Saturday, 27 July 2013 13:47

አትሌት ሀይሌ በመጪው ምርጫ ፓርላማ መግባት ይፈልጋል

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ባሳለፍነው ሳምንት የሻቃ ሀይሌ ገ/ስላሴን ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጐትና ያገኘውን ትኩረት በሚመለከት ከአትሌቱ ጋር ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረ ስህተት ቃለ-ምልልሱ ሙሉ ለሙሉ አልቀረበም፡፡ ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን ይቅርታ እየጠየቅን ሳምንት የቀረውን ቀጣይ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሀይሌ አለም አቀፍ ሰው ነው ከፍተኛ እውቅናም አለው ነገር ግን አሁን ሩጫ የሚያቆምበት ዘመን ስለሆነ ላለመረሳት ነው ወደ ፖለቲካው ለመግባት የሰበው ይባላል እውነት ነው?
አቤት አቤት! (በግርምት ጭንቀላቱን እያወዛወዘ) አንድ ነገር ልንገርሽ እኔ እንዳልረሳና ዘላለም እየታወስኩ እንድኖር ከፈለግኩኝ ኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ተወዳድሬ መግባት እችላለሁ፡፡ ጓደኛዬ ፖልቴርጋት አሁን እዚያ ሊገባ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከዚህ በላይ ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም በቂ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከፈለኝ እዚያ መስራት እችል ነበር በቃ ይሄው ነው፡፡
ቀደም ሲል ልጆቼ ሲቪክ ስለሚማሩ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት እንደሚመረጥ ያውቃሉ ብለሀል ይሁን እንጂ ሃይሌ ልጆቹ አማርኛ መናገር በማይችሉበት ሁኔታ እንዴት አገር ልምራ ይላል የሚሉ አሉ ምላሽህ ምንድነው?
እንዴት ያለ ነገር ነው በናትሽ እንደው በአሉ አሉ ወሬ ስንቱ ገደል ገባ መሰለሽ፡፡

በነገራችን ላይ የኔ ልጆች ይህንን ነገር አለ የተባለው ሰው ጋር ልካተገናኘን ሞተን እንገናኛለን አሉ፡፡ “እሱ እና እኛ ቁጭ ብለን የትኛችን አማርኛ እንደምንችል እንተያይ” ብለው ነበር፡፡ አንድ መጽሔት ላይ ነው ይህ የተፃፈው፡፡ እና እኔ እንዴት እንዳስቆምኳቸው ታውቂያለሽ ይሄ እኮ የቀልድ መጽሔት ነው በቃ ጆክ ነው ብዬ ነው ያሳመንኳቸው፡፡ በነገራችን ላይ በእኔ እምነት አማርኛ ማወቅና አለማወቅ የኢትዮጵያዊነት መገለጫው አይደለም፡፡ እንግሊዝኛ ማወቅም ምሁርነት አይደለም፡፡ እኔ በልጆቼ ከምረካባቸው ነገር አንዱ አገራቸውን መውደዳቸው ነው፡፡ ሁለቱ ትልልቆቹ የ15 እና የ13 ዓመት ናቸው፡፡ (ቢሮው ግድግዳ ላይ ወደተሰቀለው የልጆቹ ፎቶ እያመለከተ) አሁን አንድ ትምህርት ስላላቸው አሜሪካ ነው ያሉት፡፡ አሁን ደውዬ ባሰማሽ “ወደ ኢትዮትያ የምንመለስበት ጊዜ አይደርስም እንዴ” ነው የሚሉት ትላንትና ማታ ለ30 ደቂቃ ነው ያዋራኋቸው ከሄዱ ገና ሁለት ሳምንታቸው ነው፡፡ ይታይሽ እና አንዳንድ ጊዜ መፃፍ ቻልን መድረክ አገኘን ብለው ሃላፊነት የጐደለው ስራ ባይሰሩ ደስ ይለኛል፡፡ የግል አስተያየት በቃ የግል ነው፡፡ ወደ አድማጭና አንባቢ ሲደርስ የሚያመጣውን ችግር መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ነገሩ የገጠመበት ደግሞ ምን መሰለሽ ሃዋሳ ላይ አንድ ኢንተርቪው ነበረን፡፡ እኔ እየተጠየቅኩ ሳለ በመሃል ሁለቱ ልጆቼ መጡ፡፡ ደንግጠው የሚሉት ሲጠፋባቸው እንግሊዝኛ እየቀላቀሉ ሲያወሩ በቴሌቪዢን ስለታዬ ነው እንዲህ የሚባለው፡፡ ግን ልጆቼ ጥሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉንም እየዞሩ ማስረዳት አይቻልም የቢግ ብራዘሯ ቤቲ ገና ሁሉንም ዞራ ማስረዳት ስላልቻለች እንደውም ነገሩ ወደ ክስ እየሄደባት ነው ከአዲስ አድማስ ከጋዜጣሽ እንዳነበብኩት በነገራችን ላይ አንድም ዕትም ሳያመልጠኝ እገዛለሁ የማነበው ጋዜጣ ነው አዲስ አድማስ፡፡
ሰው ወደ ሃላፊነት ሲመጣ ነገሮች አልጋ በአልጋ አይሆኑም ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ውጣውረዶች የሚገጥሙህ ይመስልሃል?
እሱማ ቻሌንጅ እንደሚገጥመኝ አውቄ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ አሁንም ወደ ቻሌንጁ እየባሁ ነው፡፡ ለምን እንዴት፣ ገብተህ ምን ትፈጥራለህ፣ እያሉ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በጥያቄ ሲያጣድፉኝ እኮ ይሄ የቻሌንጅ መጀመሪያ ነው፡፡ ወደ ውድድር ውስጥ ስትገቢ ደግሞ በርካታ ቻሌንጆች አሉ፡፡ እንዲህ ታግሰሽና ተዘጋጅተሽም አለመመረጥ ይመጣል፡፡ ከተመረጥሽ በኋላ ሌላ ከፍተኛ ቻሌንጅ አለ፡፡ እኔ ወደ ፓርላማ ልግባ ወይም ፕሬዚዳንት ልሁን ስል ላገልግል እንጂ ልገለገል አይደለም፡፡ ምንድነው የምታገለግለው ካልሽኝ በርካታ ነገሮች አሉኝ ልሠራቸው የማስባቸው፡፡
ወደዚያ እንድትገባ የሚፋፋህና አንገብጋቢ የምትላቸው ጉዳዮች ወይም ፓርላማ ብገባ እቀርፋቸዋለሁ ፕሬዚዳንት ብሆን እልባት እሰጥባቸዋለሁ የምትላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በኢኮኖሚው ላይ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡ በስራ አጥነት ላይ ከፍተኛ ሥራ መሠራት አለበት፣ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የኤክስፖርት ከሶስትና ከአራት ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ላይ ሁሌ እናወራለን፡፡ ግን መልካም አስተዳደር በአንድ ምሽት የሚመጣ አይደለም፡፡ ሂደት ነው በዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያ ነን እያሰብን ያለነው መካከለኛ ገቢ ያለን ዜጐች ስለመሆን ነው ይሄ እንዴት ይመጣል እነማን ናቸው መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት እከሌ እከሌ፣ እኔ ብዙ አገሮችን በመጐብኘት ባገኘሁት ልምድ የእነዛን አገሮች የማደግ ምስጢር በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርተን ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ላይ መስራት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ለመናገር ወደ ፓርላማ የምገባው ተሞክሮዬን ለማካፈል ነው፡፡ ልምዴን ሳካፍል ግን በፖለቲካም በይው በማህበራዊም በይው በኢኮኖሚው በሁሉም ረገድ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ማህበራዊ ነገሮችን እናውራ ቢባል ጠቃሚ ባህል እንዳለን ሁሉ ጐጂም ባህል ሞልቶናል፡፡
ምሳሌ እየጠቀስክ ብትነግረኝ …
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ የሠርግና የሀዘን ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰርጋችንም ሀዘናችንም ከአንድ ሳምንት በላይ ይወስዳል ሰርግም ሀዘንም አያስፈልግም እያልኩ አይደለም በዓላት አከባበር ላይ ብታይ ጊዜ የሚድል ነገር ነው የምታይው ይህ ሁሉ ካልተስተካከለና ጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ( ) ካለመድን ለውጥ ማምጣት አይቻልም በዚህ ላይ እሠራለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሴ ምሳሌ ሆኜ መገኘት አለብኝ፡፡ ሠርቼ ነው ማሳየት ያለብኝ
ሰርግን በተመለከተ ላነሳኸው አንተ በሠርግ ነው ያባኸው መልስም እንደነበረህ አልጠራጠርም በዚህ እንዴት ሌላውን ማስተማር ትችላለህ?
እኔ ሰርጌ የዛሬ 16 ዓመት ነበር፡፡ ሠርግ ነበር ግን ይህን ያህል ቀን የፈጀ አይደለም አላደረግኩትም፡፡ ከሰርጌ በኋላ በማግስቱ ልምምድ ላይ ነበርኩ፡፡ መልስ ሄደሃል ወይ አዎ ሄጃለሁ፡፡ ነገር ግን ልምምድ ሰርቼ ስጨርስ ነው መልስ የሄድኩት፡፡ ይሄው ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ መስራት አለብን፡፡ ይሄ ያሳስበኛል እሠራበታለሁ፡፡
አንተ በግልህ ይህቺን አገር ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመምራት አንድ ሰው ምን ምን ነገሮችን ሊያሟላ ይገባል ትላለህ?
ከበርካታ ነገሮች ውስጥ አንቺ ጣል ጣል ያደረግሽው እውቅና ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ካለኝ እውቅና እና እንደ ኢትዮጵያዊ አትሌቲክስ በውጭው ያሉ የአለም መሪዎችን የማግኘት እድል ገጥሞኛል መሪ ስትሆኚ ደግሞ የዛን ሁለትና ሶስት እጥፍ ነው ስለዚህ እውቅና አንዱ ሊሆን ይችላል ማለቴ እውቅና ካለ ያግዛል ግን ግድ አይደለም በተረፈ ዋናው ግን ልምድ “Experience” የሚባለው ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሁኑን ፕሬዚዳንት አቶ ግርማን እያቸው ልምዳቸው የትናየት እንደሆነ፡፡ በተለያየ ዘርፍ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ያስፈልጋል በተረፈ አገሪቱን እና ህዝቧን በደንብ ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም ኢትዮጵያ የህዝቡን ስነ - ልቦና የዝቅተኛውን ህብረተሰብ ኑሮ ማወቅ መረዳት ለአንድ መሪ ወሳኝ ነው እነዚህን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በዋናነነት የምትመሪውን ህዝብ ማወቅ አለብሽ ማወቅ ያለብሽ በከፊል ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ነው፡፡ ለሁሉም አባት ሆኖ ነው መሪ የሚመረጠው አንዱ ሀብታም ነው ሌላው ደሀ ነው ያልተማረነው የተማረነው የሚል የለም፡፡ ሁሉንም እኩል ማየት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ሁሉ የምነግርሽ የእኔ የራሴ የግሌን አስተያየት ነው፡፡
ካነሳሀቸው ሀሳት አንፃር አንተ እነዚህን ጉዳዮች አሟላለሁ ብለህ ታስባለህ በእውቅናስ ብቻ አገር ይመራል የሚል እምነት አለህ?
እሱማ እግር ነቃ ማለት ጭንቅላት ነቃ ማለት አይደለም ነገር ግን የተሻለ የብዙ አገር ልምድ አለኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ እውቅና ብቻ ሳይሆን በተዘዋወርኩባቸው በርካታ አገራት የተለያዩ ለአገር የሚበጁ ልምዶችን አካብቻለሁ መስፈርቶቹን ከሞላ ጐደል አሟላለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን ስንት አመትህ ነው
አርባ አመት ሞላኝ
እድሜም ለመሪነት ወሳኝ ነው አይደለም እንዴ?
በትክክል ወሳኝ ነው አሁን ስለፕሬዚዳንት “ስላወራን ነገ ዘልዬ ፕሬዚዳንት ልሆን አልችልም፡፡ አሁን ፕሬዚዳንት የተዘጋጀ ይመስለኛል ከመስከረም ጀምሮ በአዲስ ፕሬዚዳንት እንመራለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ፓርላማ እገባለሁ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ስድስት አመት ይመራሉ እስከዛ እኔ ፓርላማ እቆያለሁ እድሜዬም ያን ጊዜ ይታያል፡፡

 

Read 5780 times