Saturday, 19 November 2011 14:56

ያመኑትን ማወቅ

Written by  ሌሊሣ
Rate this item
(0 votes)

ምንም ነገር በማይታወቅበት ሁኔታ … ምንም ነገር አይከለከልም፡፡ ለመከልከል እና ለመፍቀድም … ቀዳሚው ነገር እውቀት ነው፡፡ …ያመኑትን ማወቅ፤ ያወቁትንም ማመን፡፡ለምሳሌ የእግር ኳስ ጨዋታ አለ፡፡ በጨዋታው ላይ ኳሷ መረብ ላይ በተጫዋቹ ተለግታ ትገባለች፡፡ “ጐል” ተብሎ ይጠራል፡፡ ነገር ግን ጐልን ብቻ በመመልከት የእግር ኳሱ ጨዋታ ህግ ሊገባን ይችላል? ጐሉ ራሱ ትርጉም የሚኖረው የጨዋታውን ህግ መገንዘብ ከቻልን ብቻ ነው፡፡ አስቡት፤ አሁን ራሳችሁን ድንገት በአንድ ጨዋታ መሀል አግኝታችሁታል፡፡ መሀሉ ሆናችሁ የተገኛችሁበት ጨዋታ፤ “እግር ኳስ” እንኳን ተብሎ እንደሚጠራ ገና አታውቁም፡፡ ከሁለቱ ቡድን የአንዱን የሚወክል “ማሊያ” ለብሳችኋል፡፡

ሁለቱንም ቡድን ልትሆኑ አትችሉም፡፡ ቢያንስ ይሄንን ታውቃላችሁ፡፡ … ግን፤ ይሄንኑም ያወቃችሁት የራሳችሁን መሰል ለባሽ ተጫዋቾች ጋር በማመሳሰል እንደዚሁም ከማይመስሉት ጋር በማለያየት ነው፡፡ ይህንን እንኳን ለማወቅ፤ ሰላሳ ደቂቃ ቢፈጅባችሁ ነው፡፡ …ይህ “የማሊያ” መለየት ግን፤ የጨዋታውን ህግ ወዲያው እንድታውቁ አያደርጋችሁም፡፡ ኳሱን በእግር ነው በእጅ የምትይዙት? … በእጅ ወይንም በእግር ከያዛችሁ በኋላስ ወደ የትኛው የጐል መረብ ነው ማስገባት ያለባችሁ?... ከባድ ነው፡፡ … ከባድም ቢሆን የጨዋታውን ህግ ለማወቅ የተሰጣችሁ ሰአት 90 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ የጨዋታውን ህግ የምታውቁት በጨዋታው ላይ ሆናችሁ ነው፡፡ 
… ህይወትን እንደዚህ የእግር ኳስ ጨዋታ ልትመስሏት ትችላላችሁ፡፡ በህይወት ላይ ያላችሁ እድሜ 90 አመት ነው፤ የእግር ኳስ ጨዋታው ደግሞ 90 ደቂቃ …፡፡ በተረፈ፤ አንድዓይነት ናቸው፤ ሁለቱም፡፡ የእግር ኳሱ ጨዋታ ዘጠና ደቂቃ ቢሆንም አስተማማኝ አይደለም፡፡ የህይወት ዘመን ቆይታም 90 አመት እንደሚሆን ማስተማመኛ የለም (ያውም የባከነ ሰአት ተጨምሮም)፡፡ … የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች ቢመታችሁ እና ቁርጭምጭሚችሁን ቢሰብረው፤ በቃሬዛ ላይ ሆናችሁ ከጨዋታው ትወጣላችሁ፡፡ ትወገዳላችሁ፡፡ በህይወት ላይ ደግሞ መኪና ቢገጫችሁ … በሬሳ ሳጥን ሆናችሁ ትቀበራላችሁ፡፡ የ90ናም ደቂቃ ሆና የዘጠና አመት ቆይታ አያስተማምንም፡፡
በእጃችሁ ሳታውቁ ኳሷን ብትነኩም ሆነ ኳሷ ሳታውቅ እጃችሁን ብትነካችሁ ቢጫ ካርድ ይሰጣችኋል፡፡ በህይወትም ላይ ሰውን ሳታውቁ በመኪና ብትገጩም ሆነ ሰውም ሳያውቅ መኪናችሁን ቢገጭ እና አደጋ ቢደርስበት … በሁለቱም ረገድ ትከሰሳላችሁ፡፡ በሁለቱም አጋጣሚ ያለጥፋታችሁ ጥፋተኛ ናችሁ፡፡ … ጥፋቱን መከላከል መቻል አለባችሁ፡፡ ጥፋቱን በማወቅ ብቻ ነው መከላከል የሚቻለው፡፡
በጨዋታው ወይንም በህይወት ቆይቻለሁ፤ ጨዋታውን መጫወት ወይንም ህይወትን መኖር ብቻ ሳይሆን … የጨዋታውን ህግ መረዳት … የህይወትን ትርጉም መፍታት መቻል አለብኝ፡፡ እውነታ የጨዋታው ህግ የሰፈረበት፣ የህይወት ትርጉም የተፃፈበት መፅሐፍ ከሆነ … መፅሐፍን ማንበብ መቻል የተጫዋቹ ሰው ግዴታ ነው፡፡ አቦ ምን ነክቶኝ ነው! ምንም ነገር ግዴታ አይደለም … (ግዴታ ራሱ ገደል ይግባ! … አሜን!)
መፅሐፉ የተፃፈው በተፈጥሮ ቃላት ከሆነ፤ የተፈጥሮ ቃላትን የማንበቢያ ዘዴ “ሳይንስ” የሚባል ይሆናል፡፡ … ለዚህም ነው:- ጋሊሊዮ ከአራት መቶ አመት በፊት የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ ሜካኒክስን በመጠቀም ወደ ሂሳባዊ ስሌት ቀይሮ በመግለፅ “ሀ” ብሎ የጀመረው፡፡ ጅማሬው በተፈጥሮ መፅሐፍ ላይ ያሉ ፊደላትን አገጣጥሞ እንደማንበብ ነው፡፡ ጋሊሊዮ በጀመረው ላይ “ይሳቅ” ኒውተን አጠናክሮ ገፋበት፡፡ ውስብስብ የሚመስሉ የተፈጥሮ እንቅስቃሴ ሂደቶች በቀላል ህጐች ቅልብጭ ብለው ተቀመጡ፡፡ ስላስቀመጣቸው የሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የአንስታይን የንፅፅር ፅንሰ ሀሳቦች፣ የሬዲዮ አክቲቭ ጨረር ግኝቶች ኩዋንተም ቲዎሪ … ድረስ ተመነደገ፡፡ ይህ ሁሉ ግን የመፅሐፉን ህግ ለማንበብ የሚጠቅሙ የሳይንስ ዘርፎች ናቸው፡፡ ሳይንስ በተለያየ የሰው ልጅ አንደበት ቢገለፅም፤ የገለፃው ትርጉም ግን አንድ ነው፡፡ ትርጉሙ:- የተፈጥሮ ህግጋት ሚስጢር የተፃፈበትን መፅሐፍ መግለፅ መቻል ነው፡፡ “መፅሐፉ አጭበርባሪ ነው” ማለት መብታችን ነው፡፡ አእምሮ አጭበርባሪ ነው ከማለት አይለይም፡፡ … ግን ማጭበርበርን የተረዳሁት በአጭበርባሪነቴ ነው እንደማለት መሆኑ ግልፅ ይሁን፡፡ ወደ አስራ ዘጠነኛው ምእተ አመት ገደማ፣ በኬሚስትሪ እና ፊዚክስ የሳይንስ ዘርፎች መሀል የነበረው ልዩነት በአንድነት መተሳሰር ጀመረ፡፡ ፊዚካል ኬሚስትሪ እና ኬሚካል ቴርሞዳናሚክስ በኬሚስትሪ እና ፊዚክስ ጥምረት ተወለዱ፡፡
በመጨረሻ፤ ሁለቱ ወላጆች አንዱን ከሌላው መነጠል የማይቻል ትዳር መሰረቱ፡፡ ይህ እስካሁን የገለፅኩት የተፈጥሮ ህግ በሰው ልጅ ጭንቅላት አማካኝነት የሚያደርገውን የመረዳት ሙከራ እና ንባብ ነበር፡፡ ንባቡ የተሳካ በመሆኑ፣ፊዚካል ሳይንሶች ከመጠን ያለፈ አደጉ፤ ተመነደጉ፡፡ … የእግር ኳስ ጨዋታውን ህግ ጨዋታ ላይ እያለ መረዳት ቻለ፡፡ ግን አንድ ሌላ ንባብ ይቀረዋል፡፡ የሰው ልጅ አእምሮ የውጫዊውን ተፈጥሮ በስኬት ማንበብ ቢጀምርም፤ የራሱን ተፈጥሮ ግን በጥልቀት ማንበብ አልሞከረም፡፡ እርግጥ አልጀመረም ሳይሆን አልዘለቀም ማለቱ ይሻላል መሰለኝ … ከ1830 እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ ሀያኛው ክፍለ ዘመን ሦስት ትላልቅ ግኝቶች ተደርገዋል፡፡ አንደኛው በጀርመኑ ባዮሎጂስት ስለ ሰውነታችን ህዋሳት የቀረበው ፅንሰ ሀሳብ (Cell theory) ሲሆን፤ ከሀሳቡ መሰረት ሁሉም ህይወት ያለው ነገር የተነገባው ከትንንሽ እና ጥቃቅን መሰረታዊ ጡብ መሳይ ነገሮች እንደሆኑ እና የሰውነት እድገት ከእነዚህ ህዋሳት መባዛት እና መከፋፈል የመነጨ እንደሆነ ገለፀ፡፡ እነዚህን መሰረታዊ የግንቡ ጥሬ እቃዎች ሴል ብሎ ሰየማቸው፡፡”
በመከተል በ1850 እንግሊዛዊ የተፈጥሮ ተመራማሪ ሁሉንም የህይወት አይነቶች በየፈርጁ የሚመለከት ዝግመታዊ ለውጥ ሀሊዮት ይፋ አደረገ፡፡ ሀሊዮቱ ህይወት ከምን ጀምሮ በተፈጥሮ የምርጫ ጐዳና እያሳበረ እስከ ምን እንደሚደርስ የሚተነትን ነው፡፡ ይሄንኑ ጥናቱን ያቀረበበት ብቸኛ መፅሐፍ “The Origin of Species” ተብሎ የሚጠራ …ተመራማሪው ደግሞ በስፋት ስሙን ከሳይንስ ጋር ያስተሳሰረው ቻርልስ ዳርዊን ነው፤
ሦስተኛው ፈረንሳዊ ነው፤ የቻርልስ ዳርዊንን የተፈጥሮ ንባብ ዱካ በመከተል ከአስር አመታት ቆይታ በኋላ አዲስ ነገር ይዞ መጣ፡፡ ለሰው የአካል ህይወት ከፍተኛ ጠላት የሆነው በሽታ “ጀርም” ከሚባሉ ተዋህሲያን ጋር የተያያዘ መሆኑን … በሽታውን ከመድሀኒቱ ጋር አድርጐ አቀረበ፡፡ … በማቅረቡም በጨዋታው ላይ ለመቆየት ከተፈቀደለት የእድሜ ርዝመት በጣም ባነሰ ቆይታ ይወገድ (ይሞት) የነበረው ሰው የቆይታ ጊዜውን (Life expectancy) ማራዘም ቻለ፡፡
እርግጥ የህይወት ቆይታ የፈለገ ቢሻሻልም ከመቶ አመት አይበልጥም፡፡ የድሮ ዘመን ሰዎች እንደ ማቱሳላ 900 አመት ኖረዋል የሚለውም ንግርት በድጋሚ መወርወር ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በሆሜር ትልቅ የኤፒክ ድርሰት ላይ ሁለት በእድሜ የገፉ ሽማግሌዎችን እናገኛለን፡፡ ድርሰቱ ”አሊያድ (Iliad)” ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡
ከሽማግሌዎቹ አንዱ [ኔስተር(Nestor)] ሶስት ትውልድ የኖረ እንደሆነ በድርሰቱ ላይ ተገልጿል፡፡ አንዱ ትውልድ መቶ አመት ከኖረ … ኔስተር ሶስት መቶ አመታት በህይወት ቆይቷል ማለት ይመስላል፡፡ ነገር ግን ኔስተር የኖረበት ዘመን በጦርነት ይታመስ የነበረ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ በወጣትነት መሞት የተለመደ ነበር፡፡ ከ20-25 ያለው አመት የአንድ ትውልድ እድሜ ነው፡፡ ሶስት ትውልድ ኖረ የተባለው ሽማግሌም በእውነቱ ከ70-75 አመት የማይበልጥ ሰው ነው፡፡ እውነትም ንፅፅር ነው፡፡ ሰው በአስር አመቱ ህይወቱን አጠናቆ የሚያልፍ ከሆነ፤ ባለ ዘጠና አመቱ ማቱሳላም ዘጠኝ ትውልድ የኖረ ሰው ይሆናል፡፡ በአሁኑ ዘመን ለሚሰማ ጆሮ ዘጠኝ ትውልድ 900 አመት እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ … ከመቶ አይበልጥም ያልኩት እድሜ ከሺ አይበልጥም እንደ ማለት ይመስላል ያኔ፡፡ “እቺ ጀንበር ሳትጠልቅ ትሞታለህ” ያለው ፈጣሪ ለአዳም ነበር ይባላል፤ የፈጣሪ አንድ ጀንበር ለሰው የአንድ ሺ አመታት ጀንበሮች ናቸው፡፡ ዘጠኝ መቶኛው ጀንበር ላይ መሞትም “እቺ ጀንበር ሳትጠልቅ ትሞታለህ” የሚለውን ትዕይንት ለሰው ያሟላለታል፡፡ …እንደ እምነቱ፡፡
“ማወቅ” የሁሉንም የተሳሳተ እምነት ማጥሪያው ብቸኛ ዘዴ ነው፡፡ ፍልስፍና “የማወቅ ፍቅር” ነው ተብሎ ቢተረጐምም … እውቀት ያለ ተጨባጭ ሙከራ ዋጋ የለውም፡፡ ስህተት ውስጥ በስተመጨረሻ መጣሉ አይቀርም፡፡
ከክርስቶስ ልደት 300 አመታት ቀድሞ የነበረው ኢዩሲሊድ ሳይንስን ከፍልስፍና ነፃ ለማውጣት የሞከረው የመጀመሪያ ሰው ነበር፡፡ ኢዩሲሊዮ ከአንድ መሰረታዊ የእውነት መነሻ በመጀመር ሌሎች የተበታተኑ የእውቀት እምነቶችን ለማስተሳሰር ሞከረ፡፡ … ሁሉም ሌሎች እውቀት እና እውነት የሆኑ ነገሮች በአንዱ የተረጋገጠ ነገር ላይ መሰረት ያደረጉ ሆነው ማስተሳሰር ነበር ሙከራው፡፡ የመነሻው እውነት “Axiom” ተብሎ ይጠራል፡፡ የመነሻው እውነት ቀላል እና ሁሉም ሰው ያለ ምንም ማመንታት የሚስማማበት ነገር ነው፡፡
ግን ዋናው ችግር ያለው ይህ የመነሻ እውነት “Axiom” የተባለው ነገር ላይ ነው፡፡ አሪስጣጣሊስ በዛው የኢዩሲሊዲያዊ መንገድ ከአንድ እውነት ተነስቶ ወይንም የተነሳ መስሎት ብዙ ስህተቶችን ያስፈለፈለበት ሁኔታም አለ፡፡
ለምሳሌ በአሪስጣጣሊስ የመነሻ እውነት:- ክብደት ያለው ነገር ቀላል ከሆነው ነገር የበለጠ እና በፈጠነ ጊዜ ወደ መሬት ይወድቃል ይላል፡፡ በዚህ አስተሳሰቡ የተስማማ ማንም ሰው፤ የስነ ስበት (የግራቪቲ) ጽንሰ ሀሳብ ላይ ሊደርስ አይችልም፡፡ ሁሉም ሰው የተሳሳተ ሊሆን እንደሚችል የማይጠረጥረው እምነት ላይ የተገነባ እውቀት… ያልተጠረጠረው እውነት ውሸት ቢሆን፤ እውቀቱ ገደል ይገባል፡፡
በአንድ እውነት ላይ መሰረት አድርገን የምናያይዘው የሀሳብ ገመድ “ዲዳክሽን” ተብሎ ይጠራል፡፡ የምጽፍበት ጠረጴዛ በቁጥር አራት እግር ካለው ወዲያ ማዶ ካለው ጠረጴዛ ጋር በአንድ ላይ ስምንት እግር አላቸው፤ ካልን፤ ስሌታችን (ትንቢታችን ትክክል ነው፡፡ ግን መጀመሪያ አንዱ ጠረጴዛ አራት እግር እንዳለው እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ የመነሻው እውነት እምነት ከሆነ… የምንሠራው ስሌት እውቀት ሳይሆን እብደት መሆኑ ያሰጋል፡፡
ጋሊሊዮ ጋሊሊ የአሪስጣጣሊስን የመነሻ እውነት ለመፈተን ባይነሳ ኖሮ…የሰው ልጅ ስለ ግራቪቲ ትክክለኛ ባህሪ ወደማወቅ አይመጣም ነበር፡፡ ሳይንስ በ”Common sense” አይሰራም፡፡ ጋሊሊዮ በገዳዳው የፒዛ ፎቅ ላይ ወጥቶ ሁለት በክብደት የተለያዩ ነገሮችን ሰው በተሰበሰበበት በእኩል ቅጽበት ወደ መሬት ለቀቃቸው፡፡ ሁለቱም ነገሮች እኩል አረፉ፡፡ ሁሉም ሰው ያለ ጥርጥር የሚቀበለው ነገር በድንገት ሲለካ… ውሸት ሆነ፡፡ መለኪያው ሳይንስ የሆነው፤ በሎጂክ ወይንም በምክንያታዊነት ብቻ ሳይሆን፤ በተጨባጭ ሞክሮ ማሳየት ስለሚችል ነበር፡፡
በጋሊሊዮ አማካኝነት አዲስ በሙከራ የሚረጋገጥ የተፈጥሮ ህግ አሰራርን የማወቂያ ፍልስፍና ተፈጠረ፡፡ በሙሉ ባህሪው ፍልስፍና ባለመሆኑ የላቲን ስያሜ ተሰጠው “to know (ማወቅ)” አሉት፡፡ የላቲን ቃሉ “Science” በመባል በስፋት ከዚያ በኋላ ታወቀ፡፡
ፍልስፍናም ከተጨባጭ ነገር ተነስቶ ተመልሶ ወደተጨባጭ ነባራዊ አለም ላይ የሚጠቅም እስካልሆነ ድረስ፤ ዝምድናውን ከእምነት ጋር እንጂ ከእውቀት ጋር እንዳልሆነ ተሰመረበት፡፡
ሁሉም የሰው ልጅ ከሚስማማበት እምነት መሀል አንዱ “የማንም የሰው ልጅ ህይወት እንዲጠፋ መፍቀድ የለብንም” የሚል ነው፡፡ የሞት መቀነስ የህይወት መጨመር ነው፡፡ የህዝብ ብዛትን ያስከትላል፡፡ ቶማስ ሮበርት ማልታስ የሚባል ሰው በ1798 አንድ ጥናቱን “ማንም አይሙት” ለሚለው አስተሳሰብ በተቃራኒ አቀረበ፡፡ ማንም ራዕዩን አልወደደለትም፡፡ “የምግብ አቅርቦት አቅማችን ከመዋለድ አቅማችን እኩል መራመድ አይችልም” አለ ቶማስ ማልተስ “መራመድ ባለመቻሉ ረሃብ እና ጦርነት ይከሰታል” አንዳችም ህይወት እንዳይጠፋ በሚለው እምነት ላይ መሰረት ያደረገ እውቀት ሁሉንም የሰው ህይወት አንድ ላይ ይደመስሰዋል፤ እንደ “ሲሲፈስ” ወደ ዳገቱ የምናደርገው መሻሻል ተመልሶ ወደ መሬት ለመውደቅ ነው፤ እንደ ማለት ነው፡፡ ወደ እግር ኳስ ጨዋታ ምሳሌዬ ስቀይረው:- ጨዋታውን እኛ ትክክል ነው ባልነው መንገድ ኳሱን አንከባልለን ጐል ብንከተው ውጤት አይቆጠርልንም፡፡ ተፈጥሮ በሠራው የጨዋታ ህግ እኛ የራሳችንን ህግ በግዴታ ብንተገብር በተፈጥሮ ዳኝነት ከጨዋታው እንባረራለን፡፡ ግን ተፈጥሮ የጨዋታውን ህግ ለምን አያስረዳንም?… ወይንስ እያስረዳን ይሆን?... ደደብ ሆነን ቢሆንስ?... ኳሱን በደንብ ለመጫወት መደደብ ግዴታ ቢሆንስ…? …እውነት ብለን የያዝነውን ማንኛውንም አይነት የእውቀት መነሻ በሙሉ መመርመር አለብን፡፡ ብዙ የመነሻ እውነቶች አሉን፡፡ ለምሳሌ:- መልካም እኩይን ያሸንፋል አንዱ እምነታችን ነው፤ ሰው ለነፃነት የተገባ ፍጡር ነው ሌላው… እንዲደረግብህ የማትፈልገውን በሌሎች አታድርግ፣ የሰው ልጅ በመሰረቱ ምክንያታዊ ፍጡር ነው፣ ከምንም ነገር በፊት ቀዳሚው በህይወት መቆየት ነው፣ እውነት ትዘገያለች እንጂ መውጣቷ አይቀርም ወዘተ፡፡ ሌላም ብዙ እውነቶች አሉን፡፡
ሁሉም የመነሻ እውነቶቻችን (Axiom) ናቸው፡፡ በእነዚህ የመነሻ እውነቶች አማካይነት ነው እውቀቶቻችንን የምንገነባው፤ ውሸቶቻችንን የምናነጽረው፡፡
አሪስጣጣሊስም የራሱን የመነሻ እውነት ይዞ ተፈላሰፈ፡፡ እውቀትን ለዘመኑ አለም አበረከተ፡፡ የሱን ፍልስፍና ይዞ… አለም የእግር ኳስ ጨዋታውን ተጫወተ፡፡ የተፈጥሮ ጨዋታ ህግ “The law of identity” በአሪስጣጣሊስ ቀመር መሆን አለበት ተባለ፤ ሆነ፡፡ ስህተቶቹ ቀስ እያሉ ነው ብቅ ያሉት፡፡ እውነት እንደሆኑ እርግጠኛ የሆንንባቸው ነገሮች፤ በተጨባጭ መለኪያ ውሸት ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡ የዳርዊን የመነሻ እውነት ደግሞ “የእግር ኳስ ጨዋታው ህግ በራሱ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ኳሷን ራሷን ወደ ማሊያ ለባሽ ተጫዋች ነገር ሊቀይር ይችላል” ይለናል፡፡ የሱም የመነሻ እውነት “ምክንያታዊ” ቢሆንም፤ እውቀት ነው ለማለት ግን… ብዙ ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ያስፈልጉታል፡፡ የጨዋታውን ህግ ሳናውቀው መጫወታችን፤ ስንጫወት ኖረን መሞታችንስ አይገርምም?

 

Read 3582 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 14:58