Saturday, 26 November 2011 07:48

ጩኸቶች በልዩነት ለምን ሆነ?

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

ጥቃት በደረሰባቸው ሴቶች መካከል አድልዎ እየተደረገ ነው
ለአንዷ ጩኸትና ድጋፍ ይጐርፋል፤ ሌላዋ ግን የሚያስታውሳት የለም
በአሲድ ጥቃት የደረሰባቸው፤ በቀን 500 ብር ለህክምና ይከፍላሉ
ጥቃት ለደረሰበት ሰው ነፃ ህክምና መስጠት ክልክል ነው
ማንንም ለይተን አናውቅም ፤ አድልዎ አንፈጽምም
በየካቲት 12 ሆስፒታል ከሁለት ወር በላይ እንደሆናት የተናገረችው ቤተል አዲሱ፤ ከምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ ነው የመጣችው፡፡ የአሲድ ጥቃት
የደረሰባት የ21 አመት ወጣት ቤተል፤ ሳትውል ሳታድር ለህክምና አዲስ አበባ መምጣት ብትችል ኖሮ፤ ጉዳቷና ስቃይዋ ትንሽ በቀነሰላት ነበር፡

በአሲድ የተቃጠሉ አይኖቿ፤ ጆሮዎቿ፣ ፊቷና ደረቷ የሚፈጥሩት ስቃይ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ፤ ራሷን ሳትስት መቆየት ለቤተል እጅግ ከባድ ነው፡፡ ስቃዩ ባይኖርባት እንኳ አይንና ጆሮዋ በፈጣን ህክምና ሊተርፍ አይችልም፡፡ የቤተሰቦቿ የገንዘብ አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ፤ ከጐረቤትና ከዘመድ ገንዘብ እስኪዋጣ ድረስ ሁለት ቀን መጠበቅ የግድ ነበር፡፡ ከልጅነት ጀምሮ የቤተል ኑሮና እድገት፤ ከድህነት ጋር የሚደረግ ትግል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማትሪክ ተፈትና ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ መሄድ ራሱ ትልቅ ፈተና እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የጐረቤት ሠዎች በሚያደርላጉት እርዳታ የኑሮ ችግርን ለመቋቋም ብትሞክርም፤ ጦም የማደር ያህል እየኖረች በዲላ ዩኒቨርሲቲ እየተማረች ነው አምና በዲግሪ የተመረቀችው፡፡ ትምህርቷን አጠናቅቃ በመመረቋ እየተደሰተች፤ ስራ ለመያዝም በተስፋ ተሞልታ ወደ ወላጆቿ ሄደች፡፡ ስራ ይዛ የራሷንና የቤተሰቦቿን ኑሮ ስታሻሽል 
እየታያት መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም ያላሰበችው ነገር ደረሰ፡፡ ከምሽቱ 2 ሠአት ተኩል ገደማ፤ አንድ ሠው ወደ ቤታቸው መጥቶ ይጠራታል፡፡ በሩን ከፍታ ስትወጣ፤ ሰውዬው ሠልፈሪክ አሲድ ደፋባት፡፡ ከፊቷ ጀምሮ ደረቷ እና ሌላው ሠውነቷ ላይ፡፡ ሁሉም ነገር እሳት ሆነባት፡፡ ጥቃት የፈፀመባት ሰው፤ እዚያው በወደቀችበት ትቷት ሔዷል፡፡ የቤተልን የስቃይ ድምፅ የሰሙ ጐረቤቶች፤ ዘግናኙን ጥቃት በማየት እየተጯጯሁ ከወደቀችበት አንስተው ተሸከሟት፡፡ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ሆስፒታል ሲያደርሷት፤ የጉዳቷ መጠን ከባድ እንደሆነ ለመገንዘብ ሃኪሞቹ አልከበዳቸውም፡፡ ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ ተወስዳ መታከም እንዳለባት ነው ሃኪሞቹ የተናገሩት፡፡ ወላጆቿም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ቤተልን ፈጥነው ወደ አዲስ አበባ የሚያመጡበት አቅም አልነበራቸውም፡፡ መዋጮ እስኪሰበሰብ ሁለት ቀን አለፈና መስከረም 6 ቀን አዲስ አበባ የካቲት 12 ደረሰች፡፡ መድረሷ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በሸራተን በተካሔደው “አሁን ባይኔ መጣ” የተሰኘ ፕሮግራም ላይ፤ የቤተል እናት “ልጄን አትርፉልኝ” ሲሉ የተማፀኑት፡፡ “ልጄን አስተምሬ ለቁም ነገር አበቃሁ ስል፤ እንዲህ ያለ ችግር ደረሠብኝ” በማለት እንባቸውን እያፈሰሱ የተማፀኑት እናት፤ ከታዳሚው ሀያ ሺህ ብር ተሠብስቦ ተሰጥቷቸዋል - ልጃቸውን እንዲያሳክሙበት፡፡ በፋሻ ተጠቅልላ የምትሰቃየው ቤተል፤ በሆስፒታሉ አቅም ያህል ስትታከም ቆይታለች፡፡ ፈተናው ግን ገና ነው፡፡ አካሏ ተቃጥሏል፤ ስቃይዋ ፋታ አይሰጥም፡፡ ለህክምና የሚያስፈልገው ገንዘብ ደግሞ፤ ያስደነግጣል፡፡ በየቀኑ በአማካይ ከ500 ብር በላይ ያስፈልጋል፡፡ ቤተል በሆስፒታሉ 70 ቀናትን አስቆጥራለች፡፡20ሺ ብር ደግሞ፤ ለ40 ቀን እንኳ አይበቃም፡፡ በእርግጥ የመንግስት ሆስፒታሎች፤ ለድሃ ቤተሰቦች ነፃ ህክምና የሚሰጡበት አሰራር እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ ከቀበሌ ደብዳቤ አስጽፎ ለሚመጣ ሰው፡፡ ቤተል ግን ቤተሰቦቿ ድሃ ቢሆኑም፤ ነፃ ህክምና የማግኘት እድል የላትም፡፡ መክፈል ይኖርባታል፡፡ ሆስፒታሉ እንደሚለው፤ ጥቃት ደርሶበት ለሚመጣ ህመምተኛ የነፃ ህክምና አገልግሎት መስጠት ክልክል ነው፡፡ ታካሚዎቹ መክፈል እንደሚኖርባቸው የገለፁት አንድ የሆስፒታሉ ኃላፊ፤ ወደፊት ጥቃት አድራሹን ሰው በመክሰስ ካሳ ማግኘት ይችላሉ ተብሎ እንደሚታሰብ ተናግረዋል፡፡በፖሊስ እንደተያዘ የገለፀችው ቤተል፤ ነገር ግን ገና ፍርድ ቤት አልቀረበም፤ ለምን እንደተጓተተም አላውቅም ብላለች፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ የተፈፀመ ሌላ ጥቃት አለ፡፡ አበራሽ ላይ በደረሰ ጥቃት ተጠርጣሪው ተይዞ፣ ክስ ለፍ/ቤት ቀርቦ፣ ምስክርና ማስረጃ ተሰምቶ፣ ጉዳዩ ለብይን ተቀጥሯል፡፡ የተለያዩ የሴት ማህበራት ባነር በማሳተምና መግለጫዎችን በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን፤ በፍ/ቤት ቀጠሮ ቀን ሁሉ በርካታ ሰው እንዲገኝ በማድረግ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ነው፡፡ በተቃራኒው የቤተል ጉዳይ ገና ወደ ፍ/ቤት አልደረሰም፡፡ ቅስቀሳውና ዘመቻው ቢቀር እንኳ፤ ጉደዩ እንዳይጓተት በሴት ማህበራት በኩል ጥረት ተደርጓል ወይስ፤ አንደኛውን ጉዳይ ብቻ አጉልቶ በማውጣት ሌሎቹ እየተዘነጉ ይሆን? ለህክምና በየወሩ ከ15ሺ ብር በላይ የመክፈል አቅም 
የሌላት መሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ የነፃ ህክምና ለተጠቂዎች ክልክል መሆኑ፤ ጥቃት አድራሹን ሰው በመክሰስ የመታከሚያ ገንዘብ ለማግኘት ይቅርና፤ 
ተጠርጣሪው ገና ወደ ፍርድ ቤት አለመቅረቡ የቤተልን ስቃይ እጥፍ ድርብ አድርጐታል፡፡በደረሠባት ጥቃት የግራ አይኗ እንደጠፋና የግራ ጆሮዋም ሙሉ በሙሉ እንደማይሠራ የምትገልፀው ቤተል፤ ወጣት በመሆኗ የችግረኛ ቤተሠብ ልጅ በመሆኗ የተሻለ ህክምና አግኝታ ብትድንና ቤተሠቧን መርዳት ብትችል ትመኛለች፡፡ የውጭ አገር የተሻለ እንደሆነም ሃኪሞቿ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን፤ 
ለውጭ አገር ህክምና ሳይሆን እዚሁ ሆና ለመታከምም በቂ እርዳታ ልታገኝ አልቻለችም፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ዘግናኝ ጥቃት እንዲቆም፤ የፍርድ ቤት ጉዳይ እንዲፋጠንና ተጐጂዎቹ በቂ እርዳታና ህክምና እንዲያገኙ በተለያዩ ወገኖች የሚደረግ ጥረት ጥሩ ነው፡፡ ታዲያ የቤተል ጉዳይ ለምን ተዘነጋ በማለት ሃዘኗን የገለፀችው የቤተል እህት፤ በተጐጂዎች መካከል አድልዎ ማድረግ በጣም ያሳዝናል ትላለች፡፡ በቀን ስራ በማገኘው ገቢ ደብተር እየገዛሁላት ነው የተማረችው የምትለው ታላቅ እህቷ ነፃነት፣ “ዛሬም እያስታመምኳት ነው፤ ለህክምና ወጪ የሚሆን ገንዘብ ግን ማግኘት አቅቶኛል” ትላለች፡፡ “ለሌሎቹ ጥቃቶች እንደሚጮኸው ሁሉ ለቤተልም ሊጮህላት ይገባል፡፡ በየጓዳውና በየሆስፒታሉ ያልታዩና ያልተነገረላቸው በርካታ ሴቶች አሉ ብላለች ነፃነት፡፡ ሌላዋ ተጐጂ ወ/ሮ ትዕግስት መኮንን ነች - በተጠርጣሪው ባለቤቷ በአቶ ምናለ አቻም የቤቷ መግቢያ ላይ በዱላ በተደጋጋሚ ተደብድባ በአሲድ አካሏ የተቃጠለው ወ/ሮ ትዕግስት፤ የካቲት 12 ሆስፒታል ወር ከ15 ቀን ብትታከምም ለመትረፍ አልቻለችም፡፡ ጥቃቱን ፈፅሟል የተባለው ተጠርጣሪ ባለቤቷ ከድርጊቱ በኋላ ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም፤ በደቡብ ሱዳን ፖሊስ ተይዞ መጥቷል፡፡ በሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የሴት ማህበራት በብዙ ሰው አጀብ ፍ/ቤት እየተገኙ ይከታተላሉ፡፡ በወ/ሮ ትዕግስት ጉዳይ ግን በፍ/ቤት በመገኘት ጉዳዩን የሚከታተሉት ቤተሠብና ጐረቤት ብቻ ናቸው የሚለው የሟች ወንድም ዮሐንስ፤ ጉዳዩ የኔም ነው ብሎ ባነር የሚያዘጋጅና ፍ/ቤት የሚከታተል የሴት ማህበር የለም ብሏል፡፡ ትዕግስት እህቱ ከፍተኛ ህክምና እንድታገኝ በተደጋጋሚ ወደ ሴቶች ማህበራት ጥምረት እየሄድኩ ባመለክትም መልስ አልሰጡኝም የሚለው ዮሐንስ፤ “በሌላ ተመሳሳይ ጉዳይ ደግሞ ስራችን ብለው እየተከታተሉ ፍርድ ቤትን ሲያጣብቡ ይታያል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የጥቃት ወንጀሎች እኩል መታየት ነበረባቸው፡፡ ማህበሩ የሴቶች እንደመሆኑመጠን አንዳንዶቹን ጉዳዮች ወደ ጐን እያለ፤ ሌላውን ብቻ አጉልቶ ማውጣት ደስ የማይል አድልዎ ነው” ይላል፡፡ የሴት ማህበራት፤ የጥቃት ወንጀሎች እንዲቆሙ፤ የተጐዱ ሴቶች እርዳታና የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ የመጣር፤ የተጐጂዎችን ልጆች የመጠየቅ፣ የፍ/ቤት ጉዳዮችንም የመከታተል፣ ሀላፊነት አለባቸው ብሎ እንደሚያስብ ዮሐንስ ጠቅሶ፤ አሁን ግን ዝና የሚያስገኝላቸውን ብቻ እየመረጡ የሚንቀሳቀሱ ይመስላል ብሏል፡፡ “የሴቶች ማህበራት ቅንጅት ሀላፊዋ የመጣችው በመጨረሻው እለት ነው፤ በማግስቱ ትዕግስት አረፈች ብሏል፡፡ የሴቶች ማህበራት ቅንጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን ግን፤ ማህበራችን አድልዎ አይፈጽምም በማለት ያስተባብላሉ፡፡ እንከን የሌለው ስራ እየሠራን ነው የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፤ ስለ ቤተል እርዳታ እንድታገኝ በሚዲያም እንዲነገር አድርገናል፤ ስለ ህክምናዋም እየተከታተልን ነው ብለዋል፡፡ ለምሳሌ የካሚላትን ጉዳይም ቢሆን ለብቻ አጋነን አላወጣንም፤ የሚረዳት አካል ለማግኘት ጥሪ ስናቀርብ ሼህ መሐመድ አልአሙዲ አሳከሟት እንጂ፤ ደብዳቤም እንኳ አልፃፍንም ብለዋል - ወ/ሮ ሳባ፡፡ ደብዳቤ ከመፃፍ ይልቅ ብዙ ሰው እንዲሰማ በሚዲያ እንናገራለን የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፤ አንድ ሠው አንድ ነገር ይሠራል እንጂ ሁሉንም ማድረግ አይችልም ብለዋል፡፡ ማህበራችን አገር በቀል ማህበር እንደመሆኑ በበጐ ፈቃደኞች የሚንቀሳቀስ እንጂ ልዩ የገንዘብ ምንጭ የለውም የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፤ የተጠቂዎች ፈንድ መቋቋም ይገባል የምንለውም የሠው እጅ ላለመጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ አይኗ ላይ ጉዳት የደረሰባት ወ/ሮ አበራሽ ሀይላይ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ህክምና የተጠየቀላት፤ እንጂ ባንኮክ ከሔደች በኋላ ነው ጉዳዩን የሠማነው እና የተለየ ድጋፍ አላደረግንም ይላሉ ወ/ሮ ሳባ፡፡ ቤተል ላይ ጥቃት ያደረሰው ተጠርጣሪ ወደ ፍርድ ያልቀረበው ፖሊስ ገና እያጣራሁ ነው በማለቱ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሳባ፤ የትዕግስትን ጉዳይ ደግሞ እየተከታተልን ነው ብለዋል፡፡

 

Read 7498 times Last modified on Monday, 05 December 2011 05:39