Saturday, 12 October 2013 13:10

የባንክ ደብተሬ

Written by  ድርሰት - ስቴፈን በትለር ሊኮክ ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ
Rate this item
(10 votes)

                      እግሬ ገና የባንኩን ደጃፍ ሲረግጥ ነው ፍርሃት የወረረኝ፡፡ ሰራተኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ወንበር እና ጠረጴዛው፣ የማያቸው ብሮች ሳይቀሩ አስፈሩኝ፡፡ በቃ ሁሉም ነገር ፍርሃት ለቀቀብኝ፡፡
ለነገሩ ይሄ ሃሳብ ድንገት ነው ብልጭ ያለልኝ፤ በባንክ ቤቱ ደጃፍ ሳልፍ፡፡ ከዚህ ቀደም ባንክ ቤት ወደ አዕምሮዬ መጥቶብኝ አያውቅም፡፡ አሁን ደመወዜ ወደ ሃምሳ አምስት ብር በማደጉ ነው ባንክ ቤትን ያሰብኩት፡፡
እናም ወደ ውስጥ ዘው ብዬ ገባሁና በካውንተሩ ዙሪያ የተቀመጡትን ሰራተኞች በፍርሃት ማስተዋል ጀመርኩ፡፡ መቼም አዲስ የባንክ ሂሳብ መክፈት የፈለገ ሰው የባንክ ቤቱን ስራ አስኪያጅ ማማከር ይገባዋል ብዬ አሰብኩ፡፡
“የሂሳብ ክፍል” የሚል ፅሁፍ ወደተለጠፈበት አቅጣጫ አመራሁ፡፡ የሂሳብ ባለሙያው ረዥም ሰው ነው፤ ቅዝቅዝ ማለቱ በፍርሃት የሚያርድ፡፡ ካቀረቀረበት ቀና ሲል አስተያየቱ ሽብር ለቀቀብኝ፡፡ ድምፄ መቃብር ፈንቅሎ የሚወጣ ያህል ተርገበገበ፡፡
“ሥራ አ…ስኪያጁን ማነጋገር እችላለሁ?” አልኩትና ወዲያው ጠነን ብዬ “ለብቻው?” ስል አከልኩበት፡፡ “ለብቻው” ማለቱ ለምን እንዳስፈለገኝ ግን አልገባኝም፡፡
የሂሳብ ባለሙያው “ይችላሉ” አለኝና ሥራ አስኪያጁን ጐትቶ ይዞት መጣ፡፡
ሥራ አስኪያጁ ረጋ፣ ኮስተር ያለ ሰው ነው። ኪሴ ውስጥ ሃምሳ አምስት ብሮቼን እንደ ኳስ አድቦልቡዬ በመዳፌ ይዣለሁ፡፡
“ሥራ አስኪያጁ እርስዎ ነዎት?” ስል ጠየኩት። ሥራ አስኪያጁ እሱ መሆኑን ቅንጣት ታህል እንዳልተጠራጠርኩ ግን እግዚሀር ያውቃል፡፡
“አዎን” አለኝ፡፡
“ላነጋግርዎ እችላለሁ?” አልኩት “ብቻዎን?”
ደግሜ “ብቻዎን” ማለት አልፈለግሁም ነበር፤ እንደዚያ ባልል ግን ጥያቄዬ ተራና ዋጋ ቢስ ይመስልብኛል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ጭንቅ ጥብብ እያለው ትክ ብሎ ያስተውለኝ ጀመር፡፡ የምነግረው አንዳች ጥብቅ ሚስጥር እንዳለኝ ገምቷል፡፡
“ተከተለኝ” ብሎ ብቻችንን ወደምንሆንበት ክፍል ይዞኝ ገባና፣ በሩን ከውስጥ ቆለፈው፡፡
“ለደህንነታችን እዚህ ይሻላል፤ ማንም ሳያናጥበን ለብቻችን ማውራት እንችላለን… አረፍ በል” አለኝ፡፡
ሁለታችንም ከተቀመጥን በኋላ ለአፍታ ተፋጠጥን፡፡ እኔ ጉሮሮዬ ደርቆ ድምፅ ማውጣት ሁሉ ተስኖኝ ነበር፡፡
“ካልተሳሳትኩ…ከወንጀል ምርመራ ቢሮ ነው የመጣኸው አይደል” አለኝ፤ በከፊል እርግጠኛ ሆኖ።
ሥራ አስኪያጁን ወንጀል መርማሪ ነው ብሎ እንዲያስበኝ ያደረገው እንቆቅልሽ ባህሪዬ መሆን አለበት፡፡ በዚያች ቅፅበት በአዕምሮው ምን እያብላላ እንደሆን ስለገባኝ የበለጠ ተረበሽኩ፡፡
“አይ ከወንጀል ምርመራ ቢሮ እንኳን አይደለም የመጣሁት” አልኩት፡፡ አነጋገሬ ግን ከዚያም በላይ ከሆነ የደህንነት መስሪያ ቤት የመጣሁ የሚመስል ድምፀት ነበረው፡፡
“እውነቱን ለመናገር…” ብዬ ቀጠልኩ፤ ልክ የመጣሁበትን ዋና ጉዳይ ሸፋፍኜ ውሸት እንድናገር ያስጠነቀቀኝ ሰው ያለ ይመስል፡፡ “እኔ በፍፁም ወንጀል መርማሪ አይደለሁም… የመጣሁት የባንክ ሂሳብ ልከፍት ነው፡፡ ገንዘቤን በሙሉ በዚህ ባንክ ቤት በአደራ ለማስቀመጥ አቅጃለሁ፡፡”
ሥራ አስኪያጁ አንቆ ከያዘው ጭንቀት ፈታ ያለ መሰለ፤ ግን ኮስተር ብሎ እያየኝ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ያለጥርጥር ከቤተሰብ የወረስኩት ብዙ ገንዘብ ይዤ የመጣሁ ዲታ እንደሆንኩ የገመተ ይመስላል፡፡
“በርከት ያለ የገንዘብ መጠን መሰለኝ?” አለኝ ወደ እርግጠኝነት በሚያደላ ቅላፄ፡፡
“በርግጥ ብዙ ነው” አልኩ፤ ዝቅ ባለ ድምፅ፡፡
“እንግዲህ እንደኔ እቅድ በዚህ ባንክ ቤት ውስጥ በአደራ ለማስቀመጥ ያሰብኩት… አሁን በድምሩ ሀምሳ አምስት ብሮችን ሲሆን በቀጣይም በየወሩ ሃምሳ ሃምሳ ብሮችን ማጠራቀሜን እቀጥላለሁ ማለት ነው፡፡”
ሥራ አስኪያጁ ከወንበሩ ተስፈንጥሮ ተነሳና የቆለፈውን በር ከፈተው፡፡ የሂሳብ ባለሙያውን ተጣራ፡፡
“እኒህ የተከበሩ ደንበኛ፤ የቁጠባ ሒሳብ ከፍተው ሃምሳ አምስት ብር ማስቀመጥ ይፈልጋሉ” አለውና ወደኔ መለስ ብሎ “መልካም ቀን” አለኝ፡፡
ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡
በክፍሉ ሌላ ጥግ ላይ የተከፈተ ትልቅ የብረት በር ያለው ክፍል ይታያል፡፡ “መልካም ቀን!” አልኩትና ራመድ ራመድ ብዬ ወደ ትልቁ ብረት በር ክፍል ስገባ፤ ሥራ እስኪያጁ በታከተ ድምፅ “ና በዚህ ውጣ” ብሎ ቀድመን የገባንበትን በር ጠቆመኝ፡፡
የሂሳብ ባለሙያው ባልጠበቀው ቅፅበት ድንገት አጠገቡ ደርሼ፣ ልክ አስደናቂ የምትሃት ትርኢት በሚያቀርብ አስማተኛ ፍጥነትና ቅልጥፍና፣ እንደ ኳስ የተድቦለቦሉትን ሃምሳ አምስት ብሮች ከኪሴ አውጥቼ፤
“እነሆኝ!” አልኩ “የባንክ ደብተሬ ላይ መዝግብልኝ” አባባሌ ግን “ያው እንግዲህ ይህን የመጣብንን መከራ እንሸከመዋ፤ መቼስ አንድ ጊዜ ፈቅድን ገብተንበት የለ” የሚል ቃና ነበረው፡፡
የሂሳብ ባለሙያው ገንዘቡን አነሳና ለሌላ ገንዘብ ተቀባይ አስተላለፈለት፡፡
ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጀ ቅፅ ላይ ሙሉ ሥሜንና የብሩን መጠን ፅፌ እንድፈርም ካደረገ በኋላ፤ ስሜን ከቅፁ እያየ ወደ ባንክ ደብተሬ ላይ ገለበጠ፡፡ እኔ ለራሴ ነገር አለሙ ተደበላልቆብኝ የማደርገውንም አላውቅም ነበር፡፡ የማየው ሁሉ ብዥ ብሎብኝ፣ የባንክ ቤቱ ዙሪያ ማዕበል እንደሚያንገላታው ባህር ሆኖ በአይኔ ስር ወዲያ ወዲህ ይዋዥቃል፡፡
“እህ? በባንክ ደብተሬ ላይ ተመዘገበ?” ስል ለዛው በተሟጠጠ የሚንቀጠቀጥ ድምፅ ጠየቅሁ፡፡
“በትክክል” አለ አካውንታንቱ፡፡
“ጥሩ፤ አሁን ደግሞ ከባንክ ደብተሬ ተቀማጭ ሂሳብ ላይ ወጪ ማድረግ እፈልጋለሁ”
ለማውጣት ያሰብኩት ለጊዜው የሚያስፈልገኝን አምስት ብር ብቻ ነው፡፡ አንዱ የባንክ ቤቱ ሠራተኛ ወጪ ማዘዣ ቅፅ ሲያቀብለኝ፣ ሌላው ደሞ ቅፁን እንዴት መሙላት እንዳለብኝ ያስረዳኝ ጀመር፡፡ በባንክ ቤቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ተቀማጭ ገንዘብ ያለው፤ ሆኖም ግን ስሜቱ የተረበሸበት ሰው አድርገው ሳይቆጥሩኝ አልቀሩም፡፡ ገንዘብ ወጪ ማድረጊያ ቅፁ ላይ ፃፍ ፃፍ አደረግሁና ከስሩ ፊርማዬን አኑሬ በቅርቤ ወዳለ ገንዘብ ከፋይ ገፋ አደረግሁለት፡፡ ገንዘብ ከፋዩ ቅፁን አንስቶ ተመለከተና፤
“ምን?! ያስገባኸውን ገንዘብ እንደገና ልታወጣው?” ሲል በመገረም ጠየቀኝ፡፡
ለካስ አምስት ብር ለማውጣት አስቤ፣ ሃምሳ አምስት ብር ብዬ ነበር የፃፍኩት፡፡ ሆኖም ግን አሁን ምክንያት ለመደርደርም ሆነ ስህተቱ ከቁጥጥሬ ውጪ በሆነ መንገድ እንደተፈጠረ የማስረዳበት እንጥፍጣፊ አቅም የለኝም፡፡ የባንኩ ሰራተኞች ሁሉ ስራቸውን አቁመው እኔ ላይ አፈጠጡ፡፡ እኔ ግን አይኔን በጨው አጥቤ፤
“አዎ፤ አንድም ሳይቀር” አልኩት
“በባንክ ቤቱ ውስጥ ያስገባኸውን በሙሉ መልሰህ ልትወስደው ትፈልጋለህ?”
“አንዲትም ሳንቲም ሳላስቀር፤ሁሏንም!” ድርቅ ብዬ መለስኩለት፡፡
“ከዚህ በኋላ በቁጠባ ደብተርህ ውስጥ ገንዘብ ማጠራቀም አትፈልግም ማለት ነው?”
“በጭራሽ!!”
የገንዘብ ማውጫውን ቅፅ ስሞላ ሀሳቤን እንድቀይር ጫና ያሳደረብኝ አንድ ነገር መፈጠሩን ሊያስቡ ይችላሉ ብዬ በከንቱ ተፅናናሁ፡፡ ከዚያም ደሞ ሌላ ሀሳብ መጣልኝ፡፡ በቃ ባልተጠበቀ ጊዜ የሚነሳ የሚጥል በሽታ አይነት ያደረበት ወይም የሆነ በፍርሃትና ጥርጣሬ የሚንጥ ክፉ መንፈስ የተጠናወተው ንክ ሰው መስዬ እንደምታያቸው ተስፋ አደረግሁ፡፡ በእርግጥም ነገረ ስራዬ እንደዚያ ነበር፡፡
ገንዘብ ከፋዩ ብሩን ሊከፍለኝ እያዘጋጀ…
“እሺ እንዴት እንዲሆንልህ ነው የምትፈልገው?” ሲል ጠየቀኝ
“ማለት?”
“ድፍን ይሁንልህ ወይስ ዝርዝር?”
አሀ! ማለት የፈለገው ገብቶኛል፡፡ እናም ጊዜ ሳላጠፋ፤
“ሃምሳ ብሩ ድፍን ይሁንልኝ” አልኩት
ድፍን ሃምሳ ብር ሰጠኝ፡፡
“አምስት ብሩም ... ድፍን ይሁንልኝ”
ገንዘብ ከፋዩ፤ ድፍን አምስት ብር ጨመረልኝና ከባንክ ቤቱ ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡ ትልቁ ተንሸራታች በር ከጀርባዬ ጥርቅም ብሎ ሲዘጋ፣ የባንክ ቤቱን ጣሪያ የሚነካ የሳቅ ፍንዳታ ተሰማኝ፡፡ በቃ! ከዚያን ጊዜ ወዲህ የባንክ ቤት አገልግሎት ተጠቃሚነቱን እርም ብዬ ተውኩት… ተውኩት… ተውኩት፡፡ የቀን ወጪ ዝርዝር ብሮቼን በኪሴ፤ እንደ ወረቀት የሚንቋቁ ተቀማጭ ድፍን ባውንዶቼን ደሞ በካልሲ ውስጥ ነው የማጠራቅመው፡፡

Read 3295 times