Saturday, 03 August 2013 10:51

ያልነገርኩሽ ነገር

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(7 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
ሀሌሉያ ሚናን እንዳፈቀረው አፍቅሮ አያውቅም፤ ኧረ እሱ ጭራሽ አፍቅሮ አያውቅም፤ አሁን ግን የሚያስበው ስለ ፍቅር፣ የሚያነበው ስለ ፍቅር፣ የሚያደምጠው የፍቅር ሙዚቃ ነው፡፡ በየቀኑ ከሚሰማቸው የፍቅር ዘፈኖች የወደዳቸውን ሀረጎች ስንኞች እየፃፈ ለሚና ስልኳ ላይ ይልክላታል። የትኛውም ሀረግ፣ የትኛውም ስንኝ ግን እንደልቡ አልሆነለትም፣ ግን ዝም ከማለት ይሻላሉ ብሏል፡፡
ከሚልክላት እያንዳንዱ መልእክት ሥር እንዲህ የሚል ሀረግ ያክልበታል፡፡ “ግን ያልነገርኩሽ ነገር አለ፡፡”
“ከወደድኩሽ በላይ ወደድኩሽ መልሼ …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
“Truly, Deeply, Madly …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
መውደዴን ወድጄዋለሁ …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
“I love you eight days a week …”
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ…)
Said I love you but I lied, cause this is more than love I feel inside.
(ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ)
(ሀሌሉያ ከላይ የተጠቀሱትን ሀረጎች የወሰዳቸው፣ በቅደም ተከተል፡- ከጥላሁን ገሰሰ፣ ከሳቬጅ ጋርደን፣ ከዳዊት መለሰ፣ ከዘ ቢትልስ፣ ከቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ከማይክል ቦልተን የፍቅር ዘፈኖች ነው፡- ደራሲው፡፡)
ግን አንድ ያልነገርኩሽ ነገር አለ የሚለው ያልነገራት ነገር ኖሮ አይደለም፤ ሁሉን ነገር ነግሯታል፤ ግን ቢነግራት፣ ቢነግራት፣ አልጠግብ ያለው … እንደሚወዳት ነው፤ እና አንድም ቀን እንደሚወዳት ነግሯት የሚያውቅ አይመስለውም። ደውላ ወይ አግኝታው፡- “ምንድነው ያልነገርከኝ ነገር?” ብትለው “እንደምወድሽ ነዋ!” ይላታል፡፡
ኧረ እንደውም ጠይቃዋለች፡-
“ምንድነው ያልነገርከኝ ነገር?!” አለችው አንድ ቀን ቆጣ ብላ፡፡
“እንደምወድሽ ነግሬሽ አውቃለሁ እንዴ?” አለ የምሩን፡፡
“አስጠሊታ፤ ያልነገርከኝ ነገር ምንድነው?”
“ምንም ያልነገርኩሽ ነገር የለም፤ የደበቅኩሽ ምስጢር እንደምወድሽ ብቻ ነው፡፡”
አንድ ቀን፡-
“ከአሁን በኋላ የማንንም ሙዚቃ፣ የማንንም ግጥም እንድትጋብዘኝ አልፈልግም፣ ከአሁን በኋላ የምፈልገው የአንተ ቅንብር የሆነ ሙዚቃ፣ የአንተ ድርሰት የሆነ ግጥም፣ የአንተ ቅብ የሆነ የሥዕል ሥራ ነው፡፡”
“እሺ እስማማለሁ፤ ግን ለመጨረሻ ጊዜ የገብረክርስቶስን፣ አንድ ግጥም ልበልልሽ፡፡” እስከዛሬ የራሱን ገለፃ ተጠቅሞ ፍቅሩን ባለመግለፁ፣ እሷም ይህን አስተውላ በግልፅ በመናገሯ አፈረ፡፡
“ከዚህ በኋላ ያንተ ካልሆነ የሌላ የማንንም አልፈልግም፡፡”
“መልካም”
የሚወደውን የገብረክርስቶስ ደስታን “ለሚወዱት ምነው?” የሚለውን ግጥም አለላት፡፡
አንድ ቀን የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ሀሌሉያን አስጠራው፡፡
“ከፕሬዚዳንት ቢሮ አስቸኳይ ደብዳቤ መጥቶ ነበር”
“ምን የሚል?”
“የትምህርት እድል ነው፤ በሲኒየርነትህ እና ባለህ የትምህርት ዝግጅት ብትወዳደር የምታልፈው አንተ ነህ፤ ግን ደግሞ ሴቶች ይበረታታሉ ይላል ደብዳቤው፡፡” አለው፡፡
ወዲያውኑ የሆነ ነገር ብልጭ አለለት፤ ሀሌሉያ፡፡
“እኔ በቅርቡ የመማር ፍላጎት የለኝም፤ ለምን ሚናን አታናግራትም?” ድምጹ ውስጥ ጥያቄ ሳይሆን ትእዛዝ አለ፡፡
“እኔም የፈለኩህ ምን እንደምትል ልሰማህ ብዬ ነው”
“የኔን ሰምተሃል፤ ሚናን አናግራት” ትእዛዝ ነው አሁንም፡፡
የትምህርት እድሉን ሚና አገኘች፤ በስውዲን ሀገር ለአንድ አመት የሚዘልቅ በሰብአዊ መብት ህግ ላይ የሚሠጥ ስልጠና ነው፡፡ ሚና ስላገኘችው የትምህርት ዕድል ስትነግረው፤ ‘Congra’ አላት አቅፎ፡፡ የትምህርት እድሉን እሱ አሳልፎ እንደሰጣት አልነገራትም፡፡
ታህሳስ ሀያ ዘጠኝ ቀን የሚና የልደት ቀን ነው፡፡ ጥር አንድ ቀን ከባህር ዳር አዲስ አበባ፣ ጥር ሁለት ቀን ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ስቶክሆልም የምትበርበት ቀን ነው፡፡
ይህን ድርብ በአል ለማክበር ፓፒረስ ሆቴል ተቀጣጠሩ፡፡ ሚና የምትወደው ወይ የምታዘወትረው ጥግ ላይ ተቀመጡ፡፡ ሀሌሉያ ቀደም ብሎ ሁሉ ነገር እንዲዘጋጅ አዞ ነበር፤ ኬክ፣ ሻማ፣ ሻምፓኝ … ሁሉም ተዘጋጅቷል፡፡ ሚና ይህን ሁሉ ጠብቃለች፤ ኬክ፣ ሻማ፣ ሻምፓኝ … አለ፤ የምትወደው ሠውዬ ጥቁር ሙሉ ሱፍ፤ በነጭ ሸሚዝ ለብሷል፤ ለብሶላታል። አምሮበታል፤ ሚና ግን አንድ ነገር በጉጉት እየጠበቀች ነው፡፡ በዚህ ቀን ሰውዬው ምን አይነት ስጦታ እንደሚያበረክትላት ለማየት ጓጉታለች፡፡ እራሷን እስክትታዘብ፣ እስኪያስታውቅባት ድረስ ተቅበጠበጠች፡፡ ሀሌሉያ እጅ ላይ ደግሞ ምንም አይነት ለስጦታ የሚሆን ጥቅል አይታይም፡፡ ይበልጥ ተቅበጠበጠች፡፡ እሷ ለዚህቀ ድንቅ ሠው ዛሬ ልዩ ስጦታ አዘጋጅታለታለች፡፡ ቀይ ስጦታ፡፡
እሱስ? ያ አይደለ እንዴ ታዲያ ጥያቄው፡፡
“እወድሻለሁ” አላት፡፡
“ቀጣፊ፣ ውሸታም!”
“እንዴት እንደምወድሽ ታውቂያለሽ?” አላት እንዴት ነው የምትወደኝ? እንድትለው አማልክቶቹን እየተማፀነ፤ አማልክቶቹ ፀሎቱን ወዲያው ሠሙት፡፡
“እንዴት ነው የምትወደኝ?” አለችው ሚና። ተነስቶ ቆመ፣ ከኪሱ ወረቀት አወጣ፣ በእርጋታ ዘረጋው፡፡
“ክብርት ሆይ ይህ ግጥም ላንቺ በረከት ይሁን ብዬ እራሴ የፃፍኩት ነው”
የሚከተለውን ግጥም አነበበላት፡፡
እንዴት ነው የምወድሽ እንኳ?
እንደ አበቦቹ ሽታ፣
እንደ ቢራቢሮ እስክስታ፣
እንደ ጥርኝ ጭቃ፣
ልክ እንደ ስጦታ እቃ፣
እወድሻለሁ እኔ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ፍልስፍና ሃሳብ፣
ሊጠግብ እንዳለ ረሀብ፣
እንደ ህፃን ልጅ ሳቅ፣
እንደ ዘላለማዊ ሀቅ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ሎጂክ፣
እንደ ተፈጥሮ ህግ፣
እንደ ቋንቋ፣
ልክ እንደ ሙሉ ጨረቃ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ሙዚቃ ቅንጣት፣
እንደ አልጋ ውስጥ ትኩሳት፣
ልክ እንደ እናቴ ስም፣
እንደ ልጅነቴ ህልም፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ግጥም ስንኝ፣
አንጀሎ እንደጠረበው ቋጥኝ፣
እንደ ጠዋት እንቅልፍ፣
እንደ አየር ራንድ ፅሁፍ፣
እወድሻለሁኝ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
እንደ ብርቱካን ውሃ፣
እንደ ብርሃን ዘሃ፣
እጄ ላይ እንደያዝኩት ሲጋራ፣
እንደ ቀዝቃዛ ቢራ፣
እንደ ሊዮናርዶ ስራ፣
እወድሻለሁ እኔ፣ እወድሻለሁኝ፡፡
ፍቅሬ ሁሉን እንደ እርሺ
ይህን እንደ ብቻ ያዢ፤
አፈቅርሻለሁ ነፍሴ፣
ልክ እንደ እራሴ፡፡
ልክ አንብቦ እንደጨረሰ አካባቢያቸው በጭብጨባ ቀለጠ፤ ሁለቱም ደነገጡ፤ የምር ደነገጡ፡፡ ዙሪያቸውን ቢያዩ በቤቱ አስተናጋጆች እና በሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ተከበዋል፡፡
“አንድ ጊዜ …” አለ የፓፒረስ ሥራ አስኪያጅ፡- “አንድ ጊዜ፣ የሆቴሉ ሠራተኞች ስጦታ ስላዘጋጀንላችሁ እንድትቀበሉ በላቀ አክብሮት እንጠይቃለን” ድምፁ ውስጥ ፍቅር ነው ያለው፤ ድምፁ ውስጥ እና አኳኋኑ ውስጥ ቅርበት አለ፡፡
ብዙ ጊዜ ሚናን እና ሀሌሉያን የሚያስተናግደው ልጅ፣ ኬክ እና ብላክ ሌብል ውስኪ ከጎናቸው ያለው ጠረጴዛ ላይ አኖረ፡፡ ሀሌሉያ ያዘዘውን ኬክ ሚና እየተጨበጨበላት “Happy Birthday to Mina” እየተባለላት ቆረሰችው፡፡ የሆቴሉ ሠራተኞች ለሁለቱ ያበረከቱትን ኬክ ሀሌሉያ እንዲቆርስ ተጋበዘ፡፡ ከፈተው፡- “ለሚና እና ለቴታ፡- ከፓፒረስ” ይላል፤ ሀሌሉያ ግንባሩን ቅጭም አደረገ፤ ሊና አጠገቡ ናት፤ እሷም እሱን ተከትላ ቅንድቧን ቅጭም አደረገች፡፡
“ቴታ ምን ማለት ነው? ምንድነው?” አሉ ሀሌሉያ እና ሚና አንድ ላይ፡፡
“Tamed Tiger ማለት ነው፤ ያንተ ቅፅል ስም ነው” አለች ፊቷ፣ አንገቷ፣ እና እጆቿ በአረንጓዴ የደም ስሮች የተሞሉ፤ ቀጭን፣ ረዥም፣ ቆንጆ አስተናጋጅ፡፡ ስሙን እሷ እንዳወጣችለት ያስታውቅባታል፡፡
የሬይ ቻርለስ Hallelujah-I Love Her So የሚለው ዘፈን በሆቴሉ ማጫወቻ እየተጫወተ ሀሌሉያ ኬኩን ቆረሰ፡፡ የሬይ ቻርለስ ዘፈን ሲያልቅ የቢሊ ኦሽን Caribbean Queen ቀጠለ፡፡ የሚከተሉትን ስንኞች፡- “In the blink of an eye I knew her number and her name; yeah; She Said I was a Tiger She wanted to tame” ሲሰማ ፈገግ አለ፤ ሀሌሉያ፡፡ Tamed Tiger ያለችውን አስተናጋጅ በአይኑ ፈለጋት፤ አገኛት፤ እየሳቀች አየችው፤ በአይኗ ቀስ ብላ ሳመችው፤ አፈረ፡፡
አሪፍ ፌሽታ ሆነ፡፡
ለሁሉም ከብላክ ሌብሉ ከተቀዳ በኋላ ሀሌሉያ ውስኪውን ከነጠርሙሱ ያዘው፤ በጠርሙሱ ነበር የሚጠጣው፡፡ ሚና ሻምፓኙን ተያይዛዋለች፤ በየመሀሉ የሀሌሉያን ጠርሙስ እያነሳች ትጎነጫለች።
ሞቅታ፡፡
ሚና ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ደስታ ተሰምቷት አያውቅም፤ ከዚህ የሚልቅ ደስታም አለ ብላ አታስብም፤ ፍፅምና፣ ፅድቅ፣ ከፍታ፣ ልዕልና፣ … ይህ ሁሉ ነው የተሠማት፤ እና ለዚህ ሁሉ ደስታ መነሻ ለሆነው ለአቶ ቴታ፡- “እንዴት ደስ የሚል ቅፅል ስም ነው ግን? እኔንም እሱንም የሚያወድስ ስም ነው፤ እሱ ነብር ነው፤ የገራሁት ደግሞ እኔ፤ አይ መመፃደቅ አበዛሁ መሰለኝ፤ እኔ አይደለሁም ፍቅር ነው የገራው፣ እያለች አሰበች፡፡
ለሀሌሉያ፣ ለተገራው ነብር ስጦታ አዘጋጅታለታለች፤ ቀይ ስጦታ፡፡ ዛሬ አብረው ነው የሚያድሩት፤ አልተባባሉም፤ እንዲያ አልተባባሉም፤ አብረን እናድራለን አልተባባሉም፤ አብረው አድረው አያውቁም፤ ግን ዛሬ አብረው ያላደሩ መቼ ሊያድሩ ነው? ዛሬ አብራው ታድር እና ሲነጋ ሴት ሆና ትነቃለች፡፡ አሪፍ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ናት፡፡
እራት አልበሉም ነበር፣ ኬኩን ቀመሡ፣ መጠጡን አጣጣሙት፤ ሀሌሉያ ድሮም ቢሆን ምግብ ላይ ብዙ አይደለም፡፡
“እራት ልጋብዝህ፤ ሰመር ላንድ እንሂድ” አለችው፡፡
ሞቅ ብሎታል ቴታ፡፡
ለብቻው ሲያስብ እንዲህ እያለ ነበር፡- እራት? አዎ፤ እርቦኛል፤ ሰመርላንድ? ለምን እዚያ?
“እዚሁ እንብላ!” አላት ድምጽ አውጥቶ፡፡
“አይሆንም፤ ሰመርላንድ ፒዛቸውን ለጉድ ነው የምወድላቸው” አለችው፡፡
ውሸቷን ነው፣ ከአዲስ አበባ መጀመሪያ ባህር-ዳር ስትሄድ ያረፈችው ሠመርላንድ ነው፤ መኝታቸውን ወዳላቸዋለች፡፡
ዛሬም እዚያ ነው ማደር፡፡
ሰመር-ላንድ ሆቴል ሄደው እራታቸውን ፍቅራቸውን በጉርሻ እየገለፁ፣ በአይኖቻቸው አድናቆት እየተቀባበሉ በሉ፡፡
እሷ እንዲህ ስትል እያሰበች ነበር፣ “ምናለ፤ ባልጐ ባያውቅ ኖሮ?! ልክ እሱ ለኔ የመጀመሪያዬ እንደሆነው ሁሉ፣ እኔም ለሱ የመጀመሪያው ብሆን ኖሮ እንዴት ድንቅ ይሆን ነበር?! በስመአብ ግን ከስንቶቹ ጋር ተኝቷል? … ግን ይተኛ፣ ምርጥ ሰው ነው …”
እሱ በበኩሉ፡- “ቴታ ነው ያሉኝ? ይገርማል … ይህች ነብስ ነገር የሆነች ልጅ ናት የገራችኝ … ሲከታተሉኝ ነበር ማለት ነው? ይገርማል፤ ቴታ? … እኔ ደግሞ ይህቺን ብርሃን የሆነች ልጅ ፊኒክስ ብያታለሁ … እንደ እሷ አይነት በሺህ አመት አንዴ ነው የሚገኘው … ለዚያውም ፊኒክሶች አይወልዱም፤ አይወለዱም፤ እራሳቸውን ከራሳቸው ነው የሚፈጥሩት፤ ለዚያውም በሺህ አመት አንዴ … ሚና ፊኒክስ ናት … አፍቅሬ አላውቅም ነበር … ፍቅር ይሉት ነገር ግን ደስ የሚለው ነገር አለው … በተለይ ከእንደዚህች አይነቷ ጋር ሲሆን የፅድቅ ይሆናል … የዛሬ አመት ከስዊድን ስትመለስ አለምን በሚያነጋግር ሠርግ አገባታለሁ … እስከዚያ እጠብቃታለሁ … አቦ እስከዘላለም እጠብቃታለሁ …”
ግን ገላው ገላዋን ከጅሎ በረሃብ እየተቃጠለ ነው፤ እየነደደ፡፡
“እስከዛሬ ወሲብን አራክሼዋለሁ … አሁን ግን አልስገበገብም … ፈፅሞ አልስገበገብም … እጠብቃታለሁ … ስልጠናዋን ጨርሳ ከስቶኮሆልም ስትመለስ … የሠርግ ዳስ አስጥዬ ነው የምጠብቃት … ከዚያ ብር አምባር ሰበረለዎ፤ ሆሆ ጀግናው ልጅዎ … ይባልልናል … አንድ አመት በጣም ቅርብ ነው፣ እጠብቃታለሁ …”
ግን አሁንም ገላው ገላዋን ከጅሎ በረሃብ እየተቃጠለ ነው፤ እየነደደ፡፡
ሚና በበኩሏ በደስታና በፍርሃት ተውጣለች፡- “…የመጀመሪያው ቀን እንዴት ይሆን?... እንዴትም ይሁን … ሀይለኛ ደስታ ሳይኖረው አይቀርም … ደሞ እኮ ልጁ ሀሌሉያ ነው…”
ሳትነግርው ተነስታ ወደ ሆቴሎ እንግዳ መቀበያ ሄደች፤ አልጋ ተከራየች፤ በመጀመሪያ ባህር-ዳር ስትመጣ ያረፈችበትን ክፍል ነው የተከራየችው፤ ክፍል ቁጥር 113፡፡
ሀሌሉያ የሠውነቱን ረሃብ ስላልቻለ አንድ መላ ዘየደ፤ ወደ ቤቱ መሄድ፤ ሄደ፡፡ ወደ ቤቱ እየተንገዳገደ ሲሄድ በቀስታ እንዲህ እያለ እየዘፈነ ነበር፡-
“… ብር አምባር ሰበረልዎ፣
ብር አምባር ሠበርልዎ
ሆሆ ጀግናው ልጅዎ፤
አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ
ሆሆ! እቴ ሸንኮሬ …”
እዚህ ጋ በሀሳቡ ቆም አለ፡- “…አሃ! አሃ! በመጀመሪያ በሠርግ ያገባችው ድንግል ሙሽራ የወይዘሮ ሸንኮሬ ልጅ ነበረች ማለት ነው …?” ከት ብሎ ሳቀ፡፡ “ይኸው የወይዘሮ ሸንኮሬ ስም እስከዛሬ ሲጠራ ይኖራል፤ የወይዘሮ ሸንኮሬ ልጅ ስሟ ማን ነበር ይሆን…? ሚና እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ…”
እንዲህ እያለ ቤቱ ደረሠ፡፡ ቤቱ እንደደረሰ ጫማውን ብቻ አውልቆ አልጋው ላይ ተዘረረ፤ ወዲያውኑ እንቅልፍ አቀፈው፡፡
ሚና ስትመለስ ሀሌሉያ የለም፤ መታጠቢያ ቤት ሄዶ ይሆናል ብላ ጠረጠረች፣ ብትጠብቅም አይመጣም፡፡ ስልኩ ላይ ደወለች፤ ዝግ ነው፡፡
ጥግ ላይ ቆሞ አትኩሮ የሚመለከታትን አስተናጋጅ ጠራችው፡፡
“እሱስ?!” አለችው፤ ሀሌሉያ ተቀምጦበት የነበረውን ወንበር እየጠቆመች፡፡
“ሄዷል፤ ሂሳብ ከፍሎ ሄዷል” አነጋገሩ ሀሌሉያን በደንብ እንደሚያውቀው ያስታውቃል፡፡
አላመነችም፡፡ ካለማመኗ እና ግራ ከመጋባቷ የተነሳ፡- “እስኪ!” ብላ እጇን ዘረጋች፤ ለአስተጋናጁ እንዲምልላት፡፡
እጇን ግጥም አድርጐ መታት፤ አመታቱ ያማል።
ስልኩ ላይ ደግማ ደወለች፤ ዝግ ነው፡፡ ዝግ መሆኑን እያወቀች ደጋግማ ደወለች፡፡ ዝግ ነው!
ሀሌሉያ ትቶት የሄደውን ውስኪ ከነጠርሙሱ አንስታ አንደቀደቀችው፤ ጠርሙሱ በትንፋሿ ድምፅ እስኪጮህ ድረስ አንጠፈጠፈችው፡፡ አስተናጋጁ በቅርብ እርቀት አለ፤ በምልክት ጠራችው፤ ተጠጋት፤ በእጇ ያለውን ቁልፍ አቀበለችው፤ የቁልፉ ማንጠልጠያ 113 ይላል፡፡
በጥያቄ ዓይን አያት፡፡
“ውሰደኝ” አለችው፡፡ ደጋግፎ አነሳት፡፡ ሠክራለች፤ ሚዛኗን ጠብቃ መቆምም መራመድም አልቻለችም፡፡ ግማሽ አቅፎ፤ ግማሽ ደግፎ ወሰዳት - ወደ 113 ቁጥር፡፡ በአንድ እጁ እሷን ደግፎ በሌላ እጁ የመኝታ ክፍሉን ቁልፉ ከፈተው፡፡
ይዟት ገባ፡፡
ውስጥ ሲገቡ ከእቅፉ ተላቃ እንደምንም ብላ እራሷን ችላ ቆመች፤ ቆሞ ያያታል፡፡
“በሩን ዝጋው”
ዘጋው፡፡
“አታፍጥብኝ፤ ና ዚፔን ክፈትልኝ”
ከማጅራቱ እስከ ወገቧ ያለውን የቀሚሷን ዚፕ ከፈተው፤ እጆቿን ከቀሚሷ ስታወጣ፣ ቀሚሷ መሬት ወደቀ፤ ቀይ ቀሚስ፡፡
ወደ አስተናጋጁ ዞረች፤ ጡቶቿ፤ እዚህ ጋ አንድ የሀገሬ ፀሐፊ ያለውን መዋስ ግድ ነው፤ “ጡቶቿ የመዳይ ክዳን ይመስላሉ”
አስተናጋጁ አፈጠጠባቸው፡፡
“ያዛቸው!” አለችው ሚና፡፡
በቀስታ ያዛቸው፡፡
“በደንብ ያዛቸው”
ጨመቃቸው፡፡
ከዚያ ከንፈር፣ ትንፋሽ፣ ምራቅ፣ ሙቀት፣ ላብ፣ ብርሃን፣ ቃጠሎ፣ ሲቃ፣ ፀጉር፣ ገላ፣ ትኩስ ገላ፣ የሚሞቅ ነገር … ሙቀት፣ ሙቀት ላብ፣ … እሳተ ገሞራ፣ ህመም፣ ደም … ፍሬ፣ እንቁላል፣ ዘር …
ድካም፡፡
እንቅልፍ፡፡
ተፈፀመ፡፡

Read 7750 times