Friday, 13 September 2013 12:38

ሆደ ሰፊው ባሕር

Written by  ነ.መ
Rate this item
(1 Vote)

ሆደ ሰፊው ባሕር
የአዲስ ዓመት ንጋት
የአዲስ ዓመት ጠዋት
ምን ያሳየኝ ይሆን?
እያልኩኝ ስጠይቅ፣ በማለዳ ጉጉት፤
የመጣውን ዘመን፣ ወንዝ ሆኖ አገኘሁት፡፡
የመስከረም ፀሐይ፣ የአደዬ ጅረት ነው
የመስከረም ፀሐይ፣ የአበባ ወንዝ ነው
የአበባ ፍቅር ጽንፍ፣
አሊያም የመንፈስ ጐርፍ፤
በራሪው ጊዜ ነው፣ ክንፉ እማይታጠፍ፡፡
ወንዝ ሆኖ አገኘሁት፣ የ’ስካሁኑን ዘመን
ስንት ዓመት የኖረ፣ የዕድሜ አበባ - ጉንጉን
የባሕሩ እርጋታ …አሁን ያገኘነው፣
ከብዙ ርኩቻ፣ ኋላ ነው የመጣው፡፡
ጠብታ ከሰማይ ምድር ተጠራቅማ
ወንዝ ሆና፣ ጐርፍ ሆና- ስታንቀሳቅሰው
ያን የክረምት አጀብ ያን የውሃ ጀማ
አንድ አገር አክላ
ከባህሩ ስትገባ፤
መናገሯ ነ በውሃ ልሣኗ፣ በውሃ ትረካ
እያደር ማደጉን፣
ቀንም ወደዘመን፣ችግኝ ወደ ዋርካ፡፡
አንዱ ውሃ ሌላውን ሲያባርረው ውሎ
ሂያጅም ሆነ ኗሪ
ክፉም ሆነ በጐ፤ ሰብቶም ሆነ ሰልሎ
ማረፊያው ባህር ነው፤ ሞቶም ሆነ ገሎ
“እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ”
የተባለለት ወንዝ የውሃው ሙላት
ባሕሩ ውስጥ ያርፋል ቀን የሞላ ለት፡፡
ዘመን ይለወጣል በወንዙ ፍሰት፡፡
ሆደ ሰፊው ባሕር ስንቱን አስተናግዷል
ያገር እኩያ ነው ዛሬም ገና ያድጋል፡፡
ጊዜም ፈስሶ ፈስሶ፣ ከወንዞቹ ጋራ
ባሕሩ ላይ ይከትማል፣ የውሃው ደመራ፡፡
ሆደ ሰፊው ባህር፣ ሁሉን አቻቻይ ነው
የኢትዮጵያ ምልክት፣ የዘመን ባሕር ነው!
ስንቱን ደራሽ ውሃ
ስንቱን ውሃ ሙላት
ስንቱን ዱታው ዘራፍ
ስንቱን የድንገት ጐርፍ፤
ቁጣውን አብርዶ
እንደምድር ችሎ
እንደልጅ አባብሎ፤
ገላው ያረገዋል፣ ስሙን ባሕር ብሎ!!
ሆደ - ሰፊው ባሕር፣ የውሃ እልፍኝ ነው
ሆደ - ሰፊው ባሕር፣ የውሃ ሸንጐ ነው
ሆደ - ሰፊው ባህር የኢትዮጵያ እኩያ ነው፡፡
ማዕበል ንፋሱ፣ ውሃውን ይገፋል
ሶምሶማው ሲረግብ፣ ባህሩ ዳር ያበቃል፡፡
ጐርፉም ጐርፎ ጐርፎ፣ ባህሩ ውስጥ ይተኛል
ባሕሩ ሆደ - ሰፊው፣ ስንቱን አስተናግዷል
የኢትዮጵያ ሙቀት ነው፣ ዘመን ይለውጣል፡፡
ከማዕበል በፊት የባህሩ እርጋታ
የዓለምን ሁለት ፊት፣ ተፃራሪ ፋታ
ያሳያል ያን ዳገት፤ ያሳያል ቁልቁለት
ያሳያል አፋክሮ፣ ያሳያል አፋቅሮ፣
ያሳያል አካሮ፤
ተለዋዋጩን ገጽ አጥንቶና አጥቁሮ
የዘመኑን ልደት ዛሬም ዳግም ቆጥሮ!
የባሕሩ ቀን ሆኗል፣ የዓመታት ጅማሮ!!
የባሕሩ ቀን ሆኗል፤ የአበቅቴ ቋጠሮ፡፡
ጳጉሜ 1 2006 ዓ.ም
(ለእንቁጣጣሽ 2006 እና ለ25ኛው)

Read 3224 times