Saturday, 17 August 2013 11:21

የአገር ሰምና ወርቅ 

Written by 
Rate this item
(13 votes)

ልለምንህ ጣና - ልማጠንህ ዓባይ - አዋሽ እሺ በለኝ
አገሬ ተድራ - አገር ጠርቻለሁ - የአገር ድግስ አለኝ፤
አገሩን የዳረ - አገር ህዝብ የጠራ
ለአገር የጠመቀ - ለአገር የደገሰ፣
መሬቱ እንጀራው ነው - ሀይቁም ወይንጠጁ
መች ይጨንቀውና - ደረሰ አልደረሰ፤
ይኸው አገር መጣ!
ይኸው አገር ወጣ!
አገር ድግስ በይ - አገር ላይ የወጣ - አገር ሊያይ የመጣ
ብትታየው ጊዜ - አገር ሙሽራዬ - ከአገር ሁሉ በልጣ
አገር ልቡ ቆመ - አገር ማድነቂያ አጣ - አገር አቅም አጣ፡፡
ይኸው ይቺውልህ፤
በአገር ፍቅር ቬሎ - በአገር ሰረገላ
አገር ስትመዘን - በሰው ተመስላ
ይህን ታህላለች
ይህን ትመስላለች
በል ሀቅ እንፈልቅቅ - ከሯጭ ህብረ - ቀለም
በአትሌት ሰምና ወርቅ - በ‹‹ሀገር›› ቀልድ የለም!!
ለዚያም ነው ጥሩዬ
አገር በልቧ አዝላ - በአገር ተውባ
በአገራት ሙሽሮች - በአገራት ተከባ
በአገር አደባባይ - አገር ስታገባ
አገር ወዲያ ጥላ - ወደ አገር ስትገባ
አገር ምድሩ ያለው - ጉሮዬ ወሸባ!!
ነው እንጅ ነውና!!
‹‹ጥሩ›› አገር ብትሆን ነው - አገርን ያከለች - አገር የተሰጠች
ከአገር ተፎካክራ - አገር ያስከተለች - አገር የበለጠች!!
ይኸው ነው ቀለሙ - ይኸው ነው እውነቱ
እሷ ስታሸንፍ - እኛ ሁላችንም - የጨፈርንበቱ!!
ስማ ጋዜጠኛ፤
ይኸውልህ እውነት - የሀቅ ህብረ - ቀለም
በጥሩነሽ አገር - ስለ አገር ቀልድ የለም፡፡
ካላመንክ ጠይቃት - ከአንደበቷ ስማ
እንዲህ ትልሃለች - አገር አስቀድማ...
‹‹ለሌላ አገር አትሌት - እንኳን ሜዳሊያ - መጨረስም ድል ነው
ለኔ አገር ህዝብ ግን - ብር ሽንፈት ሲሆን - ነሀስም ውራ ነው፤
በቃ በኔ ሀገር - ድል ነው እሚባለው
ወርቁን ከነክብሩ - ያስገኘህ ጊዜ ነው!!››
ይህ ነው ሰምና ወርቅ - በጥሩነሽ አገር - የአገር ህብረ - ቀለም
ወርቅ ለለመደ - ነሀስ ግድ አይሰጥም - ብርም ድል አይደለም፡፡
ነሐሴ 5 - 2005 ዓ.ም
(ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የሞስኮ ድል)

Read 8460 times