Print this page
Saturday, 07 September 2013 11:05

የሶሪያ ነገር - የማን ዘር ጐመን ዘር!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የዛሬ አምስት ወር ገደማ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ ተጠራርተው፣ በኳታሯ መዲና ከአንዱ የስብሰባ አዳራሽ ወደ ሌላኛው ሽር ብትን ሲሉ የነበሩትን የሶርያ ተቃዋሚዎች “የወቅቱ ዋነኛ አጀንዳችሁ ምንድን ነው?” ብላችሁ ብትጠይቋቸው፣ ሁሉም በአንድ ቃል የሚሰጧችሁ መልስ ከቀናት ምናልባት ግፋ ቢልም ከሳምንታት በኋላ ስለሚያቋቁሙት አዲሱ የሶርያ መንግስትና ስለሚመሠርቷት አዲሷ ሶርያ ብቻ ነበር፡፡
ከዛሬ ሁለት አመት በፊት በቱኒዚያ የተቀጣጠለውን የአረብ ህዝባዊ አብዮት ተከትሎ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ፣ የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን መንግስት ለመጣል ነፍጥ አንግበው ግብግብ የገጠሙት አማጽያን፣ በወቅቱ በጦር ሜዳው ጐራ እያደረጉት የነበረውን ትግልና ግስጋሴ በቅጡ ከተገነዘባችሁ፣ የተቃዋሚዎችን ይህን መሰል መልስ ለመጠራጠርና ምናልባትም የቀጣዩን ቀን ብርሃን ለማየት የማይበቃ ዋጋ ቢስ ቀቢፀ - ተስፋ ነው በሚል ለመሟገት አትዳዱም፡፡
እርግጥ ነው በዚያን ወቅት የመንግስት ወታደሮች እግራቸው በረገጠው ቦታ ሁሉ፣ የተቃዋሚዎችና የደጋፊዎቻቸው ይዞታ ነው የተባለውን አካባቢ ሁሉ ባገኙት መሳሪያ በምድርና በአየር እየደበደቡ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶርያውያንን መፍጀታቸውን ለአፍታም ቢሆን አላቆሙም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በዚያን ወቅት ለወትሮው ተከፋፍለው እርስበርስ በመናቆር የሚታወቁት የሶርያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አንድ አላማና አቋም የያዙ መስለው ታይተው ነበር፡፡ ያ ወቅት የበሽር አልአሳድ መንግስት ጉድጓዱ የተማሰ፣ ልጡ የተራሰ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ተገምቶ ነበር፡፡ ይህንን የብዙዎች ግምት በዋናነት መሰረት ያደረጉ ግንባር ቀደም አለምአቀፉ የዜና አውታሮች፣ የጧትና ማታ የዜና እወጃቸው፣ የመንግስት ወታደሮች ቅጥ የለሽ የጅምላ ድብደባ፣ የጣር ድብደባ እንደሆነና የፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ ጉዳይ ያለቀ የደቀቀ መሆኑን የሚያስረዳ ነበር፡፡
ይህንን ትንታኔ መሠረት ያደረጉና በተቃዋሚዎች የሚመሠረተውን አዲሱን የሶርያ መንግስትና አዲሲቷን የድህረ አሳድ ሶርያን በራስ አምሳያ ለመፍጠር ያለሙ ሁሉ፣ የመንግስት ወታደሮች ድብደባ እያደረሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም በሚል ሰበብ፣ ቀጥተኛ ሁሉን አቀፍ ጣልቃ ገብነት ለመፈፀም ቋምጠው ነበር - ከቻይናና ከራሺያ በስተቀር፡፡
ከመካከለኛው ምስራቅ አንስቶ እስከ አሜሪካና አውሮፓ ድረስ ሶርያን በተመለከተ ዋነኛ የውይይት አጀንዳ የነበረው አዲሲቷን ሶርያ ለመፍጠርና ለማቋቋም እንዴት ቻይናና ራሺያን ማግባባት ይቻላል የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ የሶርያ ህዝባዊ አመጽ ከተቀጣጠለበት ከዛሬ ሶስት አመት ጀምሮ ቻይናም ሆነች የፕሬዚዳንት ፑቲኗ ራሺያ አቋማቸውን በግልጽ ከማስረዳት ፈጽሞ ቦዝነው አያውቁም፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን መንግስት በሀይል ለመገልበጥ የሚደረግን ማናቸውንም አይነት የውጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የምራቸውን እንደሚቃወሙ ሁልጊዜ በይፋ እንደገለፁ ነው፡፡
አሜሪካና የአውሮፓ ወዳጆቿም፤ ቻይናና ራሺያ የያዙትን አቋም ቀይረው ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን ለማስወገድ ከጐናቸው እንዲቆሙ ለማድረግ፣ በእርስ በርስ ጦርነቱ የተነሳ በተለይም በመንግስት ወታደሮች የጅምላ ድብደባ አማካኝነት በሶርያ የደረሰውን አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ እንደዋና ምክንያትነት በመጠቀም የቻሉትን ያህል ለማሳመን ጥረው ነበር፡፡ እንደእውነቱ ከሆነም ነገርዬው ከአለም አቀፉ የብሔራዊ ጥቅምና የዲፕሎማሲ ቁርቁስ በላይ ነበር፡፡
ከዛሬ አምስት ወር በፊት የተባበሩት መንግስታት ያወጣው መረጃ፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ መቶ ሺ የሚልቁ ሶርያውን ህይወታቸውን እንዳጡና አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ቤት ንብረታቸውንና ቀያቸውን ጥለው ወደ ጐረቤት ሀገራት እንደተሰደዱ ያስረዳል፡፡
የሊቢያውን አምባገነን መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣናቸው ለማስወገድ በተወሰደው የኔቶ ወታደራዊ እርምጃ፤ በአሜሪካና በአውሮፓ አጋሮቿ “አይሆኑ አሸዋወድ ተሸውደን ተጃጅለናል” ያሉት ቻይናና ራሺያ ግን በዚህ የሶርያ ሰብአዊ ቀውስና በቀረበላቸው የእልቂትና የሰቆቃ መረጃ ለአፍታም ቢሆን ልባቸው ሊራራ አልቻለም፡፡ ዛሬም የያዙት አቋም አንድ ነው፡፡ ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የውጪ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትንና በሶርያ ላይ የሚወሰድን ወታደራዊ እርምጃ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ግልጽ አድርገዋል፡፡
ዛሬ በሶርያ ያለው ጠቅላላ ሁኔታ የዛሬ አምስት ወር ከነበረው በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ እናም አሁን የሶርያን ተቃዋሚዎች “ነገሩ እንዴት ነው” ብትሏቸው፣ ጨርሰው ባላሰቡትና ይሆናል ብለው ባልገመቱት ሁኔታ በሼህ ናስሩላህ የሚመራው የሊባኖስ የሂዝቦላ ተዋጊዎች የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን መንግስት በመደገፍ የውጊያውን አውድማ በመቀላቀላቸው፣ ሊጨብጡት በእጅጉ ተቃርበው የነበረውን የረጅም ዘመን ህልማቸውን እንዳጨናገፉባቸው ይነግሯችኋል፡፡
ይህ ደግሞ አንዳችም ሀሰት ነገር የለውም። ትናንት አለቀላቸው የተባሉት ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ፤ ድል እየቀናቸው ተቃዋሚ አማፂያንን ይዘውት ከነበረው አካባቢ እያስለቀቋቸው ይገኛሉ። እየወሰዱት ያለው የጭካኔ እርምጃም ግለቱን አልቀነሰም፡፡
ሶቪየት ህብረትን ከሠላሳ አመታት በላይ ሰጥ ለጥ አድርጐ የገዛው ጓድ ዋና ፀሐፊ ጆሴፍ ስታሊን፤ በአንድ ወቅት የሰዎችን መንጋ እልቂት አስመልክቶ “የአምስትና አስር ሰው ሞት አሳዛኝ ነገር ነው። የሺዎች እልቂት ግን ተራ ስታቲስቲክስ ነው፡፡ በማለት እንደተናገረ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ ነገርም እንዲሁ ነው፡፡ ለእሳቸው የመቶ ሺ ሶርያውያን ወገኖቻቸው እልቂት አሳዛኝ ክስተት ሳይሆን ተራ የስታቲስቲክስ ጉዳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ የአባታቸው ልጅ ናቸው፡፡ በ1971 ዓ.ም የፖለቲካ የጡት አባታቸው የነበሩትን ጀነራል ሳላህ አልጀዲድን በወታደራዊ ሃይል ገልብጠው ስልጣን ላይ በመውጣት፣ በከባድ የልብ ህመም የተነሳ ህይወታቸው እስካለፈበት እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ለሃያ ዘጠኝ አመታት ድፍን ሶርያን ከብረት በጠነከረ እጃቸው አንቀጥቅጠው መግዛት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ የአሳድ ፕሬዚዳንታዊ ስርወ መንግስት መመስረት የቻሉት አባታቸው ፕሬዚዳንት ሀፌዝ አል አሳድ፤ በተግባር እያሳዩ ያሳደጓቸው የሶርያውያን ህይወት ከእርሳቸው ስልጣን የበለጠ ዋጋ እንደማያወጣ ነው፡፡
የአይን ህክምና የዶክትሬት ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አውሮፓ ከመሄዳቸው በፊትም በ1982 ዓ.ም በሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት አማካኝነት የተነሳባቸውን ጠንካራ ተቃውሞ፣ ከሃያ ሺ በላይ የሆኑ የሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት መሪዎችን፣ አባላትንና ደጋፊዎችን በሃማ ከተማ ልዩ የደህንነት ኮማንዶ ጦራቸውን በማሰማራት ያለ ርህራሄ በማስጨፍጨፋቸው የተነሳባቸውን ተቃውሞና አመጽ ፀጥ ረጭ ሲያደርጉ፣ ወጣቱ ባሻር አልአሳድ በአይናቸው በብረቱ አይተዋል። ከዚያን ጊዜ በኋላም ፕሬዚዳንት ሃፌዝ አልአሳድ ለተቃዋሚዎቻቸው እንዴት ያለ ጠንካራ ክንድና ድርብ አንጀት እንደነበራቸው ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በሚገባ ተገንዝበዋል፡፡
እና ታዲያ የማን ዘር ጐመን ዘር! በአባታቸው እግር የተተኩት ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድም፣ በአመጽ ለተነሱባቸው ተቃዋሚዎቻቸው የሚዝል ክንድም ሆነ የሚራራ አንጀት ጨርሶ አልነበራቸውም፡፡ ከእርሳቸው ስልጣን የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና እንኳን በመቶ ሺዎች ቀርቶ በሚሊዮኖችም ቢሆን የሶርያውን ህይወት ቢጠፋ ከቁም ነገር የሚጥፉት ጉዳይ አይደለም፡፡
የአማፂያኑን አከርካሪና የደጋፊዎቻቸውን ቅስም ለመስበር፣ በአየርና በምድር ያልተጠቀሙት የመሳሪያ አይነት አልነበረም፡፡ ሰሞኑን ግን ከአጋሮቻቸው ቻይናና ራሺያ በስተቀር ድፍን አለም የፈራው ደርሷል፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ሶርያውያን በኬሚካል የጦር መሳሪያ ጥቃት ያለ ርህራሄ ተጨፍጭፈዋል፡፡
ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ፤ “ጭፍጨፋውን ሆን ብለው ያደረሱት የአማጽያኑ ወታደሮች እንጂ እኔስ የኬሚካል ጦር መሳሪያ በዞረበትም አልዞርኩ” በማለት ማስተባበያቸውን ሰጥተዋል። የሚያምናቸው ግን ጨርሶ ማግኘት አልቻሉም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ለአስራ ሶስት አመታት በዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን አስከፊ ድርጊት ይቅር ቢባሉ እንኳ አመጽ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰነዝሩት በነበረው እጅግ አሰቃቂ ጥቃት የተነሳ ሰውየው ያሉትን አምኖ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ቀድሞ ነገር ሰውዬው እኮ የአባታቸው ልጅ ናቸው!
የአሁኑ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ግን እንዳለፉት ጊዜያት ጥቃቶች በቸልታ የሚታለፍ አልሆነም፡፡ ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ አልፈፀምኩም ብለው ምለው ቢገዙቱም፣ አሜሪካና የአውሮፓ አጋሮቿ ከእርሳቸው ራስ አንወርድም ብለዋል፡፡
አሜሪካ በተለይ በዚህ ብቻ አልተወሰነችም። “የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድን ወታደሮች ደምስሼ የስልጣን ገመዱን ባላሳጥረው አገር ብላችሁ አትቁጠሩኝ” ብላ አካኪ ዘራፍ ፎክራለች፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሯ ቸክ ሀግልም “አስፈላጊውን ወታደራዊ ዝግጅት አጠናቀን እየጠበቅን ያለነው፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ተኩሱ የሚል ትዕዛዝ ብቻ ነው” በማለት የአሜሪካ ፉከራ ተራ ፉከራ እንዳልሆነ በግልጽ አሳውቀዋል፡፡ ራሺያም በበኩሏ እስኪ የምታደርጉትን አያለሁ ብላለች። መንግስታዊው “ኮስሞፖልስኪ ፕራቭዳ” የተሰኘው ጋዜጣ፤ “ራሺያ እንደሌላው ጊዜ እጇን አጣጥፋ በማስጠንቀቂያ ብቻ ትቀመጣለች ብሎ የሚገምት ካለ እርሱ እርሙን ያውጣ” በማለት አስፈራርቷል፡፡
አሁን ባለው አጠቃላይ የሶርያ ሁኔታ ሁለት ነገሮች እርግጠኛ የሆኑ ይመስላል፡፡ አንደኛው አሜሪካ ተባባሪ አገኘች አላገኘች ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷና ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ ከስልጣናቸው መፈናቀላቸው ነው፡፡ ቁርጡ ያልታወቀውና መጨረሻውን ለማወቅ የሚያጓጓው ደግሞ ራሽያ የዛተችውን ታደርግ ይሆን? ወይስ “ቆይ ነገ አገኝሻለሁ” ብላ በዛቻ ብቻ ትቀራለች? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ጊዜ ለዚህና ለሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ምላሹን ይሰጠናል፡፡

Read 4221 times