Saturday, 24 August 2013 11:00

ወደ እራት

Written by  በዕውቀቱ ስዩም
Rate this item
(1 Vote)

ጀንበሪቱ ወደ ማደሪያዋ አልዘለቀችም፤ ጨርሶ አልመሸም፡፡ በጊዜ እራት ወደሚያገኙበት ቤት እየሄዱ ነው፡፡
አምስት አመት የሞላው የልጅ ልጃቸው መዳፋቸውን በትንሽ እጁ ጨብጦ ይመራቸዋል፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“ወደ እማማ ታንጉት ቤት ውሰደኝ”
ወደተባለው ቦታ የሚያደርሰውን መንገድ አግኝተዋል፡፡ በሶስት ብሩ እራት ይበሉበታል፡፡ በተረፈው ጠጅ ይጨልጡበታል፡፡ ይህን ሲያስቡ የታንጉት ቤት ራቃቸው፡፡
“ደህና ውለዋል ወይ?”
ማንነቱን በሚንቀጠቀጥ ድምፁ ለዩት፡፡ እግር አልባው ተመጽዋች ነው፡፡
“ደህና አምሽተሃል?...ውብ ሊቀር?”
“ዘሀርምስጌን…ዝምበላቸውን ጠየቁት?”
“ዝምበላቸው ይሄ የኛው?” በአይነስውርነትና በግብር የሚመስላቸውን ባልንጀራቸውን አስታወሱ፡፡
“ኋላ ሌላ ዝምበላቸው አለ?”
“እኮ እሱ ምን ሆነ?”
“ምን ገጥሞት አንተ?” ጮኹ፡፡
“ጉድጓድ አደናቅፎት ሲወድቅ ጥርብ ድንጋይ አግኝቶ ጭንቅላቱን ተረተረው”
“በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ያለመሪ መንገድ ምን አስከጀለው?”
“አሂሂ…መሪ ሲኖር አይደል”
“ትንሽ ልጁ የት ሄዶ?”
“አልሰሰሜን ግባ በለው…ተኮበለለ አንድ ሰንበት አልፎት”
ውስጣቸው በድንጋጤ ተናጠ፡፡ ድንገት የዝምበላቸው ገጽታ በሃሳባቸው መስኮት ብቅ አለ፡፡ ዧ ብሎ ተኝቶ ከጭንቅላቱ ላይ የፈሰሰው የረጋ ደም ፊቱ ላይ ደለል ሰርቶ እንደዐይኑ ብርሃን የልቡ ተስፋ ጠፍቶ…
“ልጁ የኮበለለ ተማርሮ ነው፡፡ ከፍቶት ነበር…የዘመኑ ልጆች መከፋታቸውን በልባቸው ይሸሽጉታል፡፡ እኛም ቻይና ገራገር መስለው ይታዩንና እንዘናጋለን፤ የቆረጡ ቀን ግን አጋንንት ናቸው፤ አይጨበጡም”
ይህን ካለ በኋላ እየዳኸ ራቀ፡፡ የዳናው ድምጽ ሲጠፋ ፍርሃት ወረራቸው፡፡ ከንፈራቸው መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡
“አቡሽ” ደግመው ጠሩት፡፡
“እ”
መንገዱን እያሳበረ ይመራቸዋል፡፡
የባልንጀራቸው ዝምበላቸው ስዕል ህሊናቸው ውስጥ ገዘፈ፡፡ አወዳደቁ እንደዋርካ በቁሙ ሲገነደስ፣ ምድር ላይ የተተከለ ስል ድንጋይ ከታች ሲቀበለው…
“አያቴ!”
“አቤት አቡዬ”
“ደፍተሬና እስኪብርቶዬ ሊያልቅብኝ ነው”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “አንድ ቀን ይገዛልሀል” ብለው ያዘናጉት ነበር፡፡ አሁን ግን ግብራቸውን ለወጡት፡፡ እጃቸው ወደ ኪሳቸው ፈጠነ፡፡
“በል!..ባለአስራስድስት ሉክ ደፍተርና አንድ እርሳስ ገዝተህ ና”
የጠወለገች የሰንሰል ቅጠል የመሰለችውን አሮጌ ብር ተቀብሏቸው ቱር ብሎ ሄደ፡፡
ወዲያው እንግዳ ብቸኝነት ሲሰፍርባቸው ተሰማቸው፡፡ የልጅ ልጃቸው የዘገየ መሰላቸው፤ “የውብ ሊቀር ንግግር ወደ ልቡ ሰርጐ ይሆን?” ብለው አሰቡ፡፡ “አይ ውብ ሊቀር…አሁን ያን የመሰለ ወግ በልጅ ፊት ይነገራል?”
የትንሹ ልጅ ዳና አልተሰማም፡፡
ዝምበላቸው ዳግመኛ ህሊናቸው ውስጠ ተከሰተ፡፡ ክንዶቹ ተሰብረዋል፡፡ ቅልጥሞቹ ተጋግጠዋል፡፡ ያቃስታል፡፡ “ምነው ጌታዬ…ብታሳርፈኝ” የሚለውን ምሬት ይደጋግማል፡፡
“የዘመኑ ልጆች መከፋታቸውን በልባቸው ይሸሽጉታል፤ እኛም ቻይና ገራገር ይመስሉንና እንዘናጋለን”
የእግር አልባው ተመጽዋች ማሳሰቢያ እዝነ ልቡናቸው ውስጥ ነጠረ፡፡ ሥጋት አጥለቀለቃቸው፡፡
“መጥቻለሁ አያቴ”
አላመኑም፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“አንተ ነህ”
“እራሴ ነኝ”
“ደፍተሩንና እርሳሱን ገዛህ”
“አዎ አያቴ”
“ተመስገን” አሉ በልባቸው…ለማረጋገጥ የፈለጉ ይመስል መዳፋቸውን ቁልቁል ሰደዱት፡፡ አግድም የታረሰ ጉድባ የመሰለውን ሸካራ ራሱን ሲነኩት ተረጋጉ፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“እስኪብርቶ ነበር የጠየቅኸኝ…ለጊዜው በርሳሱ ጣፍበት፡፡ ነገ ከነገወዲያ እስኪብርቶውን እገዛልሃለሁ”
ዝም አለ ልጁ፡፡
“እውነቴንኮ ነው…እርሳሱንም በደህና ምላጭ ተቀረጽኸው ተእስኪብርቶ አንሶ አያንስም”
በዝምታ ይመራቸዋል፡፡ ዝምታው ረበሻቸው፡፡
“አኩርፈህ ነው?...አሁን ይሄ የሚያስኮርፍ ነገር ሆኖ ነው በጊዮርጊስ…ነገ ከነገ ወዲያ’ኮ ደፍተሩንም እስኪርብቶውንም ጨመር አርጌ እገዛልሃለሁ…ብቻ አንተ ጥሩ ልጅ ሁነህ ተገኝ”
በአርምሞ እንደተከረቸመ ቁልቁል ይዟቸው መውረድ ጀመረ፡፡
በኪሳቸው ከቀሩት ብሮች አንዷን መዘዙ፡፡
“ይቺን ያዝና ነገ እስኪብርቶ ትገዛባታለህ…
እስቲ የልብህ ይድረስ”
ተቀበላቸው፡፡
እናም የሚወዱት ጠጅ በጉሮሮአቸው እንደማይወርድ አወቁ፡፡ እንጀራ በሽሮ የሚገዛ ብር ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡
“አያቴ”
“አቤት ጌታዬ”
“እዚህ መንገዱ ዳር እኔን እሚያካክሉ ሕፃናት እንጐቻ ይሸጣሉ”
“እውነትህነው?”
“ማርያምን”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “ይሄውልህ እንዲህ እያረጉ ነው ወላጆቻቸውን የሚያስተዳድሩ” ይሉት ነበር፡፡ አሁን ግን “ይገዛልህ እንዴ?”
“እሺ”
እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ላኩት፡፡
ሁለት ዳቦዎችን ገዝቶ ከተመለሰ በኋላ
“አንዱን ልስጥህ?” አላቸው፡፡
“የለም ላንተ ይሁንህ”
የማላመጥ ድምጽ በጆሮአቸው ሲገባ፣ የዳቦ መዓዛ ባፍንጫቸው ሲሰርግ ጨጓራቸው ይገላበጥ ጀመረ፡፡ ምራቃቸውን በየቅጽበቱ መዋጥ ያዙ፡፡
“አቡሽ”
“እ”
“ጥሩ ልጅ መሆን አለብህ፡፡ ጥሩ ልጅ በምድር ይባረካል፤ ይወልዳል ይከብዳል”
የተለመደው ዝምታ፡፡
“ነፍሳቸውን ይማርና እናትህና አባትህ ደዌ አከታትሎ ሳይፈጃቸው ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡
ሳይታክቱ ይታዘዙኝ ነበር፡፡ ለዚያ ነው ባሁኑ ጊዜ ኑሯቸው በገነት የሆነ”
ዝም፡፡
“ደጋግ ልጆች በምድር ብቻ አይደለም፤ በወዲያኛው አለም በገነት ከመላዕክት ጋር ይኖራሉ፡፡ መላዕክቱ በለስላሳ ክንፎቻቸው አዝለው ገነትን ያስጐበኟቸዋል…እዚያ መራብ የለም፤ መጠማት የለም፡፡ ተራሮች ሁሉ የሚጣፍጡ ዳቦዎች ናቸው፡፡ ወንዞች ማርና ወተት ያፈሳሉ”
ዝም፡፡
“ጥሩ ልጅ የማይሆኑ ልጆች ግን ፈጣሪ ይቀጣቸዋል፡፡ በምድር ላይ ረሀብተኛና ተቅበዝባዥ ይሆናሉ፡፡ አይወልዱም፤ አይከብዱም”
ክርችም፡፡
“አንድ ልጅ አያቱን ከድቶ ከሆነ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር፣ “በእርጅና ዘመኑ የታወረውን አያትህን ለምን ከዳህ” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም የሚመልሰው አይኖረውም፡፡
ከዚያማ…ሲዖል መግባት ዕጣ ክፍሉ ይሆናል፡፡ በሲዖል መብላት የለም፣ መጠጣት የለም፣ ትምህርት ቤት የለም…”
“አያቴ!”
“አቤት!”
“ረስቼው?”
“ምኑን?”
“ትምህርት ቤት”
“እ”
“የስፖርት ብር አምጡ ተብለናል”
ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ “ደሞ የምን እስፖርት ነው?” ብለው ኩም ያረጉት ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሳግ በተቀላቀለበት ድምጽ “ምን ያህል?” ብለው ጠየቁት፡፡
“እንደተገኘው…አምስት፣ አራትም፣ ሶስትም” ሃሳብ ገባቸው፡፡
“ሁለት ይበቃህ ይሆን?”
“እኔንጃ ይበቃኝ ይሆናል”
ከጥቂት እርምጃዎች በኋላ “እማማ ታንጉት ቤት ደርሰናል” አላቸው፡፡
“አልጠፋህም ማለት ነዋ!”
“ምኑ…አያቴ?”
“የማማ ታንጉት ቤት”
“ኧረግ አይጠፋኝም”
“ጐሽ! በል አሁን ወደመጣንበት መልሰኝ!”
ትንሹ ልጅ አመነታና የመንገዱን አቅጣጫ ቀየረ፡፡
(አዲስ አድማስ፤ ሰኔ 15 ቀን 1994 ዓ.ም)

Read 3123 times