Saturday, 26 November 2011 08:36

መሬት ይዛችሁ ስለመሬት እናውጋ! “መሬት ሳትበላኝ ልብላት ብዬ ነው” - (ወግ)

Written by  በእምሻው ገ/ዮሐንስ
Rate this item
(1 Vote)

የማወራችሁ ስለመሬት ስለሆነ መሬት ይዛችሁ አድምጡኝ፡፡ በነገራችሁ ላይ ስለመሬት በመሬት ብዙ ተብሏል፡፡ እስቲ ጥቂቶቹን ከመሬት ዘግነን እንያቸው፡“ከመሬት ተነስቶ”፣ “መሬት ከዳችው”፣ “ኖሮ ኖሮ ከመሬት”፣ “መሬት የሆነ ሰው”፣ “መሬት ላራሹ”፣ “መሬት ያበቀለችው” …ወዘተ በተረፈ ደግሞ እናንተ ትዝ ያላችሁን ልታክሉበት ትችላላችሁ፡፡ዛሬ ከእናንተ ጋር የሆድ የሆዳችንን እንድናወጋ የመረጥኩት ርእሰ ጉዳይ ስለመሬት ነው ብያለሁ፡፡ ስለመሬት ምን ለምትሉኝ… በቅርቡ በወጣው የመሬት አጠቃቀም ዙሪያ መሆኑን እነግራችኋለሁኝ፡፡

አንድ ወዳጄ ነው… ወንድሜ ብለው ይሻላል… ባለፈው ጊዜ የአዲስ ዓመት ዕቅዱን ሲያወጋኝ እንዲህ አለኝ “ፉት ቢሏት ጭልጥ የሆነች ደሞዜን በየወሩ በቁጥቁጥ ከምጠብቅ ያንን መሬቴን ሸጬ ላንድ ክሩዘር እገዛና አስጐብኝነት እሰራለሁ”
በሆዴ ቅናት ቢጤ ቢፈጥርብኝም የሆዴን በሆዴ ይዤ በአፌ “ይቅናህ!” ብዬው ነበር - ወዳጄን፡፡ ከአፌ ይልቅ የሆዴ ሠራ መሰለኝ በቀደም ስንገናኝ አለመሳካቱን አረዳኝ ወይም አበሰረኝ፡፡ “ይሄውልህ ያንን የመሰለ እቅዴ በመመሪያ ክሩዘር ተመቶብኝ ‘ላንድ’ ላይ ቁጭ ብዬልሃለሁ” ሲለኝ “እምባና ሳቅ” የሚለውን መፅሃፍ ጋብዤው ከአጠገቡ ዞር አልኩኝ፡፡
ሰለሞናዊውን ስርወ መንግስት በሃይል በማሽቀንጠር በ”ዘውድ” ፋንታ “መለዮ” ደፍቶ ዙፋኑ ላይ ጉብ ያለው ደርግ አገሪቱን “መንዳት” በጀመረበት ወራት ነው - ስፍራው ደብረማርቆስ ከተማ፡፡ በኢጣልያ ወረራ ወቅት በአርበኝነት ያገለገሉት ቀኛዝማች ሰውነቴ የተባሉት እኚህ አርበኛ በከተማዋ ዙርያ የነበራቸውን ርስት በሙሉ እንደ “ድፎ ዳቦ” በመሸንሸን፣ እንደ ጉዱ ካሣ ከብቶች ባገኙት ዋጋ መቸብቸብ ያዙ፡፡ በእንግዳ ድርጊታቸው ግራ የተጋባው ወዳጅ “ምነው ጋ?” ሲላቸው መልሳቸው ቁርጥ ያለ ነበር “መሬት ሳትበላኝ ልብላት ብዬ ነው” እውነትም መሬታቸውን ቸብችበው ሲያጠናቅቁና የከተማና ቦታ ትርፍ ቤት አዋጅ ሲታወጅ የአንድ ቀን ጀንበር ልዩነት እንኳን አልነበረውም ይባላል፡፡ እንደ ጊዜው አባባል የፈዘዘ ግን በአየር መወዛወዙን ቀጠለ፡፡
የሰሞኑን የመሬት አጠቃቀም መመሪያ እንድናወጋ ስወጥን “አህያም የለኝ ከጅብ አልጣላ” ከሚለው ተረት ይልቅ “የጨው አምድ ሲናድ ሞኝ ይልሳል፤ ብልጥ ያለቅሳል” የሚለውን በመምረጥ ነበር፡፡ ከመመሪያው መውጣት በኋላ መክሰም የጀመረውን የአከራዮቼን ፈገግታ እያየሁ ሰሊጥ ሆኜ ተገኝቼ ከኑግ ጋር የሚወርድብኝን የሙቀጫ ዱላ በመስጋት እንጂ ነገርዬውን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም አስቤ አይደለም፡፡ ምን አግብቶኝ! እኔ እንደሁ ያለ ቅያሬ በኖርሁባት ብቸኛ ሀገሬ ላይ የፑል መጫወቻ ስፖንዳ የምታህል መሬት እንኳ በስሜ አስከልዬ አላውቅም፡፡ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ስሞትም እንኳ ለመቀበሪያዬ ስንዝር መሬት ስለማግኘቴ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን ማን ነበር “እንደ አብርሃም ቤት የለኝ! እንደሙሴ መቃብሬ ላይታወቅ” ያለው? እንግዲህ የእኔና የመሰሎቼ እጣ ፈንታ እንደነገሩ ኖሮ፤ እንደነገሩ መሞት ሊባል ይችላል (መቼስ የድሃ ጥፋቱ እንጂ ሞቱ አይሰማምና)
ይሄ የመሬት ነገር ሲነሳ ቶሎ ወደ አእምሮዬ ከች የሚልልኝ “ሙስና” የሚለው ቃል ሲሆን፤ ስለሙስና ሳስብ ደግሞ ፍቺው፡፡ መቼም የአገራችን ባለስልጣናት የቃሉ ትርጉም “መሞት”፤ “መበስበስ”፤ ወይም “መፍረስ” መሆኑን ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም በመሬት ጉዳይ ከሆነ የቃሉን ፍቺ አናውቀውም ብለው ይፈጠሙና እስከ አንገታቸው ድረስ ይነከሩበታል፡፡ ከስልጣን ሲወርዱ እንዳይቆጫቸው ነው መሰለኝ የደረቡትን የስልጣን “ኤርሳክ” በመጠቀም የሙስናን ባህር ያለ ሃሳብ ይዋኙበታል፡፡
አንድ ሰሞን በየሚዲያው ስማቸው እየተጠቀሰ ሲወደሱ የነበሩ አንድ የዳር አገር (ክልል) ፕሬዚዳንት አስር ሺህ ካሬ መሬት እንደ ቁራጭ ዳቦ በጉያቸው ሸጉጠው ቆይተው ድንገት ተያዙ ልበል! እንዴ በረዶ ወርዶበታል እንጅ ከቶ በሀገሩ ላይ ምን መሬት ተርፏል ይባላል?
በቀደም’ለት ወደ ማታ ላይ ወደ ኪራይ ቤቴ ስጣደፍ ከአሕያ ማሰሪያ ጠጅ ቤት እንደወጣ የሚያስታውቅበት አንድ ጐልማሳ አንድ ወደፊት፤ ሁለት ወደኋላ በሚሉት የእርምጃ ስሌት መንገዱን በመንገዳገድ እየሞላ፣ በከፊል መጠጥ በለጐመው አንደበቱ:-
“ቤት የእግዚአብሔር ሲባል
መሬት የመንግስት
ምኑ ሊተርፈን ነው
እኔና የእኔ ሚስት” እያለ እያንጐራጐረ ወዲያው ደግሞ “መሬት አስለኩ አሉን አስለካን፤ ገንዘብ ክፈሉ እሺ አልን፤ ካርታ ሰጥተው አትሸጡትም አትለውጡትም ማለት ንቀት ነው፤ ምንድነው አሁንማ በቃ እነሱ እንደገቡት መግባት ነው፤ መግባት ብቻ! መግባት እያለ መግባት ይቸግራል እንዴ” እያለ ከራሱ ጋር ሲከራከር እንዳልሰማ ሆኜ አለፍኩት፡፡ የመሬት ነገር ጠጪውን እንኳ ዝም አያሰኝም!
በሀገራችን ውስጥ የመኖሪያ ቤት ሀሳባቸው የሞላላቸው ብዙ ዜጐች፤ በተረፈው ደግሞ የ”መኖሪያ መቃብራቸውን” በሠፋፊ መሬቶች ላይ በሚያማምሩ ዲዛይኖች በማሳነጽ በሠረገላ ቆልፈው መክፈቻውን አንገታቸው ላይ በማንጠልጠል፣ ሕይወታቸውን በዘመናዊ ሕክምና እያስጠበቁ፣ ሕንፃውን ያለስራ ከማስቀመጥ ይልቅ በእግረ መንገድ ለጽድቅም ይሆናቸዋልና ለእኔና ቢጤዎቼ ለዕለተ ኑሯችን በመጠነኛ ዋጋ ቢያከራዩን… ብዬ አሰብኩ፡፡ መንግስትም በነካ እጁ “የመቃብር ቤት ለሕያውያን” የሚል የአጠቃቀም መመሪያ አውጥቶ ከባለሀብቶች ጋር እንዲያደራድረን ለማን አቤት ማለት ይቻላል? ይሔንን ሠሞን መቼስ ይሕ አዲሱ የመሬት አጠቃቀም መመሪያ ዳር እስከዳር ከተማውን እያነጋገረ ለመሆኑ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ሁሉ ማስረጃ ነው፡፡ እና በቀደም እለት አውቶቡስ ተሣፍሬ ስጓዝ ከጐኔ የወንበሬ ተደባይ የነበር ወጣት፣ በሞባይል ስልኩ እያወራ ነበር፡፡ እኔም ጆሮዬን ጥዬ ሳዳምጥ ርዕሰ-ወሬው ይሔው የመሬት ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቤ ትኩረቴን ወደዚያው አደረኩ፡፡ ወጣቱ በራሱ ላይ መቀለድ የማይከብደው ሠው ሳይሆን አይቀርም እናም በስልኩ ውስጥ እንዲህ ሲል ሰማሁት “ሔሎ! ይገርምሀል! አዎ! እኔማ ያሠብኩት ካርታ ሲመጣልኝ ጠብቄ ቤቱንና መሬቱን በመሸጥ ያልኩህን ያንን “አባዱላ” ገዝቼ ታክሲ ለመስራት ነበር! ነገር ግን ሳይሆን ቀረ! አዎ! አዎ! ለነገሩ ለእነሡ ይብላኝ እንጂ ዞሮ፣ ዞሮ፣ “አባዱላውን” እንደሆነ አላጣውም… እንዴት? እንዴትማ ያው ሠሞኑን ጭንቅላቴን ሰወር ስለሚያደርገኝ አባ ጋ ሔጄ ፀበል ለመጠመቅ አስቤአለሁ፤ “ዱላ” ውን ደግሞ ጣራና ግድግዳው የአንተ ነው ስለተባልኩ፣ ቀጠን ረዘም ያለውን ከቤቱ ላይ እመዛለሁ! ታዲያ ይሔ አባዱላ አይባልም?” እያለ ይስቅ ነበር፡፡
እንደ እኔ፣ እንደ እኔ ይሔ የሚባለው የመሬት አጠቃቀም መመሪያ፤ በዕውነቱ ሀገርን ከማረጋጋት አንፃር ጥቅም ሊኖረው ይችላል ብዬ የምለው፣ በአንድ መንደር ውስጥ ካለ ቅያስ ላይ ከሚኖሩት ሀያ አባወራዎች መካከል (ለመድገም ያሕል ከሀያ አባወራዎች) ሀያ አምስቱ ካርታ ሲሰጣቸው፣ ቤትና መሬታቸውን ሸጠውና ዕድራቸውን በትነው በየፊናው ለመበታተን በደላላ አማካኝነት በየግላቸዉ ከገዥ ቀብድ ተቀብለው ነበር! የሚባለውን ያልተረጋገጠ ወሬ ከሠማሁ በኋላ ነው (እዚህች ላይ ማነህ! ወንድሜ! እንዲያው በከንቱ ከቤተሠብህ ጋር ቁጭ ብለህ ካርታ ስትጠብቅ መክረምህ እኮ ልብ ካለማለት እንጂ የካርታ ነገር እኮ ለአንተ እንደማይሆንህ የወርቅ ጥርስህን ሳይቀር አስይዘህ እየተጫወትክ የምትበላበት የ”ሴካ” እና “ኮንከር” ጨዋታ ትምህርት ሊሆንህ ይገባ ነበር፡፡)
በእርግጥ አንዳንድ የመሬት አጠቃቀም መመሪያውን ክፉ አድርገው የሚያስወሩ አሉባልተኞች ከአምስት መቶ ካሬ ሜትር በላይ የሆነ ቦታ ይወሰዳል እያሉ ያስወራሉ አሉ! ይሔ የፀረ ሕዝቦች ወሬ ሲሆን ስድስት መቶ ያለው መቶው ይወስድበታል እንደማለት ነው፡፡ ይሔ ሀሰት ሲሆን እውነታው ግን ስድስት መቶ ያለው ስድስት መቶውም ይወስድበታል የሚለው ነው፡፡ መቼስ ይሔ የሠሞኑ “የመሬት አጠቃቀም” መመሪያ ያልነካካው የሕብረተሠብ ክፍል የለምና የእርምጃው ግምባር ቀደም ተጠቂዎች የመሬት ደላሎች መሆናቸው ይታመናል (እዚህች ላይ! ማነህ ወንድሜ ደላላው “ጀቶ”፤ እንዲያው ወሬህ ሁሉ፣ “ግምባር ቦታ” “ግምባር ቦታ” እንዳልነበር ሁሉ ለራስህ ግን “የጦጣ ግምባር” የምታህል “ጭራ ቦታ” እንኳ ሳትይዝ በመሳሳትሕ እና ይሔ ጉዳይ በመፈጠሩ “ከስህተቱ መማር የማይችል ፈንጂ አምካኝ ብቻ ነው” የሚለውን የታክሲ ውስጥ ጥቅስ የማይታረም ስህተትን በመድገም ጥቅሱን “ፉርሽ” ያደረግኸው ሲሆን ለከእንግዲሁም ግምባርህን ያሣምርልሕና በቶሎ ወደ ሌላ ስራ እንድትሠማራ እመኝልሀለሁ)
እንግዲህ በእዚህ የመሬት አጠቃቀም ላይ የእኔም አንዱ የቅሬታዬ ምንጭ የሆነው ገዥና ሻጭ ሲዋዋሉ አብሮ በመቆም፣ የዕለት ባጀቴን ይዘጋልኝ የነበረው የ”ፍንጥር” ግብዣ ሠሞኑን መሬት የበላው በመሆኑ፣ ለዕለት ጉርሴ በሌላ ዘርፍ “ሮጥ፣ ሮጥ” ማለት ስላለብኝ ሳልሰናበታችሁ ሄድኩኝ፡፡

 

Read 3466 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:38