Saturday, 10 August 2013 10:33

ለካ ሞት ግጥም አይችልም!!

Written by 
Rate this item
(34 votes)

እንደመግቢያ
ክፍት የሥራ ቦታ
ግጥም ፅፌ ፅፌ፣
አላነብም ብሎ ሰዉ ቢያስቸግረኝ
“ክፍት የሥራ ቦታ”፣ የሚል ከባድ ርዕስ-ያለው ግጥም ፃፍኩኝ!
ማ ጮክ በል አለኝ?... ተሻማ ህዝብ ሁሉ፣ግጥሜን ገዛልኝ!
በየቤቱ ሄዶ-ተስገብግቦ ጠግቦ፣ ዋለበት ቢመቸው-
ሦስቴ አራቴ፣ አምስቴ፤ ደጋግሞ አነበበው-
ግጥሙ እንዲህ አለቀ፡-
“ውድ አንባቢዬ ሆይ በቢሮ፣ በቤትህ፣ በፍራሽ ላይ ያለህ
መንግስት ያላየውን፣ ውለታ ዋልኩልህ፡፡
ምሁር ያልተካነው፣ ትምህርት አስተማርኩህ፡፡
ትግል ያልፈታውን፣ ቅን መላ ሰጠሁህ፡፡
ይህን በማንበብህ፣ የሥራ-አጥ ቁጥር፣ በጦቢያ ቀነሰ
ቢያንስ የዛሬውን ቀን፣ ስራ በማግኘትህ የልብህ ደረሰ!!
ግጥሜም ስራ አገኘ የአንጀት አደረሰ
እኔም ስራ አገኘሁ ምኞቴ ታደሰ!!
የዕድሜ ሙሉ መክሊት፣ ለዛ ነው አስቤዛ
እንዲህ ያለው ስራ በዋዛ አይገዛ!!

ውለሃል በል አንጋ
ፌዝ አይደለም ቅኔው፣የስራ ፍለጋ
ስራ ስትፈልግ ብቅ በል እኔጋ!...
ልምድ ይኑር አይኑርህ
አበባም ሁን ቀጋ
ወለላም ሁን ፉንጋ
ደማም ሁን ጠሟጋ፤
ወጣት ሆይ ነብር ጣት! ልክ እንደተመረቅክ፣ ብቅ በል ግጥም ጋ!!
ማስታወቂያ መስሎት ይህን ግጥሜን ሰምቶ
“ስራ እፈልጋለሁ” ብሎ ተሟሙቶ
ሞት መምጣቱን ሰማሁ እሱም ስራ ሽቶ!....
(ለዓለም ባንክ እና ለስራ - አጡ ወጣት እንዲሁም ለፀጋዬ ገ/መድህን
ሐምሌ 2005ዓ.ም
ለካ ሞት ግጥም አይችልም
ሰሞኑን፣
ሞትን መንገድ ላይ አየሁት፡፡
አለባበሱ ገረመኝ፡፡
ዥጉርጉር ቲ-ሸርት አድርጓል
ከታች ራንግለር ለብሷል!
አሃ?!
እሱም ፋሽን ይከተላል? ፍንዳታ መሆን ያምረዋል?
ያው እቲ-ሸርቱም ላይኮ፣ ከፊቱም ገፅ፣ ከኋላውም፤
መፈክር መሳይ ተፅፏል፡፡
ከፊት ለፊቱ በኩል፣ long live death ይላል
“ሞት ለዘላለም ይኑር”
ከጀርባው follow me ይላል “ተከተይኝ” ስለፍቅር!
ወይ ጉድ፤ ይሄስ ሞት ይገርማል!
ይሄ ጅል የጅል ቆንሲል
እሱም ህይወት ይፈልጋል?
ፍቅረኛ ማግኘት ያምረዋል?
ሞት፤የብርሃን ባላንጣ፣ ፀሀይ ይፈራል መሰል
ጥቁር ዣንጥላ ዘርግቷል፡፡
በእጁ ደሞ እንደወጉ፣ ደብተርና እርሳስ ይዟል!
እኔ፤ ገጣሚው ልቅሶ ቤት፤ ልቤን ላነባ ስገባ
ሞትም ተከትሎኝ ገባ፡፡
እኔ ወዲህ ማዶ ቆምኩኝ
እሱ ወዲያ ማዶ ቆመ
ከማህል ገጣሚው አለ
የፊደል አርበኛ አደለ? አስከሬኑ ጃኖ ለብሷል
ገጣሚ ማለት ፈሣሽ፣ ስደተኛ ወንዝ አደለ?-
ወንዝ አለት እንደሚንተራስ፣ ብረት ሳጥን ተንተርሷል፡፡
ሞትን ከገጣሚው ማዶ፣ በስሱ አሻግሬ እያየሁ፣
“ለምን መጣህ?” ብዬ ብለው
ሞት ፈጣጤ አፍ-አውጥቶ
“ግጥም ልማር!” አለኝ ኮርቶ፡፡
ይሄኔ ገጣሚው ነቃ!
አስክሬኑ ተግ አለና
ብድግ አለ ከተኛበት!
ሞትን በደም ዐይኑ አየና
“ሀጠራው!” አለ
‘ሞት ለዘላለም ይኑር!’
የሚል ሸቃባ መፈክር
እርኩስ ደረትህ ላይ ፅፈህ
ግጥም መማር ታስባለህ?
ግጥም የህያው ልሣን ነው፣ ለሞት አንደበት አይሆንም፡፡
የስንኝ ጠበል እሚፈልቅ፣ በድን አለት ውስጥ አደለም፡፡
ግጥም ከነብስ ቃል እንጂ፣ ከሥጋ ትንፋሽ አይነጥብም፡፡
አንዳች ህይወት ውስጥህ ሳይኖር፣ ፊደል በመቁጠር አትገጥምም!!
አንተ ግንዝ ነህ ግዑዝ!
ጥላ የነብስ ባላንጣ
ዛሬ ደግሞ ብለህ ብለህ፣ ግጥም ልትማር ትመጣ?
ሀጠራው! ዐይን - አውጣ! ውጣ!”
ይህን ሰምቶ መልስ ሲያጣ
ሞት የሚባለው ፈጣጣ
ጭራውን ሸጉቦ ወጣ፡፡

ወይ ጉድ!
ስንቴ በኛ ቂም አርግዞ
ስንቱን ባለቅኔ ወስዶ፣ ስንቱን ቅኔ አግዞ አግዞ፤
“ግጥም ልማር መጣሁ” ይበል? ይሄ ሞት እሚባል ፉዞ
ያውም ከማይጨበጠው፣ ከእሳት አበባው ወዳጄ
ከንጋት ግጥም አዋጄ
ከሞት - ገዳዩ ቀኝ እጄ?
ግን፤
ምን ደስ አለህ አትሉኝም?
ለካ ሞት ግጥም አይችልም
ለካ ሞት ቅኔ አይገባውም!!
የካቲት 27/1998
(ለወዳጄ ለፀጋዬ ገ/መድህን እና ለጥበብ ለቀስተኞች)
/የጋሽ ፀጋዬ አስከሬን ከአሜሪካ መጥቶ፤ ቤቱ ሄጄ በተሰማኝ ስሜት መነሻነት የተፃፈ/ ብሔራዊ ቴያትር በፖለቲካ የግጥም ምሽት ላይ በነሐሴ ልደታ የተነበበ/

Read 18234 times