Saturday, 17 August 2013 11:54

የአምባገነኖች መዘዝ ማብቂያ የለውም!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(2 votes)

ግብጽን ከሠላሳ አመት በላይ ከብረት በጠነከረ እጃቸው ሰጥ ለጥ አድርገው የገዙት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፤በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አብዮት ፕሬዚዳንቱን ዜን አብዲን ቤንአሊን አገር ጥለው እንዲሰደዱ እንዳደረጋቸው ዋነኛው የደህንነት ምኒስትራቸው ሲያስረዷቸው፤ “ምስኪን ቤንአሊ! ለጥቂት አመፀኛ ጐረምሶች ብሎ አገሩን ጥሎ ተሰደደ?” በማለት ማሾፋቸውን፤ግብጻውያን በተራቸው እያሾፉ ተናግረው ነበር፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ፕሬዚዳንት ሙባረክ በቱኒዚያው ፕሬዚዳት ከአገር ጥሎ መጥፋት ቢያሾፉ አይፈረድባቸውም ነበር፡፡ ለምን ቢባል--- ከሠላሳ አመት በላይ በዘለቀው አምባገነናዊ አገዛዛቸው፣ በህዝባቸው ላይ ምን አይነት አስተሳሠብና ስሜት መፍጠር እንደቻሉ በሚገባ ያውቁ ስለነበር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት አንዋር አልሳዳት በ1981 ዓ.ም በካይሮ አደባባይ ወታደራዊ ትርኢት እየተከታተሉ እንዳለ የኢስላሚክ ጅሀድ አባላት በሆኑ ጽንፈኛ ሙስሊም ታጣቂዎች በጠራራ ፀሀይ በጥይት ተደብድበው ከተገደሉ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ከሁሉም አስቀድመው የወሰዱት እርምጃ ስልጣናቸዉን ማደላደል ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ የመጀመሪያው ስራ የስልጣናቸውን ተቀናቃኞች ቀድሞ መጥረግ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የመጀመሪያውን እርምጃ ለመውሰድ የቅጣት ሰይፋቸውን የመዘዙት ጽንፈኛ ሙስሊም ድርጅቶች ናቸው በተባሉት በኢስላሚክ ጅሀድና በሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ድርጅቶችና አባሎቻቸው ላይ ነበር፡፡
ስልጣን በያዙ ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ኢስላሚክ ጅሀድ የተባለውን የፖለቲካ ድርጅት ከነመላ አባላቶቹ ጨርሶ ያልነበረ ያህል ድምጥማጡን ሲያጠፉት፣ሙስሊም ወንድማማቾች የተሠኘውን እስላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ አከርካሪውን በመስበር፣ ከግድያና ከወህኒ ቤት እስር ያመለጡ አባላቶቹ ህቡዕ እንዲገቡ አስገደዷቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በመጡት ጥቂት አመታት ውስጥ ደግሞ ፊታቸውን በህዝቡ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነት ቀላል ሚዛን ናቸው ወደተባሉት ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች በማዞር፣በግብጽ የፖለቲካ መድረክ ላይ ቅንጣት ታክል የእግር መትከያ ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረግ ከፖለቲካ ጨዋታው ጨርሰው እንዲወጡ አደረጓቸው፡፡
የፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳትን አስረኛ የሙት አመት፣ የእርሳቸውን ደግሞ አስረኛ የፕሬዚዳንትነት አመት በመስከረም 1991 ዓ.ም ሲያከብሩ፣ በመላዋ ግብጽ ውስጥ የነበረው አንድ ፓርቲና ምክትል ፕሬዚዳንት እንኳ ለመሾም ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ አምባገነን መሪ ብቻ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ፓርቲና ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፡፡ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ይህንን ካደረጉና ስልጣናቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ካረጋገጡ በኋላም እንኳ የብረት መዳፋቸውን በህዝባቸው ላይ ላላ ለማድረግ ጨርሶ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ቀጣዮቹን ሀያ አመታት ያሳለፉትም ስልጣናቸውን ከእለት እለት ፍፁም የለየለት አምባገነን በማድረግና በህዝባቸው ልብና አዕምሮ ውስጥ ልብ የሚያቆምና አጥንት የሚያጐብጥ ፍርሀት በመትከል ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ ከሠላሳ አመታት በላይ የዘለቀውን ፍፁም አምባገነናዊ አገዛዛቸውን በምድረ ግብጽ መመስረት የቻሉት እንደው እንደዘበት አልነበረም፡፡ የዚያ ምህረት የለሽ የብረት መዳፋቸው ልዩ ጡንቻዎች የደህንነት ሀይላቸውና በፊልድ ማርሻል ሞሀመድ ታንታዊ ፊት አውራሪነት የሚመራው የጦር ሀይሉ ከጎናቸው ነበሩ፡፡ ህዝባዊውን አመጽ መቋቋም ተስኗቸው የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ሀገራቸውን ለቀው የመሰደዳቸው ዜና ሲነገራቸው፣ ያሾፉትም በሌላ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በእሳቸው ቁጥጥር ስር ባለው የደህንነትና የጦር ሀይላቸው በሙሉ ልብ በመተማመናቸው ነበር፡፡
በእርግጥም ፕሬዚዳንት ሙባረክ የስልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ሁሉ፣ እንኳን በምድረ ግብጽ በመላው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሳይቀር እገቡበት እየገባ፣ አንገታቸውን በመቀንጠስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በፍፁም ታማኝነት ለሠላሳ አንድ አመታት ባገለገሏቸው የደህንነትና የጦር ሀይሉ በመተማመን ነገር አለሙን ሁሉ ጥለውት ነበር፡፡ ከቱኒዝያ የተነሳው የአረብ ህዝባዊ አብዮት የሰደድ እሳቱ ድንገት ካይሮ ታህሪር አደባባይ ከች ብሎ ባልጠበቁት ጊዜና ባልታጠቁበት ሁኔታ የለበለባቸውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ግብፃውያን የአምባገነኑን የፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ጨቋኝና አፋኝ አገዛዝ ለመገርሰስ ያካሄዱት አብዮት ሁለት ነበር፡፡ ሁለተኛውንና ዋናውን አብዮት ታህሪር አደባባይ በመውጣት ከማካሄዳቸው በፊት የመጀመሪያውን አብዮት ያካሄዱት ለሰላሳ አንድ አመታት ክፉኛ ተጭኗቸው የነበረውን ከፍተኛ ፍርሀት በማሸነፍ ነበር፡፡ ግብፃውያን ፕሬዚዳንት ሙባረክን ከስልጣናቸው ነቅሎ ለማባረር ባካሄዱት አብዮት ክፉኛ ፈርተውት የነበረው የፕሬዚዳንቱ ቀኝ እጅ የነበረውን የግብጽን ጦር ሀይል ነበር፡፡ በተግባር የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱን በመደገፍ አብዮቱን ሊያከሽፍ ይችላል ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈርቶ የነበረው ጦር ሀይል፣ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወገንተኝነቱን ለህዝብ ማሳየት ቻለ፡፡
ፕሬዚዳንት ሙባረክም እስከመጨረሻው ድረስ የቻሉትን ያህል ቢፍጨረጨሩም በህዝባዊው አብዮት ሰደድ እሳት ከመለብለብ ራሳቸውንና አገዛዛቸውን ማዳን ሳይችሉ ቀሩ፡፡ በቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካገር ለቆ መጥፋት ያሾፉት ሙባረክም ግብጽን ለቀው ለመውጣት ሳይችሉ ቀርተው፣ተቀናቃኝና ተቃዋሚዎቸቸውን ሲያጉሩበት በነበረው ወህኒ ቤት፣ የማታ ማታ እርሳቸውም የእድሜ ልክ እስር ተበይኖባቸው ለመታጐር በቁ፡፡ የግብጽ ህዝባዊ አብዮት፣ ከአምባገነኑ የሙባረክ አገዛዝ ነፃ ያወጣው የግብጽን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶችንም ጭምር ነው፡፡ ይህ ህዝባዊ አብዮት በተለይ ከሠላሳ አመታት በላይ ቁም ስቅሉን ላየው ሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ድርጅትና ደጋፊዎቹ በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ የግብጽ ህዝባዊ አብዮት የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅትን ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የአመራር ወንበሩንና በትረ ስልጣኑን ነበር ያስጨበጠው፡፡ ህዝባዊ አብዮቱን ተከትሎ በምድረ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣኑን መቆናጠጥ የቻለው የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ነው፡፡
በግብጽ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ምርጫ፣ በህዝብ ድምጽ ተመርጠው ስልጣን መያዝ የቻሉት ፕሬዚዳት ሞሀመድ ሙርሲም የሙስሊም ወንማማማቾች ድርጅት ያቀረባቸው ናቸው፡፡ በምርጫው በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፍተኛ ፉክክር ቢያደርጉም፣ ካለው የደጋፊ ቁጥርና ተቀባይነት አንፃር የሙስሊም ወንድማማቾች እንደሚያሸንፍ አስቀድሞም ቢሆን ተገምቶ ስለነበር አንድም ግብፃዊ በውጤቱ አልተገረመም ነበር፡፡ አስገራሚው ነገር ከምርጫው በኋላ ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሙርሲ ህዝቡ የሰጣቸው ማሳሰቢያ ነበር፡፡ ህዝቡ ለፕሬዚዳንት ሞርሲ የሰጣቸው ማሳሰቢያ፣ ደምና ህይወት ከፍለው እውን ያደረጉት አብዮት ግቡን እንዲመታ፣ ቃል የገቡትን ሁሉ በተግባር ለመተርጐም የአንድ አመት ጊዜ እንደሠጧቸው፣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ውጤት ማምጣት ካልቻሉ ግን በምርጫ የሠጧቸውን ስልጣን መልሰው እንደሚነጥቋቸው የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሞርሲም “ግዴላችሁም በእኔ ይሁንባችሁ” ብለው ተጨማሪ ቃል ገብተው ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ በምርጫው ወቅት የገቡትን ቃልና ህዝቡ የሰጣቸውንም ማሳሰቢያ ጨርሰው የረሱት ምናልባትም ሆን ብለው ችላ ያሉት በብርሀን ፍጥነት ነበር፡፡ ግብጽን ለመምራት ቃለ መሀላ ፈጽመው የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ፣ በማግስቱ ራሳቸውን በዋናነት የጠመዱት የጦር ሀይሉን አንጋፋ መሪዎች በጡረታ በማሰናበት፣ የእሳቸው ደጋፊ የሆኑ ከፍተኛ መኮንኖችን መተካት፣ የግብጽን ጠቅላይ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶችን በደጋፊዎቻቸው መሙላት፣በተለይ ደግሞ የግብጽን ህገመንግስት ፈላጭ ቆራጭ ስልጣን እንዲኖራቸው አድርገው በማሻሻል ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሞርሲ፣ራሳቸውን የህዝብ መሪ ከማድረግ ይልቅ በለየለት አምባገነንት ህዝባዊው አብዮት ያስወገዳቸውን ፕሬዚዳንት ሙባረክን ለመተካት አለመጠን መጣደፋቸውን የተገነዘበው የግብጽ ህዝብ፣ “ኧረ እርሶ ሰውዬ ያድቡ!” በማለት በየጊዜው ማሳሰቢያውን ቢሰጥም እርሳቸው ግን የሚሰሙበት ጆሮ አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንስ “ሁሉም ነገር ወደ ብቸኛ የስልጣን ባለቤትነትና አምባገነንነት!” በማለት ሲጋልቡ ነገር አለሙን ሁሉ እርግፍ አድርገው ተውት፡፡ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ቀስ በቀስ ስር እየሰደዱ በመምጣት፣ ግብጽንና ግብፃውያንን እግር ተወርች ጠፍረው አላላውስ አሏቸው፡፡
ቻይናውያን “አስፈሪው ማዕበል እንዳለፈ ሰላምና መረጋጋት ይሆናል” የሚል አባባል አላቸው፡፡ ግብፃውያንም የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበት ህዝባዊው የአብዮት ማዕበል እንዳለፈ ሰላማዊ፣ የተረጋጋና፣ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ህይወት ይከተለናል ብለው በእጅጉ ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ በሀገራቸው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄዱት ህዝባዊ ምርጫ አማካኝነት የመሪነቱን ስልጣን ከታላቅ አደራና ማሳሰቢያ ጋር ለሞሃመድ ሞርሲ የሰጡትም ወደ አዲሱ ህይወት ይወስዱናል በሚል ተስፋ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አብዮታቸውን በመቀልበስ ይህን ታላቅ ተስፋቸውን አዲሱ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ሞርሲ በጥቂት ወራት እድሜ ብቻ እንደጉም እንዳበነኑባቸው የተረዱት ወዲያውኑ ነበር፡፡ ግብፃውያን በተደጋጋሚ ቃል የገቡትን እንዲፈጽሙ ፕሬዚዳንት ሞርሲን ቢያሳስቡም በጄ ሊሏቸው አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለውን የፕሬዚዳንቱን እብለት እንደተረዱም በከፍተኛ ትዕግስት የሰጧቸውን የአንድ አመት ቀነ ገደብ እያንዳንዱን ቀን በመቁጠር ማስላት ጀመሩ፡፡
ጋናውያን “በተደጋጋሚ ሙከራ ጦጣ ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ መዝለልን ትማራለች” የሚል አንድ አገርኛ አባባል አዘውትረው ይናገራሉ፡፡ ግብፃውያንም ያልፈለጉትን የአገዛዝ ስርአት በህዝባዊ አመጽ ማስወገድ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ዝነኛው የታህሪር አደባባይ ለተቃውሞ በመውጣት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ እናም ለፕሬዚዳንት ሞርሲ የሰጡት የአንድ አመት የጊዜ ገደብ እንደተጠናቀቀ፣ፕሬዚዳንት ሞርሲን ከስልጣናቸው ለመንቀል ዳግመኛ በሚሊየኖች ተጠራርተው፣ታህሪር አደባባይን በተቃውሞ አጨናነቁት፡፡ “ሞሐመድ ሞርሲ ጨዋታው አብቅቷል፣ በቃህ ውረድልን” ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን አንግበው ፕሬዚዳንቱ አንጃ ግራንጃ ሳያበዙ፣ ስልጣናቸውን አስረክበው ወደሚሄዱበት እብስ እንዲሉ በግልጽ ቋንቋ ነገሯቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ሞርሲ፣ የህዝቡን ድምጽ በጥሞና ለማዳመጥ በድጋሚ አሻፈረኝ አሉ፡፡ “ግብጽን ለአራት አመታት ለመምራት በዲሞክራሲያዊ አግባብ የተመረጥኩ ፕሬዚዳንት ስለሆንኩ፣የስልጣን ጊዜዬን ሳልጨርስ ከስልጣን አልወርድም በማለት አሻፈረኝ አሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ሀሳባቸውን በመደገፍ ከጐናቸው ተሰልፈው መቆማቸውን አረጋገጡ፡፡
የተቃዋሚዎቻቸው የተቃውሞ ማዕበል ግን ከደጋፊዎቻቸው በእጅጉ የላቀ ነበር፡፡ በመሀሉ ግን የሁለቱ ጐራ ግጭትና አተካሮ እየሰፋና እየከረረ፣ግብጽ ቀስ በቀስ ወደ አደገኛ ሁኔታ መንሸራተት ጀመረች፡፡ ድንገት ግን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የግብጽ የጦር ሀይል ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን በማስወገድ፣በቤት ውስጥ እስር እንዳዋለና በአንድ አቃቤ ህግ የሚመራ ጊዜያዊ መንግስት መቋቋሙን አሳወቀ፡፡ የፕሬዚዳንት ሙርሲ ተቃዋሚዎች በጦር ሀይሉ እርምጃ ጮቤ ሲረግጡ፣ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ “ህገወጥ መፈንቅለ መንግስት ተደርጐባቸዋል” በሚል በተቃውሞ ካይሮን ቀውጢ አደረጓት፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑም ሞሀመድ ሞርሲ ወደ ስልጣናቸው ካልተመለሱ ተቃውሞአቸውን መቼም ቢሆን እንደማያቆሙ በቁርጠኝነት አስታወቁ፡፡
አዲሱ ጊዜያዊ መንግስትና የጦር ሀይሉ ግን እስከ ባለፈው ማክሰኞ ድረስ የሞርሲን ደጋፊዎች በለዘብታ ሲያባብላቸው ቆየ፡፡ ማክሰኞ ግን ትእግስቱ ማለቁን በማሳወቅ ተቃዋሚዎች የታህሪር አደባባይን እንዲለቁ አለበለዚያ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስድ አሳሰበ፡፡ የፕሬዚዳንት ሞርሲ ደጋፊዎች ግን ለጦር ኃይሉ ማሳሰቢያ ቁብ አልሰጡትም፡፡ በዚህም ሳቢያ እስካሁን ድረስ በግብፅ ምድር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ካይሮ በደም አላባ እንድትታጠብ ምክንያት ሆነ፡፡ እስከትናንት ድረስ ብቻ መንግስት በወሰደው የኃይል እርምጃ ሳቢያ 525 ግብፃውያን ህይወታቸውን አጡ፡፡ አሁን ሁሉንም የሚያስጨንቅ አንድ ጥያቄ - “የግብፅ የነገ እጣፈንታ ምን ይሆን?” የሚል ነው፡፡ ፈጣሪ ሰላሙን ያውርድላቸው!

Read 4010 times Last modified on Saturday, 17 August 2013 13:16