Saturday, 03 August 2013 10:18

አንድነት፤ በአባላቱ ላይ እስርና እንግልት እየተፈፀመ መሆኑን ገለፀ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አመራሮችና አባላቱ ላይ በገዢው ፓርቲ የድብደባ፣ የእስርና የግል ሚስጥር መበርበርና በተደራጀ ሁኔታ የመዝረፍ ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑን ገለፀ፡፡
ፓርቲው “ህጋዊና ሠላማዊ ትግላችን በህገወጥ የአፈና ስልት ሊደናቀፍ አይችልም” በሚል ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ መንግስት አንድነት ፓርቲን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ከማጣጣልና ያለ አግባብ ከአክራሪነት ጋር ለማቆራኘት ከመስራት አልፎ ሠላማዊ ሠልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎቹ እንዲደናቀፉ አፈና እያደረገበት እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
በወላይት ሶዶና በመቀሌ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ላይ የመደብደብ፣ የማሰር፣ የግል ሚስጥር የመበርበርና በተደራጀ ሁኔታ የመዝረፍ ድርጊት እንደተፈፀመበት ጠቅሶ፣ ፖሊስ ድርጊቱን አይቶ እንዳላየ ማለፉን ገልጿል፡፡
ፓርቲው በነገው እለት በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በመቀሌ፣ በወላይታ፣ በባህርዳርና በአዲስ አበባ የሚያካሂዳቸውን ሠላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማደናቀፍ በገዢው ፓርቲ አፈናና ወከባ እየተፈፀመበት እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
አንድነት ህግን መሰረት አድርጐ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ በነገው ዕለት ሊካሄዱ የታሰቡት ሁሉም ሠላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት እንደሚከናወኑና ህጋዊ እርምጃው በህገወጥ አፈናው ምክንያት እንደማይቀለበስ በመጥቀስ፣ መላው አገሪቱ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የታፈነ ድምፁን እንዲያሰማ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Read 33791 times