Saturday, 19 November 2011 14:27

የተገነዙ ትኩሥ ሬሳዎች የሚከማቹበት ዋሻና በዘመናችን ሰዎች የተሠራው ውቅር መቅደስ

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል Saache43@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

“በእርግጥ የናንተ አባቶች ያነን [ላሊበላንፀ] ካነጹ፣ ለምን በእናንተ ዘመን እንደነሱ ያለ አልተሠራም?” በማለት ታሪካችንን ለመፈታተን ሲሞክሩ ይደመጣሉ፡፡“ብዙ መልስ ቢኖርም ከ840 ዓመታት በኋላ ምስካበ ቅዱሳን መድኅኔዓለም ገዳም የማያፈናፍንና የማያዳግም ምላሽ ስለሰጠ ታሪካዊ ጠቀሜታው የጐላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡”ይህ ስለተጠቀሰው ገዳም፣ በተለይም ስለውቅርና ፍልፍል ቤተ መቅደሱ ከሚገልጸው መጽሐፍ የተገኘ ነው (ገፅ 34-35)፡፡ ከዓመት በፊት ነበር ይህን ገዳም ለማየት የቻልኩት፡፡

በሰሜን ሸዋ፣ ሞጀና ወደራ ወረዳ፣ ፊላ ገነት ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ እጅግ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ፣ ከየት እንደሆነ ባይታወቅም የተገነዙ አጽሞች፣ አውራ ዶሮ መሳይ ወፍ/አሞራ” (በዐይናቸው ሲያዩት እንደሚመስለው) ለዘመናት እየፈለሱ መጥተው ከሚጠራቀሙበት አንድ ዋሻ አጠገብ ተወቅሮው የተሠሩ መቅደሶች ያሉበት ገዳም ነው፡፡ አሁን በ2004 ዓ.ም ስለዚያ ገዳም፣ ስለ አጽሞቹ ዋሻና በ24 ወጣቶችና በአንድ መነኩሴ ካህን ተውቅሮ ስለተሰሠራው አስደናቂ ቤተመቅደስ የጽሑፍ መረጃ ስለታተመ ከዚያ በመረዳት ይህን አስገራሚ ገዳም ለማስተዋወቅ ፈለግሁ፡፡ በቦታው በመገኘት መጽሐፉን ይዞልኝ በመምጣት እንዳነብበው ላደረገኝ ተወልደ ኃይለስላሴ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ 
አዲስ ካሏት አምስት በሮች በምሥራቅ በሚገኘው የደሴ በሯ በኩል ዋናውን መስመር በመያዝ 180ኛ ኪ.ሜ ላይ ጣርማ በርን ያገኛሉ - ደብረ ብርሃንን አልፈው፡፡ ከጣርማ በር ወደ ግራ በመታጠፍ፣ ሰላ ድንጋይ የሚያደርሰውን ገረጋንቲ መንገድ በመያዝ ሲጓዙ 17ኛ ኪ.ሜትር ላይ በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ልትመሠረት የቻለችውን የደብረ ምጥማቅ ገዳም ቤ/ክርስትያን ያገኛሉ፡፡
ከደ/ምጥማቅ መግቢያ በር ትይዩ፣ በመንደሮች አናት ተሻግሮ የምትታየው አምባ "ጻድቃኔ" በመባል የምትጠራው መንፈሳዊ መካን (ዋሻ) ናት፡፡ አሁን የምንሄድበትን ውቅር ቤተ መቅደስ (ከዚህም አልፎ የሚገኘውን የሠሩት በዚህች መንፈሳዊት መካን የነበሩ አባትና ወጣቶች ናቸው፡፡
ደብረ ምጥማቅ የደረሰዎትን መንገድ ይዘው ሲሽቆለቆሉ፣ 5 ኪ.ሜ ላይ እንደተጓዙ ሰላ ድንጋይን ያገኙታል፡፡ ከአዲስ አበባ 202 ኪ.ሜ ያህል መሆኑ ነው፡፡
ከሰላ ድንጋይ ትንሽዬ ከተማ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በጥርጊያ መንገድ 4 ኪ.ሜ ያህል ቢጓዙ ያን አስገራሚ ገዳም ያገኙታል፡፡
ከአንድ ቋጥኝ ሥር ተወቅሮ የተሠራ ነው፡፡ የዚያ ቋጥኝ አናት ደልደል ያለ ነገር ነው፡፡ ምናልባትም "ውድማ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶት መኖሩ እንደ አውድማ ሊያገለግል በመቻሉ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ደልደል ያለ የሚመስለው የየጭንጫ አምባ ከወዲህ ሲታይ ግምስ ያለው አለቱ ይታያል፡፡ ከአፋፉ ላይ አንድ የጽድ ዛፍ ይታያል” ያን ዋሻ የሚጠብቅ ነብር የሚታይበት ነው፡፡ ወርዶ ደግሞ የወይራ ዛፍ ይታያል፡፡ የዚያ ዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠሎቹ ጋረድ የተደረገው ዋሻው ነው አጽሞች በአሞራ መሳዩ ወፍ እየመጡ ሲጠራቀሙ የኖሩበት፡፡ በዚህ የወይራ ዛፍ ላይም ጠባቂው ነብር ሲቀመጥ ይታያል፡፡
አጽሞቹ
እንደሚገባ፣ በወግ የተገነዙ አጽሞች በሥርዓት የሚቀመጡበት እንደሆነ ኖሯል ዋሻው፡፡ በእንዴት ያለ ሁኔታ ተቀምጠው እንደሚገኙ ማየት የቻሉ (ካህናት) እንደጻፉት፣ “በበፍታ፣ በቆዳ፣ በሸራ እንደተገነዙ” ሳይፈርሱ፣ ሳይበሰብሱ ይገኛሉ፡፡ ከውጭ በዚያ ወፍ ሲገቡ መታየት ከጀመረ ብዙ ዘመንና ትውልድ አልፏል፡፡ ግና አጽሞቹ ትኩስ አስከሬን ናቸው፡፡ ጭራሽ “አልባብ አልባብ” እየሸተቱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡ አፅማቸው ወደዚህ ዋሻ ፈልሶ ሲመጣ፣ የእነዚያ ሰዎች አንጡራ ንብረት የሆኑት መጻሕፍቶቻቸውና “እያበሩ” የሚታዩ መቁጠሪያዎቻቸው ጭምር አይቀሩም፡፡
እነዚህን አፅሞች ወደዚህ ዋሻ እያፈለሰ የሚያመጣቸው ደግሞ አንድ ግዙፍ ነጭ አሞራ መስሎ ላገሬው ሰዎች ሳይቀር የሚታይ ወፍ ነው፡፡
ከዓመት በፊት በመጋቢት ወር በቦታው በመገኘት ያነን ገዳም ባየሁበት ጊዜ በአካባቢው ተወልጄ ያደግሁ ነኝ ያለንን ጐልማሳ ገበሬ ጋር ለማነጋገር ችዬ ነበር፡፡ “ወፉ ሲመጣ “መጣ - መጣ” ተባብለን፣ ሮጠን ወደዚያ ዋሻ እንሯሯጣለን፡፡ ግን ማንኛችንም ወደ ዋሻው ይዞት የሚገባውን ተጠግተን ለማየት አንችልም” ነበር፡፡ ያለኝ፡፡
“መቼ እንደሚመጣ ስለማናውቅም እዚያ ውለን መጠበቅ አንችልም፡፡” ድንገት አጋጥሞ “በዋሻው የቀረቡ ጊዜ ነው ግዙፉ አሞራ በሰማይ ላይ ክንፉን እያማታ ሲመጣ ሊከታተሉት የሚሞክሩት “ግና እስከዋሻው ድረስ ልናየው አንችልም - ይሰወርብናል” ብሎኝ ነበር፡፡
ስለገዳሙ የሚገልጸው መጽሐፍ፣ ስለዚህ ግዙፍ ወፍ “ግዙፍ ነጭ አሞራ መሳይ” ብሎ በመጥራት፣ “ትኩስ አስከሬን በውል ከማይታወቅ ቦታ” ይዞ በመምጣት በመጀመሪያ “ውድማ” በተባለው ጭንጫ ላይ ያርፋል፤ ከዚያ በታች ከወይራው ሥር በሚገኘው ዋሻ ያመጣውን አጽም በክብር ያሳርፋል፣” ይላል፡ መጽሐፉ ይህን በራሪ “በአምሣለ ወፍ” የሚመጣ መልአክ መሆኑንም ይገልጻል፡፡
ይህንን ልዩና ዛሬም ድረስ የሚፈጸም አስደናቂ ሥራ በዚያ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ያካባቢው ሽማግሎች ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ከውጭ ሲመለከቱ ኖረዋል፡፡
በአካባቢው የዕጣን መዓዛ፣ አንዳንዴም የከበሮና የዜማ ምሥጋና እንደሰሙ የሚናገሩ እንደነበሩ፣ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡
በተለይ በጣም በራቀ ጊዜ ደግሞ፣ በትውፊት ወርዶ እንደሚነገረው ከቋጥኙ ላይ አንድ ካሉት ዛፎች ላይ ነብር፣ ወደ ምሥራቅ ወረድ ብሎ ዛሬ ወደ ቦታው ሲኬድ በሚሻገሯት ወራጅ ላይ ደግሞ ዘንዶ በመኖሩ ማንም አልፎ መሄድ አይቻልም ነበር፡፡
ውቅር ቤተመቅደሱ
መጋቢ ተክለጻድቅ ሸዋረጋ በጻድቃኔ እያገለገሉ ይኖሩ የነበሩ ካህን ናቸው፡፡ በዚያች ቦታ ሳሉ ይህ ዋሻ ወደሚገኝበት ቦታ “ነጭ የአውራ ዶሮ አምሳል ከሰማይ ሲወርድ” በራዕይ መመልከታቸውን በመግለጽ አጀማመሩን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም በላይ በራዕያቸው ወደዚያ ቦታ ተነስተው እንዲሄዱ መታዘዛቸውንና በትእዛዙ መሠረት እንደተነሱ አስነብበዋል፡፡ የሚያዩት ራእይ ከሚያምኑት ቅዱስ መንፈስ መሆኑንም ለማጠየቅ ሌሎች አባቶች በጸሎታቸው እንዲረዷቸው ነግረው፣ ራሳቸውም ሱባዔ ያዙ፡፡” በዚሁም “የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን አረጋግጠው” ሥራውን እንደጀመሩት ወደዚያ ገዳም የሚደርስ ሁሉ ይነገረዋል፡፡ በገዳሙ የተዘጋጀው መጽሔትም ይህንኑ በመግለፅ ነው እንዴትና መቼ ሊጀመር እንደቻለ የሚናገረው፡፡
አባ ተክለጻድቅ ወደሄዱት ቦታ በመሄድ ያካባቢውን ሽማግሎች አነጋግረው፣ እንዲያሟሉ የሚፈለገውን ፈፅመው ቦታውን ተረከቡ፡፡
የቤተመቅደሱ ሥራ በመጋቢት 20/1998 ዓ.ም ተጀመረ፡፡
ወደቦታው እንዲሄዱ መታዘዛቸውን ከገለጹበት ቀጥሎ በእንዴት ያለ ዐቅድና አሠራር እንደሚከናወንም ተረድተው እንደጀመሩት ያንንም ደግሞ በመጽሐፋዊ ቃል አስደግፈው ጽፈውታል፡ ንባቡ፡-
“በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስ ሥሩልኝ… እኔ እንደማሳይህ… ሥሩት” (ዘጸአት 25÷8) ይላል፡
እዚያው ለጸበልና ለጸሎት ከነበሩ ወጣቶች 12 ወንዶች 12 ሴቶች ተመርጠው እንዴት እንደሚሠሩ በመጋቢው አባ ትምሕርት ተሰጥቷቸው፣ የዚያ ገዳም ቤተመቅደሥ ሥራ ላይ ተካፋይ ሆኑ፡፡
ያላንዳች ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያ፣ ያላንዳች መሃንዲስ፣ ያላንዳች ባለሙያ እንደታዘዙት ለመሥራት መነሳታቸውንና በእምነት እንደጀመሩት ሲገልጹ የነብዩ ነህምያን ቃል ይጠቅሳሉ… “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፡፡ እኛ ባሪያዎቹ ተነስተን እንሠራለን፡፡”
በመጋቢት 20/1998 ዓ.ም ሥራውን የጀመሩት በግንባታ የሚሠራውን የፊትለፊት ገጹን ነበር፡፡ በዚያው ዓመት ይኼው ወደ ፍቅር ቤተ መቅደሱ መግቢያ የሆነው የፊት ለፊት ግድግዳው ግንባታ ተገነባ፡፡
በግንበኛ በበሃ ድንጋይ የተገነባ መግቢያ ነው፡ በሮቹም በባለሞያዎቹ ተሠርተው የተገጠሙ ናቸው፡ እንዲህ አድርገው፡፡ ቋጥኙን የተጠጋ ግንባታ ካስገነቡ በኋላ ነው እንግዲህ ወደ ውስጥ እየተወቀረና እየተፈለፈለ ሰፋፊ ክፍሎችና ሦስት መቅደሶች ያሉት የአስደናቂው ውቅር ቤተ ክርስትያን ሥራ በነዚህ ሃያ አምሰት ሰዎች የተጀመረው፡፡
በስፋቱ ቀዳሚ ይሆን?
ክረምቱ እንደወጣ በ1999 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ “ፍልፈላ” ተጀመረ፡፡ በዚህ በምስካበ ቅዱሳን መ/ዓ/ገዳም የቀረበውን መጽሐፍ ገዝቶ ያመጣውና እንዳነብ የሰጠኝ ወጣት ተወልደ ልክ እንዳገኘኝ የጠየቀኝ ጥያቄ ከጥያቄነቱ ይልቅ መገረሙን የሚገልጽለት ነበር፡፡ ስፋቱንም ጠቋሚ ነበር፡፡
“እኔ ግራ የሚገባኝ፣ አንድን ቋጥኝ ከመግቢያው ጀምረው እየፈለፈሉ ሲሄዱ፣ ድንጋዩ ያን ያህል ወደ ውስጥ የጠለቀ ሊሆን እንደሚችል በምን አወቁት? ሄዶ፣ ብዙም ሳይቦረቡሩ ድንጋዩ ቢያበቃስ?...”
ምን ልበለው? “እሱ አይደል” አንዱ የሚያስገርመው ነገር፡፡ በእነ ላሊበላም ቢሆን፣ ከላይ ወደታች እየፈለፈሉት ሲወርዱ ድንጋዩ ያንን ያህል ጥልቀት እንደሚኖረው እንዴት እንዳወቁትም አይደል እንቆቅልሽ የሚሆነው?
ይህ የምስካ በቅዱሳን ገዳም ቤተ መቅደስ በፍልፈላም ሆነ በውቀራ ከተሠሩት ሁሉ በስፋቱ የሚያኽለው ይኖር እንደሆነ ማጣራት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ከውስጡ ገብቶ ያየው ሁሉ ግን የስፋቱን ነገር ሳይመሰክረው አይቀርም፡፡ ሰፋፊ የሆኑ ሦስት መቅደሶች ያሉት ሲሆን፤ ሰፊ ቅኔ ማኅሌትና ከሦስቱም መቅደሶች ሰፋፊ በሮች ፊት ለፊት ሰፋፊ የዓምደ ወርቅ ቦታዎች ያሉበት ነው፡፡ አንድ ሰው ውሎና አድሮ ካላጠናው በቀር በውስጡ ያሉትን ክፍሎችና በሮች፣ በዚያው ዙሪያ ያሉትን መተላለፊያዎች ጨምሮ በአንድ ጊዜ ለይቶ ያውቀዋል አልልም፡ እየተዟዟረ ቆይቶ በገባሁበት ተመልሼ ልውጣ ቢል አይቻለውም፡ የሚያውቅ ሰው ካልመራው በቀር ይደነጋገራል፡ በዋናው መኻል በር ገብቼ ሦስቱንም መቅደሶችና ቅድስቶች፣ የሴትና የወንድ መቆሚያው ተለይቶ የሚታወቅበት ዙሪያውን ሁሉ ዞሬ፣ በገባሁበት ልውጣ ብዬ ብቅ ያልሁት በሌላ በር ነበር፡፡ ከቤተ መቅደሱ በስተግራ ከዚያው አንድ ቋጥኝ ወቅረው የተዘጋጁ፣ ተፈልፍለው ሱባዔ የያዙ የገዳሙ መነኮሳት ለየብቻቸው በሚገኙበት ውቅር ዋሻዎች በሚገኙበት መተላለፊያ በኩል ነበር የወጣሁት፡፡ (“40 ፍልፍል ዋሻዎች ለሱባዔና ለፀሎት መያዣ ያሉትም ነው፡፡”) በእርግጥም ከቋጥኙ የተሠራው ቤተ መቅደስ ሰፊ ነው፡፡ ጠቅላላ ስፋቱ 4000 ካ.ሜትር እንደሆነ የተጻፈው መግለጫ ይጠቁማል፡፡
“ይህን ያህል ስፋት ያለው ሌላ ውቅርም ሆነ ፍልፍል ቤተ መቅደስ ይኖር ይሆን?” ያስብላል፡፡

አንድ ዓመት ከስምንት ወር!
በጥቅምት 1999 የተጀመረው ሥራ በ20 ወራት ጊዜ ውስጥ በቀጣዩ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ተጠናቅቆ፣ የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኤፍሬም እና በአፋር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮናስ ተባርኮ ከብሯል፤ በግንቦት 27/2000 ዓ.ም፡፡ ጠቅላላ ዓመት ከስምንት ወር መሆኑ ነው፡፡ ያን የሚያህልና የውስጡ ግድግዳዎች አምረው የወጡበት ያ ሥራ በዓመት ከስምንት ወር ጊዜ ብቻ በዘመናችን ሰዎች ሊከናወን መቻሉም ጭምር ነው ድንቅ የሚያሰኘው፡፡
እነዚያ የተመረጡ ወጣቶችና አሁን የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑት መጋቢ ተክለጻድቅ ሸዋረጋ በነዚህ የሥራ ጊዜያቸው ሁሉ የዕለት ዕለት መደበኛ ሥራቸው ይሄው ሲሆን በየጊዜው ብዙ ልዩ ነገሮች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ ሳይነገር የሚታወቅ ነው፡፡ ከወጣቶቹ የየራሳቸው መዝገብም የነበራቸው ይታጣሉ አንልም፡፡ ስለገዳሙ የቀረበው ባለ 76 ገጽ መጽሐፍ ብቻ በቂ እንዳልሆነም ስለተረዱትም በቀጣይ እትም እንገናኝ ብለዋል፡፡ ምናልባት በተከታታይ በሚቀርበው በዝርዝር ይገልፁልን ይሆናል፡፡
በዚህ እትም ግን በከፍተኛ ችግርና ፈተና አስደናቂ ተአምራት እንደተሠራ ጠቆም የሚያደርጉ አንድ ሁለቱን ጠቅሰዋል፡፡
ወጣቶቹ እህል ውኃ በሌለበት ጊዜ እንኳ ምንኛ ይተጉ እንደነበር እንዲህ ተገልጾ ይገኛል፡፡
“የሚቀመስ ዳቦ፣ ንፍሮ ወይም በሶ በሌለበት ሰዓት ሳይሰቀቁ ለቀጣዩ ቀን ሥራ ራሳቸውን ያዘጋጁ ነበር፡፡”
በውቀራው ወቅት በዶማም ሆነ በሌላ ሲመታ ፍንክች አልል ያለ ድንጋይም ገጥሟቸው ነበር፡ ሲመቱት “እንደመብረቅ ብልጭ እያለ” አልበገር ቢላቸው፣ በዚያ ነገር “ሱባዔ ያዙ” እንደተጻፈው፡ እምቢ ያለው ትልቅ ዐለት እንዳለ ተፈንቅሎ ራሱ ወደቀላቸው፡፡ የተፈነቀለው ትልቅ ዐለት ከነበረበት ቦታ ደግሞ ለዐራት ቀን ያህል ፈሳሽ ነገር ይንጠባጠብ ነበረ፡፡ ያነን እንደ ጤዛ ጠብ ጠብ” የሚል ፈሳሽ እንደ ጸበል የተጠቀሙበት ብዙዎች ከነበረባቸው በሽታና ደዌ ተፈወሱ፡፡ (ገፅ 30)
የሚያስገርም ልዩ ቀለም ያለው ዐለትም ከመካከለኛው መቅደስ (የመድኃኔዓለም) የቋጥኝ ጣሪያ መኻል ለመኻል ገጥሟቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ልክ ከጣሪያ ዐናት ላይ የተሰካ የሚመስል፣ ክብ ቅርጽ ያለው፣ ብርሃን የሚፈነጥቅ (የሚያበራ) ዐለት ነው፡ የመቅደሱ አክሊል እንዲሆን ራሳቸውም ተገርመው እንዳለ ትተውታል፡፡….”የእሾህ አክሊል ምሳሌ ነው” ተብሏል፡፡
እነመጋቢ ተክለጻድቅ ሸወረጋና በመጽሐፍ ስማቸው (የክርስትና) ተጽፈው የሚገኙ ሃያ ዐራት ወጣቶች /12 ወንዶች፣ 12 ሴቶች/ በአጭር ጊዜ በዚሁ ባለንበት ዘመን እንዲህ ያለ ታሪካዊ ሥራ መሥራታቸውን በመጽሐፋቸውም እንደተጻፈው፤ ያባቶቻቸው ልጆች እና የበረከታቸውና የጥበባቸው ጸጋን ወራሾች ለመሆን ከታደሉት ቁጥር የሚገቡ ናቸው፡፡ “የታለ እሱ የነላሊበላና የአክሱማውያኑ የጥበብ በረከት?” ተብሎ በጨዋ ቃል ተለውጦ የሚቀርብ በብዙው ታካችና አማፂ ወገኖች ሲጠየቅ የኖረ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር “ተገቢ ጥያቄስ ነበረ ወይ? ሊባልም የሚችል አንድ “አደፍርሳዊ” ጥያቄ ሆኖ ኖሯል፡፡
ያለፉት “ሥልጣኔ” በእርግጥ በኢትዮጵያውያን ተሠርተው ከሆነ ዛሬ እነዚያ ሥራዎች ወደየት ጠፉ?... “ስለዚህ” የሚለው ይከተላል፡፡
በዚህ ረገድ በመጽሐፉ የተጠቀሰውን ነው ከመግቢያችን ላይ ተጠቅሶ የምናገኘው፡፡ “በእናንተ ዘመን እንደነሱ (እንደነ ላሊበላ) ያለ ለምን አልተሠራም” በማለት “ታሪካችንን ለሚፈታተኑ የማያዳግም ምላሽ የሰጠ” ሥራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
“ሞስካበ ቅዱሳን” የሚል ስም የተሰጠው ይህ ገዳም ከተመሠረተ ደግሞ ወደ አምስት መቶ ዘመን የሚጠጋው እንደሆነ ከተጻፈው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዋሻው ውስጥ በግራኝ ዘመን ተደብቀው እንዲቀመጡ የተደረጉ ታቦታትና ንዋያት እንደነበሩበት፣ ከጐንደር “ውኃ መውጫ” ተብሎ ከሚጠራ ቦታ ሦስት ሰዎች (በስማቸው የተጠቀሱ) እንዳመጧቸውም ጭምር ተተርኳል፡፡
ለመሰናበቻ አንድ ምሑር ከአፅሞቹ መካከል አንዱን ለምርምር ሥራው ጐትቶ በማውጣቱ የደረሰበትን የሚልፀውን እንዳለ እናንብብ፡-
“ከዋሻው ውስጥ ከነበረው የአጽመ ቅዱሳን አስከሬን አንዱን ጐትቶ በማውጣት፣ በተጨማሪም መጻሕፍቱንና ልብሳቸውን ለምርምር የወሰደው መምህር ብዙም አልቆየ፡፡ ታሞ በቅስፈት ሕይወቱ አልፏል፡፡” (ገጽ 45)

 

Read 4574 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:30