Saturday, 28 September 2013 11:38

የጀግና አሟሟት

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(4 votes)

              “ይኸውልሽ እህትሽ ሁሌ እንደምታስቸግረኝ ታውቂያለሽ፡፡ እንድታሳርፊልኝ ደጋግሜ ነግሬሻለሁ፤ የምሬን ነበር፤ አንቺን እንዳይደብርሽ ብዬ ነው ግን፤ ለሌላ አይደለም፤ ግድ እንደሌለኝ ታውቂያለሽ፤ እንኳን ነገር ፈልገውኝ እንዲሁም እንዲያው ነኝ፡፡” “ግን እህቴን;! አልጋዬ ላይ;!” “ምን ሆነሻል;! ሌሎች ሴቶች እንደማወጣ ታውቂያለሽ! እህትሽ መሆኗ ምን ለውጥ ያመጣል;! አንቺ እንዳይደብርሽ እንድታሳርፊልኝ ነግሬሻለሁ፤ … እህቴን ብሎ ነገር! በጣም ብዙ እህትማማቾች ተኝቻለሁ፤ እያወቁም በድብቅም፡፡” “እሺ አልጋዬ ላይ;!” “ቦታው ምን ለውጥ ያመጣል; አልጋሽ ላይ ሆነ፣ ሆቴል ሆነ፣ ጫካ ውስጥ ሆነ፣ ቢሮ ውስጥ ሆነ፣ ምን ለውጥ ያመጣል;” እነዚህ ቦታዎች ሁሉ ላይ እህቷን ተኝቷታል፡፡ ያስታውቃል፤ አውቆ ነው ቦታዎቹን የቆጠረላት፡፡ ትወደዋለች፡፡ እንደማታሸንፈው ታውቃለች፡፡ እሱ ሌላ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ እሷ በተቆጡ አይኖቿ አሻግራ ታይ ጀመር፡፡ ቅድም ከኔ ጋር ወንበር ሲናጠቅ የነበረው ሰው ሲወራጭ አየችው፡፡ ለሷ ነው የሚወራጨው፡፡ በእጁ ምልክት “እሱን ተይው…” “ወድጄሻለሁ…” “ነይ ወደኔ…” አይነት ምልክቶች አሳያት፡፡ ዝም አለችው፡፡ ምልክቶቹን ደጋገማቸው፡፡

“ግድየለሽም እሱን ተይው…” “በጣም እወድሻለሁ…” “ነይ ወደኔ…” እሷም በምልክት እና በንዴት “ከሠው ጋር ነኝ እኮ” አይነት አለችው፡፡ በምልክት እንዲህ ማውራት የሚቻል አይመስለኝም ነበር፡፡ ተችሎ እያየሁ ነው፡፡ ቋንቋው በግልፅ እየተሰማኝ፡፡ ወዲያ ማዶ የተቀመጠው ሠው፡- የሰማውን ሰምቷል፡፡ “ድንቄም ከሠው ጋር!” አይነት ምልክት አሳያት፡፡ የሰማውን ሰምቷላ፡፡ እሷንም አብሯት ያለውንም ሠው የሚያጣጥል ምልክት አሳያት፡- “ደግሞ እንዲህ እያደረገሽ!” የሚል አይነት፡፡ አይኗን ከሰውየው ላይ አነሳች፡፡ አብሯት ያለው ሠው እያጨሰ ነው፡፡ አያያትም። ጭሱ ውስጥ እህቷን እያየ ይመስላል፡፡ አሁን ወዲያ ማዶ ስላለው ሠውዬ እናውራ፡፡ ጨዋ ወልዶ ጨዋ ያሳደገው ነው፡፡ አባቱ ኮሎኔል ናቸው፡፡ ልጃቸውን ያሳደጉት እሳቸው ከኖሩበት ሙያ በጠነከረ ዲሲፕሊን ነው፡፡ የስኬት ሶስቱ ስላሴዎች የታደሉት ሠው ነበር፡፡ ለተሳካ ህይወት የሚያስፈልጉት ሶስት ነገሮች ናቸው magic, method, reason, (የአእምሮ ጥሬ ብቃት፣ ትጋት እና በምክንያት መመራት ልንላቸው እንችላልን) እሱ ሶሰቱንም ተጎናጽፏል፡፡ ሶስቱም ነገሮች ብዙ ጊዜ አብረው አይከሰቱም፤ የአእምሮ ምርጥ ጥሬ ብቃት እያለህ ሰነፍ ልትሆን ወይም በምክንያት የማታምን ልትሆን ትችላለህ፡፡) ልጅ እያለ ጎበዝ ተማሪ ብቻ አልነበረም፡፡ በሁሉም ጨዋታዎች አንደኛ ነበር፡፡

ፈጣን ሯጭ፣ አብዶ የሚችል ኳስ ተጫዋች፣ በአንድ ጠጠር አራት በልቶ ባንዴ የሚነግስ ዳማ ተጫዋች፣ በአምስት ስድስት እርምጃዎች check mate ላይ የሚደርስ ቼስ ተጫዋች ነበር፤ ገና በልጅነቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲ በማዕረግ ገብቶ፣ በማዕረግ ተመርቆ ወጣ፡፡ ስራ ያዘ፡፡ መኪና ገዛ፡፡ ቤት ገዛ፡፡ ለወላጆቹ ብቻ ልጅ ነው፡፡ እናት እና አባቱ እሱን ሲያዩ ሁሌ እንባ ይተናነቃቸዋል፤ የደስታ እንባ፡፡ ሁሌ እሱን ሲያዩት የደስታ እንባ በአይናቸው ግምጥ ይላል፡፡ ገና ፍቅር ምን እንደሆነ ሳያውቅ የፍቅር ደብዳቤዎች ይደርሱት ነበር፤ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የተጻፈለትን የፍቅር ደብዳቤ ለአባቱ ወስዶ አሳያቸው፤ ሳቁ አባቱ፡፡ “መጥፎ ነገር አይደለም፤ ግን ጊዜው ገና አልደረሰም፡፡” አሉት፡፡ “እሺ አባባ፡፡” አለ፡፡ ጊዜው መቼ እንደሚደርስ ግን አልነገሩትም፡፡ “ሌሎች እንዲህ አይነት ደብዳቤዎች ሲደርሱህ አሳየኝ፡፡” “እሺ አበባ፡፡” የተጻፉለትን ሁሉ ለአባቱ አቀበለ፡፡ ኋላ ላይ አባቱ ማንበብ ታክቷቸው፣ እየተቀበሉት ጣሏቸው።… ዘንድሮ ስራ ከያዘ አምስተኛ አመቱ ነው፡፡ ከሴት ጋር ታይቶ አይታወቅም፡፡ የተደላደለ ኑሮ እና ምርጥ ዘር የሚፈልጉ ሴቶች ሁሉ በግልፅም በስውርም ለትዳር ወይ ገፋፍተውታል ወይ ጠይቀውታል፡፡

አባት እና እናት አሁን መፍራት ጀመሩ፡፡ አሁን ልጃቸው ትዳር ይዞ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ቤተሰቦቹ የሚወዱትን ያህል ልጃቸውን ይፈሩታል፡፡ እንከን የለሽ ነው፡፡ አባቱ አንድ ቀን እየፈሩ፡- “የሚመችህ ከሆነ እራት ልጋብዝህ ዛሬ፡፡” አሉት፡፡ “እሺ አባባ፤ ይመቸኛል፡፡” እራት ጋበዙት፡፡ “አባባ የሆነ ያሳሰበህ ነገር ያለ ይመስላል!” “አዎ ልጄ፡፡” “ምንድነው;” “አንተ ነህ ዳግም፡፡” ስሙ ዳግማዊ ነው፡፡ “እንዴ አባባ;! እኔ;!” “አዎ ዳግሜ፡፡” “ምን አጠፋሁ;” “ኸረ ምንም፤ ትዳር፣ ትዳር ነው፤ ለምን ትዳር አትይዝም;” ቅልል አለው፤ አባትም እንዲሁ፡፡ “የሚገርምህ አባባ እኔም እያሰብኩበት ነበር፤ ግን አዋይሀለሁ እያልኩ ትንሽ አፍሬ ነው የተውኩት፤ እንጂ ሰሞኑን እቤት ስመላለስ የነበረው ይህንኑ ላዋይህ ነበር፤ እንዴት እንደማወራህ ግራ ገብቶኝ ነው የተውኩት፡፡” አባት የደስታ እንባ በአይናቸው ግጥም አለ፡፡ “ምኑ ነው ግራ የገባህ;” “ምን አይነት ሴት ነው ማግባት ያለብኝ የሚለው ነዋ!” “ይኸማ በጣም ቀላል ነው፤ ማግባት ያለብህ የምታፈቅራትን ሴት ነው፤ እና የምታፈቅርህን፡፡ እኔ እና እናትህ አርባ አምስት አመት በፍቅር እና ያለ አንዳች ኮሽታ የኖርነው ስለምንፋቀር ነው፤ እናትህን ያገባኋት አፍቅሬያት፣ እንደምታፈቅረኝ ካረጋገጥኩ በኋላ ነው፡፡ ፍቅር ካለ ሌላው እዳው ገብስ ነው፡፡” አባት እና ልጅ በደስታ እና በፍቅር ተያዩ፡፡ ተጨባበጡ፡፡ ልጅ ሲያስጨንቀው የነበረው ጥያቄ ተመለሰለት፡፡ አባትም ሲያስጨንቃቸው የነበረው ነገር እንዲህ በቀላሉ ሲፈታ እንደ ልጅ ሆኑ፡፡ የደስታ እንባ በአይናቸው ግጥም አለ፡፡ ሲለያዩ ዳግም አባቱን አቅፎ እንዲህ አላቸው፡- “እማማን በቅርቡ ለሰርግ ተዘጋጂ በላት፡፡” አባት መኪናቸው ውስጥ የደስታ ለቅሶ አለቀሱ። ዳግማዊም አለወትሮው እየደነሰ ነበር የመኪናውን በር የከፈተው፡፡ ማግባት ያለብህ የምታፈቅራትን ነው! አለቀ፡፡ ለካ እንዲህ ቀላል ነበር፡፡  

                                                 * * *

አሁን ወደ ቴሌ ባር እንምጣ፡፡ ዳግማዊ ልጅቷን እንዳየ አፍቅሯታል፡፡ ደግሞም አብሯት ያለዉ ሰዉ ያላትን ሰምቷል፡፡ አድርጎት የማያውቀውን እያደረገ ያለው ልጅቷን ስላፈቀራት ነው፡፡ አፍቅሮ አያውቅም፤ እና ምን እና እንዴት ማድረግ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ግን ስህተት እያደረገ እንዳይደለ ታውቆታል፡፡ ልጅቷን አፍቅሯታል፡፡ ይሄ 1 + 1 ነው፤ እውነት። ልጅቷ ደግሞ እህቷን እራሷ አልጋ ላይ ከሚተኛ ሰውዬ ጋር ናት፤ ይሄ እድል ነው፡፡ እውነት + እድል, ስኬት ልጅቷ እህቷን የተኛባትን ሰውዬ፡- “ልጃችንስ;” አለችው በሚያሳዝን እና በሚለማመጥ ድምጽ፡፡ “ልጃችንስ; የምን ልጃችን ነው;! ልጃችን የሚባል ነገር የለም፤ ልጁ ያንቺ ነው፤ እኔ ልጅ የለኝም፡፡ በመጀመሪያም ነግሬሻለሁ፤ እኔ ልጅ አልፈልግም። በምድር ላይ ልጅ እንደመውለድ ወይም ለዚያ ተባባሪ እንደመሆን ያለ ቀፋፊ ሀጢያት እንደሌለ ነግሬሻለሁ፤ አትስሚም ግን፤ ወይም አላመንሽኝም፤ እኔ አልዋሽም፡፡ በሀጢአቴ አታስሪኝም፡፡ እኔ ፤ልጅ መውለድ ሀጢአት መሆኑን ነግሬሽ እየተጠነቀቅኩ ነበር፤ አንቺ ተሳሳትሽ፡፡ ሀጢአቱ ያንቺ ነው፤ ልጁ ያንቺ ነው፡፡ ነግሬሻለሁ፡፡” ነግbታል፡፡ ተስፋ በመቁረጥ አይኗን ወደ ማዶ አማተረች፤ ዳግማዊ ይወራጫል፡፡ “ግድ የለሽም እሱን ተይው…” “በጣም እወድሻለሁ…” “ነይልኝ እና አብረን እንኑር..” ተናደደች፡፡ “እንዴት ማየት ይሳነዋል;! ምንም ይሁን ከሰው ጋር ነኝ! ምን ሆኗል ልጁ;! እንዲህ አይነት ሰዎች ናቸው ሰው በሰላም አብሮ እንዳይኖር የሚያደርጉት! እህቷን ወደተኛባት ፍቅረኛዋ አየች፡፡

አያያትም፤ እያጨሰ ነው፡፡ “ስማ!” አለችው፡፡ አያት፡፡ “እግዜርን እንኳ አትፈራም;!” ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ደስ የሚል ሳቅ፡፡ “እግዜር ! እግዜርን አትፈራም;! እግዜርን እኔን መፍራት አለበት፤ ደሞ እንደሚፈራኝ እርግጠኛ ነኝ። ይሄውልሽ እኔ እግዜርን ባገኘው፤ ሮበርት ዲኔሮ እንዳለው you have a lot of explaing to do ምናምን አይነት ቀሽም ነገር አይደለም የምለው!….” አቋረጠችው፡፤ ንዴቷ እና ንቀቷ በጣም፣ በጣም፣ በጣም ያስፈራል፡፡ አብሯት ያለው ሠውዬ እያያት ስለማያወራ አላያቸውም፡፡ “ምን ነበር የምለትለው;” አለችው በቁጣ፣ በንዴት እና በንቀት፡፡ “አናቱን ነበር የምለው፡፡” በርጋታ የምትጠጣውን ቢራ አነሳች፤ ተነስታ ቆመች፤ አናቱን አለችው፡፡ ጠርሙሱ አናቱ ላይ ተሰበረ፡፡ (እግዚአብሔር ሰውየው ያለውን ሠምቶ ተናዶ ይሆን እንዴ;) አሻግራ አየች፡፡ አሁን ዳግማዊ ክው ብሎ እያያት ነው፡፡ የተሰበረውን ጠርሙስ ይዛ በቀስታ ዳግማዊ ወዳለበት ወንበር መራመድ ያዘች፡፡

ምን ልታደርግ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ዳግማዊ በአባቱ ምክር የታጠቀውን ሽጉጥ አወጣ፡፡ “እዛው ሁኚ፤ እንዳትጠጊኝ፡፡” እንደማይተኩስ አውቃለች፤ ጆን ስቴንቤክ ፈረስ እና ሴቶች፣ ወንዶች (ጋላቢዎቻቸው) እርግጠኛ ሲሆኑ እና ሲያመነቱ በእርግጠኝነት ያውቃሉ ብሏል፡፡ “እተኩሳለሁ፤ እውነቴን ነው፡፡” በቀስታ እና በእርጋታ ተራመደች፡፡ “እ-ተ-ኩ-ሳ-ለ-ሁ፡፡” አሁን እውነቱን እንደሆነ ገብቷታል፡፡ የሽጉጡ አፈሙዝ ወዴት እንደዞረ አላየችም፡፡ መሞት ፈልጋለች፡፡ መሰንዘር የምትችልበት እርቅት ላይ ስትደርስ የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡ ፊቷ በደም ተሸፈነ፡፡ ጠርሙስ ባልያዘው እጇ ደሙን ከፊቷ ላይ ጠረገች፡፡ ዳግማዊ ሽጉጡን በአንድ እጁ እንደያዘ ተጋድሟል፡፡ እራሱን አጥፍቷል፡፡ ጀግና፡፡ ማን በሴት እጅ ይሞታል;! እኔ አሁን እራሴን ማጥፋት አልፈልግም፡፡ ለመኖር ምክንያት አግኝቻለሁ፡፡ አንድ፡- ያቺን ልጅ እስር ቤት እየሄድኩ ሁሌ እጠይቃታለሁ፡፡ ሁለት፡- ልጇን አሳድጋለሁ፡፡

Read 3358 times