Saturday, 10 August 2013 11:47

“…Still birth … ጠፍተው የሚወለዱ …”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(8 votes)

“… እኔና ባለቤቴ የልጅ ያለህ ስንል ነበር ብዙ ጊዜ ቆይተናል፡፡ ተስፋ ቆርጠን በተቀመጥንበት ጋብቻ በፈጸምን በሰባት አመት እርግዝና መጣ፡፡ በጣም ተደሰትን፡፡ ሕክምናውንም በወጉ በሰአቱ ጀመርን፡፡ ባለቤቴ ዘጠኝ ወር ሙሉ ሕክምናዋን ስትከታተል እኔም አብሬያት እየሄድኩ ስለነበር የምርመራውን ውጤት ተከታትያለሁ፡፡ እርግዝናው ልክ ዘጠኝ ወር ከአንድ ሳምንት ሲሆነው ግን ችግር ተፈጠረ፡፡ በድንገት ታማለችና ወደቤት ድረስ ተባልኩኝ፡፡ እኔም በፍጥነት ከቤት ደርሼ ወደ ሆስፒታል ወሰድኩዋት። እንደደረስን የጽንሱ የልብ ምት ቆሞአል የሚል መልስ ነበር ከሐኪሙ የተነገረን፡፡ ምክንያቱስ? አልኩኝ፡፡ እኛም ምክንያቱን ለጊዜው አናውቅም...የሚል ነበር መልሳቸው። ባለቤቴ ሙሉ ምርመራ አደረገች፡፡ ምንም የጤና ችግር አልታየባትም፡፡ ነገር ግን ሊወለድ ሲጠበቅ ልጃችን በድንገት ሳይወለድ ጠፋ፡፡ ደግሞም ወንድ ነበር ፡፡ እኔም ባለቤቴም በጣም ነው ያዘንነው፡፡ በእርግጥ ሰዎች የሚያያድገውን ይስጣችሁ እያሉ ይመርቁናል፡፡ እኛ ግን በድጋሚ እርግዝናው እንዳይከሰት ፈራን …”
ቴዎድሮስ መልካሙ/ከለቡ/
ተሳታፊያችን እንዳቀረቡት ሀሳብ አንዳንድ ቤተሰቦች በተለያየ ምክንያት በእርግዝና ላይ ያለ ልጃቸውን ገና ሳይወለድ ያጣሉ፡፡ ሕጻናት ገና ሳይወለዱ የሚሞቱበት (still birth) ምክንያት ምንድነው? ስንል ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡን ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ የጽንስና ማኅጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ብርሀኑ ሰንደቅ በአሁኑ ወቅት በመስራት ላይ የሚገኙት በማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ነው፡፡
ጥ/ ያልተወለዱ ልጆች (still birth) ህይወት የሚያጡበት ምክንያት ምንድን ነው ?
መ/ still birth እድሜው በየሀገራቱ የተለያየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከ28/ሳምንት በላይ ያሉት ሳይወለዱ እንደሞቱ የሚቆጠር ሲሆን ከዚያ በታች ግን ጽንሱ እንደተቋረጠ እንጂ እንደሞት አይቆጠርም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አገሮች እስከ ሀያ ሳምንት አንዳንዶች እስከ አስራ ስድስት ሳምንት ዝቅ ይላሉ፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የሚገልጸው ግን ከሀያ ስምንት ሳምንት ጀምሮ እና በክብደትም ከ500/አምስት መቶ ግራም በላይ ሆነው የጠፉትን still birth ይላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከሀያ ስምንት ሳምንት በላይ እና በኪሎዋቸውም ከአንድ ኪሎ በላይ ከሆኑ እንደ still birth ወይንም ጠፍተው እንደተወለዱ ይቆጠራል፡፡
ጥ/ still birth ወይንም ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ምን ያህል ያጋጥማል?
መ/ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ3.2/ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ጠፍተው ይወለዳሉ፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ እንደዚህ ጥርት ብሎ የሚታወቅ የጥናት ውጤት ባይኖርም በታዳጊ አገሮች ግን በአምስት እጥፍ ከአደጉት ይበልጥ ችግሩ ይከሰታል፡፡ የዚህ ልዩነት ምክንያት ደግሞ የክኖሎጂው እድገት ያለመኖር፣ የክሮሞዞም ጥናት ማካሄድ አለመቻል፣ አልትራሳውንድ ቀኝም ግራም አለመኖር፣ የእርግዝን ክትትል በአግባቡ አለመኖር፣ በምጥ ሰአት በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም አለመምጣት፣ ጽንሱ በሆድ ውስጥ እንዲጠፋ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ናቸው፡፡ ስለዚህም በታዳጊ አገሮች ያለው የልጆች ሳይወለዱ መጥፋት ችግር ከአደጉት ጋር ሲነጻጸር በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በኢትዮጵያም ቀላል ችግር እንዳልሆነ ይመታል፡፡ ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ከምጥ በፊት እና በምጥ ሰአት የሚሞቱት ሲሆኑ ነገር ግን ከተወለዱ በሁዋላ የሚሞቱት የጨቅላዎች ሞት ከሚባለው የሚካተት ነው፡፡
ጥ/ still birth ወይንም ጠፍቶ ለመወለድ ምክንያቶቹ ምንድናቸው?
መ/ ከ25-45 % ድረስ ያለው ምክንያት ከጽንሱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ጽንስ ከሀያ ስምንት ሳምንት በሁዋላ ሳይወለድ እንዲጠፋ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል የክሮሞዞም ችግር አንዱ ነው፡፡ ይህ ችግር ያለባቸው ከማህጸን ወጥተውም መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ይታያል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የክሮሞዞም ችግር ሳይኖርባቸውም አካላዊ ጉድለት ሊኖር ይችላል፡፡ የህብለሰረሰር ክፍት መሆን ፣ጭንቅላትን ውሀ መሙላት፣ ጭንቅላት አለመሰራት የመሳሰሉት ጉድለቶች ካሉ ሚወለዱም መኖር አይችሉም፡፡
እንደቂጥኝ በመሳሰሉ በሽታዎች ምክንያት ኢንፌክሽን ሊከሰት ስለሚችል ልጆች ሳይወለዱ ሊጠፉ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች መካከል ነው፡፡
ሌላው ከእንግዴ ልጅ እና እትብት ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል ችግር ሲሆን በእርግጥ ከእናትየው ወይንም ከጽንሱ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሊሆን ይችላል፡፡
የእንግዴ ልጅ ከተፈጠረበት ቦታ ያለጊዜው መላቀቅ እንደችግር ከሚቆጠሩ መካከል ነው፡፡ ይህም እናትየው የደም ግፊት ካለባት፣ በሆዳቸው ላይ የተለያየ አደጋ መውደቅ...የመኪና አደጋ..ድብደባ ...ወዘተ ከተከሰተ ጽንሱ ከእናትየው ሊያገኘው የሚችለው ምግብ እና አየር በሙሉ ስለሚቋረጥ ሊጠፋ ይችላል፡፡
የጽንስ መቀጨጭ በሚከሰትበት ጊዜም የእንግዴ ልጁ የሚሰራቸው አገልግሎቶች ማለትም ከእናት ወደልጅ ምግብ፣ ኦክሲጅንና ሌሎችም ፍላጎቶች በደንብ እንዳይተላለፉ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
እትብት አንገት ወይንም እግር ላይ በሚጠመጠምት ጊዜ የጽንሱ ሕይወት ሊቋረጥ ይችላል፡፡
ከእናትየው ጋር በተያያዘ፡-
በእድሜ ዘግይቶ ማርገዝ ወይም ከልክ በላይ የሆነ ውፍረት ፣የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ ልጆች ጠፍተው እንዲወለዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እድሜ በጨመረ ቁጥር የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ እንዲሁም የክሮሞዞም ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከልክ በላይ የሆነ ውፍረትም እንደዚሁ የደም ግፊት እና ስኩዋር በሽታ ሊያስከትል ይችላል፡፡
ምንም ምክንያት የሌላቸው፡-
ጠፍተው ከሚወለዱ ልጆች 1/4 እሩብ ያክሉ በዚህ ምክንያት ሊባል የሚችል ምክንያት የሌላቸው ናቸው። እነዚህ ከጽንሱ ወይንም ከእንግዴ ልጁና ከእትብቱ አሊያም ከእናትየው ጋር በተያያዘ የሚጠቀስ ችግር ሳይኖር ምክንያታቸው ሳይታወቅ የሚጠፉ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር በአደጉትና እንደእኛ ባሉ ሀገሮች ሲታይ ልዩነት ይኖረ ዋል፡፡ እሩብ ያህል ጠፍተው የሚወለዱ ልጆች ምክንያታቸው አይታወቅም ሲባል በአደጉ ሀገራት የምርመራው ክኖሎጂ በተሟላበት የሚታወቅ ሲሆን እንደእኛ በአሉ ሀገራት ግን በግልጽ ምክንያቱ ይህ ነው ብሎ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ምናልባትም እስከ 60% ያህሉ ምክንያታቸው ያልታወቀ ተብለው ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡
ጥ/ ጽንሱን ያረገዘችው እናት የአኑዋኑዋር ሁኔታ እንደችግር የሚታይበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?
መ/ እርግጥ ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ጎልተው የሚታዩ በመሆናቸው እንጂ እነሱ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌም ጽንሱ ሊቀጭጭ ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ እናትየው የእጽ ተጠቃሚ መሆን ወይንም ሲጋራ ማጤስ የመሳሰሉት ሲሆን ይህም የምግብ ፍላጎትን የሚቀንስ ነው ፡፡ አደንዛዥ እጾች በደም ዝውውር ላይም የሚያመጡት ተጽእኖ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት የእንግዴ ልጁ ከእናትየው ወደልጁ የሚያስተላልፈውን ማንኛውንም ጠቃሚ ነገር እንዳይፈጽም አጋጣሚውን ስለሚፈጥር ጽንሱ እንዲቀጭጭና ህይወቱን እንዲያጣ የሚያስችልበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በስራ አጋጣሚ ሊያጋጥም የሚችል ጎጂ የሆነ የኬሚካል ሽታ ወይንም ለመዝናናት ለማማር ሲባል የሚደረግ ኬሚካል የሆነ ምርት በጽንስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እርግዝና ደሕንነት የተሞላበትን አካባቢ ይሻል፡፡ ልጅ ሙሉ የሰውነት አካሉን የሚመሰርተው እስከ ሁለት ወር ወይንም ስምንት ሳምንት ድረስ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ ውስጥ የሚከሰት ማንኛውም ችግር በልጁ ላይ የአካል ጉድለትን የሚያደርስ ይሆናል፡፡ አንዲት ሴት ለማርገዝ ስታቅድ በቅድሚያ የህክምና ባለሙያ ጋ በመሄድ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ አካሌ ለእርግዝና የሚያበቃኝ ነውን? በስራዬ ወይንም በመኖሪያዬ አካባቢ ማድረግ የሚገባኝ ጥንቃቄ ምንድነው? በተለያዩ የጤና ሁኔታዎች የምትወስደው መድሀኒት ካላት በጽንሱ ላይ ችግር ያስከትላል? አያስከትልም? ለመፍትሔው ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? በማለት ማማከር ይጠበቅባታል፡፡
ጥ/ ቤተሰብ ጠፍቶ የተወለደ ልጅ ሲገጥመው ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን ይገባዋል?
መ/ ልጅ ጠፍቶ ሊወለድ የቻለበትን ምክንያት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ሁልጊዜም ይገጥማል የሚባል ባይሆንም ለጊዜው ግን በየትኛው ምክንያት ሳይወለድ ሊጠፋ እንደቻለ ማወቅ ለሕሊናም እረፍት ይሰጣል፡፡ ቤተሰብ ፈቃደኛ ከሆነም ልጁ ገና ከማህጸን እንደወጣ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍሮቹ እንዲሁም የአካል ጉድለት መኖር ያለመኖሩን እና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥንቃቄ የተሞላው ምርመራ ይደረ ግለታል፡፡ የእትብቱ ክብደት ፣የእንግዴ ልጁ ክብደት ፣እትብቱ በቂ የደም ስሮች እንዳሉት እና እንደሌሉት የመሳሰሉትን ሁሉ ማየት ይገባል፡፡ የክሮሞዞም ችግር አለ ወይንስ የለም ? የሚለውንም በምርመራው ወቅት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ምክንያቱን ማወቅ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ምናልባት ቤተሰቦች ሊያስተካክሉት የሚችሉት ነገር ካለ እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡

Read 4638 times