Saturday, 31 August 2013 12:49

“...ይለይልኝ ብዬ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(3 votes)

ኤችአይቪ ቫይረስ በሰዎች ላይ መከሰት ከጀመረ ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረው አድሎና መገለል በራሱ ብዙዎችን ለሞት ያበቃ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እየኖሩ መሆኑን ልባቸው እያወቀ ነገር ግን ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ በቫይረሱ መያዝ አለመያ ዛቸውን ማረጋገጥ ከማይፈልጉበት ደረጃ ላይ እንደነበሩና በድብቅ ከተኙበት እየሞቱ እንደነበረ የቅርብ አመታት ትውስታ ነው፡፡ ነገር ግን እየዋለ እያደረ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይቶች በመደ ረጋቸው እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን ትምህርት በመሰጠቱ ፣የፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት ወደ ሀገር በመግ ባቱና በስፋት እንዲሁም በነጻ መታደል በመጀመሩ ከፍተኛ የንቃተ ህሊና ማዳበር ስራ ተሰርቶ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በተለያዩ ማህበራት በመደራጀት ማንኛውም ሰው ከቫይረሱ ጋር መኖር ያለመኖሩን ምርመራ በማድረግ እራሱን እንዲያውቅ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የተቻላቸውን ያህል ምክር በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ከቫይረሱ ጋር በሚኖሩ ሰዎች ተቋቁመው ስራ በመስራት ላይ ከሚገኙት ማህበራት አንዱ ጥላ የተሰኘው በአዋሳ የተቋቋመው ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር ሲሆን ከእነሱ ጋር ያደረግነውን ውይይት እነሆ ለንባብ ብለናል፡፡
አንድ የጥላ ማህበር አባል እራስዋን ከቫይረሱ ጋር መኖርዋን እንዴት እንዳወቀች እንድትገልጽ በዚህ አምድ አዘጋጅ ተጋበዘች፡፡ እሱዋም እንደሚከተለው ገልጻለች፡፡
“እኔ እራሴን ያወቅሁት በሰው አማካኝነት ነው። በመጀመሪያ ከገጠር ስመጣ በሰው ቤት እየሰራሁ እማራለሁ ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ተቀጥሬ ከምሰራበት ቤት ፊት ለፊት የጥበቃ ስራ የሚሰራ ሰው ...ለምን ሰው ቤት ትሰሪያለሽ...ከእኔ ጋር ቤት ተከራይተን አብረን እየኖርን የቻልነውን ነገር እየሰራን እንኑር ብሎ ሲያግባባኝ እሺ ብዬ አብሬ መኖር ጀመርኩኝ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደስምንተኛው ወራችን ገደማ ሰውየው በከፍተኛ ሁኔታ ታመመ፡፡
ጥ/ ከመታመም ባለፈስ ?
መ/ .....በጊዜው ምንም አልተከሰተም፡፡ ነገር ግን ክፉኛ በመታመሙ ወደገጠር ወደቤተሰቦቹ ተወሰደ እና ብቻዬን መኖር ጀመርኩኝ፡፡ ...ለነገሩማ...ትንሽ ቆይቶ ሞተ፡፡
ጥ/ የአንቺ ቀጣይ ሕይወት ምን ይመስል ነበር?
መ/ ...ትንሽ ቆይቶ እኔም ታመምኩኝ፡፡ በጣም ትከታተለኝ የነበረች ጉዋደኛዬ ...ምን ሆነሽ ነው? አለችኝ፡፡ እኔም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያልገባኝ ሕመም እያመመኝ መሆኑን ገለጽኩላት፡፡ ጉዋደኛዬ ወደሆስፒታል እንሂድ ብላ ስታስመረምረኝ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ እንደሚገኝ ተገለጸልኝ፡፡
ጥ/ በምን ሁኔታ ተቀበልሽው?
መ/ በጊዜው በምንም ሁኔታ አልተቀበልኩትም፡፡ እንደ እብድ ወደሐይቅ እሮጥኩ፡፡ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር አብሮ መኖር ማለት ሕይወት ያበቃለት የመጨረሻው አለም ነው ብዬ ነበር ያሰብኩት፡፡ ወደሐኪም ወስዳ ያስመረመረችኝ ልጅ አብራኝ ባትኖር ኖሮ ሐይቅ ገብቼ ነበር፡፡ ነገር ግን በእሱዋ ብርታት ከአደጋ ተርፌ...ከብዙ ትግል በሁዋላ አሁን ኑሮዬን አስተካክዬ በመኖር ላይ እገኛለሁ፡፡
ጥ/ ለወደፊት በምን ሁኔታ ሕይወትን መቀጠል አስበሻል?
መ/ አሁንማ እድሜ ለጥላ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር...ስራም እየሰራሁ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜም ትዳር እመሰርታለሁ...ልጅም እወልዳለሁ ብዬ አስባለሁ...እንግዲህ እግዚ ሀር እንደፈቀደ እኖራለሁ፡፡ አሁንማ ጊዜውም ተለውጦአል፡፡ እራሱን የሚያታልል ካልሆነ በስተቀር በኤችአይቪ ቫይረስ ምክንያት መሞት ቀርቶአል፡፡ ሁሉም ሰው በትክክል ከሐኪም ጋር በመመካከር ሕይወቱ እንዲቀጥል ማድረግ ይችላል፡፡
---------////---------
ከላይ ያነበባችሁት የአንዲት የጥላ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር አባል ምስክርነት ሲሆን በተከታይነት የማህበሩ አመሰራረትና እንቅስቃሴን በሚመለከት ከሌላ የማህበሩ አባል ያገኘነውን እናስነብባችሁ፡፡
ጥ/ ጥላ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር መቼ ተቋቋመ?
መ/ ጥላ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር የተመሰረተው በህዳር ወር 1995/አመተ ምህረት ነው። ማህበሩ የተመሰረተው በ5/ ሴቶች አማካኝነት ሲሆን በጊዜው የመጀ መሪያው ስራው ያደረገውም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ወደ መድረክ እንዲወጡ በማድረግ ህብረተሰቡን እንዲያስተምሩ እና እራሳቸውንም በምን መንገድ ጤንነታቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ማስተማር ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የማህበርተኛው ቁጥር ከፍ እያለ ወደ 30/ የደረሰ ሲሆን የስራ ድርሻውም እያደገ በመምጣቱ እርጉዝ ሴቶች ወደጥላ እንዲመ ጡና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዲሁም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ወደ ማህበሩ በማምጣት አንዳንድ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ በተጨማሪም በተለያዩ ወረዳዎች በመግባት ስለኤችአይቪ ትምህርት መስጠትና ህብረተሰቡ እራሱን እንዲያውቅ የሚያ ስችሉ ቅስቀሳዎችን ያካተተ ነበር። በተለይም በህብረተሰቡ ዘንድ በጊዜው ይታይ የነ በረውን የአድሎና መገለል ሁኔታ ለመቀየር ማህበሩ የቻለውን ስራ ተሰርቶአል፡፡
ጥ/ አድሎና መገለል ምን ያህል እንደነበር ማሳያ የሚሆን ...የምታስታውሱት ነገር አለ?
መ/ ለማስታወስ ያህል፡-
..... አንዲት በእድሜያቸወ ትልቅ የሆኑ ሴት ለጉዋደኛቸው ሲያወሩ እንዲህ አሉ፡፡ ... ዛሬ ይለይልኝ ብዬ ...እከሊትን... ግጥም አድርጌ ጨበጥኩዋት...ይላሉ፡፡ ....ጉዋደኝየ ውም...ውይ.. ውይ.. ውይ..እንዴት ደፈሩ? ይሉዋቸዋል፡፡ እንዴ...ምን ላድርግ ...አብሬ ኖሬያለሁ...እንዲያው ዝም ብሎ ማለፍ ልክ አይደለም ብዬ...አስቀድሜ እጄን በነጠላዬ ጥቅልል አድርጌ የራሱ ጉዳይ ብዬ ጨበጥኩዋታ... .. ብለው መልሰዋል፡፡
የአድሎና መገለል ሁኔታ እጅግ አስከፊ ስለነበር ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች በተቻለ መጠን እራሳቸውን በመደበቅ እስከሞት የሚደርሱበት እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች አልፈ ዋል፡፡ ዛሬ ግን ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ተለውጦአል ባይባልም እንኩዋን ተሸሽሎአል፡፡
ጥ/ የማህበሩ የስራ እንቅስቃሴ ከምን ደርሶአል?
መ/ ጥላ በአሁኑ ሰአት 400/አራት መቶ አባላት አሉት፡፡ እነዚህ አባላት የገቢ ማሰባሰብን በሚመለከት፣ እራሳቸው የሚሰሩት ስራን መፍጠር እንዲሁም የማስተማር ስራን በሚያከናውኑበት ወቅት ትንሽ ክፍያ ይሰጣቸዋል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቫይረሱ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች በምግብ እና አልባሳት በኩል የሚደገፉበት ሁኔታ ተመቻችቶአል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶችም የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱ በስራ ላይ የሚሰማሩ ስለሆነ ኤችአይቪ ማለት የህይወት ማብቂያ እንዳልሆነ እንዲያስቡ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶአል፡፡
ጥ/ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ወደትዳር አለም ለመግባትና ልጅ ለመውለድ ሲያስቡ ማህበሩ ምን ያማክራል?
መ/ አንዲት ትዳር የሌላት አባል ይህንን ሰው ማግባት እፈልጋለሁ ስትል ሰውየውን ይዛ ወደማህበር ትቀርባለች፡፡ ማህበሩም ባል ስታገባ ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን ተዛማጅ ችግር እንዲሁም ወሲብ በሚፈጽሙበት ጊዜ ከኮንዶም ውጭ መሆን እንደሌለበት እና ልጅ በመውለድ እና በማጥባት በኩል ምን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባት እና በፍጹም ከሐኪምዋ መራቅ እንደሌለባት ምክር እንሰጣለን፡፡
ጥ/ የማህበሩ አባላት ማህበሩን የሚደግፉ ናቸው ወይንስ ከማህበሩ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው?
መ/ በአብዛኛው ወደማህበሩ የሚመጡት ተቸግረው ነው፡፡ ከፊሉ መጠለያ እንኩዋን የለ ውም። ግማሹ በማህበረሰቡ መገለል ደርሶበት ይመጣል። ሌሎቹ ደግሞ ልጆቻቸውን ማሳደግ ይሳናቸዋል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች በተለይም ቤተሰብ እንኩዋን አው ጥቶ ሲጥላቸው መጥተው ማህበሩ ዘንድ ይወድቃሉ። ወደማህበሩ የሚመጡትን ሁሉ እንደችግራቸው እየተመለከተ እንዲያገግሙ ሁኔታዎችን ያመቻችላቸዋል። በእርግጥ እየ ተለወጡ ሲመጡ እነርሱም በተራቸው ሌሎች ሰዎችን መርዳትና መደገፍ ይጀምራሉ፡፡
ጥ/ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ልጅ ሲወልዱ ለልጁ የሚደረገውን የህክምና ክትትል እንዳይቋረጥ ማህበሩ ምን አስተዋጽኦ ያደርጋል?
መ/ ማንኛዋም ከቫይረሱ ጋር የምትኖር ሴት በማህበሩ መዝገብ ትመዘገባለች፡፡ ልጅ ከወለዱ በሁዋላ ደግሞ ማህበሩ ለተወለዱት ልጆች የሚያደርገው ድጋፍ ስላለ እናቶቹ በምንም ምክንያት አይጠፉም። የህክምና ክትትሉን ማድረግ አለማድረጉዋን እግረ መንገድ ስለምንከታተል በእኛ ዘንድ እንደችግር የሚታይ አይደለም፡፡
ማንኛዋም የማህበሩ አባል ልጅዋ ከቫይረሱ ጋር እንዲኖር አትፈቅድም...በፍጹም አትፈልግም፡፡
ጥ/ ማህበሩ በቀጣይነት እንዲዘልቅ ድጋፍ ከማግኘት ባሻገር ምን በማድረግ ላይ ይገኛል?
መ/ ጥላ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ሴቶች ማህበር እስከአሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ባገኘው ድጋፍ ብዙ ነገር ሰርቶአል፡፡ አባላቱ በማህበር እየተደራጁ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ አስችሎአል፡፡ ማህበሩ እራሱ ትልልቅ ማሽኖችን በመግዛት ብዙ አባላትን ባሳተፈ መልኩ የራሱን ገቢ የሚያገኝበት ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ድጋፍ ከማግኘት ጎን ለጎን የራሱንም ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

Read 4043 times