Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 19 November 2011 15:00

ዘመቻ ድራገን

Written by 
Rate this item
(4 votes)

… ኣቡ እስማኤል አባታዊ ፈገግታ እያሳየ “ለዓላማችን ድጋፍ ትሰጣለህ” አለው፡፡
ፋውዚ ተጨማሪ አረቄ ቀዳ “እኔ ሽብርተኛ አይደለሁም…አንድን መሳሪያ ከሌላው መለየት አልችልም” አለ ረጋ ባለ ድምጽ
“መለየት አያስፈልግህም የሚያስፈልግህ የራስ ማጥፋት ኑዛዜ መፃፍ ብቻ ነው” ሲለው ቀዝቃዛ ላብ አጠመቀው “ምን…?”
“እኔ እየነገርኩህ ትጽፋለህ”
“ልረዳህ አልችልም…ከሞትኩ”
“የላሉ ጫፎችን መቋጠር አስፈላጊ ነው” ሲለው
ፋውዚ እየተደረመሰ ካለው ዓለሙ አንድ ትርጉም ያለው ነገር ለማውጣት እየሞከረ “ስራዬስ?” አለ፡፡

“ስራህ ከእኛ ጋር ነው”
ፋውዚ ሶስተኛ ዙር ቀዳ “ምንም ምክንያት አይኖረኝም…ማንም አያምነኝም” አለ
“ጥራው እድሪስ” ሲል
እድሪስ ወደ ኩሽናው ዞሮ “ታላት” ሲል ተጣራ፡፡ የገረጣና ፊቱ ላይ በመደብዘዝ ላይ ያለ ጠባሳ የሚታይበት ሰው ብቅ ሲል ፋውዚ ድካም ውስጥ የሚከት ድንጋጤ ወረረው፡፡
“ያንተ መንትያ ነው ፕሮፌሰር…በስምህ ምላሽ ይሰጣል”
“ግን ማነው?”
“ከተዋጊዎቼ አንዱ ነው … ለዚህ ግዳጅ ራሱን በፈቃደኝነት ያበረከተ”
ፋውዚ መንትያው ላይ ሲያፈጥ ስነ ልቦናዊ ብዥታ ውስጥ የነበረው ሰው ፈገግ አለ፡፡
“ከየት አገኘኸው?”
“በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሰራነው፤ ስፌቱ በመጠኑ ቢታይም ፊቱ ላይ የሚያሳጣ የቁስል ምልክት የለውም” ሲለው
ፋውዚ ሀሞቱ እየመረረው በጣም እንደምትፈልገኝ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም ግን አልተባበርህም፡፡ ድርጊቶችህን በሙሉ እቃወማለሁ፤ ሽብር ግድያ …” አለ በቁጣ፡፡ “ክርስትያን አይሁድና አረብ አንድ አልጋ ላይ የሚተኙበትን ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት የምታልም ሀቀኛ ምዕመን ነህ” ሲለው ፋውዚ ብድግ ብሎ “ውጣ” ከማለቱ ኣቡ እስማኤል ሽጉጡን መዘዘ “ፕሮፌሰር ልብ ብለህ ተመልከት፡ ማድረግ የምችለውን ላሳይህ እፈልጋለሁ” በማለት ወደ ፋውዚ መንትያ ዞሮ “ታላት ወደዚህ ቀረብ በል” ሲለው የፋውዚ መንትያ በተጠንቀቅ ቆሞ “እዘዘኝ አል ማህዲ” አለ
ፋውዚ ይህን የቅዱስ ኢማም ስም የጠራውን መንትያውን በድንጋጤ መመልከት ጀመረ፡፡ ኣቡ እስማኤል ሽጉጡን እየሰጠው “ሽጉጡን ይዘህ ወደ በረንዳው ወጥተህ ለመጨረሻ ጊዜ አየር በረጅሙ ሳብ” ሲለው “ታዛዥ ነኝ አል ማህዲ” ብሎ ሽጉጡን ተቀብሎ በሩን ከፍቶ ወደ በረንዳው ወጣ፡፡
ኣቡ እስማኤል ወደ ፋውዚ ዞረ “አሁን የራስ ማጥፋት ኑዛዜውን…”
“አልፅፍም”
የእድሪስ ዓሊ ጣቶች አንገቱ ላይ ሲያርፉ ለመጮህ ሞከረ፡፡ ግን ሌላው የእድሪስ እጅ አፉ ላይ ነበር፡፡ ኣቡ እስማኤል እስክሪብቶና ከራሱ የመፃፊያ ወረቀቶች አንዱን አቀበለው
“በል ፃፍ…” “አንድ ፊዚስት ያለው አጭር የፈጠራ ህይወት ነው፤ ተቃጥሎ ካበቃ ግን ጥቅም የለውም፤ አሁን ይህ የእኔ ዕጣ - ፈንታ ሆኗል…” ብለህ ፃፍና ፈርም” ሲለው
ፋውዚ በመደነቅ አየው፡፡ ራሱን ለማጥፋት ብዙ ጊዜ አስቦበታል፡፡ ይህን ውስጣዊ ፍላጐቱን ኣቡ እስማኤል እንዴት ሊያውቅ ቻለ?
የእድሪስ ዓሊ ጣቶች ያሳደሩበት ህመም ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ሲሆንበት እንባውን እያፈሰሰ ማስታወሻው ላይ ጽፎ ፈረመ፡፡
እድሪስ ዓሊ ጣቶቹን ፈታ አደረጋቸው፡፡
ኣቡ እስማኤል ሁኔታውን በተመስጦ ሲከታተል ወደነበረው የፋውዚ መንትያ ሲዞር ቀይ ብርትኳንማ ቀለም ያላት ፀሐይ ከባህሩ ማዶ አድማስ ላይ ተንጠልጥላ ትታይ ነበር፡፡
“ታላት”
“አቤት አል ማህዲ”
“ለአላህ ክብር የመሞቻው ሰዓት አሁን ነው፤ ሽጉጡን ግንባርህ ላይ ደግነህ ሶስት ከቆጠርክ በኋላ ምላጩን ሳበው” ሲለው
“እሺ አል ማህዲ” አለ
መንትያው ትዕዛዙን ተግባራዊ ሲያደርግ ፈዞ አየው፡ ጥይቷ ስትፈነዳ በቀላችው ፀሐይ ውስጥ ለቅጽበት ያየው የተፈረካከሰ ጭንቅላት የሰውን ልጅ ጥልቅ አዕምሮ በጨረፍታ ለመመልከት ያስቻለው ምትሀታዊ ገጽታ ነበረው፡፡
(“The Last of Days” ከሚለው መፅሃፍ “ዘመቻ ድራገን” በሚል በአያሌው ካሳ ተተርጉሞ በቅርቡ ለንባብ ከበቃው የስለላ መፅሃፍ የተቀነጨበ)

Read 5278 times