሊፈፀም ይችላል፡፡ እንደውም ይኸኛው እንደሚቀላቸው ይናገራሉ - የሱማሌ ተራዎቹ “ሰዎች” መኪናቸው ከቆመችበት ከነነፍስዋ ተወስዶባቸው እምጥ ትግባ ስምጥ ባለማወቅ ሲባዝኑ ኖረው፣ ተስፋ ቆርጠው የቀሩ፣ መኪናቸው እንደ ቅርጫ ሥጋ ተበልታና ተቆራርጣ ቀፎዋን ያገኙ በርካቶችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
ስዩመ ታደሰ ይህንን የሱማሌ ተራንና የመኪና ዕቃ ስርቆትን ትስስር የሚያወጋው ከራሱ ገጠመኝ ተነስቶ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ብሔራዊ ቲያትር ፊት ለፊት ያቆማት ራቫ ፎር መኪናው ወላልቃ ቆየችው፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያበሳጨውም መፍትሄው እቃው ከሌቦቹ እጅ ሳይወጣ ፈጥኖ አግኝቶ መግዛት እንደሆነ በመረዳት ወደ ሱማሌ ተራ አቀና፡፡ የመኪናዋን ታርጋ በማየት ዕቃው ከጥቂት ሰአታት በፊት እንደገባ የተረዱት ደላሎች፣ ዋጋ ይደራደሩና 2800 ብር ከፍሎ ዕቃውን ይሰጡታል፡፡ ተሰረቀብኝ ካላቸው ዕቃዎች ውጭ የሰጡትን ሌሎች ንብረቶችን “ይሄ የእኔ አይደለም” ብሎ ሊመልስላቸው ቢሞክር፣ “ሰውዬ ዝም ብለህ ይዘህ ሂድ፣የራስህ ነው” ተባለና ይዞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡

ቤቱ ደርሶ የሆነውን ሁሉ ለሚስቱ ሲያጫውታት እጅግ ደነገጠች፡፡ ጠዋት እሷን መ/ቤቷ በራፍ ላይ አድርሷት ሲለያዩ፣ ለእናቷ ከውጭ አገር በውድ ዋጋ ተገዝቶ የመጣላቸው መድሃኒቶችን መኪናው ኪስ ውስጥ በፌስታል እንደታሰረ ማስቀመጧን ነገረችው፣ ኪሱ ሲከፈት ባዶ ነበር፡፡ ድንገት አንድ ነገር ትውስ አለው፡፡ ለሶማሌ ተራዎቹ ሰዎች “የእኔ አይደለም” ብሎ ሊመልስላቸው ሲሟገት የነበረውን ዕቃ ከፌስታል ውስጥ አወጣው፡፡ ባለቤቱ ፊቷ በደስታ በራ፡፡ ባልም እንዲህ ሲል አሰበ “ሶማሌ ተራዎች የሰው ዕቃ አያጐድሉም፣ ታማኞች ናቸው”
መኪና ከነነፍሱ ገብቶ ተበታትኖ የሚወጣበት ሱማሌ ተራ፣ በመኪና ስርቆት “ሥራ” ላይ ለተሰማሩ ሌቦች መናኸሪያ በመሆን አመታትን አሳልፏል፡፡ ዛሬ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ የመኪና ዕቃና የመኪና ዝርፍያዎች ማረፊያቸው ሶማሌ ተራ ነው፡፡ በተለይ እንደ አሁኑ ባለ የክረምት ወቅት የመኪና ዕቃ ዝርፍያ ይጧጧፋል፡፡
ህሊና ታየ በያዝነው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ መኪናዋ በሌቦች ተፈታትታ ቀፎዋን እንደቀረች ትናገራለች፡፡ በተፈፀመባት ስርቆት አንጀቷ ብግን ቢል ለፖሊስ ጣቢያ አመለከተች፡፡ ሆኖም ብትጠብቅ ብትጠብቅ ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ቢቸግራት ለመካኒኳ ነገረችውና፣ የተሰረቁትን ዕቃዎች ገዝቶ እንዲገጥምላት ነገረችው፡፡ መካኒኩ ዕቃውን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁሟት ልሞክር ብሎ ደወለ፡፡ ከሶማሌ ተራ ያገኘው ምላሽ ግን “ሴትየዋ ያልተወሰደባትን ነገር ሁሉ ለፖሊስ አስመዝግባለች፡፡ ደግሞ ስትቆይ ዕቃውን አትፈልገውም ብለን ለሌላ ሰው ሸጥነው” የሚል ነበር፡፡ ህሊና እጅግ ተገረመች፡፡ ሌቦቹ ለፖሊስ ማመልከቷን በምን ተዓምር ሊያውቁ እንደቻሉ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነባት ነው፡፡ በመጨረሻም ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት አዳዲስ ዕቃዎችን ለመኪናዋ ለመግጠም መገደዷንም ተናግራለች፡፡መኪኖችን ከነነፍሳቸው አቁሞ ለመበለት፣ አሁን አሁን ከሱማሌ ተራ ይልቅ ሎሚ ሜዳ፣ አብነት ፊሊጶስና ሰበታ አካባቢዎች ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ በሱማሌ ተራ ግን ዛሬም የተሰረቁ የመኪና ዕቃዎች የተሰረቁበት መኪና ታርጋ፣ ቀንና ቦታ ተፅፎባቸው በማዳበሪያ ወይንም በፌስታል ተቋጥረው ባለቤቶቻቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የዕቃዎቹ ባለቤቶች ወደ ሶማሌ ተራ እንደሚመጡ ሌቦቹ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ሱማሌ ተራ ህገወጦች የነገሱባት ግዛት ሆና የምትዘልቀው እስከመቼ ይሆን?

 

Read 4987 times