Saturday, 03 August 2013 11:03

“…የወንዶች መካንነት…”

Written by 
Rate this item
(30 votes)

ቀደም ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለዘር መካንነት የሚበቁ ወንዶች ችግር ከአእምሮ ጋር የተገናኘ መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን በቅርብ የወጡት ደግሞ 90% የሚሆኑት ምክንያቶች የተፈጥሮ ወይንም አካላዊ ችግሮች መሆናቸውን ይገልጻሉ ፡፡ ቢሆንም ግን ከአካላዊ ችግር የተነሳ መውለድ ያቃታቸውም ቢሆኑ ሁኔታው በመከሰቱ እራሳቸውን ዝቅ አድርገው መመልከት፣ መበሳጨት፣ እራስን እንደጥፋተኛ የመቁጠር ሁኔታዎች ስለሚታይባቸው የአእምሮ ወይንም የአስተሳሰብ ችግርም ይገጥማቸዋል፡፡ ወንዶች ለመካንነት ያላቸው ድርሻ ምን ያህል ነው? የሚለውን በዚህ እትም ለንባብ ያልን ሲሆን ማብራሪያውን የሚሰጡት ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ትምህርት ቤትጥቁር አንበሳ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህር ናቸው።
ጥ/ መካንነት እንዴት ይገለጻል?
መ/ መካንነት ማለት ጥንዶች ለአንድ አመት ያህል አብረው እየኖሩ ነገር ግን ሴቲቱ ልጅ ማርገዝ ካልቻለች የመካንት ችግር አለ ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ይህ አገላለጽ የሚጠቅመው ጥንዶች አብረው እየኖሩ ልጅ መውለድ አልቻልንም ብለው ምክንያቱን ሊያስቡና ወደሕክምና ሄደውም መፍትሄውን መጠየቅ የሚችሉበትን ጊዜ ለመጠቆም እንዲረዳ ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን ጊዜ በእድሜ ልዩነት ከፋፍሎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ተጋቢዎቹ ወጣት ከሆኑ እስከ አንድ አመት ሁኔታውን በትእግስት መከታተል ሲገባ ነገር ግን ሴቲቱ ከ35/አመት በላይ ከሆነች እስከአንድ አመትም መታገስ ሳያስፈልግ ቀደም ብሎ መከታተል ይገባል፡፡
ጥ/ ለመካንነት የወንዶች ድርሻ ምን ያህል ነው?
መ/ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጥንዶች ልጅ መውለድ ካልቻሉ መካን የሆነችው ሴትዋ ነች እንጂ የወንድ መካን የለም ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአለው የሳይንስ እድገት እንደተረጋገጠው ከሆነ በጥንዶች መካከል ለመካንነት የወንዶች ተሰትፎ ወደ 20% ይሆናል፡፡ በእርግጥ በሴትዋም በወንዱም በኩል ልጅ ያለማግኘት ችግር ሲከሰት ለምክንያትነቱ ከ20-40% ያህል ወንዶች ናቸው።
ጥ/ ለወንዶች መካንነት ምክንያቱ ምንድነው?
መ/ ወንዶች መካን ሆኑ ሲባል በአራት ሊከፈል ይችላል፡፡
በጭንቅላት አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች (1-2%)
ፒቱታሪ ግላንድ ላይ ስራቸውን የሚሰሩ ሆርሞኖች ማነስ ፣የፒቱታሪ ግላንድ እጢዎች መኖር ፣በተለያዩ ሕመሞች ምክንያት የሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች ፣በተለያዩ ምክንያቶች በጭንቅላት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች፣ እንደ ቲቢ ፣የስኩዋር በሽታ ያሉ አድካሚ በሽታዎች ፣መነንጃይትስ የመሳሰሉ ለኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ሕመሞች፣ ከመጠን በላይ ውፍረት መካንነትን በወንዶች ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡
በዘር ፍሬ ማምረቻ Testis ላይ የሚፈጠር ችግር (30-40%)
የዘር ማመንጫ ወይንም ማስቋሽቋ የሚ ባለው የሰውነት ክፍል በትክክለኛው አፈጣጠር 46/ ክሮሞዞም ሊኖረው ሲገባ ነገር ግን አንድ ተጨማሪ ማለትም 47/ክሮሞዞም ቢኖራቸው ሙሉ በሙሉ መካን ያደርጋል፡፡
ወንድ ሲፈጠር የዘር ማመንጫው የሚገኘው በሆድ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደ ትክክለኛው ቦታው የሚመጣ ይሆናል፡፡ ልጁ ከተወለደ ከአንድ አመት በላይ የዘር ማመንጫው በተፈጠረበት ሆድ እቃ ውስጥ ከቆየ የመካንነት ችግር ሊያጋጥም ይችላልዶ/ር እስክንድር ከበደ ከመካንነት ባለፈም የካንሰር ችግርም ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስለዚህም በጊዜው በኦፕራ ሲዮን መስተካከል ይገባዋል፡፡
የደም መልስ ቡዋንቡዋዎች መስፋት የወንድ ዘርፍሬ ማመንጫ አካባቢ ሙቀት በመፍጠር ትክክለኛ የሆነ የስፐርም አፈጣጠር ሂደት እንዳይኖር ያደርጋል። ጆሮ ደግፍ የሚባል በሽታ ወንዶ በእድሜያቸው ከጉርምስና በሁዋላ ሲደርሱ ከታመሙ ወደ 25% የሚሆኑት የዘር ማመንጫ ፍሬውን ስለሚጎዱ መካንነትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአብዛኛው ግን ጆሮ ደግፍ በሽታ በልጅነት ስለሚይዝ ለዚህ ችግር ብዙዎችን አይዳርግም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስጋ ደዌ በሽታ በልጅነት እድሜ ከያዘ እንዲሁም ቲቢ የተባለው በሽታ በጊዜው ካልታከመ ለወንዶች የመካንነት ችግርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለካንሰር የሚወሰዱ መድሀኒቶች፣ የጨረር ሕክምና በዘር ፍሬ ማምረቻው ከተወሰነ መጠን በላይ ካረፈ የዘር ፍሬውን ስለሚያበላሽ መካን ያደርጋል፡፡ የኩላሊት ወይንም የጉበት በሽታ እንዲሁም ካንሰር ከመጨረሻው ደረጃ ላይ ከደረሱ የወንድ የዘር ፍሬ ውጤታማ እንዳይሆን ስለሚያደርጉ መካንትን ያስከትላሉ፡፡
ስፐርም ከተመረተ በሁዋላ ወደውጭ እንዲፈስ ባለው አካሄድ መስመሩ ወይንም
መጉዋጉዋዣው ሲዘጋ (20-30%)
እስፐርም ከተመረተ በሁዋላ ወደሴቷ እንቁላል በመጉዋዝ ልጅ እንዲመረት የሚያደ ርገው መስመር በተለምዶው የትራንስፖርት መስመር ይባላል። ይህ መስመር ማለትም የዘር ማስተላለፊያው ቱቦ በኢንፌክሽን ወይንም ቀደም ብሎ ባጋጠመ እንደ ጨብጥ ባሉ በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት መስመሩ ከተዘጋ አለዚያም በተፈጥሮ ምክንያት ቱቦው እስከጭርሱንም ላይፈጠር ስለሚችል እንደ አንድ ችግር ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡
ምክንያቱ የማይታወቅ (ከ40-50%)
በተለያዩ የአኑዋኑዋር ሁኔታዎች ማለትም ሲጋራ ማጨስ፣ የአደንዛዥ እጾችን መውሰድ፣ አልኮሆል በከፍተኛ ሁኔታ መውሰድ፣ ከባድና ተከታታይ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በጣም ጠባብ የሆነ የውስጥ ሱሪ መልበስ፣ የአካባቢ አየርን መበከል ለሚችሉ መርዛማ ኬሚካሎች መጋለጥ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ከፍተኛ ጭንቀት ...ወዘተ አንድን ወንድ ለመካንነት ሊዳርጉ ከሚችሉ መካከል ናቸው፡፡
ጥ/ ሕክምና አለው?
መ/ ሕክምና አለው፡፡ ሕክምና ሲባል ግን መጀመሪያ ጥንዶቹ መካንነትን ለማረጋገጥ በጋራ
ከሐኪሙ ጋ ሲቀርቡ የሚጀመር ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ጥንዶች ልጅ ማግኘት ካልቻሉ ተፈጥሮአዊውም ይሁን ሰው ሰራሹ ችግሩ ከሴትዋ ይሆናል የሚል ግምት በመያዝ ወንዶቹ ሐኪም ጋ አይቀርቡም፡፡ ሴቶቹ ብቻ ምርመራ በማድረጋቸው የሚገኘው ውጤት አመርቂ አይሆንም፡፡ ስለሆነም ጥንዶች በጋር ምርመራ ሲጀምሩ መጀመሪያ ዝርዝር የሆነውን ታሪካቸውን በመውሰድ በተለይም ወንዶቹን በሚመለከት፡-
የዘርፍሬው አፈጣጠር እና ያሉበት ቦታ ትክክለኛ ነው አይደለም ?
ቫሪኮስ የሚባለው ማለትም የደም ስሮቹ የመስፋት ሁኔታ ይታይባቸዋል ወይ?
ቱቦው በትክክል ተፈጥሮአል ወይ?
ሰውየው ትክክለኛ የሆነ ወሲባዊ እንቅስቃሴ አለው የለውም? ...ወዘተ
ከላይ የተመለከቱት ጥያቄዎች ባካተተ ሁኔታ በምርመራ ከተረጋገጠ በሁዋላ ፈሳሹ ተወስዶ ምርመራው ይቀጥላል፡፡ በዚህም ከወንዱ የሚወጣው ዘር መጠን ትክክለኛነት እንዲሁም አሲድ አለው የለውም? ቅጥነቱ ፣ውፍረቱ ፣የስፐርም ቁጥሩ እንዲሁም በአንድ ጊዜ በሚወጣው ፈሳሽ ውስጥ ምን ያህል ስፐርም አለ? እንቅስቃሴያቸውና አፈጣጠራቸው ትክክል ነው ወይ? የሚለው ባጣቃላይም የአለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ታይቶ ጥሩ ውጤት ካለው ወንድየው የመካንነት ችግር እንደሌለበት ምስክርነት ሊሰጠው ይችላል፡፡ ነገር ግን ውጤቱ ጥሩ ካልሆነ ምርመራው በአንድ ጊዜ አጋጣሚ የተደረገ በመሆኑና ምናልባትም ለቀጣይ የሚሻሻልበት ሁኔታ ስለሚኖር እንደገና ከአንድ ወር በሁዋላ ለምርመራ ይቀጠራል፡፡ ይህ ሁሉ ምርመራ ከተደረገ በሁዋላ እንደሁኔታው በህክምና የሚድንም የማይድንም ይኖራል፡፡

Read 22129 times