Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 14:58

“ችግራችን ብዙ ስለሆነ ብዙ ትያትር ያስፈልገናል”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አርቲስት ዘካሪያስ የድሮ ጋዜጠኝነት የአሁኑን ያስንቃል ይላል … 
- ኢትዮጵያ እንግሊዝን መርዳቷ አስገርሞታል
- የ”ስውር መንገደኞች”ን ደራሲ ብስለት አድንቋል
የመጀመርያ የሙሉ ጊዜ ትያትሩን የ19 ዓመት ወጣት ሳለ በአዲስ አበባ ባህልና ትያትር አዳራሽ አቅርቧል፡፡ ጋዜጠኝነቴንና የትያትር ደራሲነቴን እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ ይዤ ለመዝለቅ እፈልጋለሁ የሚለው ዘርፈ ብዙው የጥበብ ባለሙያ ዘካርያስ ብርሃኑ፤ በቅርቡ በብሔራዊ ትያትር “ዕጣ ፈለግ” የሚል ትያትር ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የጥበባት እና መዝናኛ አርታዒ የሆነው ዘካርያስ፤ የደራሲ አንተነህ ይግዛው ድርሰት የሆነውን “ስውር መንገደኞች” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በማዘጋጀትና “ትዝ አለኝ የጥንቱ” የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅቶ በማቅረብ እየሰራ ይገኛል፡፡ ገና ያልወጡ ሦስት ትያትሮች አሉኝ የሚለው ዘካርያስ፤ ስለ ዘርፈ ብዙ የጥበብ ሰውነቱ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለሙያውና ስለ ጥበብ ስራዎቹ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከመልካሙ ተክሌ ጋር አድርጓል፡፡

ስለ “ዕጣ ፈለግ” ቲያትር ድርሰትና ዝግጅት ንገረኝ … እንዴትና መቼ ተፃፈ?  
ምንም እንኳ ትያትሩ ሰሞኑን ቢወጣም ከተፃፈ ስምንት ዓመት ይሆነዋል፡፡ ፅፌ በመጨረስ የፈረምኩበት በየካቲት 1996 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ ምን እንዳነሳሳኝ አላውቀውም፡፡ ሀሳቦች በየትኛውም ጊዜ ይመጣሉ፤ ብልጭ ይላሉ፡፡ ቀልብህ እንዳዘዘህ ተነስተህ ትፅፋለህ፡፡ ደራሲ ነኝ፤ በየትኛውም ርእስ ጉዳይ ላይ መፃፍ እችላለሁ፡፡
“ዕጣ ፈለግ” በ1998 ዓ.ም ለተመልካች ቀርቦ ነበር፡፡ ለምን በድጋሚ መጣ? ትያትሮችን በድጋሚ ማሳየት እንደፋሽን የተያዘ ይመስላል …
ፋሽን ሆኖ አይደለም፡፡ የትያትር እጥረትም አልገጠመም፡፡ ከጠቀስካቸው የተደገሙ ትያትሮች የ”ዕጣ ፈለግ” ፍፁም ይለያል፡፡ እንዳልከው በ98 ዓ.ም ተገምግሞ አልፎ በብሔራዊ ትያትር እየታየ ነበረ፡፡ ወቅቱ ደግሞ የምርጫ 97 ትኩሳት ያልበረደበት ነበር፡፡ ፊልሞችም እንደወረት የወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ምን እንደሆነ ምክንያቱ ባይጠናም የትያትር ተመልካቾች ድርቀት ነበር፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ብዙም ሳይዘልቅ ይኼን ጊዜ አልፈን እናውጣው በሚል ከትያትር ቤቱ ሃላፊዎች ጋር ተነጋግረን ነው ያቆየነው፤ ምንም እንኳ አሁን እንደገና ተገምግሞ እንደ አዲስ ቢወጣም፡፡
በሳምንት አንድ ጊዜ እየታየ ለአራት ወር ብቻ ነው የቆየው፡፡ እንደ ፊልም በሳምንት ብዙ ጊዜ ቀርቦ አይደለም፡፡ ስለዚህ ትያትሩ አዲስ ነው ማለት ይቻላል፡
ተዋናዮቹም አዲስ ናቸው፣ ታዋቂ አይደሉም፡፡ በአዳዲስ ባለሙያ መስራት አይከብድም? አብዛኞቹ የትያትር ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ፅንሰሀሳቡን የሚያውቁ፣ በተወሠነ ደረጃ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ክፍል ምሩቃን የሆኑ ጓደኞቼ ናቸው፡፡ ፊልሞች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ትያትሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ግን በመደበኛነት፣ ፕሮፌሽናል ሆነው ትያትር እየሰሩ አይደለም፡፡ ሌላ ሥራ ነው ያላቸው፡፡ ለምሣሌ ትያትሩን አብሮኝ ያዘጋጀው ታጠቅ ነጋሽ የትያትር ባለሙያ ነው፡፡ የባንክ ባለሙያም ነው፡፡
ብዙም ባልታወቁ ባለሙያዎች ትያትር ይዘህ ስትመጣ ስጋት አላደረብህም?
ለገበያ ወይም ተመልካች ለማግኘት ዝነኛ የሆኑ ተዋንያንን ማሳተፍ ይቻላል፡፡ አንጋፋና ወጣቶችን በማቀላቀልም የሚሰሩ አሉ፡፡ እኔ ግን በዚያ አላምንም፡፡ ተመልካቹም እንደዚያ ያምናል ብዬ አላስብም፡፡ አብዛኛው ተመልካች ጥሩ ሥራ ነው የሚፈልገው እንጂ የሚያውቀውን ተዋናይ ስላየ አይደለም፡፡ ጥሩ ተዋናይም ይዘው በተመልካች ደረጃ ጥሩ ያልሆነ ምላሽ የገጠማቸው ትያትሮች እና ፊልሞች አሉ፡፡ ዝናን በሚያመጣ ሥራ እንጂ ዝነኛ በሆነ አርቲስት የጥበብ ሥራ አሰርቶ ገበያ በመሳብ አላምንም፡፡ እኔ የማምነው ጥሩ ሥራ ሠርቶ ተመልካች ማምጣት ነው፡፡ በራሳቸው የሚተማመኑ ተዋንያንን ነው በ”እጣ ፈለግ” የመለመልኩት፡፡ ጥሩ ድርሰት እና ጥሩ ተዋንያን ተዋህደው የሰሩት ሥራ ነው፡፡ ትያትር ቤቶች በተለይ ብሔራዊ ትያትር በትያትር ግምገማ ሂደት ጥሩ ተዋናይ ካልሆነ ይቀንሳል፡፡ የመቀነስ ሀላፊነትና ግዴታ አለበት፤ ጥሩ የማይሰሩትን፡፡ የሚገመገሙ ፊልሞች በሙሉ የሀገሪቱን መልካም እሴቶች እስካንፀባረቁ መታየት ይችላሉ፡፡ በትያትር ግን ተገምግሞ መውደቅና ማለፍ አለ፡፡ ትያትሩ ቤቱን ይመጥናል አይመጥንም የሚለውን የሚያዩት ከድርሰት፣ ከዝግጅትና ከትወና አኳያ ነው፡፡ አሁን ያየኻቸው የ”ዕጣ ፈለግ” ተዋንያን በትወና ብቃት ተመዝነው ያለፉ ናቸው፡፡
ተዋንያኑ ጓደኞቼ ናቸዉ ብለሃል … ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳርፍም …
እኛ በጣም የምንተዋወቅ ልጆች ነን፡፡ በየትኛውም የፊልም እና የትያትር ሥራዎች ላይ አዘጋጁ የሚመድበው የሚያውቃቸው ሰዎች ነው፡፡ የሚያውቃቸውን ማለት ወዳጆቹን ማለት ሳይሆን በሥራ የሚያውቃቸውን ማለት ነው፡፡ እኔም በጥሩ ሥራቸው የማውቃቸውን ተዋንያን ነው የመለመልኩት፡፡ ትያትር ያገናኘን ወዳጆች ነን፡፡ ወዳጅነታችን የመጣው ከጥሩ ሥራችን በኋላ ነው፡፡
የትያትር ቤቱ ዝግጅት ባለመሆኑ የመለማመጃ ቦታ አልቸገራችሁም?
ችግር ነው፡፡ በራሳችን መለማመጃ ቦታ፣ በራሳችን ጊዜ በራሳችን ሁሉም ነገር ነው ትያትሩን ሰርተን ያጠናቀቅነው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር እርዳታ ሁሉንም ነገር በራሳችን ችለን ተወጥተነዋል፡፡ ከመደበኛ ሥራችን ፈቃድ ሳንወጣ ከሥራ መልስ ምሽት ላይ ነበር የምንለማመደው፤ በተለይ ቅዳሜና እሁድ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ካስፈለገ ድር ፋውንዴሽን አዳራሽ ነበር የሠራነው፡፡ አብሮን በተማረው በኤርምያስ ፀጋዬ አማካኝነት የተመቻቸ ነው፡፡
የብሔራዊ ትያትርን ግምገማ ካለፈ በኋላ “ዕጣ ፈለግ” ሳይወጣ ዘጠኝ ወር የቆየው ለምንድው?
እንዲህ አይነት ነገር በትያትር ቤቶች ያለ ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት አንድ ትያትር መታየት ጀምሮ እስከሚወርድ የጊዜ ገደብ አለመኖሩ ነው፡፡ እናም እየታየ ያለ ትያትር ቦታ እስኪለቅ መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ቀጫጭን ቢሮክራሲዎች ነበሩ፡፡ ያም ሆነ ይህ ብሔራዊ ትያትርን እናመሠግነዋለን፡፡ በተለይ ገምጋሚዎቹ ከኛ አልተለዩም፡፡ ዋና ሥራቸውን ከሰሩ በኋላ አብሮ በማስተካከል፣ የሚታረሙትን በማረም ረድተውናል፡፡
“ዕጣ ፈለግ” የአንድ ሌሊት መቼት ነው፡፡ ይህ በሙሉ ሰዓት ቴአትርነት አያስቸግርም?
ያስቸግራል፡፡ ጥሩ ፀሐፊ እስካላገኘ ድረስ ያስቸግራል፡፡ ጥሩ ቴክኒክም ከሌለ ያስቸግራል፡፡ ጥሩ ታሪክ፣ ጥሩ ሴራና ጥሩ ቴክኒክ ያስፈልጋል፡፡ “ፎን ቡዝ” የሚል ፊልም አለ፡፡ ተጀምሮ የሚያልቀው በአንድ የሕዝብ ስልክ ቦታ ነው፡፡ የምታነሳው ታሪክ፣ አውድ … ይወስነዋል፡፡ እነዚህን የማሳካት ልምዱ ካለህ ትችለዋለህ፡፡
በ “ዕጣ ፈለግ” “የችግር ክፋቱ መለመዱ” የሚል አባባል አለ፡፡ ምን ማለት ነው?
አሪፍ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ይጠይቁኛል፡፡ ትያትሩ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ዋና ሀሳብ አምቆ የያዘ አባባል ነው፡፡ በርግጥም የችግራችን፣ የድህነታችን አንዱ ምክንያት አብሮን ለረጅም ጊዜ እንዲኖር መፍቀዳችን ነው፡፡ ችግር የሚፈጠረው እንዲፈታ ነው፡፡ ፈቺ ካላገኘ ይላመዳል፡፡ ድህነታችንን ሳንጠየፍ ቆይተናል፡፡ ይቺን ማን አየብኝ፣ ተመስገን ነው ወዘተ በሚሉ ተለምዷዊ አባባሎች ችግራችንን ታቅፈን ኖረናል፡፡
በጋዜጠኝነት፣ በፀሐፌተውኔትነት፣ በፊልም ባለሙያነት፣ በተዋናይነት፤ በሬዲዮ ድራማ አዘጋጅነት ትሰራለህ፡፡ ወደ የትኛው ታደላለህ?
ሥነ ፅሑፍ ተምሬአለሁ፡፡ በትያትርም ተመርቄአለሁ፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጋዜጠኝነት ልገባ የቻልኩት በሥነፅሑፉ ነው፡፡ በፊልሞች ላይ በፅሑፍም በትወናም ተሳትፌአለሁ፡፡ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሬዲዮ ድራማዎችን አዘጋጃለሁ፡፡ የመዝናኛና ኪነጥበብ ዝግጅቶች አስተባብራለሁ፤ ረዳት ዋና አዘጋጅ ነኝ፡፡
ትያትር፣ የሬዲዮ ድራማ ወይም ፊልም ከማዘጋጀት የትኛው ይበልጥ አድካሚ ነው ትላለህ?
ሁሉም ልፋት አለበት፡፡ የመድረክና የሬዲዮ ተውኔት ላይ ትልቁ ሥራ የደራሲው ነው፡፡ ፊልም ላይ የአዘጋጁ ሚና በአንፃራዊነት ከፍ ይላል፡፡ በሁሉም ሥራ ውስጥ የመጨረሻው ሃላፊና ወሳኙ ሰው አዘጋጁ ነው፡፡
ከቆዩ ሰነዶች የሚገኙ መረጃዎችን ከድሮ ዘፈኖች ጋር በማዋሀድ “ትዝ አለኝ” የጥንቱን የሬዲዮ ፕሮግራምን ስትሰራ በጣም ያስገረሙህ የቆዩ ፅሁፎች ይኖሩ ይሆን?
ፕሮግራሙን በዚህ መልኩ ማዘጋጀት የጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡ አራት ዓመት አልፎታል፡፡ ዝግጅቱ አዝናኝና ልዩ መረጃ ሰጪ ነው፡፡ ፅሁፎች ከቆዩ የሕትመት ውጤቶች ይቀርቡበታል፡፡ ብዙ አስገራሚ ፅሁፎች ገጥመውኛል፡፡ ከነዚህም መካከል “ኢትዮጵያ እንግሊዝን ረዳች” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ እህል ከብቶችና ገንዘብ ነው የተላከው፤ ለእንግሊዝ፡፡ ለነገሩ በዘመናችንስ ጃፓንን ረድተን የለ፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረው የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርም ይገርመኛል፡፡ ርእሰ አንቀፆቹም ጠንካራና ሳቢ ነበሩ፤ የዜና ርእሶቹም እንደዚያው፡፡ ይዘታቸውም ዜና አፃፃፋቸውም መሳጭ እና በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ከብዙ ነገር አኳያ ጋዜጠኝነት ድሮ ቀረ ሊያሰኙ ይችላሉ፡፡ አሁን በቴክኖሎጂ እየታገዝን ነው፡፡ የያኔዋ ዓለም ሰፊ ነበረች፤ አሁን በቴክኖሎጂ ጠባለች፡፡ ድሮ የፈለጉትን ያህል መረጃ አይገኝም ነበር፡፡ ያኔ ይቅርታ አድርግልኝና የመጠቀ ጋዜጠኝነት ነበር፡፡
በ”ትዝ አለኝ የጥንቱ” በተለይ የአያሌው መስፍን፣ ፍሬው ሃይሉና አለማየሁ እሸቴን ዘፈኖች በተደጋጋሚ የምትጋብዝበት የተለየ ምክንያት አለህ?
ትዝብትህ ትክክል ነው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማህሙድ አህመድ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ አያሌው መሥፍን፣ ፍሬው ኃይሉ በንፅፅር ይደጋገማሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ የሚደጋገሙ ዘፋኞች ብዙ ዘፈኖች ስላሏቸው ነው፡፡ ሌላው ቢቀር በበፊቱ የክብር ዘበኛ አሠራር ጥላሁን ገሠሠ ዘፈኖች እኮ ተመርጠው ነው የሚሰጡት፡፡ ክብር ዘበኛ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ውድድርም ስለነበረ ይኼን እገሌ ይዝፈን ይባል ነበር እንጂ እንደ አሁን ራስህ መርጠህ አትዘፍንም፡፡ ጥላሁን ደግሞ ያኔም ታዋቂ ስለነበር ብዙ ዘፈኖች አሉት፡፡ ሌሎቹም ድምፃውያን እንደዚያው ድምፃውያኑ በወቅቱ ዝነኞች መሆናቸው ብዙ ዘፈን እንዲያስቀርፁ ምክንያት ሆኖም ሊሆን ይችላል፡፡
ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ እንዴት ይመረጣል? እንዴት ይዘጋጃል?
ድራማዎች ወደ ኤፍቢሲ ሲመጡ ሥርዓት አላቸው፡፡ ማስታወቂያ በማውጣት የምናውቃቸውን ሰዎች ተወዳደሩ ብለንም እንጋብዛለን፡፡ ጋዜጠኞች ቢሆኑም የድራማ ትምህርትና ልምድ ያላቸው የኮሚቴ አባላት ሆነው ይገመግማሉ፡፡ ደራስያን ለማወዳደር የሚያስገቡት አምስት ክፍል ያለቀለት እና የሃምሳ ክፍል አፅመ ታሪክ ነው፡፡ የሚገመገሙት በዚያ ነው፡፡ በኮሚቴው ተገምግመው ብቃት ሲረጋገጥ አንዱ ይመረጥና ይዘጋጃል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው “ጠጣር ፍሬ”ን ደራሲው ይታገሱ ገሰጥ ያስገባው በዚህ መልኩ ነው፡፡ በ56 ክፍል ሲያልቅ ጥሩ ግብረ መልስ /feedback/ ነበረው፡፡ የአሁኑ “ስውር መንገደኞች” በየሳምንቱ እየተደመጠ 15 ክፍል ደርሷል፡፡ ደራሲው አንተነህ ይግዛው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚፅፋቸው ፅሑፎችና “መልስ አዳኝ” በተሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች መፅሐፍ ይታወቃል፡፡ እጅግ በሳል እና አስገራሚ ደራሲ ነው፤ እውነቱን ለመናገር፡፡ ቀድሞ የተወሠነ ክፍል ያመጣልኛል፤ የሚስተካከል ካለ አስተካክዬ ለተዋንያን እሰጣለሁ፡፡ ከዚያ አምስት ክፍል ቀድሞ ይቀረፃል፡፡ እያንዳንዱ ክፍል በአማካይ ለ25 ደቂቃ ይደመጣል፡፡ ይህን ለማቅረብ ቢያንስ ሁለት ሰአት ያህል ቀረፃ ይደረጋል፡፡ ስህተት ሲኖር እንደገና ትቀርፃለህ፤ አሁን እየቀረ መጣ እንጂ በሪል ቴፕ ከሆነ የመጨረሻ ያለቀለትን ድራማ ነው የምትቀርፀው፡፡ አሁን ድራማውን በዲጂታል ስንቀርፅ መሳሳት የማይቀር ነው፡፡ ተዋንያኑ እስከፈለጉ ይሳሳታሉ፤ እስከፈለኩ አርማቸዋለሁ፡፡ የአርትኦት ሥራውን የምሰራው እና ቀድሜም የምቀርፀው እኔ ነኝ፡፡ ቴክኒሻኖች አይኖሩም፤ በዘመናዊው አሠራር፡፡
“ስውር መንገደኞች” የሚተላለፍበት ሰዓት ለአድማጭ ምቹ አይደለም የሚል ቅሬታ ሰምቻለሁ …
በየትኛውም ሰዓት አስተላልፈው ያ ዝግጅት ጥሩ እስከ ሆነ ድረስ የትኛውም ሰዓት ላይ አድማጭ አለ፡፡ ሰዓቱ ሳይሆን ጥሩ ዝግጅትነቱ ነው ወሳኙ፡፡
የሥራ ውጥረት ቤተሰባዊ ህይወትህ ላይ ችግር አልፈጠረብህም?
ጋዜጠኛ ነኝ፡፡ ከጋዜጠኛም የሬዲዮ ፋና ጋዜጠኛ፡፡ ፋና ውስጥ ብዙ ሥራ ይሰራል፡፡ ከመደበኛዬ ሥራዬ በተጨማሪ የጣቢያውን ድራማ አዘጋጃለሁ፡፡ የድራማው ቀረፃና አርትኦት ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ መደበኛ የጋዜጠኝነት የአርትኦት ሥራዬም እንደዚያው፡፡ በዚህ ምክንያት ለሊት የምወጣበትና አምሽቼ የምገባበት ጊዜ ይበዛል፡፡
መጀመርያ ድምፅህ አየር ላይ ሲውል ምን ብለህ እንደተናገርክ ታስታውሳለህ?
ሬዲዮ ፋና፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሆኖ ወደ አዲሱ ሕንፃ ሲገባ አየር ላይ የዋለው የመጀመርያ ድምፅ የእኔና የጋዜጠኛ ራህዋ ይፍጠር ነው፡፡ የመጀመርያ ድምፄ ደግሞ ኤፍኤም 98.1 ተመርቆ ሥራውን ሲጀምር ከረጲ ዋና ዝግጅት ስፍራ በቀጥታ ስርጭት /Live/ ዘግቤአለሁ፡፡ ከተቀጠርን ከአራት ወር በኋላ ነው ኤፍኤሙ የተከፈተው፡፡ ከዚያ ቀድሞ በሬዲዮ ፋና መካከለኛ ሞገድ በሚሰራጨው ፕሮግራም የገበያ ሁኔታ፤ ከሾላ የዘገብኩት የመጀመርያ የሬዲዮና ድምፄ ነው፡፡
ከ“ዕጣ ፈለግ” ሌላ የሰራኻቸው ትያትሮች …?
“የተረሳው ዕዳ” በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ፤ “ናፋቂዎች” የተሰኘውን ደግሞ በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት አቅርቤአለሁ፡፡
ጋዜጠኝነትና ደራሲነት ምን ያህል ይቀራረባሉ? ምናልባት አንዱን መምረጥ ቢኖርብህ ለየትኛው ታደላለህ?
ጋዜጠኝነትና ድርሰት አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ እነ ጳውሎስ ኞኞ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን ሌሎችም ሁለቱን አጣምረው ሲሰሩ ነበር፡፡ ምንም እንኳ እስካሁን የፃፍኳቸው ትያትሮች በሙሉ ጋዜጠኝነት ከመጀመሬ በፊት ቢሆንም ጋዜጠኝነቴ ለትያትር ደራሲነቴ አግዞኛል፡፡ አንዱን ብቻ መምረጥ ካለብኝ ደራሲነቴን እመርጣለሁ፡፡
“ስውር መንገደኞች” ከሌሎች የሬዲዮ ድራማዎች የሚለየው ምንድነው?
ዋና ገፀ-ባህርዮቹ ድምፃውያን ናቸው፡፡ ድምፃውያን ከመሆናቸው ጋር አንዳንድ ትዕይንቶች ስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ እየሰሩ ነው የሚቀረፁት፡፡ የሙዚቃ ቡድን እንዲመስል ኦርጋንና ሌሎች የሙዚቃ መሳርያዎች አስገብተን እያንጎራጎሩ የቀረፅንበት ከባድ ቀረፃ አለ፡፡ የመለመልኳቸው ዋና ተዋንያን ድምፃውያን ናቸው፡፡ ትዕግስት ግርማ የተዋጣላት ድምፃዊትና ተዋናይ ነች፡፡ በግሌ አደንቃታለሁ፡፡ መኮንን ተፈሪ እና ሽመልስ አበራም እንደዚያው፡፡ በተዋንያን ምልመላ ረክቻለሁ፡፡
ከአንጋፋና ወጣት አርቲስቶች ጋር ትሰራለህ፤ አነፃፅራቸው እስቲ …
ፍቃዱ ተክለማርያም እና ሽመልስ አበራ ልምምድ ጨርሰን ቀረፃ ውስጥ ሲገቡ ያማትባሉ፤ ፀሎት ያደርጋሉ፡፡ ሙያውን ይበልጥ በማክበራቸውና ለሚሊየኖች እንደሚደርስ ስለሚያውቁ የሚያደርጉት መንፈሳዊ ዝግጅት ነው፡፡ ወጣቶቹ ሲያደርጉ አላየሁም፡፡ ይኼ ስለቀደሙትና ስለአሁኖቹ አርቲስቶች የሚነግረን አለ፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያህ ምን አተረፍኩ ትላለህ … ከእርካታም አንፃር ሊሆን ይችላል …
ጋዜጠኛ መሆን ሁሌም ከአዳዲስ ነገሮች ጋር መተዋወቅ ነው፡፡ መግለፅ ከምችለው በላይ ብዙ ነገሮችን የተዋወኩት ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው፡፡ ለግሌ ይህን አትርፌአለሁ፡፡ በምሠራቸው ሥራዎች ደግሞ ለብዙ ሰዎች ተርፌ ሊሆን ይችላል፡፡
በሕይወትህ የመጨረሻ ቀናት ምን ብትሠራ ትመርጣለህ?
ብዙ ትያትሮች መፃፍ እፈልጋለሁ፡፡ አቅሙም ተሰጥኦውም አለኝ፡፡ እስከ ዛሬ የሠራሁዋቸው ይሄንኑ ይመሠክራሉ፡፡
ሁልጊዜ የምፀልየው ብዙ ትያትሮችን እንድፅፍ ነው፡፡ በሀሳብ ደረጃ የተቀመጡ አሉ፡፡ አሪፍ ልምዴ ሀሳብ ሲመጣልኝ በአጭሩ ፅፌ ማስቀመጤ ነው፡፡ እነዚህን እየዘገንኩ ነው ትያትር እና ፊልም የምፅፈው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገና ያልወጡ ሦስት ትያትሮች አሉኝ፡፡ በብዙ ትያትሮቼ ፅሑፍ ውስጥ ለሀገር የሚጠቅም አዳዲስ ሀሳብ አለ፡፡ ችግራችን ብዙ ስለሆነ ብዙ ትያትር ያስፈልገናል፡፡ ትያትር የችግር መቅረፊያ ነው እያልኩህ አይደለም፡፡ በትያትር ውስጥ ግን ችግር መቅረፊያ መንገዶች ትመለከታለህ፡፡

 

Read 6769 times Last modified on Tuesday, 22 November 2011 14:13