Print this page
Friday, 13 September 2013 12:35

ጭፈራችን ተመልሷል!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ጭፈራችንን መልሱ”፤ ብለን ነበር ትላንት በስቲያ
“አገራችንን መልሱ”፤ ብለን ነበር ትላንት በስቲያ
የሰሙን ምሥጋን ይግባቸው፤ እሰየው አለች ኢቶ’ጵያ!!
ወትሮም መደማመጥ እንጂ፣ መደነቋቆር ክሶ አያቅ
ቆርጠው ካልበጠሱት በቀር፣ ከዘመዘሙት ቂም አያልቅ
ዛሬን ድል አገኘሁ ብሎ፣ የነግ ፈተናም አይናቅ!

በአገር ጉዳይ ቂም አያቅም፣ ይሄው ህዝቡ ይጨፍራል፡፡
ይሄው መሬቱ ይጨሳል፡፡
ባንዲራው እንደነበልባል፣ ዳር ከዳር ይንቀለቀላል!!
መብራት ቢጠፋ ምን ግዱ፣ ህዝቡ እሳት ሆኖ ይበራል
ብርሃን ነው ይነድዳል አበሽ፤ ኤሌትሪክ ነው ይያያዛል!!
ዕድሜ ለልጆቻችን ጭፈራችን ተመልሷል፡፡
“…እስኪበጣጠስ ላንቃችን”
መጅ እስኪያወጣ ጉሮሮአችን
“አገር ላዕላይ ነው” እንዳልን
እንደህፀፁ ብዛት ሳይሆን፣ እንደልባችን ጽናት
አቆጥቁጦ ልሣናችን፣ እስከነገና እስከትላንት
እንደፊኒክስ ከረመጥ፣ ከትቢያ እንነሳለን፡፡
እንደ ድመት ዕድሜ ጥናት አሥራ ሶስት ነብስ ነው ያለን፤

ከሣግ ጩኸት ሞታችን ውስጥ፣ ለእንቁጣጣሽ ፀሐይ በቃን!
ህይወትም ትግል ነውና፣ መከራችንም ባያልቅ
ይውለበለባል እንጂ፣ ባንዲራ አያዘቀዝቅ
ልብ ነብሱን ይገብራል፣ ጀግና አገሩ እስከምትስቅ
ዕድሜ ለልጆቻችን እግራቸው ላልዶለዶመ
ያም ያን ቢል፣ ያም ያን ቢላቸው፣ ቅን ቅስማቸው ላልታመመ፡፡
ወትሮም አቀርቅረው እንጂ፣ አንዴ ከተለኮሱማ
የወይራ ለበቅ ናቸው፣ የቁርጡ ቀን ከመጣማ
በአሸዋ እርሻም ሜዳ ቢሆን፣ አንዴ አውድማ ከገቡማ
መንሽ ነው ልባም እግራቸው፣ አሂዶ እኮ ነው ኳሱማ!!
ምሥጋና ይግባቸው አቦ!!
ዕድሜ ለልጆቻችን
ተመልሷል ጭፈራችን!!
አካፋን አካፋ እንዳልነው
ወርቅ እግሩን እናመስግነው፡፡
ይህንን ባህል እናርገው፡፡
ዛሬስ ህዝባችን ታድሏል
የእንቁጣጣሽ ድል አዝምሯል!
የሀገር ፍቅር ነው እንጂ፣ ወኔ ወጌሻ አይፈልግም
ወድቆ መነሳትን ማወቅ፣ ልብ እንጂ ወግ አይክሰውም
ሐሞትን አጠንፍፎ እንጂ፣ በዕንባ ጐርፍ ጉድፍ አይጠራም፤
በቆራጥነት በተቀር፣ የልባም ቀን ጥም - አይቆርጥም፡፡
ጨክነው ከተዘጋጁ፤ እንዲህ እዚህ ይደረሳል
ህዝብም አካሉን ሁሉ፣ በባንዲራ ይነቀሳል…
የአገሩን ቀለም ይኳላል
አገሩን ፊቱን ይቀባል፡፡
በቄጤማ በዐደይ ማህል፣ ኳስም ጮቤ ረገጠች
ኳስም አበባ - አየሁ አለች
የነግ መንገዷን ለማብራት፣ የተስፋ ችቦ ለኮሰች
“የሽንፈት ምንቸት ውጣ”፣ “የድሉ ምንቸት ግባ” አለች!!
ዕድሜ ለልጆቻችን፣ ተክሷል ህዝብ ተክሷል
የአዲሱን ዓመት፣ ድል ለብሷል
በደልም በድል ይረሳል፤
ድል በትግል ይወረሳል!!
ጭፈራችን ተመልሷል!
ጳጉሜ 2 2005 ዓ.ም
(ዛሬም ለኳስ ተጨዋቾቻችንና
ለቅኑ የኢትዮጵያ ህዝብ)

Read 2972 times
Administrator

Latest from Administrator