Saturday, 19 November 2011 15:02

Romantic Love - በባለሙያ መነፅር “እሷ የምትወደውን ሁሉ እወዳለሁ”

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(9 votes)

ዛሬ የምናወጋው ስለፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ስላችሁ ደግሞ የእናት አገር ፍቅር ወይም ደግሞ የጥበብ ፍቅር አሊያም ሌላ አይነት የፍቅር ዘርፍ አይደለም፡፡ በቀጥታ ስለወንድና ሴት ልጅ ፍቅር ነው የማወጋችሁ - ፈረንጆቹ Romantic Love ስለሚሉት፡፡ ግን ብቻዬን አይደለሁም፡፡ ከአንዲት አሜሪካዊት የRomantic love ባለሙያ ጋር ሆኜ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በጥበብ አምድ ላይ ያስነበብኳችሁን “የፈጠራ ሰዎችና ውስጣዊ ፍርሃታቸው” የተሰኘ ፅሁፍ ያገኘሁት ዝነኛዋ ደራሲ ኤልዛቤት ጊልበርት በTed talk ፕሮግራም ላይ ካደረገችው ንግግር ወይም ከሰጠችው ሌክቸር እንደነበር መግለፄ ይታወሳል፡፡ ይሄም የዛሬው መጣጥፌ ምንጩ ተመሳሳይ ነው - “Ideas Worth Spreading” በሚል መሪ ቃል ተቀርፆ የሰማሁትን ንግግር ነው የማስቃኛችሁ፡፡

የዛሬዋ እንግዳችን ሄለን ፊሸር ትባላለች፡፡ ለበርካታ አመታት በፍቅርና በፍቅር ግንኙቶች ዙሪያ መጠነ ሰፊ ጥናትና ምርምር አድርጋለች፡፡ “Romantic Love” የሚል መፅሃፍ ማሳተሟንም ትናገራለች - ደራሲዋ፡፡ እንግዲህ እኔ በሰማኋትና በተረዳሁት መጠን ፊሸር ካደረገችው ንግግር የማረከኝን እየነቀስኩ ላካፍላችሁ እሞክራለሁ፡፡
በነገራችን ላይ አሜሪካዊቷ የሮማንቲክ ላቭ ተመራማሪ ንግግሯን ለታዳሚዎቿ ያቀረበችው እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ነበር፡፡ አምስት አመት ገደማ አልፎታል፡፡ ሆኖም ግን ርእሰ ጉዳዩ በጊዜ ገደብ ኤክስፓየርድ የሚያደርግ አይነት አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ጭብጡ ዩኒቨርሳል ነው - ለሁሉም የሰው ልጅ በየትም ቦታና ጊዜ የሚሆን እንደማለት፡፡ ስለዚህ እንቀጥል፡፡ሄለን ፊሸር ለሴሚናር ተካፋዮቿ ካቀረበቻቸው ዘና የሚያደርጉ ቀልዶች በአንደኛው እንጀምር፡፡ አንድ የወንዶች ባህርይ ያስገረመው ሰው ለአንድ የፍቅር ባለሙያ እንዲህ የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ “ለምንድነው ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ሴሰኞች የሆኑት?”ባለሙያ “ምን ማለትህ ነው? እነዚህ ወንዶች ከማን ጋር የሚተኙ መሰለህ?” ብሎት አረፈው፡፡ እኔም የነቃሁት ይህችን ከሰማሁ በኋላ ነው፡፡ አይገርምም… ለካስ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ሴሰኞች ናቸው የሚባለው ሃሰት ነው፡፡ ለምን ቢባል? ወንዶች ያለ ሴቶች መልካም ትብብርና ድጋፍ ሴሰኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ወንዶች ሴሰኛ ሆኑ ስንል የተባበሩ ሴሰኛ ሴቶችም አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሴሰኝነቱ መጠን እኩል ነው - በወንዱም በሴቱም፡፡ እድሜ ለሄለን ፊሸር ወንዶች ለብቻቸው ሴሰኛ እንዳልሆኑ ተረዳሁ፡፡ አሁን ቢያንስ ሃጢያት የመጋራት አሰራር ይኖረናል ማለት ነው - እንደ “ኮስት ሼሪንግ” ነገር፡፡ በነገራችን ላይ ሴቶችና ወንዶች በዚህ ዓለም ላይ ሲኖሩ ግንኙነታቸው የሚደጋገፍ ነው፡፡ “We are like two feet” አንደኛው እግር ያለሁለተኛው (ብቻውን) መራመድ አይችልም፡፡ እንዲያ ነው የወንድና የሴት ግንኙነት ትላለች - ፊሸር፡፡ 

ፍቅር እውር ነው?
እውነት ፍቅር እውር ነው? አንዳንድ ወገኖች እውሩ ፍቅር ሳይሆን አፍቃሪዎቹ ናቸው ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ በመላው ዓለም 130 ማህበረሰቦችን ያነጋገረችው ሄለን ፊሸር ግን Love is blind ወደሚለው ታደላለች፤ በስሜት ተመርታ ሳይሆን በጥናት ላይ ተመስርታ፡፡
ፍቅር የያዘው ሰው ለነገሮች ልዩ ትርጉም መስጠት ይጀምራል የምትለን ፊሸር፤ ሙሉ ሃሳቡና ትኩረቱም የሚያፈቅረው ሰው ላይ ያነጣጥራል ትላለች፡፡ ያፈቀራት ሴት በሁሉም ነገር እንከን ተፈልጐ የማይገኝላት ላትሆን ትችላለች፡፡ አንዳንዴም እንከን በእንከን ትሆናለች፡፡ ለወዳጃችን አፍቃሪ ግን ይሄ ብዙም የሚያመጣው ለውጥ ያለ አይመስልም፡፡ ያፈቀራት ሴት ላይ የሚታዩ እንከኖችን እንዳያይ ዓይኑን ይጨፍንና በጐ ነገሮቿ ላይ ብቻ ያተኩራል፡፡ ለዚህ ነው ፍቅር እውር ነው የሚባለው ትላለች - የRomantic Love ደራሲዋ ሄለን ፊሸር፡፡ በፍቅር ላይ በምትሰራቸው ጥናቶች ለአፍቃሪዎች ከምታቀርባቸው ጥያቄዎች አንዱ “በቀን ለምን ያህል ጊዜ ስለምታፈቅሩት ሰው ታስባላችሁ?” የሚል እንደሆነ የምትገልፀው ፊሸር፤ አብዛኞቹ አፍቃሪዎች ሙሉ ቀንና ሙሉ ሌሊት ብለው እንደሚመልሱላት ተናግራለች፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ “ለምታፈቅሩት ሰው ህይወታችሁን ትሰዋላችሁ?” የሚል ነው፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ? ፍቅራችሁ የህይወት መስዋእትነት እስከማስከፈል የሚደርስ ነው፡፡ ፊሸር የጠየቀቻቸው አፍቃሪዎች (ሁሉም ማለት ይቻላል) “የምንኖረው ለማን ሆነና!” ሲሉ ነው የመለሱት፡፡
በፍቅር ስለሚወድቁ ሰዎች ከበቂ በላይ ጥናት ያደረገችው ሄለን ፊሸር የአፍቃሪዎችን የጋራ መገለጫ ስታሳይ እንዲህ ትላለች፤ አፍቃሪዎች ከስንት መቶ የቆሙ አውቶሞቢሎች መሃል የፍቅረኛቸውን ለይተው እንደሚያዩ ትናገራለች፡፡ ስለፍቅር ግንኙነቱ እንዲገልፅ የተጠየቀ አንድ አፍቃሪ ደግሞ “እሷ የምትወደውን ሁሉ እወዳለሁ” ማለቱን የምታወሳው ደራሲዋ፤ ሮማንቲክ ላቭ ማለት ይሄ ነው ስትል ቀለል አድርጋ ትነግረናለች፡፡ ግን አልመሰለኝም፡፡ የዚህን ያህል ቀላል እንዳልሆነ እናውቀዋለን፡፡ እሷም ወደኋላ ላይ ትናገረዋለች - እንዲህ ስትል፡፡ “ሰዎች ለፍቅር ይኖራሉ፤ ለፍቅር ይሞታሉ፤ ለፍቅር ይገድላሉ” አያችሁት በፍቅር መውደቅ ቀላል አለመሆኑን?
ከአንጋፋው ድምፃዊ ባህታ ገብረህይወት የዘፈን ግጥም ስንኞች ይሄን ስሜት በከፊል የሚያንፀባርቁትን ቆንጥረን እንመልከት፡፡
“በፍቅርሽ ሰንሰለት ታሰረና ልቤ
በፍፁም አቃተኝ መናገር አስቤ
አንቺን ሳስታውስሽ እንባዬ እየመጣ
እህል ውሃ ጠላ ገባሁልሽ ጣጣ
ምን ትጠቀሚያለሽ ብሞት ባንቺ ፍቅር
ተይ አብረን እንሁን ማመንታትሽ ይቅር፡፡”
አንድ ሰው ከአንደኛዋ ይልቅ ሌላዋን የሚያፈቅረው ለምንድነው? በሂሳብ ስሌት ወይም በሳይንሳዊ ማብራሪያ መግለፅ ይቻል ይሆን? አልመሰለኝም፡፡ ከምናያቸው እልፍ ሴቶች አንዷ ላይ የሙጥኝ ለማለት ጊዜ ወሳኝ ሚና እንዳለው ትናገራለች - ፊሸር፡፡ ምናልባት ነፍሳችን የምትፈቀር ፍለጋ ስትማስን ብቅ ያለች ሴት ልትሆን ትችላለች፡፡ ያኔ (በዚያች ጊዜ) የመጣችልን ላይ እንወድቃለን ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ቀረቤታ (proximity) ነው፡፡ የኬንያ ሴት የምናፈቅርበት እድል በጂኦግራፊያዊ ርቀት የተነሳ እጅጉን ያነሰ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የአዋቂነት የዕድሜ ዘመኑን ኬንያ ውስጥ ላሳለፈ የአበሻ ወንድ ግን ይሄ አይሰራም፡፡
ሦስተኛው በማይታወቅ ምስጢራዊ ምክንያት ሊሆን ይችላል - በቃ ወደዳት ወደደችው! ምስጢሩን ፍቅረኛሞቹም ጭምር ላያውቁት ይችላሉ - ሄለን ፊሸር እንደምትለው፡፡ ሌላው ወደዚያ ሰው የመሳብ ሁኔታ ነው - አንዷን ከብዙዎች መሃል የሚያስመርጠን፡፡

ያለአቻ ጋብቻ እየቀረ ይሆን?
የRomantic Love ባለሙያዋ ሄለን ፊሸር በፍቅር በኩል አድርጋ ወደ ትዳርም ትዘልቃለች፡፡ ከዚያ በፊት ግን ሴቶች ባለፉት 45 ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ከፍተኛ አቅም እየተቀዳጁ መሆናቸውን ትገልፃለች፡፡
“We are really moving forward to the past” በማለት - (እኛ ስትል ሴቶች ማለቷ ነው) ከ500 ዓመት በፊት እንደነበረው ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ስራ (Business) እየገቡ ናቸው የምትለው ፊሸር፤ ይሄም የሚመሰርቱትን ትዳር የፀና እያደረገው መሆኑን ትናገራለች፡፡ ምሳሌ ስትጠቅስም በአሜሪካ የፍቺ ቁጥር መቀነሱን ትገልፃለች፡፡ ሴቶች በሁሉም የኑሮ ዘርፎች አቅማቸው የበለጠ እየተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ ፍቺ ከዚህም የበለጠ ይቀንሳል ባይ ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካ ደራስያን መካከል 54 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው ያለችው ባለሙያዋ፤ ታላላቅ ፀሃፊያን ማግኘት ማለት ሌላ መንግሥት ማግኘት ነው የሚለውን አባባል ትጠቅሳለች፡፡ በሌላ አነጋገር አሜሪካን የሚመሯት ሴቶች ናቸው እያለችን ነው፡፡ ዋናው ጉዳዩዋ ግን ይሄ አልመሰለኝም፡፡ ፊሸር ማሳየት የፈለገችው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ትዳራቸው ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ መምጣቱ ይመስለኛል፡፡
አሁን ያለንበት 21ኛው ክ/ዘመን የአቻዎች ጋብቻ የሚመሰረትበት ወቅት እንደሆነ የምትገልፀው ፊሸር፤ ጥሩ ትዳር ለመመስረት ጊዜው አሁን ነው ትላለች፡፡ በአሜሪካ ባሁኑ ጊዜ ጥንዶች ወደ ትዳር የሚገቡት የሚፋቀሩ ብቻ ከሆነ ነው ያለችው ደራሲዋ፤ ለኢኮኖሚ ጥቅም ሲባል ጐጆ መቀለስ መቅረቱን ማሳያ ነው ብላለች፡፡ የፀሃፊ ተውኔት አብዬ መንግስቱ ለማ “ያለአቻ ጋብቻ” ትያትር በአሜሪካ ቦታ የለውም ማለት ነው፡፡ ያለጥንዶቹ እውቂያ በወላጆች የሚቀነባበር ጋብቻም ህልውናው እያከተመለት ነው ባይ ናት - ፊሸር፡፡
የፍቅር ግንኙነትንና ጋብቻን በተመለከተ እየተከሰተ ያለውን በጐ ለውጥ በስሜት ስታብራራ የቆየችው ሄለን ፊሸር፤ ንግግሯ መዝጊያ ላይ ፍርሃትና ስጋት እንዳላት ትናገራለች፡፡
የሄለን ፊሸር ፍርሃትና ስጋት ምን ይሆን? በመላው ዓለም በየዓመቱ ከድብርት ጋር ለተያያዙ ችግሮች ከ100 ሚሊዮን በላይ መድሃኒቶች በሃኪሞች እንደሚታዘዙ የምትጠቅሰው ፊሸር፤ መድሃኒቶቹ ለረዥም ጊዜ በተወሰዱ ቁጥር የፍቅርና የወሲብ ስሜትን የበለጠ እየገደሉ ይመጣሉ ትላለች፡፡ ታዲያ ስጋቷ ምኑ ላይ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ሄለን ፊሸር መልስ አላት “ፍቅር የሌለባት ዓለም አደገኛ ስፍራ ናት” ትላለች፡፡ አንጋፋው ድምፃዊ ግርማ በየነ ባቀነቀነው ዜማ ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ስንኞችን የጽሑፌ መቋጫ አድርጌዋለሁ፡፡
“መጀመሪያ አንቺን ሳገኝ ተደስቼ፣
እውነት መስሎኝ ልቤን ሰጠሁሽ ተፅናንቼ፣
ከሴቶቹ ሁሉ አብልጬ አንቺን ወደድኩ ተሳስቼ
ቁጭ ካልኩበት አስነስተሽ ተዋወቅሽኝ፣
ጠብቀኝ ብለሽ ሳላስበው ተለየሽኝ፡፡
ካንቺ ወዲያ ሴት አላምንም
ለማግኘትም አልሞክርም”
ፍቅር የሌለባት ዓለም እንዲህ ተስፋ ያስቆርጣል ለማለት ይሆን? ፍቅር ይብዛላችሁ!!

 

Read 10277 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 15:05