Saturday, 12 October 2013 13:30

..ለእናቶች ጤና ... ያለውን ዘዴ በሙሉ.....

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

            ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም በኢፊድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀውን የፊጎ አፍሪካ የመጀመሪያ አህጉራዊ ስብሰባ በዘጉበት ወቅት የተናገሩትን አባባል ነበር ለርእስነት የመረጥነው፡፡ ከ67/ አገራት የተውጣጡ ወደ ስምንት መቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች የታደሙበት ስብሰባ ሲጠናቀቅ ዶ/ር ዎድሮስ የስብሰባውን በስኬት መጠናቀቅና የአባላቱን ጥረት ካደነቁ በሁዋላ ወደምእተ አመቱ የልማት ግብ ስኬት ነበር ንግግራቸው ያመራው፡፡
እ.ኤ.አ እስከ 2015/ዓም አለም እንድትከውናቸው የሚፈለጉ ግቦች በስምንት የተከፈሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ቁጥር 4/ ከአምስት አመት በታች ያሉትን ልጆች ሞት መቀነስ ሲሆን ቁጥር 5/ ደግሞ የእናቶችን ጤና ማሻሻል የሚል ነው። የልጆችን ሞት መቀነስ የሚለው ስሌት 2/3ኛ ያህል ሲሆን በዚህም በኢትዮጵያ ጥሩ ውጤት እንደተመዘገበና የእናቶች ሞት ደግሞ በ3/4ኛ እንዲቀንስ ጥረት በመደረግ ላይ ቢሆንም እስከአሁን ግን ከትክክለኛው መስመር ላይ አለመደረሱን ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርመሑሀ ፣የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህራት ፌደሬሽንሑሀ፣ የአለም አቀፉ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበራት ፌደሬሽንህሀሑ እና የመሳሰሉት የህክምና ባለሙያዎች ማህበራት ሐገር እንዲሁም ህብረተሰቡ ብዙ እንደሚጠብቅ አውቀው በቀረው ጊዜ አስፈላጊውን እርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም፡፡
የምእተ አመቱን ግብ ለመምታት እንደ ዶ/ር ዎድሮስ ማብራሪያ ሙያው ሊተገበር የሚችልበትን ዘዴ አሟጦ መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ የህክምናው አገልግሎት እና እርዳታ ፈላጊ እናቶች የሚገናኙበ ትን ዘዴ በተገቢው መቀየስና በቅያሱ መሰረት እዚህ ቀረሽ ሳይባል ማከናወን ከተቻለ ከሚጠበቀው ግብ መድረስ ቀላል ነው፡፡
በኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት ከመቀነስ አኩዋያ እንደጥሩ ምሳሌ የሚቆጠረው በትብብር የመስራት አቅምን ማጎልበት ነው፡፡ ከዚህም አኩዋያ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር በመተባበር በተለይም ከዋና ከተሞች ራቅ ባሉ ስፍራዎች የሚገኙ ሐኪሞችን የማሰልጠን ስራ እየሰራ መሆኑ ብዙ ችግሮ ችን ለማቃለል አስችሎአል፡፡ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ከተጠቃሚው ሕብረተ ሰብ ቁጥር ጋር የማይነጻጸር ቢሆንም የጠቅላላ ሐኪሞችን እና በተመሳሳይ በገጠር ሆስ ፒታሎች የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ትምህርቱን በስልጠና በማግኘታቸው አፋ ጣኝ የሆነ ውን የማዋለድ ስራ በቀዶ ሕክምና ጭምር እያገዙ ውጤ ታማ የሆነ ስራ እንዲሰራ በማስቻሉ የሚበረታታ እና የሚመሰገን ተግባር ነው ብለዋል ዶ/ር ዎድሮስ አድሀኖም የኢፊድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡
በስተመጨረሻም ዶ/ር ዎሮስ እንደአሉት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የመላው አፍሪካም ጭምር ከተማ በመሆንዋ የአፍሪካ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህራት ፌደሬሽን ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት ቢፈልግ የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል ፡፡
የፊጎ አፍሪካ የመጀመሪያው ስብሰባ በተካሄደባቸው ቀናት ከመስከረም 22-25 ድረስ የስብ ሰባው ተሳታፊዎች በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ለጉብኝትና ለግብይት የተንቀሳቀሱ ሲሆን ከእነዚህም መሀከል ሐምሊን ኢትዮጵያ ፊስቱላ ሆስፒታል አንዱ ነበር፡፡ ጎብኝዎች በየቀኑ በአንድ ጊዜ አርባ ያህል እየሆኑ እንደፍላጎታቸው ይጎበኙ የነበረ ሲሆን የአንዱን ቡድን ጉብኝት የዚህ አምድ አዘጋጅ ተሳትፋለች፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ሐምሊን ኢትዮጵያ ፊስቱላ ሆስፒታል ማለት ማን እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን አንባቢ ዎችም እንዲያስታውሱት ያህል በመጠኑ ቀንጨብ እናደርጋለን፡፡
ሐምሊን ኢትዮያ ፊስቱላ ሆስፒታል የተቋቋመው የዛሬ 53/ አመት ገደማ ባልና ሚስቱ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ዶ/ር ሄግ እና ካትሪን ሐምሊን በቀየሱት ዘዴ መነሻ ነት ነው፡፡ እነዚህ ባልና ሚስት ወደኢትዮጵያ ለስራ በመጡበት ወቅት ከስራቸው ጎን ለጎን ሁኔታዎችን ሲመለከቱ በኢትዮያ ብዙ በፊስቱል የተጎዱ ሴቶች በቂ ሕክምና እና ድጋፍ ሳያገኙ እንደሚቀሩ እና ምን ያክል በቤተሰቦቻቸው መገለል እንደሚደርስባቸው በመመልከታቸው እነዚህን ሴቶች መደገፍ ይገባናል ሲሉ ይወስናሉ፡፡ ከዚህም መነሻነት ሆስፒታሉ አገልግሎቱን እያስፋፋ በአሁኑ ወቅት በአምስት መስተዳድሮች ቅርንጫፎችን በመክፈት እናቶች በአቅራቢያቸው ሳይንገላቱ እንዲታከሙ ማድረግ ችሎአል።

የፊስቱላ ሆስፒታል ቅርንጫፍ የሚገኝባቸው አካባቢዎችም መቀሌ ፣ይርጋለም ፣ሐረር ፣ባህርዳር እና መቱ ናቸው፡፡
ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ሕመማቸው ለጠናባቸው እና ታክመው ወደቤተ ሰቦቻቸው መመለስ ለማይችሉት እንዲሁም ከህክምናው መራቅ የሌለባቸውን ሴቶች የተለያየ ስልጠና እየሰጠ ስራ ሰርተው እንዲተዳደሩ የሚችሉበት ከአዲስ አበባ 17/ኪሎ ሜትር ታጠቅ ከሚባለው አካባቢ የደስታ መንደር በሚል ስያሜ አንድ ትልቅ መንደር ከፍቶ እንዲያገግሙ የማገገሚያ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
የፊስቱላን ሕመም ለመከላከል እንዲቻልም እያንዳንዱዋ እናት በተማረ የሰው ኃይል አማካኝነት ካለችበት አካባቢ ሳትርቅ በሕክምና እየተረዳች ልጅ እንድትወልድ ለማስቻል የሚረዳ አንድ ኮሌጅ በመክፈት አዋላጅ ነርሶችን በማስተማር በዲግሪ እያስመረቀ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ባለሙያዎችንም በስልጠና ያግዛል፡፡
ከጎብኝዎች የተገኘውን አስተያየት ወደ አማርኛ መልሰን ለአንባቢዎች እንላለን፡፡
“...እኔ ታቦኒ እባላለሁ፡፡ የመጣሁት ከኒውዝላንድ ነው። ዜግነ ግን ዚምባቡዌ ነው፡፡ እንደሐምሊን ኢትዮጵያ ፊስቱላ ሆስፒታል አይነት አገልግሎት የትም ሐገር ሄጄ አላጋጠመኝም፡፡ እንደዚህ አይነት አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም እስከአሁን ድረስ አላየሁም፡፡ እጅግ አስደሳች ነው፡፡ ልክ በታሪክ የማዳምጠው እንጂ በዚህ ጊዜ በአይኔ የምመለከተው አልመሰለኝም፡፡ ለእኔ ብዙ ሀሳብ ሰጥቶኛል፡፡ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ እንደመሆኔ ይህ አይነት አገልግሎት በሀገሬ ዚምባቡዌ እንዲሰጥ የበኩሌን እጥራለሁ...”
                                            -----///------
“...እኔ ኢማን አቡጋጃ እባላለሁ፡፡ በዜግነት ሱዳናዊት ስሆን የምሰራው ግን በዩኬ ነው፡፡ እኔ በሕይወ ካየሁዋቸው ተቋማት የሚበልጥ በጣም አርኪ የሆነ ስራ የሚሰራበት ግሩም ሆስፒታል ነው፡፡ ለእናቶች አገልግሎት የሚሰጡ እንደዚህ ያሉ የህክምና ተቋማት በአፍሪካ በብዛት ቢኖሩ ኖሮ ለብዙዎች መፍትሔ በሆነ ነበር፡፡ የእናቶችን ጤና ከማሻሻል አንጻርም ብዙ ውጤት በተመዘገበ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ አላየሁም፡፡ ዶ/ር ሐምሊንን አግኝቻቸው ነበር፡፡ ያልኩዋቸው ነገር ቢኖር... እርግጠኛ ነኝ እስከአሁን ከታካሚዎችዎም ሆነ ከጎብኝዎችዎ ብዙ ምስጋናና ሙገሳን አግኝተዋል ፡፡ እኔ የምጨምረው ብዙም ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እድለኛ የሆኑ ታላቅ ሴት ነዎት ማለት እፈልጋለሁ፡፡ እራስዎን ለሌ ሎች አሳልፈው የሰጡ እና ትልቅ መስዋእትነትን የከፈሉ ነዎት ፡፡ ልዩ ክብር እና ምስጋና ይገባዎታል፡፡ አምሳያም የለዎትም ነበር ያልኩዋቸው። ከዚህ ሆስፒታል ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ እኔን ጨምሮ ሌሎቹም ምሳሌነቱን ለመከተል ለራሳችን ቃል ገብተናል...”
                                                   -----///------
“...እኔ ናይጄሪያዊ ነኝ ፡፡ በሙያዬም የጽንስና ማህጸን ሐኪም ነኝ፡፡ በቃ... እኔ ለዚህ የምሰጠው አስተያየት ...እራስን መርሳት ...ብዬ ነው፡፡ በዚህ ሆስፒታል የሚሰሩት በተለይም ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በጭራሽ እራሳቸውን እረስተው ብዙ ዜጎቻችሁን ከሞት ወደ ሕይወት መልሰዋል፡፡ እጅግ ያስደንቃል። በአሁኑ ሰአት ሆስፒታሉን በመጎብኘት ላይ ያለነው ሁላችንም በአንድ መንፈስ ነው እርካታችንን የገለጽነው፡፡ እሳቸውንና የሆስፒታሉን ሰራተኞች በሙሉ እግዚአብሄር ይባር ካቸው እላለሁ ፡፡ ይህ ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እናቶችን ለማዳን ይህንን አይነት ከባድ ስራ ሲሰራ ከማየት በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ “
                                                             ------///------
ከላይ ያነበባችሁት የጎብኝዎች አስተያየት ነበር፡፡ የሀምሊን ኢትዮጵያ ፊስቱላ ሆስፒታል ወደ 150/ አልጋ ያለው ሲሆን በመላው ቅርንጫፎች ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ተዳምሮ በአመት ወደ 3/ ሶስት ሺህ ለሚሆኑ ሴቶች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ባለቤታቸው በህይወት ባይኖሩም እሳቸው ግን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እስከአሁን ድረስ ሕመምተኞችን የማከምና የማዳን ስራቸውን ቀጥለዋል፡፡
የፊጎ አፍሪካ የመጀመሪያው አህጉራዊ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ሳይንሳዊ መረጃዎች ለውይይት ቀርበው ነበር፡፡

Read 2864 times