Saturday, 05 October 2013 11:04

የተሸረበ ሤራ

Written by  ገዛኸኝ ፀጋው (ፀ.)
Rate this item
(5 votes)

                          የማዘጋጃ ቤቱ ሹፌር ወንደሰን ተክለጻድቅ፣ ከጓደኛው ጋር ሞቅ ያለ ጭውውት የያዘ ይመሥላል- ቸኮሌት ኬክ ቤት በረንዳ ላይ፡፡ አንድ ከገላው ጋር የነተበች ቀይ ካኒቴራ ከአንድ እንደመነፅር ከሁለት ቦታ ላይ ከተነደለ ቁምጣ ጋር ያደረገ ጥውልግ ህፃን፣ ከፊታቸው እጁን ዘርግቶ ቆሟል። ያዩታል፤ ግን፣ አላስተዋሉትም። ከአሁን አሁን ከሻዩ ሂሣብ ተመልሰው ጠረጴዛ ላይ ከተበተኑት የሣንቲም ሽርፍራፊዎች፣ አንዷን እንኳ ይሠጡኛል ብሎ የጓጓው ህፃን ግን ከፊታቸው ዞር አላለም፡፡ የወንደሠን ጓደኛ አንገቱን በመነቅነቅ እንደማይሠጥ አሣወቀው። ይሉኝታ የማያውቀው የሥምንት ዓመቱ ህፃን ግን፣ በረሃብ የሚንጫረሩ ወሥፋቶቹን እያዳመጠ፣ ወደ ወንደወሠን ቀረብ ብሎ የልመና እጁን ዘረጋ፡፡
ትዕግሥት የለሹ ወንደሠን፤ በእጁ ሲያፍተለትል ያቆየውን መስቲካ፣ ከህጻኑ ጆሮ ግንድ ላይ እያጣበቀ “ምን አባክ! …ሂድ ሲሉህ አትሠማም” ብሎ ገፈተረው፡፡ “ይገርማል! … ሁሉም ለማኝ ሆነ …! ሠርቶ አይበላም! … መንገድ ላይማ መሄድ እኮ አትችልም” አለ፡፡
“አይ ወንዴ! አሁን ይሄ የአምሥት ዓመት ህፃን ምን ይሠራል! እንኳን እሡ የአምሥት ዓመት ዲግሪ ያለው የሚሠራው አጥቶ በተጐለተበት አገር …” አለ ጓደኛው፤ ሥራ አጥነቱ እየታወሠው፡፡
“እሡማ--እንደኔ ቆሻሻ ለመልቀምም ዲግሪ ሣይጠየቅ አይቀርም …” ብሎ ዞር ሲል፣ ጆሮ ግንዱ ላይ የቤት ሥራ የተሠጠው ህጻን ከፀጉሩ ጋር የተጣበቀውን ማስቲካ በጣቱ እየቆፈረ፣ አስፋልት አቋርጦ ሢሄድ አየው፡፡ እንባ ተናንቆታል። ወንደሠን ግን “ልጅና ችግር በሩቁ” ባይ ሥለሆነ በድርጊቱ አልተፀፀተም፡፡
ትላንት ጧት በበላት ጥቂት የተበላሹ ፍራፍሬዎች አድሮ የዋለው ህፃን፣ የረሃብ ግርፊያው ሢብሥበት የሰሞኑ የረሃብ ማስታገሻውን አሥታወሠ፡፡ ተስፋ ቢጤ ብልጭ አለለት፡፡ አዎ! ሌሎች የጐዳና ተዳዳሪዎች ካልቀደሙት፣ ቢያንሥ ማስታገሻ አያጣም፡፡
አመድ የተነፋባቸው ማማሠያ የሚመሥሉ ሁለት እግሮቹን እያማታ፣ በወሎ ሆቴል ሽቅብ ወጣ። የተወሠነ መንገድ እንደሄደ በሥተቀኝ ታጠፈ፡፡ አሁን በርግጥ ያቺ ትንሽ ልቡ በአንድ በኩል በችጋር፣ በሌላ በኩል በወላጅ ናፍቆት ተጠብሳለች። ስለ አባቱ ማንነት እያሰበ ነበር፡፡ “ግን አባቴ ማነው?” ሲል ጠየቀ-ራሱን፡፡ ይህን ጥያቄ እንኳን እሱ እናቱም አልመለሠችለት…
                                                   * * *
መልከ ቀናዋ ቦረኔ አስቴር ከመለው፣ በልጅነቷ ሣትፈልግ በቤተሠብ ጫና ከመሠረተችው ትዳር ኮብልላ መካነሠላም ከተማ የገባችው፣ ከዛሬ አስር አመት በፊት ነበር፡፡ በከተማው ካለው ቡና ቤት መቀነቷን ፈትታ፣ የሴተኛ አዳሪ ቀሚሥ አጠለቀች። መልከ ቀና ሴት ሢያዩ የወሢብ ፈረሣቸውን የሚጋልቡት ወንዶችም፣ እርሷን ሢያዩ ለአንድ ሰሞን ልጓማቸውን በጥሰዋል፡፡ እርሷም በጥቂት ቀን ብዙ ገንዘብ ሥላገኘች፣ የሥራውን አዋጭነት ተረድታለች። የራሷን ቤት ተከራይታም አረቄ በመሸጥ፣ ቀረጥ የማይከፈልበትን ግብሯን ቀጠለች።
ከከተማዋ ነዋሪዎች ውጭ ያሉ የሌላ አካባቢ ሹፌሮችም ቤቷን ለመዱላት፡፡ እንደውም ሁሉም ቅምጣቸው አደረጓት፡፡ በተለይ በዛ መስመር ብዙ ጊዜ የሚመላለሰው የቶዮታ ፒክአፕ ሹፌር እንዳፈቀራት አውቃለች፡፡ በተደጋጋሚም አብረው ሥለተኙ፣ ከእሱ እንዳረገዘች ገምታለች፡፡
ስድስተኛ ወሯ ላይ አረገዝኩለት ለምትለው ሹፌር አባትነቱን አረዳችው፡፡ “ምን አልሽ? የትም ሥትቀብጭ ያመጣሽውን ዲቃላ የኔ ልታደርጊው አሠብሽ! ሰማሽ ሁለተኛ እንዲህ አይነት ወሬ ብሠማ ደፍቼሽ ነው የምሄደው!” አለ ሹፌሩ፣ ጣቱን ፊቷ ላይ ቀሥሮ፡፡
ከዚያ ቀን ጀምሮ ሥለ ልጇ አባት ለማንም ትንፍሽ ብላ አታውቅም፡፡
ለእለት ጉርሷ አረቄዋን ትቸበችባለች። የባሠበትም ሆዷ እንደ ተራራ ተቆልሎ እያየ፣ አብሬሽ ካላደርኩ ሲላት፣ ሳትወድ በግዷ ለገንዘብ ብላ ትተኛለች፡፡
በተለይ አንድ ቀን አይረሣትም፡፡ ከቤቷ ምንም ነገር የለም፡፡ ደንበኞቿም ፊታቸውን ወደ ጐረቤቷ ቤት እያዞሩ ነው፡፡ ሆዷም በጣም ገፍቷል - ዘጠነኛ ወሯ ላይ ናት፡፡ እሷ ግን ቀኑን በውል አለየችውም። ከምሽቱ አምስት ሠዓት አካባቢ ነው። አንድ ሠካራም ቤቷን አንኳኳ፡፡ ከፈተች፡፡ አንድ መለኪያ አረቄ ከጠጣላት በኋላ፣ በኮልታፋ አንደበቱ የጠየቃትን ልታሟላ ከቦንዳ አልጋዋ ላይ ተቆልላለች፡፡ በአረቄ የነፈዘው ገበሬ፤ ከሆዷ ተራራ ላይ ተከመረ፡፡ አንዳች ነገር ማህፀኗን ወጋት፡፡ ሆዷ ውስጥ ያለው ህጻን “በህግ ዓምላክ!” ሲል የተፈራገጠ ይመሥላል። በቃ ተሠቃየች፡፡ የተቀበለውን የእርዳታ እህል ሸጦ ለልጆቹ ሳያደርሥ፣ ከእርሷ ጋር ያደረው ገበሬ ለሊት ላይ ነቃ፡፡ ክፍያውን ሊያሥተካክል ሲደባብሥ፣ ሞፈር ለመጨበጭ የሠነፈው እጁ፣ከተራራው ቁልል ጋር ተጋጨ፡፡ ደነገጠ፡፡ እሷ በላብ ተጠምቃ ታቃሥታለች፡፡ በድንጋጤ በር ከፍቶ ወጣ፡፡ ጧት ላይ ጐረቤቶቿ ተረዳድተው ጤና ጣቢያ ወሠዷት … ከብዙ ስቃይ እና እንግልት በኋላ፣ ወንድ ልጅ ተገላገለች፡፡
“ወንድሜነህ ከመለው” አለችው - በእሷ አባት ሥም፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከልጇ ጋር የችጋር ሕይወት መጋራት ጀመረች፡፡ ኑሮው ሢፈትናት ወደ ቀን ሥራ ገባች፤ ማታ ማታ የድሮውን፡፡ ውበቷ ግን ከሥሟል። ጤንነትም እያጣች ነው፡፡ የሰውነቷ መቀነስም የሽሙጥ ጣት አሥቀሥሮባታል፡፡ እንደዚህም ሆና ለአንድ ልጇ አልተሸነፈችም፡፡ ወንድሜነህ ስድስት ዓመት ሲሞላው ትምህርት ቤት አሥገባችው፡፡
አንድ ቀን ወንድሜነህ ትምህርት ቤት ቆይቶ ሲመጣ፣ “እናቴ … እነከዲር አባት የለህም አሉኝ! … አባቴ ማነው ግን?” አላት፡፡ በጣም ደነገጠች፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሥለ አባቱ፣ በአጠቃላይ ሥለ ሕይወቷ ማታ ማታ ትተርክለታለች፤ በትምህርት ባልተገራ ምላሷ፡፡ በልጇ ላይ የምትፈጥረውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመገንዘብ አቅሟ አይፈቅድላትም፡፡
ወንድሜነህ የአባቱን ሥም በሚገባ አጥንቷል፡፡ ወደ ኋላ ላይ በሽታውም እየጠነከረባት ሄደ፤ የልጇ ብሶትም ሰላሟን ነሣት፡፡
“አወይ … ያንተኮ እናት ኤድስ ይዟታል! … አንተም እኮ ኤድስ አለብህ … ታለበለዚያ ለምን ቀጭንዬ ሆንክ? … እኛ መቼም ካንተ ጋር አንጫወትም...” እያሉ የመንደር ጓደኞቹ ሲያገሉት እያለቀሠ መጥቶ ይነግራታል፡፡ እርሷም እንደተሸነቆረ ማሠሮ ውስጥ ውስጡን ታነባለች። የሃሜቱ መብዛት የኤድስ በሽተኝነቷን አምና እንድትቀበል አደረጋት፡፡ የነገራት ሐኪም የለም እንጂ፣ ህመሟ የማህጸን ካንሰር ነበረ፡፡
“ጠጋ በል! አትንካን፣ …ኤድሣም” እያሉ የክፍል ጓደኞቹ ከወንበር ላይ ያሥነሡታል፡፡ ሥቅሥቅ ብሎ እያለቀሠ ብቻውን ከመሬት መቀመጥ ጀመረ፡፡ ሠፈር ውስጥ አብሮት የሚጫወት ልጅ አጣ፡፡ ቤት ውስጥ እናቱ፣ አልጋ ላይ ወድቃለች፡፡ በሰው ሽሙጥና ሀሜት ሣቢያ ሞትን የተጋፈጠችው እንስት፣ ልጇን ሥታይ ገመምተኛ አንጀቷ ይላወሥባታል፡፡
ልጇም ከጐኗ ጋደም ብሎ፣ “እናቴ …” ብሎ ይጠራትና “አባቴ እዚህ ከመጣ ዘልዬ እቅፍ አደርገውና ‘ልጅህ እኮ ነኝ’ ስለው ‘እሺ’ ይለኝ የለ… ከዛ እናቴን አሟታል ብዬ፣ ብር ሲሠጠኝ እሰጥሻለሁ … እሽ? አይዞሽ…” እያለ ሲያባብላት ላየ ሰው፣ ልቡ በሀዘን ይደማል፡፡
አስቴር የወንድሜነህን አባት ካየችው ድፍን አምሥት ዓመት ሆኗታል፡፡ የልጁን ቁመት ማጠርና የጆሮዎቹን መተለቅ ሥታይ ግን፣ አባቱ ትዝ ይላታል። ከቀናት በኋላ የአስቴር ሞት ቁርጥ ሆነ። አዋጥቶ ያላሥታመማት መንደርተኛ፣ አዋጥቶ ቀበራት። የወንድሜነህም እጣ ፈንታ መንደር ለመንደር ማውደልደል፣ በየሰው ቤት መቀላወጥ ሆነ፡፡
በቅርቡ ግን አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ መካነሠላም ያሉ ጐረምሶች አንድ ቁራጭ ወረቀት ለባለቡና ቤቷ ወሰኔ እንዲያደርሥ ይልኩታል። “ማነው የሰጠህ?” አለችው -ጠይሟ እንስት፡፡ ነገራት። ገለጥ አድርጋ እንዳነበበች፣ “ማን አባህ ይዘህልኝ ና አለህ!” ብላ በጥፊ አጠናገረችው። ወደ ቤርጐውም አሥገብታ፣ “ሁለተኛ እዚች ትርው ትላለህ!? አንተ ገፊ!” እያለች በቴፕ ሶኬት ጀርባው ደም እስኪያዝል ገረፈችው፡፡ በእንባ ጐርፍ እየታጠበ ከከተማው ወጣ ብሎ ብቻውን ሢያለቅስ ዋለ። የሰው አጥር ተጠግቶ እያነባ አሸለበው። ብትት ሲል፣ ሆዱ ውስጥ ያሉት ወሥፋቶች በህብረት ይዘላሉ፡፡
በተላከባት አሥር ሣንቲም ሸንኮራ አገዳ ገዝቶ እያላመጠ፣ የጨከነበትን ህዝብ በመሸሽ፣ አባቱን ፍለጋ፣ በጭነት መኪና ላይ ተደብቆ ወደ ደሴ አቀና። የአባቱን ሥም ብቻ በልቡ ከትቧል፡፡ እንዴት ብሎ እንደሚፈልገው ግራ ገብቶት ሳያስበው በደሴ የጐዳና ሕይወት ተሞሸረ፡፡
አዲስ ያሟሸው የጐዳና ሕይወት ግን ከመካነ ሠላም ኑሮ የበለጠ ፈተና ሆኖበታል፡፡
                                                        * * *
አሁን ግን የጆሮ ግንዱን ፀጉር ሞጭጮ ይዞ አለቅለት ያለውን መሥቲካ እየፋቀ፣ ሊመልሠው ያልቻለውን የአባቱን የዘወትር ጥያቄ ለራሡ እየጠየቀ፣ ቁልቁል ወደ አዜንዳ ሠፈር አቀና። በርቀት ታየው፡፡ ሆዱ ጮኸ፡፡ ግን አንድ ነገር ፈርቷል - ተልከስካሽ ውሻ፡፡
ከቦታው ሲደርሥ በጉጉት ሲያሥበው የነበረው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ፣ በቆሻሻ ቁልል ተራራ ተሠርቶበት አገኘ፡፡ ከገንዳው በተረፈውና ዳር ላይ በተደፋው ቆሻሻ አካባቢው ተልከሥክሷል፤ የሚበላ ነገር ግን የለም፡፡ ወደ ገንዳው ሲጠጋ ዝንቦች ግር ብለው ተነሡ፡፡ ደንግጦ ቆመ፡፡ ከዚህ በፊት ያጋጠመው ታወሠው …
አንድ ቀን ከገንዳው ሥር የወደቀውን የተበላሸ ፍራፍሬ በነፃነት ይበላል፡፡ ከእጁ የያዛትን የተላጠ ብርቱካን እንዳጠናቀቀ፣ ሌላኛውንም ሊያነሣ ጐንበሥ ሢል እና ተልከሥካሽ ውሻ ከገንዳው ሢዘል አንድ ሆኑ፡፡ ውሻው ጀርባው ላይ ሲያርፍ፣ ሁለቱም ጮኹ፤ ሁለቱም ሮጡ- በተለይ ውሻዉ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ውሻ ሲፈራ ለጉድ ነው፡፡ ዛሬም ውሻ እንዳያጋጥመው ነው፣ በርቀት የሚያገበግበዉ።አሁን ግን ዝንቦች ግር ብለው እየተነሡ ያርፋሉ እንጂ፤ የሚዘል ውሻ የለም፡፡ ቢጨንቀው ድንጋይ ወረወረ። ሁለት ድመቶች በፍጥነት ከገንዳው እመር ብለው ወጡ፡፡ ውሻ አለመኖሩን አረጋገጠ፡፡ አሁን በሰላም ወደ ማይከፈልበት ሆቴል ቀረበ … ከመሬት ላይ የወዳደቀ ነገር አጣ፡፡ የአቦካዶ፣ የፓፓዬ፣ የሙዝ … ልጣጮች ከተቆለለው ቆሻሻ አናት ላይ ተኮፍሠው ታዩት፡፡ እያወረደ ይገምጣቸው ዘንድ ቁመቱ አልፈቀደላትም፡፡ የቆሻሻ ገንዳውን የሚሸከመው መኪና ሠንሠለቱን በሚያሥገባባቸው ተለጣፊ ብረቶች ላይ ለመንጠልጠል ሞከረ፤ አልተሣካለትም፡፡ ከገንዳው ጀርባ ያለችውን ጅረት ለመከለል በታጠረው አጥር በኩል ተንጠላጥሎ ገንዳው ላይ ጉብ አለ፡፡
የጓጓበትን የረሀቡን ማስታገሻ፣ ከተጣሉት የፍራፍሬ ልጣጮች ጐን አገኘ፡፡ በሥብሠው የተጣሉት ብርቱካኖች ለእርሡ ልዩ ምግቦቹ ናቸው። አንድ ደህና የሚመሥል ሙዝም አየ፤ ተሽቀዳድሞ ከቤት ጥራጊ ቆሻሻው መሃል መዞ አወጣው፡፡ አሁን እርግጠኛ ነው፤ ባልደረቦቹም አልቀደሙትም፡፡ ሙዙን ሁለት ጊዜ እንደጐረሠ ያቆበቆቡት ወሥፋቶች እረብ ያሉለት መሠለው፡፡
አሁንም ሌላ የተጣለ ፍራፍሬ ለማውጣት በጣቶቹ ጥፍሮች መቆፈር ያዘ ... ከደቂቃዎች በኋላ ግን አንዳች ነገር ሆዱን አሸበረው፡፡ በገንዳው ጠርዝና ጠርዝ ላይ የተንፈራጠጡት ቀጫጭን እግሮቹ ሊሸከሙት አልቻሉም፡፡ አንደኛውን እግሩን ከገንዳው ጠርዝ ላይ አንሥቶ ቆሻሻው ላይ ሲያደርግ፣ ታላቁ የቆሻሻ ቁልል ተገነበረ፡፡ የወንድሜነህ እጣ ፈንታም ከገንዳው ውስጥ ከተጣሉ የበግ ራሶችና የበሬ ሽሆናዎች ላይ በጭንቅላቱ መቆም ነበረ። ያ ሁሉ የቆሻሻ ናዳ እላዩ ላይ ተከመረበት፡፡ በደመነፍሥ እየተወራጨ ከራሡ ላይ የተቆለለውን ቆሻሻ ለማንሳት ይንፈራገጣል፡፡ ዘለው ገንዳው ላይ ቁብ ያሉት ድመቶች አንዳች ነገር ቆሻሻው ውስጥ ሲላወሥባቸው፣ ነፍሴ አውጭኝ እየሮጡ ነው፡፡ ወንድሜነህ ግን በግንባሩ በኩል ደሙ ቲልቲል እያለ ከወደቀበት ደንዝዞ ቀረ …
የቆሻሻ መኪናው ሹፌር ከሰዓት በኋላ የሰዓት ፊርማ እንደፈረመ፣ በቀጥታ ወደ አዚንዳ ሠፈር አቀና፡፡ መኪናው ፊቱን አዙሮ መንታ ተለጣጭ ብረቶቹን እስከ መሸከሚያ ሠንሠለቱ ወደ ቆሻሻው ገንዳ ዘረጋ፡፡ የሹፌሩ እረዳት አፍንጫውን እስከ ጆሮው በጭንብል ሸፍኖ፣ በፍጥነት ሠንሠለቱን ከገንዳው ጋር እንዳገናኘ ጋቢናውን ከፍቶ ገባ፡፡ መኪናውም እያንቧረቀ፣ የቆሻሻ ቁልሉን አነሣ፡፡ ያ ምስኪን የጎዳን ህፃን ከደነዘዘበት እየነቃ ነው፤ ምን እየሆነ እንዳለ ግን በውል አያውቅም …
መኪናው ፍጥነቱን ጨመረ፡፡ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በኩል አድርጐ ወደ መብራት ሃይል ከነፈ፡፡ ወንድሜነህ አሁን ከፍተኛ ሥቃይ ሆዱ ላይ ቢሠማውም፣ ምን እንደተፈጠረ እንደ ህልም ከሚታየው ውጭ ለይቶ አልተረዳውም፡፡
መኪናው “ከበደ አበጋዝ” ሆቴል ላይ ሲደርስ ግን፣ የሆዱ ሥቃይ ‘ከቆሻሻ ጋር ልገለበጥ ነው’ ከሚለው ሥጋት ጋር አብሮ ወንድሜነህን በሀይል አስጮኸው፡፡ ባለ በሌለ ሀይሉ የጩኸት ጥሩንባውን አንባረቀ፤ ከመኪናው ሞተር ድምፅ በልጦ ሊሠማለት ግን አልቻለም፡፡ በመንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች መኪናው ላይ ያለው ቆሻሻ እየታመሰ ተመለከቱ፡፡ አንዳች ድምፅም የሠሙ መሰላቸው … “ቃኘው ሆቴል” ጋር ሲደርሥ፣ የቆሙ መኪኖች መንገድ ያዙበት፡፡ መኪናውም ፍጥነቱን ለመቀነስ ተገደደ፡፡ ወንድሜነህ በጣም ሲጮህ “ቃኘው ሆቴል” የፎቅ በረንዳ ላይ ያሉ ሰዎች ሰሙት፡፡ ቆሻሻው ነፋስ እንደገባበት አመድ እየተበተነ ነው …
መኪናው መንቀሣቀሥ ጀመረ፡፡ ሰዎቹ ጮኹ። በፊት ለፊታቸው ላሉት ሰዎች፣ ምልክት እያሣዩ፤ ተንጫጩ፡፡ መኪናውን አሥቆሙት … ሹፌሩ ለምን እንዳሥቆሙት አላወቀም፡፡ የሰው መዓት በመኪናው ዙሪያ ባንድ ጊዜ ተሠበሠበ፡፡ የወንድሜነህ ጩኸት አስተጋባ፡፡ ሊስትሮዎች ቆሻሻ ከያዘው መኪና ላይ ተንጠላጠሉ፡፡ “ኸረ! ልጅ አለ!?” ብለው ዘለው ገንዳው ውስጥ ገቡ፡፡ አካባቢው በምድረ አዳም ተጥለቅልቋል … ወንድሜነህን ተጋግዘው አንጠልጥለው ብቅ እንዳደረጉት፣ የተሠበሠበው ሰው ሁሉ ጮኸ፡፡
አጋጣሚውም ታምር ተባለ፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተወካይ ወደ አቀደው ሥራ መሄዱን ትቶ፣ መቅረፀ ምስሉን ይዞ ከምን ጊዜው ከተፍ እንዳለ አልታወቀም፡፡ የተሰበሰበው ሰው ከፖሊስ መምሪያው በመጡ ፖሊሶች ባይበታተን ኖሮ፣ ይህን ምስኪን ህፃን አፍነው ይገሉት ነበረ - ለወሬ ሢሉ …
የትራፊክ ፖሊሶቹ የሹፌሩን መንጃ ፍቃድ ተቀብለው ያናዝዙታል፤ “እኔ ምን ላድርግ! እረዳቱ አለ … እኔ እኮ መኪናው ውስጥ ነኝ፡፡ እሡ ነው እንጂ … ይሄ ደንባራ! እንዴት እንዳላየው!” እያለ ሹፌሩ ረዳቱን ገላመጠው፡፡
ከግርግሩ መሃል ከቆሻሻ ጋር ሊጣል የነበረውን የነተበ ቀይ ካናቴራ ለባሽ ህፃን ሲያይ ግን፣ በጣም ደነገጠ፤ ከተወሠነ ሠዐት በፊት ቸኮሌት ኬክ ቤት በረንዳ ላይ በማስቲካ የቤት ሥራ ሠጥቶ ያባረረው “ለማኝ” … ነው …
                                                   * * *
ሪፖርተሩ መቅረፀ ድምፁን አሥጠግቶ ያናዝዝዋል፡፡ “እስኪ ሌሎቻችሁ ወደዛ በሉ! አይዞህ ወንድሜነህ … ታዲያ አባትህን ታውቀዋለህ?” አለው ዘጋቢው ጋዜጠኛ፡፡
“አላውቀውም … ስሙን ብቻ ነው የነገረችኝ …” አለ ወደ አፉ የተጠጋውን መቅረፀ ድምፅ እያሥተዋለ፡፡
“ታዲያ አባትህ ማነው አለችህ? … ሥራው ምንድነው?”
“ሹፌር ነው፡፡ ወንደወሠን ተክለፃድቅ ነው የሚባለው …” ብሎ ሣይጨርስ፣ የትራፊክ ፖሊሱ ድንግጥ ብሎ የመንጃ ፈቃዱ ላይ ያነበበውን ሥም ደግሞ እያነበበ፣ “ይሄ ሰውዬ ነው እንዴ ማሙሽ?” አለ ጣቱን ወደ ሹፌሩ ቀስሮ፡፡ ሹፌሩ በድንጋጤ ክው ብሎ ቀረ … ፖሊሱም በሁኔታው በጣም ተገርሟል፤ … ሊፈጠር ስለነበረው ወንጀልም አሠላሠለ …
“ከየት--- ነው የመጣኸው?” አለ ሹፌሩ አፉ እየተሣሠረ፡፡
የትራፊክ ፖሊሡ የመንጃ ፈቃዱን አንቀርፍፎ እንደያዘ፣ “አሃ! … ምሥጢሩ ሳይወጣ ሊያጠናቅቀው ነበር! … ሃምሣ አለቃ የተሸረበ ሤራ ያለ ይመሥላል …” ሲለው ሃምሣ አለቃው በአንገቱ ምልክት እየሠጠ፣ ሁሉንም በህግ ሊዳኛቸው ለራሡ ቃል ገባ፤ ይዟቸውም ሄደ … እርግጥ ነው፣ ሴራው ባጋጣሚ እንጂ ሆን ተብሎ የተሸረበ እንዳልነበረ ማስረዳትም ሌላ ፈተና ነው - የተሸረበ ሤራ፡፡

Read 3736 times