Monday, 16 September 2013 08:07

ሮሽ ሐሻና፣ የአይሁዶች አዲስ አመት አከባበር

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(3 votes)

            ዛሬ የኢትዮጵያውያን አዲሱ የ2006 ዓ.ም ከገባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ነው፡፡ ይህን የአዲሱን ዘመን መልካምና አስደሳች ስሜት እያጣጣሙ ያሉት በሀገራቸው ውስጥ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም። በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ይህንን አይነቱን ጣፋጭ ስሜትና ደስታ ይጋራሉ፡፡
በምድረ እስራኤል ለሚኖሩትም ሆነ በመላው አለም ተበትነው ለሚገኙት አይሁዶች የዛሬው ቅዳሜ አዲሱን አመት ከተቀበሉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያከብሩት የሻባት (ሰንበት) ቀን ነው፡፡ መላ አይሁዳውያን “ሮሽ ሐሻና” እያሉ የሚጠሩትን የአዲስ አመት ክብረበአላቸውን ከዛሬ አስራ አንድ ቀን በፊት ነሐሴ 29 ቀን በታላቅ ስነስርዓት አክብረዋል፡፡ አይሁዳውያን ይህን የሮሽ ሃሻና ክብረበአል ካከበሩት እነሆ ዛሬ ስምንተኛ ቀናቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የበአል ስሜታቸው ገና አልበረደም፡፡ እናም እርስ በርስ ሲገናኙ “ሻና ቶቫ” (እንኳን አደረሰህ) እየተባባሉ መልካም ምኞታቸውን ይገላለጣሉ፡፡
እንደተቀሩት አይሁዳውያን ሁሉ ቤተእስራኤል በመባል ተለይተው የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን አይሁዶችም የሮሽ ሀሻናን ክብረበአል ያከበሩት በሞቀ ስሜትና በአዲስ ተስፋ ተሞልተው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው ከኢትዮጵያ የሄዱ መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
እንደ እስራኤል መንግስት ይፋ መግለጫ ዛሬ ከአንድ መቶ አርባ ሺ በላይ ቤተእስራኤል ይሁዲዎች በመላ እስራኤል ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህ ቁጥራቸው ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ ጋር ሲነፃፀር ሁለት በመቶ ያክላል፡፡
ከጠቅላላው የእስራኤል ከተሞች ውስጥ በርካታ ቤተ እስራኤሎች (ወደ 12ሺ የሚጠጉት) የሚኖሩት በናታንያ ከተማ ሲሆን ሪሾን ላዚወንና አሽዶድ ከተሞች ከስድስት ሺ በላይ የሚሆኑትን ቤተእስራኤሎች በመያዝ በሁለተኛና በሶስተኛነት ይከተላሉ፡፡ ጥቂት ቤተእስራኤሎች የሚኖሩባት ደግሞ የባትያም ከተማ ብቻ ናት፡፡ በዚች ከተማ የሚኖሩት ቤተእስራኤሎች ቁጥራቸው ሁለት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሰባት ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን የአዲሱን አመት መቀበያ ክብረበአላቸውን ያከበሩት መስከረም 1 ቀን ረቡዕ እለት ነበር፡፡ አይሁዳውያንም የአዲሱን አመት መቀበያ የሮሽ ሀሻና በአላቸውን ያከበሩት አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ነሐሴ 29 ቀን ረቡዕ እለት ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከአስር ቀን በኋላ በታላቅ ስነስርአት የሚያከብሩት “መስቀል” የተሰኘ ክብረበአል አላቸው፡፡
አይሁዶችም ዬምኪፑር (አስተሰርዬ) የተሰኘውን ታላቅ ክብረ በአላቸውን አዲሱ አመት በገባ ወይም በቲሸሪ አስረኛው ቀን ላይ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርአት ያከብራሉ፡፡
እነዚህ ሁለት ጉዳዮች የቀረቡት የዚህን አመት ግጥምጥሞጽ ለማመልከት ብቻ ነው፡፡ የእስራኤል የቀን አቆጣጠር በጨረቃ ኡደት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ የሮሽ ሀሻና በአል አንዳንዴ ጳጉሜ ላይ፣ አንዳንዴ መስከረም መጀመሪያ ላይ ወይም መስከረም አጋማሽ ላይ፣ በጣም ሲረዝም ደግሞ መስከረም መጨረሻ ላይ ይውላል እንጂ እንደ ኢትዮጵያውያን አሊያም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠሮች የተወሰነ አይደለም፡፡
የሆነ ሆኖ ምንም እንኳን ኢትዮጵያውያንና አይሁዳውያን በአንድ ሳምንት ልዩነት አዲስ አመት ቢቀበሉም የአቀባበል ስርአታቸውን የሚያከብሩት እንደየራሳቸው ባህል፣ ወግና ሃይማኖታዊ ስርአት መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተእስራኤሎችን ጨምሮ አይሁዳውያን የአዲሱን አመት መቀበያ የሮሽ ሀሻና በአላቸውን ያከበሩት ወይም የሚያከብሩት በሚከተለው አኳኋን ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና ፈጣሪ አምላክ መላ አይሁዳውያንን በታላቅ ስነስርአትና፣ ሀይማኖታዊ መገዛት እንዲያከብሩት የአይሁዶች ቅዱስ መጽሀፍ በሆነው በቶራህ (ኦሪት) ካዘዛቸው አምስት ዋና ዋና በአላቶች (ዬምኪፑር፣ ሱከት፣ ፔሳህና፣ ሻሾች) አንዱ ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና የሚለው የእብራይስጥ ቃል ተራ ትርጉሙ ሲተነተን እንዲህ ነው፡፡ ሮሽ ማለት ራስ ማለት ነው፡፡ ሀሻና ማለት ደግሞ አመት፣ ዘመን ማለት ነው፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ሲተረጐም ደግሞ “የአመቱ ራስ” ማለት ነው፡፡ የዚህ ቃል ጥልቅ ትርጉምና ትንታኔ ደግሞ “አኑመዲ” ወይም በኦሪት ዘፍጥረት 1÷5 “ብርሀን ይሁን አለ፡፡ ብርሀንም ሆነ” በሚል የተጠቀሰውን የአለምን መፈጠር ያመላክታል፡፡
ሮሽ ሀሻና በምድረ እስራኤል የሚኖሩ አይሁዶች ለአንድ ቀን፣ በመላው አለም ተበትነው የሚኖሩት አይሁዶች ደግሞ ለሁለት ቀናት ያከብሩታል፡፡ በዚህም መሠረት የዚህን አመት ሮሽ ሀሻና ክብረ በአል እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ አይሁዶች ረቡዕ ነሀሴ ሀያ ዘጠኝ ቀን ሲያከብሩ ከእስራኤል ውጪ ያሉት ደግሞ ከነሀሴ 29 ፀሀይ ግባት ጀምረው እስከ አርብ ጳጉሜ አንድ ውድቅት ድረስ በሞቀ ስሜትና በአዲስ መንፈስ አክብረዋል፡፡
በመላው አለም የሚኖሩ ህዝቦች እንደየባህልና ወጋቸው አዲስ አመትን ሲያከብሩ ያለፈውን አመት ስኬትና ውድቀታቸውን በትዝታ እየቃኙ በመገምገም፣ በአዲሱ አመት አዲስ ነገር ለመፈፀም በአዲስ መንፈስ ሲነሳሱ ማየትና መስማት የሰው ልጅ ሰው ሆኖ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረ ክስተት ነው፡፡ አይሁዳውያንም ከተቀረው የአለማችን ህዝቦች የተለዩ አይደለምና በሮሽ ሀሻና በአላቸው ላይ ያለፈውን አመት ስኬት በአዲሱ አመትም ለመድገም ወይም ያለፈውን አመት ውድቀታቸውን በአዲሱ አመት ሲሆን በስኬት ለመለወጥ አሊያም ላለመድገም በሞቀ ስሜትና በአዲስ መንፈስ ይነሳሳሉ፡፡
በሮሽ ሀሻና ቀን ወይም ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ የሚቀርበውና የሚበላውም የምግብ አይነቶች የአሳ ራስ (ጭንቅላት) ማር በዳቦና በማር የተነከረ አፕል ናቸው፡፡
እነዚህ ሶስት የምግብ አይነቶች ራሳቸውን የቻሉ ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡ የአሳው ራስ የሚቀርበው በአዲሱ አመት አምላካችን ለመልካም ነገር ሁሉ ራስ ያድርገን ለማለት ሲሆን ዳቦ በማር የሚቀርበው ደግሞ በአዲሱ አመት አምላካችን ህይወታችንን እንደ ማር የጣፈጠ ያድርግልን፣ በቶራህ ልባችንን ደስ ይበለው ወይም አምላካችን ልባችንን ደስ ያሰኘው ለማለት ነው፡፡ በማር የተነከረ አፕል የሚበላውም ፈጣሪ አምላክ መጭውን ህይወታችን እንደ ማር የጣፈጠ፣ እንደ አፕል አስደሳችና ረጅም ወይም ያልተቋረጠ (አፕል ክብ ስለሆነ) ያድርግልን ለማለት ነው፡፡
ከምግቡ ስነ ስርአት ቀጥሎ በእለቱ የሚከናወነው ሌላኛው ሀይማኖታዊ ስርአት የ “ሾፋር” ወይም ቀንደ መለከት የመንፋት ስርአት ነው፡፡ በዚህ የሮሽ ሀሻና በአል ላይ የሚነፋው ሾፋር የሚሠራው ቢያንስ አንድ ዙር ከተጠመዘዘ የራም ወይም የከነአን አካባቢ ሙክት በግ ወይም ፍየል ቀንድ ነው፡፡
የቀንዱ መጠማዘዝ ታላቁ የእስራኤላውያን አባት አብርሀም ልጁን ይስሀቅን ፈጣሪ አምላክ እንዳዘዘው ሊሰዋው ባለ ጊዜ አምላክ ያደረገውን ለማስታወስ ነው፡፡
ሾፋርን የመንፋት ስነ ስርአቱ የሚከናወነው በሶስት የአነፋፍ ስልት ነው፡፡ “ሐዘኑ” ወይም ፀሎቱን የሚመራው ራባይ ወይም በቤተእስራኤሎች ዘንድ ቄሱ፣ አሊያም እንደሚገባ አድርጐ መንፋት የሚችል ሌላ ማንኛውም ሰው አጠገቡ ቆሞ ቶራህን የሚያነበውን ሰው የአነባበብ ስልት በመከተል ይነፋል፡፡
በሮሽ በአል ወቅት ከሞላ ጐደል ሾፋር እየተነፋ ዘወትር የሚነበበው የቶራህ ክፍል፣ ፈጣሪ አምላክን በፍፁም ልብና ታማኝነት የመታዘዝን አስፈላጊነትና በእምነት የመጽናትን ፀጋ ለማስረዳት በኦሪት ዘፍጥረት 22÷2-15 የቀረበው የአብርሀምና የልጁ የይስሀቅ ታሪክ ነው፡፡
ሮሽ ሀሻና በሚከበርበት እለት “ሴፈር ቶራህ” ወይም “የኦሪቱ ጥቅል” እንዲወጣ ከተፈለገ “ማኒያን” ወይም ኮረም መሙላት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ ማኒያን እንዲሞላ የሚያስፈልጉት አስርና ከአስር በላይ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎቹ ዘጠኝ ቢሆኑ እንኳ ሴፌር ቶራህ በፍፁም መውጣት አይችልም፡፡
ሮሽ ሀሻና በሚከበርበት እለት ማንኛውም አይሁዳዊ ምንም አይነት ስራ መስራት አይችልም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከስራ ቁሳቁሶችና ከስራ ቦታ አካባቢም ዝር እንዲል ፈጽሞ አልተፈቀደለትም፡፡
በዚህ ቀን ማድረግ የሚችለው መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ወደ መኖሪያ ቤቱ የመጡትን በመልካም ሁኔታ ተቀብሎ ማስተናገድ አሊያም ወደ ምኩራብ ጐራ ብሎ በዚያ ለፈጣሪ አምላክ ምስጋና ማቅረብና መፀለይ ብቻ ነው፡፡
በዚህ በሮሽ ሀሻና ክብረበአል ይሁዲዎች እርስ በርስ ሲገናኙ “ሻና ቶቫ” መልካም አዲስ ዓመት ወይም “ሻና ቶቫ ቭሚቡራሸት!” መልካም አዲስ አመት ከአምላክ በረከት ጋር! ወይም ደግሞ በረጅሙ “ሻና ቶቫ ቴካቴቭ ቭትሀቲሙ!፡- ለመልካሙ ዘመን በህይወት መጽሀፍ ታተሙ! ይባባላሉ፡፡
ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩት፤ ኢትዮጵያውያን በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት እንቁጣጣሽ ወይም ቅዱስ ዮሀንስ የተሰኘውን የአዲስ አመት ክብረ በአላቸውን ካከበሩ በኋላ ቀጥለው ለሚያከብሩት የመስቀል በአል መዘጋጀት ይጀምራሉ፡፡ አይሁዳውያን ደግሞ የሮሽ ሀሻናን ክብረ በአል ካከበሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚከተለውን የዮምኪፑር (የመስተሰርየት) በአልን በታላቅ ስነስርአት ለማክበር በሚገባ መዘጋጀት ይጀምራሉ፡፡
የሮሽ ሀሻና በአል አከባበር ግን ይህንን ይመስላል፡፡ በመጨረሻ ሁላችሁንም “ሻና ቶቫ ቭሚቡራሸት!” እላችኋለሁ፡፡

Read 7291 times