Saturday, 19 November 2011 14:25

ትልቅ የአስተሳሰብ አብዮት ያፈነዳችው መፅሐፍ

Written by  ገዛኸኝ ፀ.
Rate this item
(0 votes)

ሰው በሥራ ሳለ አይበድልም፤ አያጠፋም … ከቦዘነ ግን … 
ማህበር ከሠርግ ዕብደት፣ ከልቅሶ ሞኝነት አያንስም …
በምግብ ማህበር ዘጥዘጥ እንጂ ፅድቅ የለም …
ባለፈው ሳምንት፡ “የባለቅኔው የአለማየሁ ሞገስ አስገራሚ የጋብቻ አፈፃፀም” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አስነብቤ ነበር፡፡ “ሠርግና ልማድ” በሚለው መጽሐፍ መነሻነት የደራሲውን የአለማየሁ ሞገስን አስገራሚ የጋብቻ ሁኔታ በማስታወስ ሞክሬያለሁ፡፡ በመጣጥፉ መዝጊያ ላይ ታዲያ፣ “ሠርግና ልማድ” የሚለው መጽሐፍ ያነሳቸው፣ በአጉል ልማዶቻችን ላይ ያነጣጠሩ ሂሶችን ይዤ ለዛሬ እንድንገናኝ በገባሁት ቃል መሠረት፣ ዳግም መገናኘታችን ቁርጥ ሆኗል፡፡ እናም ባለ 72 ገጿን አብዮታዊ መጽሐፍ፣ የተወሰኑ ተራማጅ አስተሳሰቦቿን ማንፀሪያ በማድረግ እንደሚከተለው በአጭሩ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡

“ሠርግና ልማድ” ወደ 20 የሚሆኑ አብይና ንዑስ ርዕሶችን በ14 ምዕራፎች ከፋፍላ አቅርባለች፡ አብዛኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ሃይማኖታዊ ልማዶች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት እራሱን አስችለን የተመለከትነው የባለቅኔው የሠርግ ሥነስርዓት በ3 ምዕራፎች የቀረበ ሲሆን፣ ባለጉዳዩ አለማየሁም ሆኑ ሌሎች የመረጃ ምንጮች እንደጠቆሙት ባለቅኔው ጋብቻቸውን የፈፀሙት ዕለተ ማክሰኞ፣ ጥር 5 ቀን 1956 ዓ.ም ነበር፡፡ በሌላ በኩል፣ የባለቅኔው “ሠርግና ልማድ” መጽሐፍ በፊትለፊት ሽፋኗም ሆነ በውስጥ ገጿ ጥር 5 ቀን 1956 ዓ.ም የሚል የጊዜ ምዕራፍ አስፍራለች፡፡ የጊዜ ልኬታ ጠቋሚ አሀዞቹ ደግሞ፣ የመጽሐፏን የህትመት ጊዜ ለመግለጽ የቀረቡ ይመስላሉ፡፡ 
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን፡፡ ባለቅኔው አስገራሚ የጋብቻ ሥነስርአታቸው ከፈፀሙ በኋላ በዚሁ ዕለትና ቀን መጽሐፋቸውን አሳተሙ? ማለት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ በመጽሐፉ ገጽ 31 ላይ ደግሞ፣ “የኢትዮጵያ ድምጽም [የካቲት 18፣ 1957 ዓ.ም] ባመቱ ባወጣው ቁጥሩ የሚከተለውን ጽፏል” የሚል መረጃ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፏ የደራሲው የጋብቻ ሥነስርዓት ከተካሄደ ከዓመት በኋላ የተከሰቱ ታሪኮችን ብትተርክም፣ የታተመችው በጋብቻ ሥነስርአቱ ዕለት (ቀን) እንደሆነ ነው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በምንም መልኩ ሊታመን አይችልም፡፡
“ሠርግና ልማድ” በፊትለፊት ሽፋኗም ሆነ በውስጥ ገጿ የጠቀሰችው ጊዜ በርግጠኝነት የታተመችበትን ጊዜ አያመለክትም ማለት ይቻላል፡፡ አለማየሁ በመጽሐፏ የውስጥ ገጹ ላይ “ይህ መጽሐፍ [1956 ዓ.ም] ተዘጋጅቶ በምርመራ ምክንያት እስካሁን ቆየ፡፡ ምዕራፍ ስድስትና ሰባት ግን በተለየ [በ1949 ዓ.ም] ለጋዜጣ ቀርበው ነበር፡፡ ግን ያን ጊዜ ባለመፈቀዳቸው እስካሁን ቆዩ” በማለት የተወሰነ መረጃ ለመስጠት ቢሞክሩም፣ መጽሐፉ የታተመችበትን ትክክለኛ ወርና ዓመተ ምህረት ግን ለማወቅ አይቻልም፡፡ ያነሳቻቸው ርዕሰ ጉዳዮች ግን ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ የእድሜ ባለፀጋ እንደሆኑ መጽሐፏ ካነሳቻቸው መረጃዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማረጋገጥ የሚቻል ይመስለኛል፡፡
መጽሐፏ፣ በሠርግና ልማዶች ላይ ብቻ አይደለም የአስተሳሰብ አብዮት ለማምጣት የሞከረችው፤ በአፃፃፍ ቅርጿም (አቀራረቧም) የራሷን አሻራ ማቅለም የቻለች ይመስለኛል፡፡ ይዘቷን አስመልክተው አለማየሁ በመጽሐፉ መቅድም “መጥፎ ልማድ የታሪክ ቁስል፣ የባህል በሽታ፣ የኑሮ ደመኛ ስለሆነ፣ የሚከተሉት ልማዶች፣ ሀ) የሠርግ ድግስ፣ ለ) ልቅሶ፣ ሐ) ተዝካር፣ መ) ማኅበር፣ ሠ) የወር በዓል፣ ረ) የልደት ዛፍ ሲሆኑ መቅረት ያለበለዚያ መሻሻል አለባቸው” ብለዋል፡፡ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች፣ የተለያዩ የሀይማኖት መፃሕፍትና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን ዋቢ ተደርገው በአጭር በአጭሩ ከተተነተኑ በኋላ፣ ማሳረጊያቸው የልማዶቹን አጉልነት የሚያስተነትኑ ግጥሞች ናቸው፡
የግጥሞች አብዛኞቹ ስንኞች ባልተለመደ ሁኔታ በጣም ረጃጅም ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስለ ሠርግ አክሣሪነት ከቀረበው ግጥም ላይ፣ “ንብረቱን በሞላ፣ ላልፎ ሃጅ አብልቶ፣ ላንድ ቀን ጭፈራ በጣም ከመቸገር ጦሙንም ከማደር፣” የሚለው መዋቅር አንድ ስንኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ መጽሐፏ በይዘቷ ብቻ ሳይሆን በቅርጿም የራሷን አሻራ ማሳረፍ የቻለች መጽሐፍ ናት ያልኩት፡፡
የባለቅኔው ትንሽ መጽሐፍ፣ የባለቅኔውን ትልቅ የአስተሳሰብ አብዮት አፈንድታለች፡፡ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ይዘት ባላቸው ልማዶቻችን ላይ የሰሉ ሂሶችን ሠንዝራለች፡፡ ሥርነቀል ሂሶቹ፣ ልማዶቹ የበቀሉበትን ሃይማኖት ያገናዘቡ፣ በተለያዩ የሃይማኖት መፃሕፍትና ሥርአቶች ዋቢነት ተጠያቂያዊ (ምክንያታዊ) ሆነው በእውቀት የቀረቡ ይመስላሉ፡፡ በተለይም ሂሶቹ፣ መንግስታዊ ስርአቱና ሃይማኖታዊ ሥርአቱ በአንድ በቆሙበት ዘመን የቀረቡ መሆናቸውን ስናስተውል፣ ዘመናዊ ትምህርትና ስልጣኔ አልተስፋፋበትም በሚባልበት ጊዜ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የተሰነዘሩ መሆናቸውን ስንመረምር፣ ባለቅኔውም ሆኑ መጽሐፏ የከፈሉት ዋጋ ገዝፎ ይታየናል፡፡
የባለቅኔው የሰላ ሂስ ያረፈባቸው ልማዶች፣ ዛሬም አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በተወሰነ መልኩ ቢቀንሱም፣ ዛሬም ሀገርን ሠቅዘው የሚይዙ የእድገት ማነቆዎች ናቸው፡፡ ዛሬም የለውጥ እንቅስቃሴያችን ላይ የሚሰነቀሩ አጉል ልማዶች መሆናቸውን በተለያዩ መድረኮች እየተመሰከረ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ካባ የለበሱ አጉል ልማዶችን በይፋ መሄስ፣ መተቸት ቀርቶ መነካካት እንኳ ምን እንደሚያስከፍል ይታወቃል፡፡ ዛሬ 11 በመቶ አመታዊ “እድገት” ባስመዘገብንባቸው ዓመታት፣ ዛሬ አለምን በሚያስገርም “እድገትና ስልጣኔ” ርካብ ላይ ወጥተናል በተባለበት ወቅት እንኳ ልማዶቹን መነካካት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ግን ሃይማኖታዊና ንጉሳዊ ዘውድ የደፉ የሚመስሉትን ልማዶች በቀጥታ በተግባር ጭምር መተቸት ይቅርና በአእምሮ ማሰላሰልም የሚከብድ ይመስላል፤ ባለቅኔው አለማየሁ ሞገስ ግን አድርገውታል፡፡ ሃይማኖታቸውን በእውቀት ላይ ተመስርተው የሚያቀነቅኑ ባለቅኔ፣ ጋብቻቸውን በስርአተ ቁርባን የፈፀሙት የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የሃይማኖት መጻሕፍትን በግዕዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በልተው እያነበቡ በበሰለ እውቀት የሚያስተነትኑት የቤተክህነት ሊቅ፣ በሃይማኖታቸው ውስጥ ተሰክስከው የጐለበቱ አጉል ልማዶችን በይፋ የተቹበት እውቀትና ድፍረት በርግጥም ያስገርማል፡፡ የባለቅኔውን የዘመን ሙግት ጥቂት ዋቢዎችን በማጣቀስ እናጽናው፡፡
“ሠርግና ልማድ” ባጉል ልማድ ፈርጃ የሰላ ሂስ ከሠነዘረችባቸው ተግባራት መካከል ማህበር አንዱ ነው፡፡ መጽሐፏ፣ “ማህበር ከሠርግ እብደት፣ ከልቅሶ ሞኝነት አያንስም” በማለት ስጋዊ፣ መንፈሳዊ እና ወንፈላዊ (ሽርካዊ) በማለት በሶስት ትከፍላቸዋለች፤ ሥጋዊ ማህበር፣ “ገንዘብ አዋጥቶ ገንዘብ ወይም ፋብሪካ አቋቁሞ ለራስ ተጠቅሞ ወገንን ለመርዳት የሚደረግ” (ገጽ 35) ተግባር እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ መንፈሳዊ ማህበርም፣ ገንዘብ እያዋጡ ለአካል ጉዳተኞች ለህፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች በመስጠት በጐ ተግባር የሚፈፀምበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ወንፈላዊ ማህበር ያሉትን ግን አለማየሁ በጽኑ ተችተውታል፤ “በእመቤታችን፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በመላዕክት ስም እየተሰበሰቡ፣ ዛሬ እኔ ላብላህ፣ ላጠጣህ፣ የሚመጣው ወር ደግሞ አንተ ብድሬን መልስ እየተባባሉ፣ ያላቅማቸው እየደገሱ፣ የሚገባበዙበት፣ የምግብ ወንፈል፣ የመጠጥ ደቦ፣ የመብል ወበራ ነው” (ገጽ 36) በማለት፡፡ ቀጥለው “የሆድ ማኅበር” ያለበትን ጉድለት ይዘረዝራሉ፤ “በምግብ ማህበር ዘጥዘጥ እንጂ ጽድቅ የለም” (ገጽ 37) በማለትም በምክንያት የተደገፈ አቋማቸውን ለማስተጋባት ይሞክራሉ፡፡
ፀሐፊው አጉል ልማድ በሚል ቀጥለው ያነሱት ሂስ ያነጣጠረው በዓላት ላይ ነው፡፡ በዓላት በ3 ተከፍለው ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው “የሳምንት በዓላት” ያሉት ሲሆን፣ “…በህግ ሳይሆን በልማድ፣ በትውፊት፣ ሁለት ሁለት ቀናት፣ ሁለት ሰንበታት እሁድና ቅዳሜ በየሳምንቱ ይከበራሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ቅዳሜ የአይሁድ፣ እሁድ የክርስቲያን መሆናቸውን ግጥም አርጐ ያውቃል፡፡ ግን ዝንባሌው ወደ ስንፍና ስለሆነ አንዱ በሌላው እያመካኘ ቅዳሜንም የእሁድ መናጆ፣ የእሁድ አድማቂ አድርጐ ያከብራል፤ አዝመራውን በዋለበት አውሬ በልቶት ሲቀር ተቀምጦ ሰው ሲያማ ይውላል” በማለት ጦሱን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
በመቀጠል “የዓመት በዓላትን” አስመልክቶ የተለያዩ መረጃዎችን አጣቅሰው አስተንትነዋል፡፡ አብዛኞቹ የዓመት በዓላት ከሌሎች ሃገሮች በተለየ፣ በኛው ሀገር የበቀሉ (“ከደብረ ብርሃን በዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ጊዜ ተሠርተው ትውፊት ሆነው እስከ አሁን የኖሩ” ገጽ 43 እንደሆኑ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡ ባለቅኔው ከሁሉም የሰፋው የበዓላት አይነት የወር በዓል ነው ይላሉ፤ “የወር በዓል ካከበርን ዓመት እስከ ዓመት የሥራ ቀን አይገኝም፡፡ ሰላሳው ቀን ሰላሳ የወር በዓል አለው፤ ያውም ድርብርብ” (ገጽ 45) በማለት በሰላሳውም ቀን ኢትዮጵያዊያን የምናከብራቸውን በዓላት ዘርዝረዋል፡፡
ለምሣሌ - በወር የመጀመሪያው ቀን (በአንድ) “ልደታ፣ ራጉኤል፣ ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ሚልኪ፣ በር ተሎሜዎስ” እንደሚከበሩ አስረድተዋል፡፡
መምህር አለማየሁ፣ የተለያዩ ቅዱሳት መፃሕፍትን አጣቅሰው፣ በወር ውስጥ መከበር ያለባቸው በጣት የሚቆጠሩ በዓላትን ለመጠቆም ሞክረዋል፡፡ አስከትለውም፣ የበዓላት ቀናትን አብዝተው እራሳቸው ቦዝነው ህዝቡን አስቦዝነዋል ያሏቸውን አካላት የተቹበት ድፍረት በጣም ገርሞኛል፤ ይህችን መጽሐፍ ባላገኛት ኖሮ ከዚህ በታች የቀረበውን ጠንካራ ትችት ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የቀረበ (የተነገረ) ነው ብባል በፍፁም የማምን አይመስለኝም፤ ታላቁ መምህር ግን ለቤተክህነት ሰዎች በፊት ለፊት ተናግረዋል፤
“ገና ለገና ብዙ በዓል ካለ እየዞርሁ ለመቀላወጥ ይመቸኛል ብሎ፣ ይህን በጥንተ ተፈጥሮ የተሰጠ አምላካዊ ሕግና ትዕዛዝ አፍርሶ፣ በወር በዓል እያመካኘ ድሃ ሠርቶ እንዳይበላ የሚገዝት ያልተማረ ቄስ ስንፍና በማስተማሩ ድህነት ዘርቶ፣ ኅጢአት አርብቶ፣ የእግዚአብሔርን መንግስት አፍርሶ፣ የሰይጣን ቤት ይሠራል፡፡ ሰው በሥራ፣ በተግባር ሳለ አይበድልም፤ አያጠፋም፡፡ ወንጀል የሚሠራው፣ ጥፋት የሚያጠፋው፣ ክፉ ነገር የሚፈጽመው ሥራ ሲፈታ ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የወር በዓል ነው፡፡ በእየወህኒ ቤቱ ያለው ወንጀለኛ ቢመረመር ጥፋቱን የፈፀመው ከመቶ ዘጠና ስድስቱ ሥራ በመፍታት፣ በመቦዘን ምክንያት እንደሆነ ይረጋገጣል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅም መቦዘን የሃጢያት ሁሉ እናት ናት ብሏል፡፡ በማንኛውም ምክንያት ሰው ሰርቶ እንዳይበላ፣ እንስሳዊ ተፈጥሮውን በተግባር ልጓም እንዳይገታ የሚጥሩ ሰዎች ሁሉ ያምላክ ዐመፀኞች፣ የሰው ዘር ደመኞች ናቸው” (ገጽ 45)፡፡
በባለቅኔው ትንሽ መጽሐፍ፣ ትልቅ ትች ከቀረበበባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ ፆም ነው፡፡ መጽሐፏ፣ የፆምን ጥቅምና ጉዳት፣ ሊፆሙ የሚገቡ አጽዋማትን ወዘተ ቅዱሳት መጻሕፍትን እያጣቀሰች ምክንያታዊ ትንታኔ ለማቅረብ የሞከረች ይመስለኛል፡፡ ከአጽዋማት መካከል “ጾመ ነነዌን” በትሁት ቋንቋ የገለፀችበትን መንገድ በዋቢነት መመልከት እንችላለን፤ “ጾመ ነነዌ፤ በመጽሐፈ ዮናስ እንደተፃፈው ይህችን ጾም የየነዌ ሰዎች ናቸው፡፡ ከአንድ ጊዜ በቀር እራሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ስላልፆሟት ስለማይጾሟት የሁሉንም ጓዝ ተሸካሚዎች፣ መከረኞች እኛው ኢትዮጵያዊያን እንጾማታለን፤ እንጾምላቸዋለን” (ገጽ 51)፡፡
አለማየሁ ሞገስ፣ በ”ሠርግና ልማድ” አፈንጋጭ መጽሐፋቸው ካነሱት አጉል ልማድ አንዱ የልቅሶ ሥነስርዓት ነው፡፡ “ልቅሶ በፍልስፍናም ሆነ በሃይማኖት ዋጋ የለውም” (ገጽ 52) የሚሉት መምህር፣ በሳይንስም ሆነ በሐይማኖት የሰው ልጅ አልቅሶ የሚፈጥረው ቅንጣት ነገር አለመኖሩን የራሳቸውን የሕይወት ልምድ ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ፤ “ሰው ሲሞት ወደማይቀርበት ዓለም በክብር ሸኝቶ ወደ ሥራ በመመለስ ፈንታ ደረትን ሲደቁ፣ ሰውነት ሲያቆስሉ መዋል ከቂልነት ይቆጠራል” (ገጹ 52) በማለትም የልቅሶን ጐጂነት በአጽንኦት ያስተነትናሉ፡፡
ባለቅኔው መምህር የንድፈ ሃሳብ ሰው ብቻ አይደሉም፤ ከሁሉም በላይ ሕይወትን ከተግባራዊ የአስተሳሰብና የአሠራር ለውጥ ውስጥ ጨምቀው የሚያወጡ፣ አስተሳሰባቸውን በአፈፃፀማቸው የሚያፀኑ ብልህ ሊቅ ናቸው እንጂ፡፡ በልቅሶ ላይ ያላቸውን ፍልስፍና እናታቸውን በተረዱ ጊዜ በተጨባጭ ተፈትነውበታል፡፡ የእናታቸውን ማረፍ ሲሰሙ ምን አሉ? ምን አደረጉ? ባለቅኔው መምህር በርግጥም የሚገርም ሰብዕና ያላቸው ሰው ናቸው ለማለት ቅንጣት አላቅማማሁም…
አሁን የምናነሳው የባለቅኔው ታሪክ፣ ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት የተፈፀመ ነው፡፡ ባለቅኔው እናታቸው ናፈቋቸውና አንድ ነገር ለማድረግ ወጠኑ፡፡ በጉዳዩ ብዙ ካወጡና ካወረዱ በኋላ ወሰኑ፤ “እናቴ አብራኝ እንድትኖር ፈልጌ፣ አንድ ክፍል ለብቻው አሰናድቼ፣ የምትተኛበት አልጋ ገዝቼ ከሀገሬ ነጋዴዎች አንዱን አቶ አድማሴ የሻነህ የሚባለውን ስትመለስ እናቴን ይዘህልኝ ና ብዬ ገንዘብ ሰጠሁት” የሚሉት አቶ አለማየሁ ያሰቡት ግን አልሆነም፡፡
አንድ ቀን ጧት አለቃ ታምራት ዘገየ የሚባል ዘመዳቸው ልክ ከለሊቱ 11 ሰዓት ተኩል ሲሆን በር አንኳኩ፡፡ በሩን ሲከፍቱላቸውም፣ ከጐረቤት ሰው ፈልገው እንደመጡና የተባለው ሰው ባለመንቃቱ ከባለቅኔው ቤት ሆነው ለመጠበቅ እንደፈለጉ እንዲህ በማለት ተናገሩ፤ “ወዳንተ መስኮት ብመለከት መብራትህ ሲበራ ሳይ ጊዜ በኮርዱ ከዳሪ ከምቆም ከዚህ ሁኜ አንድ መጽሐፍ ሰጠኸኝ ሳነብ ልቆይ ብዬ ነው” አሉ፡፡ ወዲያው ተያይዘው ወደ ባለቅኔው የቤት ውስጥ ቤተመጻሕፍት ገብተው ማንበብ ጀመሩ፡፡ ልብ በሉ ጊዜው ከሌሊቱ 11፡30 ነው፡፡
ከዚህ በኋላስ ባለቅኔው ምን ይላሉ? “ይህ ከሆነ ከሩብ ሰዓት በኋላ፣ አሽከሬ ደግሞ አንኳኳ፣ ከፍቼ ባይ እሱ፤ እኔም ገረመኝና አንተ ደግሞ በሌሊቱ ምን ትፈልጋለህ ብለው ቀን ብዙ ሥራ ስላለብኝ አሁን ቤቱን ልጠርግ ነው አለኝ፤ ወዲያው ዳናው ደመቀ፤ ጓጓታው በዛ፤ ያለወትሮው ምን ያደርጋል እያልሁ አንቋቋ ጀመር፡፡ አብሮኝ የነበረው ሰውዬ እንደነቃሁ ገባውና ያላፊ አግዳሚውን እያወራ፤ አሽከሬን እያመሰገነ እንዳላዳምጥ ለማድረግ ሞከረ፡፡ ድምጽና ጓጓታ እየበረከተ ስለሄደ፣ ምን ታደርጋለህ በማለት እያጉረመረምሁ በር ከፍቼ ስወጣ የሳሎን ዕቃዬን በብዙ ሰዎች እየተረዳ ወደ ውጭ ሲያጉዝ አየሁና፣ አወቅሁባችሁ፣ የያዛችሁት መርዶ ነው፤ ለምን እሁድ ቅዳሜ የለት እሬሳ ይመስል አታደርጉትም? ዛሬ በሥራው ጉዳያችሁን ጥላችሁ እኔን ሥራ ልታስፈቱ የመጣችሁት? ለምንስ ጽፋችሁ ማታ በምተኛበት ጊዜ እንዳነበው ካልጋዬ ትታችሁልኝ አትሄዱም ብዬ በኃይል” ጮኹ (ገጽ 56) ፡፡
ባለቅኔው፣ ቅኔያዊው የመርዶ ስርዓት አልበገራቸውም፡፡ ሊያረዷቸው የመጡት ሰዎች ከሳሎናቸው ያወጡትን ዕቃ መልሰው፣ የመርዶውን ደብዳቤ ሰጥተዋቸው እንዲሄዱ ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን የሞተው ዘመዳቸው ማን ይሆን? በሚል ነፍሳቸው ተጨንቃለች፡፡ የመርዶውን ደብዳቤ ገልጠው ሲያነቡ፣ እናታቸውና የአጐታቸው ልጅ መሞታቸውን ተረዱ፡፡ ለእናታቸው ስንት እያሰቡ መሞታቸውን ሲሰሙ ትንሽ ተቆጩ፤ “እኔ በሕግ፣ በወግ ጡሬ እመረቃለሁ ስል የሞተችው እንዳትጦር ነው? ወይስ እንዳትመርቀኝ? ይህ ሀሳቤን የጠላ እግዚአብሔር ነው? ወይስ እሷ?” (ገጽ 56) በማለት መራር ጥያቄዎች እያነሱ ቆዘሙ፡፡
ባለቅኔው መምህር የእናታቸውንና የአጐታቸውን ልጅ ሞት ከተረዱ በኋላ ያደረጉት ተግባር፣ ቃላቸውን በተግባራቸው ማጽናት የሚችሉ መሆኑን በሚገባ የሚያሳይ ይመስለኛል፤ የመጨረሻውን ቃል ለጀግናው ተውለት እንደሚሉት እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፣ የባለቅኔ የአለማየሁ ሞገስን የመጨረሻ ተግባር ከራሳቸው እንስማ፤ “አንድ ወር ለሆነው መርዶ ዛሬ ካልነገርነው ያላችሁበት ምክንያት አሁንም አልተሰማኝ፣ በትኩሱ ወዲያው እንኳ ቢሆን ኖሮ፣ ሞቱ እኔን ፈርቶ ይመልስልኝ እንደሆነ፣ ጩኼም፣ አልቅሼም ዐየው ነበር፣ አሁን ግን ከወር በኋላ ምን ለማድረግ ይቻላል አልሁና ከዚያ የተሰበሰቡትን ሁሉ የሠርጌ ለት ያላደረግሁትን ቁርስ አብልቼ፣ ወደ እየሥራቸው ቢሄዱ ተሻይ መሆኑን ነግሬ ለማስተማር ወደ ትምህርት ቤቴ ተጓዝሁ” (ገጽ 57)፡፡

 

Read 3419 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:29