Saturday, 31 August 2013 12:09

“ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ሆነን እንቀጥላለን”

Written by  ኤልሳቤት እቁባይ
Rate this item
(17 votes)

በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የገንዘብ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ይልማ ደሬሳ የተወለዱት ወይዘሮ ሶፊያ ይልማ፤ ላለፉት 22 አመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ለሁለተኛ ጊዜ የኢዴፓ ምክትል ፕሬዚደንት ሆነው በመመረጥ ፓርቲውን እያገለገሉ ነው፡፡ በደርግ እጅግ የተጎዳሁ ነኝ የሚሉት ወይዘሮ ሶፍያ፤ ኢህአዴጐችን “ደርግን የጣሉ ጀግኖች” ብለው እንደተቀበሏቸው ጠቅሰው፤ወደ ፖለቲካ የገባሁትም እነዚህን ሰዎች ለማገዝ ነበር ይላሉ። “በኋላ ግን ተስፋ መቁረጥ መጣ” ባይ ናቸው። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ፤ ከፖለቲከኛዋ ሶፊያ ይልማ ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ፣ተስፋ ያስቆረጣቸውን ጉዳይ ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ አነጋግራቸዋለች፡፡

የአገራችን የምርጫ ሥርዓት በሚያሳዝን መልኩ እየተበላሸ ነው…
ኢዴፓ ቅንጅትን አፍርሷል የሚለውን ውንጀላ አይቀበሉትም …
ንጉሱ “ጀግና መሪ”፣ ደርግ “የጥፋት መልዕክተኛ”፣ ኢህአዴግስ?

ስለራስዎ ይንገሩኝ….
ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ በትንሽነቴ እንግሊዝ ትምህርት ቤት ነው መማር የጀመርኩት፡፡ በዘጠኝ አመቴ አባቴ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው እዚያም ተምሬአለሁ፡፡ አባቴ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ትምህርቴን ቀጠልኩ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ገብቼ ተምሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ትምህርቴን ሳልጨርስ ወደ ጀርመን ሄድኩ። ምዕራብ በርሊን ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተምሬ መጣሁ፡፡ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ የጋዜጠኝነት ሙያን ስለምወድ በጋዜጠኝነት መስራት ጀመርኩ፡፡
ስራው እንዴት ነበር?
ስጀምር ሪፖርተር ነበርኩ፡፡ መንገድ ለመንገድ እየሮጥኩ ዜና እሰራለሁ፡፡ ጫማ ጠራጊውም ባለሱቁም ያውቀኝ ነበር፡፡ ባለፍኩበት መንገድ ሁሉ ሶፊ እያሉ ይጠሩኝ ነበር፡፡ ሬዲዮ እያለሁ ወይዘሮ ሮማንን አውቃቸው ነበር፡፡ ከሳቸው ስር ስር እያልኩ ሙያዬን በተግባር አዳብሬያለሁ፡፡ በጣም የማደንቃቸው ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የኔ ፍቅር የህትመት ጋዜጠኝነት ላይ ስለነበር በወቅቱ የነበሩትን ባለስልጣኖች ተማፅኜ ወደ ሄራልድ ጋዜጣ ተዛወርኩ፡፡ እዛም ስጀምር ሪፖርተር ነበርኩ፡፡ በኋላ ላይ ሹመት አገኘሁና የሴቶች አምድ አዘጋጅ ሆንኩ፡፡ ከዛ በአጋጣሚ የጋዜጣውን ኤዲተር አገባሁ፡፡ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ አንድ ላይ መስራቱ አይመችም ብዬ እኔ ሥራ ቀየርኩ፡፡
በስራዎ ከባለስልጣናት ጋር ተጋጭተው ያውቃሉ?
የሚያጋጭ ስራ ሰርቼ አላውቅም፡፡ መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠውን መንካት ወንጀል እንደሆነ አውቅ ነበር፡፡ እኔ ብዙ አደላ የነበረው ለማህበራዊ ጉዳዮች ነው፡፡ በጃንሆይ ጊዜ ብዙ ብሩክ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችም ነበሩ፡፡ ጥሩ ካልሆኑት ውስጥ አንዱ የፕሬስ ነፃነት አለመኖር ነው፡፡
ከዚያስ የት መስራት ጀመሩ?
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ቦታ ገባሁ፡፡ ረጅም አመት የሰራሁት ቴሌ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ስራውን ተውኩትና እቤቴ ቁጭ አልኩ፡፡ ከዛም ሲስተር ጀምበር ተፈራ ለሚሰሩት ትልቅ ፕሮጀክት ከሌሎች ጋር ተወዳድሬ እንድሰራ ጠየቁኝና እዛም የህዝብ ግንኙነት ሆኜ ለስምንት አመት ከሰራሁ በኋላ፣ ስራውን አቁሜ ቤቴ ቁጭ አልኩ፡፡
ወደ ፖለቲካ እንዴት ገቡ?
እኔ በደርግ መንግስት እጅግ የተጎዳሁ ሰው ነኝ። በልጅነት እድሜዬ ያገባሁት ያልኩሽ ባለቤቴ ደርግ ከገደላቸው “ስልሳዎቹ” አንዱ ነው፡፡ ተገኘ ተሻወርቅ ይባላል፡፡ ከመገደሉ በፊት ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር፡፡ ከሱ ቀደም ብሎም አባቴ ታሰሩ። ታመው ለአንድ ሳምንት ያህል ሆስፒታል ከገቡ በኋላ እስር ቤት እንደሞቱ ቁጠሪው፤ ሞቱ፡፡ ከዛም እኔና እናቴ ታሰርን፡፡ እጅግ በጣም አስከፊ በሆነ ሁኔታ ነበር የታሰርነው፡፡ ጣሊያን በሰራው የድንጋይ ንጣፍ ላይ እየተኛን ክፉ ዘመን አሳለፍን። ስታሰር የመጀመሪያ ልጄ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ እኔን ከመስሪያ ቤት ስለሆነ የወሰዱኝ ከትምህርት ቤት የሚመልሰው ሰው በማጣቱ፣ ከምሽቱ ሶስት ሰአት ነበር የተገኘው፡፡ ብዙ ችግሮች ላይ ወድቀን ነበር፡፡ ይሄ ቁስል ሆኖብኝ ስኖር ደርግ ወደቀ፡፡ እኔም በምችለው አቅም ለዚች አገር ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ መስራት አለብኝ አልኩና በወቅቱ “ኢድሃቅ” የሚባለውን ድርጅት ተቀላቀልኩ፡፡ ወቅቱ ፓርቲዎች እንደ እንጉዳይ የፈሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ያንን አየንና ጠንካራ ለመሆን፣ ለምን ከጠንካራ ፓርቲ ጋር ውህደት አድርገን አንሰራም በሚል፣ በአቶ ልደቱ አያሌው ጋባዥነት “ኢድሃቅ” የወቅቱን “ኢዴአፓ” ተቀላቀለ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በፓርቲው ውስጥ እያገለገልኩ ነው፡፡
በምን ሀላፊነት?
አሁን ለሁለተኛ ጊዜ የኢዴፓ ምክትል ፕሬዚደንት ነኝ፡፡ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ፓርቲዬን እየወከልኩ እሄዳለሁ፡፡ ፓርቲያችንን አስተዋውቃለሁ፡፡ የኢዴፓ ጠንካራ ቡድን የሚገኘው እንግሊዝ አገር ነው፡፡
ምርጫ እየደረሰ ነው?
አዎ ኢዴፓ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት በየሁለት አመቱ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል። የስልጣን ማራዘምም ካለ ጠቅላላ ጉባኤው ይወስናል፡፡ በቅርቡም ጠቅላላ ጉባኤ ይኖራል፡፡ የስራ ዘመናቸውን የጨረሱ በምርጫ ለሚመጣው ያስረክባሉ፡፡ ይህ እንደ ፖለቲካ ባህል እንዲያዝ እንፈልጋለን፡፡ አንድ ሰው ምንም ያህል ብርቱ እና አዋቂ ቢሆን ከሱ ሌላ የለም ብሎ ማመን ትክክል አይደለም፡፡ በውስጣችን ብዙ ጠንካራ ሰዎች እንዳሉ ስለምናውቅ እድሉ ይሰጣል፡፡ ያለበለዚያ ፓርቲው በአንድ ሰው ብቻ የሚታወቅና የሚታይ ይሆናል። ፓርቲ ደግሞ የግለሰብ ሳይሆን ተስማምተው የሚሰሩ ሰዎች ስብስብ ነው፡፡
የፖለቲካ ጉዞው ምን ይመስላል?
የተቃዋሚው ፖለቲካ በየወቅቱ ይለያያል። አንዴ ጠንካራ ይሆናል፤ ሌላ ጊዜ ይዳከማል፡፡ ለዚህ ከመንግስት በኩል ያለው ተፅእኖ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ፖለቲካውን ከተቀላቀልኩ በኋላ ባሉት አመታት የሚያስደስቱም የሚያሳዝኑም ሁኔታዎችን አይቻለሁ፡፡ በጣም አስደሳች የነበረውና በኋላ ሳያምርበት ቀረ እንጂ አራት ፓርቲዎች ሆነው የመሰረቱት ቅንጅት ነው፡፡ ቅንጅት በኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ፤ ከህዝብ ትልቅ ፍቅር የተሰጠው ፓርቲ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ይዞ አልቀጠለም፡፡ ነገሮች ከመበላሸታቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ሁኔታዎች በተለይ በኢዴፓ እና ኢዴፓ ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ላይ ማነጣጠሩ ደግሞ እጅግ በጣም ፈታኙ ጉዳይ ነበር፡፡ ኢዴፓ የቅንጅት አፍራሽ ሆኖ ልደቱ አያሌው ላይ የተካሄደውን ዘመቻ ሳስበው፣ ሁልጊዜም እንቆቅልሽ የሚሆንብኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ያንን መቀበሉ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በሀይል ከማመን ቀጥሎ ትልቁ በሽታ ስም ማጥፋት ነው፡፡ ከኔልሰን ማንዴላ በስተቀር ብዙዎቹ አፍሪካውያን ጀግኖች በተካሄዱባቸው የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ነው ተጠልፈው እንዲወድቁ የተደረጉት፡፡ ያ ክፉ ጊዜ ለኢዴፓ የማይረሳ ነው፡፡
ኢዴፓ ቅንጅትን አላፈረሰም የሚሉባቸው ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በወቅቱ እውነታችንን እንናገር ብንል ማን ተቀብሎን! ቅንጅትን የመሰረቱት ፓርቲዎች ወደ ውህደቱ ለመሄድ ከምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ሰርተፊኬት እና ማህተም መመለስ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ኢዴፓ በዛው ውህደቱ ሊካሄድ በታሰበበት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ ነበር፡፡ ውህደቱን በተመለከተም ጠቅላላ ጉባኤው የወሰነው ውሳኔ ቅንጅቱ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ያልጠሩ ጉዳዮች እስኪጠሩ ድረስ የፓርቲው ሰርተፊኬት እና ማህተም እንዳይመለስ የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን ከውህደቱ ሂደት ስለማያግደን እንቀጥል ተባለ፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ በላይ መሆን እንደማይቻል ሁሉም እያወቁት፣ ውሳኔው በሌላ ተመንዝሮ ከአሉባልታ ጋር ተዳምሮ ዘመቻ ተከፈተብን፡፡ እውነት ሰሚ አጣች፡፡ ህዝቡም እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ፤ ምንድን ነው የሆነው ብሎ ሳይመረምር ተቀበለው፡፡ አንዳንድ ጋዜጦችም እውነቱን ስሙ ብንላቸው “የእናንተ እውነት ጋዜጣ አያሸጥም” የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ በፖለቲካ ውስጥ ዋናው ነገር አለመቀደም ነው፡፡ እኛ ለተፈጠረው ነገር አልተዘጋጀንም ነበር፡፡ እነሱ ቀደሙን፡፡ በወቅቱ የቅንጅቱ ሁኔታም ችግር ላይ ስለነበር፣ ነገሮቹን የሚሸከም ይፈለግ ነበር፡፡ ስለዚህ ውድቀቱ ኢዴፓ እና በተለይ ልደቱ ላይ እንዲሆን ተደረገ፡፡ አሁን ድረስ የሚሞግቱኝ ሰዎች አሉ፡፡ ምን አይነት ስር የሰደደ ነገር ነው እላለሁ፡፡ እስቲ መከራከሪያችሁን ወይም እውነታችሁን ንገሩኝ ስል የለም፡፡ ለነገሩ የተወነጀልንበትን ጉዳይ እውነት አድርገነው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በከበደን ነበር፡፡ ህዝቡ ሁኔታዎቹን በሂደት እያያቸው፣ ወደ ኢዴፓ እየተመለሰ ያለውም ለዛ ነው፡፡ በወቅቱ እንግዲህ አውቆ የተኛን መቀስቀስ ባይቻልም በብዙ መልኩ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እየደረሰ ነው፡፡ የኢዴፓ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ምርጫ በዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እምነታችን ስለሆነ በምርጫ ገብተን እንወዳደራለን። ምርጫዎቹ ላይ ያለውን ችግር ጊዜ ይፈታዋል። የምርጫ ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዝን መልኩ እየተበላሹ ነው፡፡ ነገር ግን ራስን ማኩረፍ ካልሆነ በስተቀር ሳትሳተፊ ብትቀሪ ገደል ግቢ ነው የምትባይው እንጂ የሚመጣ ነገር የለም፡፡ በምርጫው ተሳትፈን እውነቱን ቆሞ መናገር ትልቅ ነገር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ሆነን ምንግዜም እንቀጥላለን፡፡
በምርጫ እጩ ሆነው ያውቃሉ?
አዎ በ1993ቱ አገራዊ ምርጫ ቦሌ ክፍለከተማ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ምርጫዎቹን ሳያቸው የመጀመሪያው ምርጫ ከኋለኞቹ የተሻለ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ሰዉ ነቅቶ በቅቶ ነበር። መንግስት ያንን እየተሻሻለ የመጣ ባህል እንዲጎለብት አልፈቀደም፡፡ ህዝቡ የመምረጥ እና በፖለቲካ የመሳተፍ ስሜት የሚኖረው በመጠኑም ቢሆን ትክክለኛ ነገር አገኛለሁ ብሎ ሲያምን ነው። ያለበለዚያ ከቤቱ ምን ሊያደርግ ይወጣል? የሱን ፍላጎት እና የሰጠውን ምላሽ ለማወቅ 1997ትን መለስ ብሎ ማየት ነው፡፡
ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
እኛ ምንግዜም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንጥራለን፡፡ ሲሆን ሲሆን የህብረት ሁኔታ ቢፈጠርም በጣም ፈቃደኞች ነበርን፡፡ ግን የገጠመንን ስናይ፣ አልፎ አልፎ ባደረግናቸው ሙከራዎች ችግሮች ገጥመውናል፡፡ ወደ ውህደት ለመግባት መቸኮሉ ዋጋ ያስከፍላል፤ አስከፍሎናልም፡፡ ለመዋሃድ ቢያንስ በመሰረታዊ ነገሮች ላይ መመሳሰልና መግባባት ያስፈልጋል። ስለዚህ ከበፊት ልምዳችን በመነሳት ነገሮችን በጥንቃቄ ነው የምናየው፡፡ ዘው ብለን ስምምነት ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡
በሦስት መንግስታት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ሶስቱን እንዴት ያይዋቸዋል?
የማወዳደር ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ በኔ አመለካከት ምናልባት ልጅነቴንም በሳቸው ዘመን ስላሳለፍኩ ይሆናል፡፡ ንጉሱ ጀግና መሪ ነበሩ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ ያሉ ብዙ መሰረታዊ ነገሮችን ያስቀመጡ መሪ ናቸው፡፡ ሰው ናቸውና ስህተት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፡፡ እንደ እግዚአብሄር እንቁጠራቸው፣ እንከን አይኑራቸው የሚለው ዝም ብሎ ሀሳብ ነው፡፡ እንደ ሰው የተሳሳቱት ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ስህተታቸው እጅግ የጎላ አይደለም፡፡ ሁሉ ነገር የሚዛን ጉዳይ ነው፡፡ ሚዛኑ የሚደፋው ወዴት ነው ያልሽ እንደሆነ ወደ ጥሩ ነገራቸው ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እዚች አገር ላይ ጠንካራ የትምህርት፤ የጤና፤ የመንገድ መሰረት ያስቀመጡ ናቸው፡፡ የወታደር መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አለም ላይ በጅቶ አያውቅም፡፡ ግሪክን ያህል ዲሞክራሲያዊት አገር ያጠፋው ወታደራዊ አገዛዝ ነው፡፡ ላቲን አሜሪካንም ተመሳሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የተለየ ነገር አልገጠማትም፤ ኢትዮጵያ አፈር ድሜ የጋጠችው በደርግ ነው፡፡ የተማሩ ሰዎች (ያለቁበት፣ ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች በጠራራ ፀሀይ ተገድለው፣ መሬት ለመሬት የተጎተቱበት ዘመን ነው፡፡ ወደ ሚዛኑ ስመጣ ደርግ ምንም ሰራ ቢባል ጭካኔው ሁሉንም ነገር ያፈርሰዋል፡፡ ሰውን የሚጨርስ መንግስት ምንም ዋጋ የለውም። አገራቸውን በእጃቸውና በእግራቸው ያገለገሉ፣ ኢትዮጵያውያንን የገደለ ነው፡፡ በእኔ በኩል ደርግን የማየው እንደ መንግስት ሳይሆን እንደ “የጥፋት መልእክተኛ” ነው፡፡
የመንግስቱ ኃይለማርያምን መፅሀፍ አንብበዋል?
አላነበብኩም ማለት ፊደል ከቆጠረ ሰው የማይጠበቅ ቢሆንም አላነበብኩም!! ምክንያቱም እሱ ከውሸት ውጪ ምን ሊፅፍ ይችላል?!
ወደ ሶስተኛው መንግስት እንምጣ?...
የኢህአዴግ መንግስት ሲመጣ በኔ በኩል ትልቅ ተስፋ ነበረኝ፡፡ ደርግን የጣለ መንግስት ጀግና ነው ብዬ ነበር የተቀበልኳቸው፡፡ ወደ ፖለቲካ የገባሁበት ምክንያትም እነዚህን ሰዎች ለማገዝ ነበር፡፡ በሂደት ግን ተስፋ መቁረጥ መጣ፡፡ አሁንም የሚዛን ጉዳይ ነው። የሚያጠፉትን እያጠፉ፣ የሚያለሙትን ያለማሉ፡፡ እንደ ደርግ ሙሉ በሙሉ የጥፋት መልእክተኛ ብቻ አይደሉም፡፡ ጥፋቱ ምን ያህል ነው ስንል ፖለቲካው ላይ፣ የሰዎች መብት ላይ፣ ፍትህ ላይ ብዙ ደካማነት ይታይባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም ያሳፍራል፡፡ ኢህአዴግ እነዚህን ነገሮች ለመለወጥ እድል የነበረው መንግስት ነው፡፡ አልተጠቀመበትም፡፡ ባለፉት ሀያ ሁለት አመታት ኢትዮጵያ አልተለወጠችም የሚል ካለም ጭፍንነት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል። ነገር ግን ለሰው ልጅ የቁሳቁስ ለውጥ ብቻ አያረካውም፡፡ ተስፋ ያስፈልገዋል፡፡ መብቱን ይጠይቃል፡፡ ፍትህ ይፈልጋል፡፡ አለአግባብ መነጠቅ እና መባረር ሊደርስበት አይገባም፡፡ ስለዚህ ሚዛኑ ላይ ሳስቀምጠው መሻሻሉን ያጨልመዋል፡፡
ወደኋላ ልመልስዎትና…ከአሜሪካ ስትመለሱ አገርዎ ላይ ምን ገጠምዎት? የባህል ግጭትና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ…
አባቴ በአምባሳደርነት የቆዩት ስምንት አመት ስለነበር፣ ከዛ ስንመለስ በሁለቱ አገሮች የባህል ልዩነት ምክንያት አንዳንድ ነገሮች አጋጥመውን ነበር። አሜሪካን አገር ምንም ያልሆኑ ነገሮች እኛ አገር በሌላ መልኩ የሚታዩባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ እኛ ወላጆቻችን የተማሩ ስለነበሩ ነፃነትን አጣጥመን ነው ያደግነው፡፡ አባቴ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ነበሩ፡፡ እናቴም በጦርነቱ ምክንያት ትምህርቷ ተቋረጠ እንጂ የህክምና ተማሪ ነበረች፡፡ ብዙ ገፋ አድርጎ መሄድ ሳይጨመርበት፣ አሜሪካን አገር በአስራ አራት አመት የወንድ እና የሴት ጓደኝነት ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ እኛ አገር ደግሞ እንደዛ አይነት ባህል የለም፡፡ ለነገሩ እኛም የማያስቀይም እንደሆነ ብናውቅም በባህላችን የማይፈቀድ ነገር አናደርግም ነበር፡፡ አባባም አይፈቅዱም፡፡ እንደመጣን ግን እኛም በጓደኞቻችን ሁኔታ ደነገጥን፤ እነሱም በኛ ደነገጡ፡፡ የሩቅ ዘመዶቻችንም ምን ጉዶች መጡብን ብለውን ነበር፡፡ እንዳልኩሽ እኛ ቤት “Can I take your daughter to dinner?” (ልጅዎትን እራት ልጋብዛት?) የተለመደ ነው፡፡
በአባትዎ በአቶ ይልማ ደሬሳ ዙሪያ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ የታህሳስ ግርግር ጊዜ እነ መንግስቱ ነዋይ ሲገደሉ አባትዎም “እቴጌ ታመዋልና ይምጡ” ተብለው ተጠርተው እንደነበርና እሳቸውም “እኔ የገንዘብ ሚኒስትር እንጂ ሀኪም አይደለሁም” በማለታቸው ከሞት እንደተረፉ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
ቀልድ ነው፡፡ በፖለቲካ ዙሪያ ብዙ ቀልዶች ይነገሩ የለ፡፡ አባባ እንደዚህ ጮሌ አፍ የላቸውም። እንዲህ እንኳን አይሉም፡፡ እውነትም ተጠርተው ነበር፡፡ በዛን ቀን በአጋጣሚ “ጌቶች” (ንጉሱ ለማለት ነው) ብራዚል ስለነበሩ፣ አልጋወራሽን አስፈቅደው ከእናቴ ጋር ወደ ጅማ ይሄዱ ነበር፡፡ አባቴ ምንም የጠረጠሩት ነገር የለም፡፡ ይፈለጋሉ ሲባሉ፣ “ኧረ እኔ መንገድ እየሄድኩ ነው” ብለው መለሱ፡፡
የደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ባለቤት የነበረችው ሀና ይልማ የእርስዎ እህት ናት፡፡ ከተፋቱ ረጅም ጊዜ ቢሆንም በህይወት እያለ ትጠያየቁ ነበር?
በሚገባ እንጠያየቅ ነበር እንጂ! ልጁ ከውጭ ሲመጣም ተገናኝተን ድሮ የምንሄድባቸው ቦታዎች በመሄድ አብረን እናሳልፍ ነበር፡፡

Read 7681 times