Saturday, 26 November 2011 08:10

በቅሎ ቤትና የወታደር ሰላምታ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ብዙዎች የአዲስ አበባ ሰፈሮች በተለምዶ የሚጠሩበት ስም አላቸው፡፡ ካምቦሎጆ፣ ንፋስ ስልክ፣ ቀበና፣ እሪ በከንቱ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ በቅሎ ቤት፣ ሸጐሌ፣ ሰባራ ባቡር፣ ዕንቁላል ፋብሪካ፣ ኮልፌ፣ … በርካታ ናቸው፡፡ የስሞቹ አወጣጥ የራሱ ምክንያት ቢኖረውም ብዛኞቻችን ስሞቹ እንዴት እንደተሰየሙ በትክክል እናውቃለን የሚል ግምት የለኝም፡፡ ዕንቁላል በፋብሪካ እንደማይመረት ከትናንሽ ልጆች በስተቀር ሁላችንም እናውቃለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ታዲያ እንዴትና ለምን ዕንቁላል ፋብሪካ ተባለ? ሁሉም ባይሆን አንዳንድ አንባቢ ስሞቹ እንዴት እንደተሰየሙና እንደተለመዱ ያውቃሉ፡፡

ስለዚህ የመንደሮቹን ስም አወጣጥ የሚያውቅ ሰው (የዕድሜ ባለፀጐችን በመጠበቅ፣ መዛግብት በማገላበጥ፣ …) መቼ፣ ለምንና እንዴት እንደወጡ በማስረጃ አስደግፎ ቢጽፍልን፣ ለአንባቢያን በማቅረብ እንማማርበታለን፡፡ ታዲያ፣ “እንዲህ ሳይሆን አይቀርም …” በሚል ግምት ባትደክሙ መልካም ነው፤ እውነተኛና ትክክለኛ ማስረጃ ያላችሁ ብቻ ጻፉልን፡፡ 
አሁን፤ የዛሬ ሳምንት፣ የቀድሞ ሠራዊት መድፈኛ ጦር መረዳጃ ዕድር፣ ጦሩ የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት ሲያከብር በስፍራው ተገኝቼ የክብር እንግዶች ከነበሩት ጄነራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የቃረምኩትን ሁለት ቁም ነገሮች ላጫውታችሁ፡፡ ዛሬ ቅዳሜም አይደል! እየተዝናናችሁ የምትሞክሩት አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ጥያቄው ስለ በቅሎ ቤት ስም አወጣጥና ስለ ወታደር ሰላምታ ነው፡፡ በአጭር ቋንቋ የበቅሎ ቤት አሰያየምና የወታደር ሰላምታ ከመድፈኛ ጦር ጋር ምን ትስስር አላቸዉ? የሚል ነው፡፡ እየሞከራችሁ ንባባችሁን ቀጥሉ፡፡
በአገራችን መድፈኛ ጦር መች እንደተመሠረተ ያውቃሉ? መድፈኛ ጦር የዛሬ 70 ዓመት በ1934 ዓ.ም በሆለታ ገነት ከተማ ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር በተማረኩ 67.17 መድፎች ሦስት ሻምበል ጦር መቋቋሙን የመድፈኛ ጦር መረዳጃ ዕድር ሊቀመንበር ኮሎኔል እሸቱ ከተማ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
ጦሩን ያቋቋመው በአማካሪነት፣ በአሠልጣኝነትና በአዛዥነት ሲመራ የነበረው የእንግሊዝ ጦር ቢሆንም ኢትዮጵያዊ አዛዥ ሥልጣን ለመረከብ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ጦሩ በተመሠረተበት ዓመት በ1934 ሥልጣን የተረከቡት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ጄነራል ገ/ሥላሴ በርካ ነበሩ፡፡ በሆለታ የመድፈኛ ጦር፣ ማዘዣ ጣቢያውን ከሆለታ ገነት ነቅሎ ወደ አ.አ የተዛወረውም ብዙ ሳይቆይ ነበር፡፡
ጦሩ አዲስ አበባ እንደመጣ ማዘዣውን የተከለው በተለምዶ አጠራር ላንቻ የሚባለው አካባቢ ነበር፡፡ ከክብር እንግዶች አንዱ የነበሩት ኮሎኔል አበራ ኃ/ማርያም የመድፈኛ አባል ናቸው፡፡ ኮሌኔል አበራ የጦሩ አባል የሆኑት በ1944 ዓ.ም ነበር፡፡ ያኔ የመድፍ አካል ይፈታታና በበቅሎ ይጫን ነበር፡፡ የበቅሎ ዋጋ 80 ብር እንደነበርና ከመቶ ያላነሱ በቅሎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ በአካባቢው በርካታ በቅሎች ስለነበሩ ሰፈሩ “በቅሎ ሰፈር” እየዋለ ሲያድርም “በቅሉ ቤት” እየተባለ መጠራት እንጀመረ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ሕግ፣ መድፈኛ፣ የጦር ንጉሥ ነው እንደሚባል የጠቀሱት ኮ/ል አበራ፣ “የአሁን መድፍ የተሻሻለ ነው እስከ 30 ኪ.ሜ ይመታል፡፡ ያኔ ከ10 እና ከ12 ኪ.ሜ በላይ አይሄድም ነበር፡፡ ከሱማሌ ጋር ስንዋጋ፣ የእነሱ መድፍ እኛ ጋ ይመታል፤ የእኛ መድፍ መኻል ላይ ነበር የሚቀረው” ብለዋል፡፡
መድፈኛና ምድር ጦር ጥሩ ተዋጊዎች ናቸው ያሉት ሌላው የክብር እንግዳ ጄነራል ከፈለኝ ይብዛ ናቸው፡፡ “እነሱ (መድፈኛ) የውጊያ ንጉሥ ነን ለሚሉት፣ እኛ (ምድር ጦር) የውጊያ ንግሥት ነን፡ ንግሥት የሌለችበት ማር አይሠራም በማለት እንነግራቸዋለን፡፡ ይኼ ለቀልድ ያህል ነው እንጂ ለአንድ ዓላማ የቆምን ስለሆነ ተግባብተን ነው የምንዋጋው” በማለት ተናግረዋል - ጄነራል ከፈለኝ፡፡
የወታደር ሰላምታ (እጅን ግንባር ላይ አድርጐ ሰላምታ መስጠት) የመጣው ከመድፈኛ መሆኑን የተናገሩት ጄነራል ከፈለኝ ይብዛ ናቸው፡፡ እንዴት መሰላችሁ? የጥንት መድፈኞች በእጃቸው ባሩድ አቡክተውና አድበልብለው መሳሪያው ውስጥ ከተው ነበር የሚተኩሱት፡፡ ታዲያ፣ ማንኛውም ወታደር አለቃው ለጉብኝትም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ሲመጣ መለዮውን አንስቶ ነው ሰላምታ የሚሰጠው፡፡ የመድፈኛ ወታደር ግን፣ አለቃው ሲመጣ መለዮውን በባሩድ በተጨማለቀ እጅ ቢያነሳ፣ መለዮው ስለሚቆሽሽ መለዮውን ያነሳ በማስመሰል እጁን ግንባሩ ላይ እንዲያደርግ ተወሰነ፡፡ ከዚያም ይህ አሠራር የመላው ወታደራዊ ሠራዊት ሰላምታ አሰጣጥ እንዲሆን ተወሰነ በማለት ጄነራል ከፈለኝ አስረድተዋል፡፡

 

Read 4761 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:32