Print this page
Saturday, 19 November 2011 15:06

ብልጣ ብልጡ የጣልያን ጠ/ሚኒስትር

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ጥሎብኝ ቆንጆ ሴቶችና ልጃገረዶች እወዳለሁ - ቤርሉስኮኒ 
የአውሮፓ ኮሜዲያን የአፋቸው መክፈቻ ግሪክ ሆናለች …
አውሮፓን ለከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ የዳረጋት ስንፍና ነው
የአለማችን ቁጥር አንድ ሃያል ኢኮኖሚ ባለቤት የነበረችው አሜሪካ በገንዘብ ቀውስ ተመትታ ስታቃስትና በግዙፍነታቸው በሚያንቀሳቅሱት ትልቅ ሀብት የተነሳ ተዓምር ቢመጣ ሊወድቁ አይችሉም እየተባለ ሲነገርላቸው የነበሩት ታላላቅ የአሜሪካ የፋይናንስና የማምረቻ ተቋማት ተራ በተራ በአስደንጋጭ ሁኔታ ሲንኮታኮቱ ችግሩ ደህና አድርጐ ያልነካቸው ወይም ሊነካን አይችልም ብለው የገመቱት አውሮፓውያን፤ አሜሪካና ተቋሞቿ በገጠማቸው አሳዛኝና አስገራሚ እጣ “ጉድ ነው” እያሉ፣ ከንፈራቸውን ሲመጡና መጠጥ ቤቶቻቸውን በወሬ ሲያደምቁ ነበር የከረሙት፡፡

ትንሽ እውቀት ዘልቆናል ያሉት ደግሞ አሜሪካንና በቀውሱ የተሽመደመዱትን ኩባንያዎቿን ከገጠማቸው ቀውስ ለማውጣት ያስችላል ያሉትን የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦችን አይነት በአይነት ዘርዝረው ማቅረባቸውም አልቀረም፡፡
አሜሪካንን በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያሽሟጥጡ የከረሙት አውሮፓውያን፤ የራሳቸው ስሪት የሆነው የገንዘብ ቀውስ እግር ከወርች ጠፍሮ የያዛቸው ሱሪያቸውን እንኳ ሳይታጠቁ ነው፡፡ በተለይ ለግሪካውያን የብራ መብረቅ ያህል ነበር ክስተቱ፡፡ በርካቶቹ የገቡበት የፋይናንስ ቀውስ መጠነ ሰፊነትና በእለት ተእለት ህይወታቸው ውስጥ የፈጠረው ምስቅልቅል ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡
አውሮፓውያን በእድገትና በብልጽግና መኖርን ሲወለዱ እንደሚጐናፀፉትና ማንም መቼም ቢሆን የማይነካባቸው ልዩ ፀጋና መብት አድርገው በመቁጠር ለረጅም ዘመናት ኖረዋል፡፡
መንግስታቶቻቸውም ይህንኑ አስተሳሰብ አምነውና ተቀብለው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአምራቹ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ተጠቃሚ ዜጐችን በየአመቱ እየፈጠሩ መጓዝን ስራዬ ብለው ተያይዘውት ነበር፡፡ እንደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ፖርቹጋልና አየርላንድን የመሳሰሉት መንግስታት ደግሞ ከማምረት ይልቅ የተመረተውን የሚጠቀም ዜጋን ከማፍራታቸው በተጨማሪ ያለ አንዳች ሀሳብና ጥንቃቄ እየተበደረ እንዳሻው የሚበትን መንግስታት ሆነው ነበር፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በርካታ የአውሮፓ መንግስታትና ዜጐቻቸው ህይወታቸውን ሲመሩ የቆዩት የቀደሙ አያቶቻቸውና ጥቂት ጐበዝ አምራቾቻቸው በፈጠሩት ላይ ነበር፡፡ የዛሬው ከባድ የፋይናንስ ቀውስ ድንገት ሲመታቸው ክው ብለው የደነገጡት፤ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ያጡትም በዚህ የተነሳ ነው፡፡
በአይሁዶች ሚሽናህ ውስጥ እንዲህ የሚል ቃል አለ፡፡ “የምድሪቱን ጠል ለማፈስ እርሻውን በጊዜ ከማረስ ቸል የሚልና የሚሰንፍ እርሱ በራሱና በቤተሰቦቹ ላይ ረሀብን ያመጣል፡፡” ይህ ቃል ለግሪክ ለጣሊያንና ለመሰል የአውሮፓ መንግስታት በትክክል ይሠራል፡፡ እነዚህ መንግስታት የእርሻ መሬታቸውን በጊዜውና በወጉ ከማረስ ለአመታት ችላ ብለውና ሰንፈው ነበር፡፡ እነዚህ መንግስታት የእርሻ መሬታቸውን በጊዜውና በወጉ ከማረስ ለአመታት ችላ ብለውና ሰንፈው ነበር፡፡ እነዚህ መንግስታት የየሀገራቸውን ኢኮኖሚ በተለይ ደግሞ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀማቸውን በተመለከተ ከአመታት በፊት ሊወስዱት ይገባ የነበረውን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ በመስነፋቸው ዛሬ ለደረሱበት ምስቅልቅል በቁ፡፡ የእነሱ ስንፍናና ቸልተኝነትም እነሆ በሚሊዮን ለሚቆጠሩት ህዝቦቻቸው ረሀብን እንኳ ባይሆን ለዘመናት አይተውትና ሰምተውት የማያውቁት ችጋርን አመጣባቸው፡፡
የአውሮፓን የዩሮ ዞን ሀገራት ከወዲያ ወዲህ እያላጋት የሚገኘው የገንዘብ ቀውስ፤ በተለይ ለግሪክ መቼም ቢሆን የማትዘነጋውን ብሔራዊ ሀፍረት ሳትወድ በግድ እንድትከናነብ አድርጓታል፡፡ የአውሮፓ ኮሜዲያኖችና ተረበኞች የአፋቸው መክፈቻ ግሪክ ናት፡፡ በአውሮፓ የሚፈጠሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቃና ያላቸው ቀልዶችም ዋነኛ ርዕሰ ጉዳያቸው ግሪክ ሆናለች፡፡
ለእርሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው የሀፍረት ማቅ ያከናነባቸውን መሠረተ ሰፊና ጥልቅ የፋይናንስ ቀውስ ለማቃለል አይናቸውን በጨው አጥበውና ባዶ የገንዘብ አኮፋዳቸውን አንጠልጥለው በድረሱልኝ ጥሪ የተለያዩ መንግስታትን በር ሲያንኳኩና ከወዲያ ወዲህ ሲራወጡ የነበሩት የግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅ ፓፓንድሪው፤ የአቅማቸውን ልክ አውቀው እጅ ሰጥተዋል፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩ መንግስታትና መሪዎቻቸው የሠሩት ስህተት ዳፋው አለአግባብ እኔ ላይ ተደፈደፈ በሚል በግልጽም በሹክሹክታም ቢነጫነጩም፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ከዚህ በላይ ማስጠበቅ አልሆነላቸውም፡፡ እናም የጥምር መንግስቱ መሪ ሆነው ለተመረጡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዲሚትሪዎስ አስረክበው ወደ ግል መኖሪያ ቤታቸው አምርተዋል፡፡
ግሪክ በገጠማት የፋይናንስ ቀውስ የተነሳ በሞት ሽረት ትግል ስታጣጥር፣ ባለ ወር ተረኛ የሆነችው ጣሊያን ቀውሱ የሚደፋኝ ባፍጢሜ ይሆን ወይስ በጀርባዬ እያለች በጭንቀት እያቃሰተች ትገኛለች፡፡ የጣሊያን የፋይናንስ ቀውስ ከግሪክ ጋር ሲወዳደር የተሻለ ነው ይባል እንጂ ዳፋው ከባድ መጠኑም ሰፊ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የሚመራው የጣሊያን የጥምር መንግስት ተቀምጦ የከረመው ከወንበር ላይ ሳይሆን ቀስ እያለ ከሚንቀለቅል እሳት ላይ ከተጣደ የብረት ምጣድ ላይ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የጥምር መንግስታቸው የተቀመጡበትን ምጣድ ግለት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የተቋቋሙት መስለው ታይተው ነበር፡፡
በርካታ የአውሮፓ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተንታኞች ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ፤ ለእሳቱ ግለት በቀላሉ ተበግረው እጅ እንደማይሰጡና የተቻላቸውን ያህል እንደሚታገሉ በእርግጠኛነት ተንብየው ነበር፡፡ ይህ ትንቢታቸው ግን የተሳሳተ እንደሆነ ግልጽ ሆኗል፡፡ ታጋዩ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የምጣዱን እሳት መቋቋም አልቻሉም፡፡ እናም እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከሌሎቹ መሪዎች በላቀ ሁኔታ ጣሊያንን ለረጅም አመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ ቤርሉስኮኒ ባለፉት ጥቂት ወራቶች፣ የስልጣን ዘመናቸው የማብቂያ ጊዜ እንደደረሰ አንዳንድ ግልጽና ዘወርዋራ ፍንጮችን አሳይተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ እንዲህ በድንገት ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው አስረክበው ላለፉት አስራ ሰባት አመታት ከነገሱበት የጣሊያን የፖለቲካ መድረክ ዘወር ይላሉ ብሎ የገመተ ግን አልነበረም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የአውሮፓ የፋይናንስ ቀውስ ከግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጆርጅ ፓፓንድሪው ቀጥሎ ጠ/ሚኒስትር ቤርሉስኮኒን ከስልጣን ወንበራቸው በማባረር ሁለተኛውን ግዳዩን ጣለ፡፡ የቤርሉስኮኒ ስልጣን የመልቀቅ ወሬ እንደተሰማም የአውሮፓ የመሪዎች የፖለቲካ መድረክ ሁነኛ አድማቂው የነበሩትን ውቃቤውን አጣ ተባለ፡፡ በእርግጥም የቤርሉስኮኒን ነገረ ስራ በቅርብ የሚያውቅ ወይም ነገሬ ብሎ ለሚከታተል ይህን አባባል አሌ ብሎ አይሟገትም፡፡ ሟቹ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ጋዳፊ፤ የአፍሪካ የመሪዎች መድረክ ላይ መሪ ተዋናይና አድማቂ ውቃቤ እንደነበሩት ሁሉ ለአውሮፓው መድረክም ቤርሉስኮኒ አውራው ውቃቤ ነበሩ፡፡
አሁን አንድ አሪፍ ጥያቄ መጠየቅ ይገባናል፡፡ ለመሆኑ እንዲህ ያወራንላቸው ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ማናቸው? የትኛው ጐዳና አመጣቸው? ከየት ተነስተውስ የት ደረሱ? እንደ አንድ የቆጠርናቸው ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው፡፡ እውነት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ማን ናቸው?
በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊግ ፍቅር ክፉኛ በወደቀችው ሀገራችን አንድ ወጣት ለመሆኑ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ማን ናቸው ተብሎ ቢጠየቅ፣ ብዙም ሳይቸገር እሳቸውማ ቢሊዬነሩ የጣሊያኑ የሴሪአ ሊግ አንጋፋ ክለብ የሆነው የኤሲሚላን የእግር ኳስ ክለብ ባለቤት ናቸው ብሎ መመለስ እንደሚችል ጭራሽ አልጠራጠርም፡፡ መልሱ ደግሞ ትክክል ነው፡፡ ለምን ቢባል ይህ መረጃ ስለ እሳቸው ቢያንስ በየሳምንቱ ሁለት ሶስት ጊዜ በአደባባይ የሚወራ ስለሆነ ነው፡፡ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ግን ከዚህም ሁሉ በላይ ናቸው፡፡
ቤርሉስኮኒ ምንም እንኳ ስማቸው በተደጋጋሚ አስነዋሪ ድርጊት በመፈፀምና በቅሌት በመዘፈቅ እየተነሳ ሲብጠለጠል ቢኖርም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ሶስት ምርጫዎችን በማሸነፍ ለረጅም አመታት ጣሊያንን በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመምራት ሪኮርዱን የያዙ መሪ ናቸው፡፡
በጣሊያን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተለይ ባለፈው ምዕተ አመት ጣሊያን የሞገደኛና ችግር ፈጣሪ መሪዎች እጥረት ጨርሶ አጋጥሟት አያውቅም፡፡ ላለፉት አስራ ሰባት አመታት የጣሊያን የፖለቲካ መድረክ መሪ ተዋናይ በመሆን ያሳለፉት ቤርሉስኮኒ፤ የስም ዝርዝራቸው የሚገኘው ከእነዚሁ ሞገደኛና ችግር ፈጣሪ መሪዎች ተርታ ውስጥ ነው፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአብዛኛው ከሙስና ወንጀል ጋር የተያያዘ ሃያ ሶስት የፍርድ ቤት ክስና የወንጀል ምርመራ ፋይሎች ነበሩባቸው፡፡ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ለሚናገሩት ነገር አንዳችም ጥንቃቄ የማያደርጉ በተለምዶ “ክፍት አፍ” እንደምንለው አይነትና እንዳመጣላቸው የሚለጥፉ ሰው ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ቤርሉስኮኒ የሀገር መሪነት የክብር ስነስርአትም ሆነ የዲፕሎማሲ ቁጥብነት ጨርሶ የማይገዛቸው እንደልቡ ተናግሮ አዳሪ ሰው ናቸው፡፡
በአንድ ወቅት የህብረት ወሲብ ሲፈጽሙ ካደሯቸው ሴተኛ አዳሪዎች አንዷ ለሆነችው ፓትሪዚያ አዳሪዋ የሰጧትን የወሲብ ምክር፣ በቁርስ ገበታ ናፕኪን ደብቃ በያዘችው መቅረፀ ድምፅ ቀድታ በኢንተርኔት ዩቲውብ ለቃው አለሙ ሁሉ ሰምቷቸዋል፡፡ በአንድ አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ፊት ለፊታቸው ያለው የድምጽ ማጉያ መጥፋቱን ሳያረጋግጡ የጀርመኗን ቻንስለር አንጌላ መርከልን አስመልክተው የተናሩትን እጅግ አስነዋሪና ፀያፍ ንግግር የስብሰባው ተሳታፊዎችና ስብሰባውን ለመዘገብ የተገኙ ጋዜጠኞች ሰምተው በድንጋጤ ክው ብለዋል፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በስፍራው የነበረ አንድ የፈረንሳይ ለሞንድ ዲፕሎማቲክ የወሬ መጽሔት ዜና ዘጋቢ፤ የቤርሉስኮኒን ንግግር በመጽሔቱ ውስጥ ለምን እንዳልዘገበው ተጠይቆ ሲመልስ “እንዴ ምን ነክቶሃል? ይህ ምኑ ይዘገባል? እንዲህ ያለ ንግግር ከአንድ የአውሮፓ ሀገር መሪ አፍ መውጣት መቻሉ በጣም የሚገርምና የሚያስደነግጥ ነገር ነው፡፡ እኔ ለእሳቸው ሳይሆን በእሳቸው ለሚመራው የጣሊያን ህዝብ አዝንለታለሁ” ነበር ያለው፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ እንደሚናገሩት ሁሉ ለሚያደርጉት ድርጊትም ግድ የሌላቸውና ደንታ ቢስ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ከሁሉም ነገር ይልቅ በቆነጃጅት ሴቶችና ሴተኛ አዳሪዎች የሚጨክን ልብ ጨርሶ አልሠጣቸውም፡፡ ቤርሉስኮኒ ለቆንጆ ሴቶችና ለወሲብ ካላቸው ወደርየለሽ ፍቅር የተነሳ ሴትነታቸውን እንጂ እድሜአቸውን የመለየት ችግር ነበረባቸው፡፡ በጣሊያን ህግና በተለይም በህብረተሰቡ ዘንድ እጅግ የተወገዘውን ለአቅመ ሄዋን ካልደረሱ ህፃናት ሴቶች ጋር ወሲብ በመፈፀም ለታላቅ ቅሌትና የህዝብ ቁጣ የተዳረጉትም በዚህ አመላቸው ነበር፡፡ ጣሊያናውያን በጠቅላይ ሚኒስትራቸው እንዲህ አይነት ወራዳና ህገወጥ ድርጊት ያገር መዘባበቻ ሆነው ሲሸማቀቁ፣ የቤርሉስኮኒ መልስ በጣም የሚያስገርም ነበር፡፡ “እንዴት እንዲህ ያለ አስነዋሪ ድርጊት ትፈጽማለህ” ተብለው የተጠየቁት ቤርሉስኮኒ የሰጡት መልስ “እንግዲህ ምን አድርግ ትሉኛላችሁ፤ እኔ በቃ ጥሎብኝ ቆንጆ ሴቶችና ልጃገረዶች እወዳለሁ፡፡ ታዲያ ምን ይጠበስ” የሚል ነው፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ለሶስተኛ ጊዜ በ2008 ዓ.ም ከያዙ ጀምሮ ለሀምሳ አንድ ጊዜ የተካሄደባቸውን የመተማመኛ ድምጽ አሸንፈዋል፡፡ በፍርድ ቤት ከተከፈተባቸው ሃያ ሶስት የወንጀል የክስ ፋይሎች ውስጥ እስካሁንም ድረስ ያልተዘጉ አራት የክስ ፋይሎች ከስልጣን ወንበራቸው ላይ ሊነቅላቸው ነው ተብሎ በተደጋጋሚ ተሰግቶ ነበር፡፡ እንደ ድመት ሰባት ነፍስ አላቸው የሚባሉት ቤርሉስኮኒ ግን ሁሉንም ተቋቁመው አልፈውታል፡፡
በሳቸው የአመራር ጉድለት የተነሳ የጣሊያን ኢኮኖሚ ማሳል ሲጀምር ስልጣናቸውን እንዲለቁ፣ በነጋዴዎች በኢንዱስትሪ ባለቤቶችና በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በየጊዜው ከፍተኛ ግፊት ቢደረግባቸውም አሻፈረኝ ሲሉ ቆይተዋል፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የጣሊያን ቁጥር አንድ ቢሊየነር መሆናቸው ለማንም የታወቀውን ያህል ቁመታቸውን ከፍ ለማድረግ ባለ ረጅም ታኮ ጫማ አዘውትረው እንደሚጫሙ፣ ራሰ በራቸውን ለመሸፈን የፀጉር ተከላ ህክምና እንደወሰዱና በርካታ የፕላስቲክ ሰርጀሪ በፊታቸው ላይ እንዳስደረጉ አንዳችም ነገር ሳይደብቁ በግልጽ ይናገራሉ፡፡
ቀደም ብለን እንደገለጽነው ጣሊያን የሞገደኛና ችግር ፈጣሪ መሪዎች ድርቅ ጨርሶ መቷት አያውቅም፡፡ ከነዚህ ውስጥ በእርግጥ የጀርመኑ ሂትለር ዋነኛ ወዳጅ የነበረውን ቤኒት ሙሶሊኒን የሚወዳደር የለም፡፡ ሙሶሊኒን ተክተው ከመጡት ውስጥ የተመሠረተባቸውን የጉቦና የሙስና ክስ ለማምለጥ በ1994 ዓ.ም ወደቱኒዚያ ሸሽተው በ2000 ዓ.ም እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ እዚያው የኖሩት ሶሻሊስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤቲኖ ክራክሲ ሌላው ተጠቃሽ አስቸጋሪና ቅሌታም መሪ ነበሩ፡፡
ለሠባት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ክሪስቲያን ዲሞክራቱ፣ ጁሊው አንድሪዎቲም ቢሆኑ ከሲሲሊ ማፊያ ጋር ባላቸው ቁርኝት የተነሳ በሙስና ወንጀል በሃያ አራት አመት እስር እንዲቀጡ የተፈረደባቸው መሪ ነበሩ፡፡
የሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ከተመሠረተባቸው በርካታ ክሶች የማምለጣቸውና በጣሊያን ፖለቲካ ግንባር ቀደም ተጽእኖ ፈጣሪ የመሆናቸው ሚስጢር፣ ሰውየው ቅሌታምና ለጥፌ ብቻ ሳይሆኑ እጅግ ብልጣብልጥና ጮሌ ፖለቲከኛም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡
በእርግጥም ቤርሉስኮኒ የጣሊያን የፖለቲካ መድረክና የተዋናዮቹ ማንነት ግልጽ ብሎ የሚታያቸውና ተውኔቱንም ከሁሉም በላቀ ብቃት ለመተወን የሚያስችል ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ ያካበቱት ችሎታ ባለቤት ነበሩ፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የአርተር ሚለር ድርሰት ከሆነው “Death of a salesman” ቲያትር ውስጥ ካለው የዊሊሎማን ገፀ ባህርይ ቀጥተኛ ተቃራኒ ባህርይ የተላበሱ ነጋዴና ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ በንግዳቸውም ሆነ በፖለቲካ አሠራራቸው መርከባቸውን በወጀባማው ባህር ላይ እንዴት አድርገው እንደሚቀዝፏት፣ ሀሳብና አላማቸውንም ለተከታዮቻቸው ብቻ ሳይሆን ለተፎካካሪዎቻቸውም ጭምር ከዋጋው የአንዲት ሳንቲም ቅናሽ ሳያደርጉ እንዴት አድርገው መሸጥ እንደሚችሉ ጥንቅቅ አድርገው ያውቁ ነበር፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የተወለዱት በጣሊያን የኢኮኖሚ እድገት ታሪክ ውስጥ ፈጣን እድገት የተመዘገበበት ዘመን በሚባለውና የጣሊያን የፋይናንስ ዋነኛ ማዕከል በሆነችው በሚላን ከተማ በ1936 ዓ.ም ነበር፡፡
ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ውድመት በፍጥነት እያገገመች የመጣችው ጣሊያን፤ በ1987 ዓ.ም ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ከአለም አምስተኛ ታላቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገር ለመሆን በቃች፡፡ የቤርሉስኮኒ የትውልድ ከተማ የሆነችው ሚላንም እንደጣሊያን ዋነኛ የፋይናንስ ከተማነቷ፣ እንደቤርሉስኮኒ አይነት ፈጣንና ጉጉ የሆነን ስራ ፈጣሪ በሚገባ ለማስተናገድ የሚያስችላትን እልፍኝ ሠፋ አድርጋ ሠርታና ወልውላ ትጠባበቅ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሚላን ለፖለቲካ እንቅስቃሴ የተመቸች ከተማ ነበረች፡፡ በተለይ ለቤርሉስኮኒ፡፡ እንዴት ቢሉ? በጊዜው የነበረው የሚላን ከተማ ከንቲባ እንደ ቤርሉስኮኒ ሁሉ በሚላን ከተማ ተወልደው ያደጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ቤቲኖ ክራክሲ የእህት ባል ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤቲኖ ክራክሲ ደግሞ ከቤርሉስኮኒ አምስት ልጆች የአንደኛው የክርስትና አባት ነበሩ፡፡
ቤርሉስኮኒ በግል የንግድ እንቅስቃሴአቸውም ሆነ በፖለቲካ ህይወታቸው ከፍተኛ እገዛ ያደረገላቸውን የሴልስማንና በጥብቅ በተሣሠረ ቡድን ውስጥ የመሥራትን ጥበብና ክህሎት በቅድሚያ የተማሩት ባለመካከለኛ ገቢ የባንክ ባለሙያ ከሆኑት አባታቸውና የቤት እመቤት ከነበሩት እናታቸው ከወይዘሮ ሮዛ ነበር፡፡
ለቆነጃጅት ሴቶች ያላቸው ወደርየለሽ ፍቅርም እድሜውን የሚቆጥረው ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበሩት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የካቶሊክ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ፊደል ኮንፋሎኔሪ ከተባለ ጓደኛቸው ጋር የትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ባንድ አባልና የቤዝ ጊታር ተጫዋች ነበሩ፡፡ በሚላን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉም ከዚሁ ጓደኛቸው ጋር ሆነው በመርከብ የሚጓጓዙ መንገደኞችን በሙዚቃ በማዝናናት ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኙ ነበር፡፡ ያኔ ቤርሉስኮኒ ጊታር ተጫዋች ሳይሆኑ ከበሮ መቺ ነበሩ፡፡ ሙዚቀኛው ቤርሉስኮኒ ትኩረታቸውን ሙዚቃው ላይ ቢያደርጉም በትምህርታቸው የዋዛ ሠው አልነበሩም፡፡ በሚላን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ያጠኑት የነበረውን የማርኬቲንግ ትምህርት በ1961 ዓ.ም አጠናቀው የተመረቁት በማዕረግ ነበር፡፡
ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ትምህርታቸውን አጠናቀው እንደጨረሱ የመጀመሪያው የንግድ ስራቸውን የጀመሩት የቤት ማጽጂያ (ቫኪውም ክሊነር) በመሸጥ ነበር፡፡ ከዚያ በሁዋላ በአባታቸው አማካኝነት ባገኙት የባንክ ብድር ኤድልኖርድ የተሠኘውን የኮንስትራክሽን ኩባንያ በትውልድ ከተማቸው በሚላን አቋቋሙ፡፡ ቀጥለውም የመጀመሪያውን የቴሌቪዥን ስቱዲዮ አቋቋሙ፡፡ የልጃቸው የክርስትና አባት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤቲኖ ክራክሲ የመንግስትን የቴሌቪዥን ሞኖፖሊ የሚያስቀር ህግ ሲያወጡም የቤርሉስኮኒ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከአንድ ወደ ሶስት ማደግ ብቻ ሳይሆን የጣሊያንን የቴሌቪዥን ሚዲያ በዋናነት ለመቆጣጠር በቁ፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያቸው አማካኝነትም የጣሊያንን ፖለቲካ ከስር መሠረቱ ለዋወጡት፡፡ በግል ሀብታቸውም ከጣሊያን አልፎ በአለም ደረጃ የተጠሩ ቢሊኒየር ባለፀጋ መሆን ቻሉ፡፡ የገዙትን የኤሲሚላን የእግር ኳስ ክለብም ከጣሊያን አልፎ በምድረ አውሮፓ የታወቀ ሻምፒዮን ቡድን በማድረግ የሚላንን ህዝብ የደስታ ጮቤ አስረገጡት፡፡ የቴሌቪዥን ተቋሞቻቸው ባጐናፀፏቸው አዲስ አይነት የፖለቲካ አሠራር በመታገዝ “ፎርዛ ኢታሊያ” የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም፣ የጣሊያንን የፖለቲካ መድረክ በ1993 በይፋ ተቀላቀሉ፡፡ በዓመቱ በ1994 የጥምር መንግስት በማቋቋም የጣሊያንን የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጨበጥ ቻሉ፡፡
በ1996 በተካሄደው ምርጫ በሮማኖ ፕሮዲ ተሸንፈው ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸዉ ወረዱ፡፡ በ2001 ዓ.ም ግን የጥምር መንግስት በመመስረት እንደገና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ብቅ አሉ፡፡ ከሠባት አመት በሁዋላ ድጋሚ በሮማና ፕሮዲ ተሸንፈው ቤተመንግስታቸዉን ለቀው ለመውጣት ተገደዱ፡፡ ያን ጊዜ በርካታ የመስኩ ባለሙያዎች የቤርሉስኮኒ የፖለቲካ ህይወት ተቋጨ ብለው በእርግጠኝነት መናገር ጀምረው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የጉቦና የሙስና ወንጀሎች ክሶችና ከትዳራቸው ውጭ ከወጣት ሴተኛ አዳሪዎች ጋር የሚያደርጉት መረን የለቀቀ የወሲብ ቅሌት በላይ በላይ መደራረብ ሠውየው ምክንያት ሆኖላቸው ነበር፡፡
ባለሙያዎችና ህዝቡ እንዲህ ይበል እንጂ ለብልጣብልጡ ቤርሉስኮኒ ግን ነገሩ ሌላ ነበር፡፡ ሌሎች አለቀላቸው ሲሏቸው እርሳቸው ያስቡትና ይሠሩት የነበረው በቀጣዩ ምርጫ ያጡትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን እንዴት መልሰው እንደሚያገኙት ነበር፡፡ እንዳሰቡትም ከሁለት አመት በሁዋላ በ2008 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ በማሸነፍ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በፈቃዳቸው እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስ ለሶስተኛ ጊዜ የጠቅላይ ማኒስትርነት ስልጣናቸውን መልሠው በመያዝ ጣሊያንን መርተዋታል፡፡
የሌሎች ሀገራት መሪዎችንና ታዋቂ ፖለቲከኞችን የስልጣንና የፖለቲካ ህይወት እስከወዲያኛው የሚቀብረው የጉቦ፣ የሙስናና የስነ ምግባር ቅሌት ለሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ተራ ነገሮች ነበሩ፡፡ ጣሊያን ለሀገራቸውና ለህዝባቸዉ ካበረከቱት መልካም ስራዎች ይልቅ በሙስና ክሶችና ለቁጥር በሚያታክት ከፍተኛ የስነ ምግባር ቅሌት የሚታወቅ መሪ ካላት ያ ሠው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ብቻ ነው፡፡
ማብቂያ የሌለው የሙስናና የጉቦ የወንጀል ክሶች እንዲሁም ከፍተኛ የስነምግባር ቅሌቶች በህብረት ያልጣሏቸው ቤርሉስኮኒ፤ የሀገራቸው የፋይናንስ ቀውስ የፈጠረውን የችግር ማዕበል በተለመደው ጮሌነትና ብልጣብልጥነት ዋኝቶ መውጣት ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ይህም ችግር የፖለቲካ አቅማቸውን የመጨረሻ ልክ አሳያቸው፡፡ እናም ምንም ሳያመነቱና አንዳች አይነት አንጃ ግራንጃ ሳይፈጥሩ ድንገት በጣሊያን ፕሬዚዳንት ቤተመንግስት ከች አሉና የስልጣንና የስራ መልቀቂያ ማመልከቻቸውን ለፕሬዚዳንት ናፖሊታኖ በማቅረብ እጅ ነሱ፡፡
የስልጣን መልቀቂያ ማመልከቻቸውን ካስገቡ በሁዋላ ቤርሉስኮኒ በቀጥታ ያመሩት ሚላን ከተማ አጠገብ በአርኮር ወደሚገኘው ተደናቂ የመኖሪያ ቤታቸው ነው፡፡ ከግብጽ የፈርኦኖች የመቃብር ቦታ ጋር እንዲመሳሠል ተደርጐ በእውቅ የጣሊያን ቀራጭ በነጭ እምነበረድ የተሠራው የቤርሉስኮኒና የቤተሠባቸው ልዩና አስደናቂ የመቃብር ቦታ የተዘጋጀው በዚሁ የመኖሪያ ቤታቸዉ ውስጥ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ስልጣን መልቀቃቸውን ያስታወቁት ቅስማቸው ተሠብሮና በህዝብ መጠላታቸውን አምርረው በመናገር ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁን ከጣሊያን የፖለቲካ መድረክ ቤርሉስኮኒ ገለል ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ መጠየቅ የሚገባን አንድ ሌላ አሪፍ ጥያቄ አለ፡፡ ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ የጣሊያንን የፖለቲካ መድረክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሠናበቱት ማለት ነውን?
በቤርሉስኮኒ መረን የለሽ ቅሌት ለብሔራዊ ውርደት ተዳርገናል የሚሉት ወገኖች፤ የቤርሉስኮኒ ነገር ከእንግዲህ ያለቀ የደቀቀ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የጣሊያን የመንግስት ብሮድካስቲንግ ድርጅት የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበረችው ወይዘሮ ሉቺያ አኑንዚታ ግን ትለያለች፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሠጠችው መልስ “የሞተን አህያ ተጠንቀቅ” የሚል ነው፡፡ መልሷ ሲብራራ፤ አህያው የሞተ ይመስልሀል፤ ወዲያው ግን ይራገጣል ማለቷ ነው፡፡ እንደሞቱ የተቆጠሩት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ድንገት ነፍስ ዘርተው ይራገጡ ይሆን? እንቆይና እንየዋ!

 

Read 6231 times Last modified on Saturday, 19 November 2011 15:13