Saturday, 19 October 2013 11:57

“ልብ አድርጉልኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ዝም የሚል ሰው አለ። የማያውቅ ሆኖ ዝም የሚልም አለ፣ እያወቀ ጊዜ እስኪያገኝለት የማይናገርም አለ፡፡” ይቺ አባባል ከታላቁ መጽሐፍ ላይ የተገኘች ነች፡፡
እናላችሁ…ነገርዬው ሁሉ ጭጭ ምጭጭ ያለ አይመስላችሁም! ሰዋችን ‘ዝም’ ብሏል፡፡ ታዲያማ…ዝም ማለት ግን ነገሩ ሁሉ ‘አልጋ በአልጋ’ ስለሆነ… ህይወት ‘ዓለም ዘጠኝ’ ስለሆነች… “እሰይ ስለቴ ሰመረ…” የሚባልለት ዘመን ስለመጣ ምናምን አይደለም፡፡ ሰዋችን…አለ አይደል…ዝምም ብሎ ድምጽ ሳይወጣውም፣ “ያዙኝ ለቀቁኝ” እያለ ለያዥ ለገናዥ ሳያስቸግር፣ ደረቱን ሳይደልቅ፣ ፊቱን ሳይቧጭር፣ ጸጉሩን ሳይነጭ… በሙሉ ጸጥታም “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም ጨዋታ ያነሳው የለ…ለምን እንደሆነ እንጃ እንጂ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…እዚህ አገር…አለ አይደል… ከዕድር ዳኝነትና ዕቁብ ሰብሳቢነት ጀምሮ ያሉ ‘ወንበሮች’ ሁሉ የ“እኔ ከሞትኩ…” ምናምን አይነት ሶፍትዌር የተገጠመላቸው ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ… አንዳንድ ቦታ የምናየው እብሪት ቀላል ነው እንዴ! (“እኛም አንድ ሰሞን እንዲሀ አድርጎን ነበር…” የሚለው ነገር የሞባይል ‘ኮምልሰሪ ሪንግቶን’ ይሁንልንማ! የምር እኮ…አለ አይደል… “ለእኛ የተደረገውን እጥፍ ለሌላው ያድርግለት…” አይነት ነገር የሚል ‘ባለ ወንበር’ እየናፈቀን ነው፡፡ እናላችሁ…“በጥፍሬም፣ በጥርሴም ወንበሬን አላስነካም…” ባይ ሲበዛበት ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ክፋቱ ምን መሰላችሁ…መጀመሪያ ሲቀመጡበት ስፖንጅ በስፖንጅ የነበረው አንዳንድ ወንበር ሳይታሰብ ‘አስፈንጥሮ ሲጥል’ እንጂ ‘አስፈንጣሪ ስፕሪንግ’ እንዳለው የሚታወቀው ኋላ መሆኑ!
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አይደለም የአገሩንና የዓለምን ታሪክ ሊያነብ…አለ አይደል…የ‘ተንኮለኛው ከበደን ታሪክ’ እንኳን የማያውቅ የእኔ ቢጤ “ፍየል ከመድረሷ…” በአገር ታሪክ ሲሳለቅ፣ እንደ ወር ወጪው የአገርን ታሪክ ቁጥር ሲቀንስና ሲያቀናንስ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ደምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ሌላ ደግሞ አለላችሁ…ነገ አልመች ሲለው ትቶ ውልቅ የሚለው፣ ነገ የሚሰጠው ድርጎ ሲያንስበት ከፍ አድርጎ ድርጐ ለሚሰጥ ሌላ ጌታ ለማገለገል በጨረታው የማይገደደው…አሁን “የምናምኖች መጠራቀሚያ…” እያለ ወደሚሰደድባት አገር ‘ሽል’ ብሎ ወይ የሚነግድ ወይ ምናምኖች ሲላቸው የከረማቸውን “ፉርሽ ባትሉኝ…” የሚለው ሁሉ…አለ አይደል…“ታራለህ ትደብናለህ፣ ታዲያ ምን አባክ ትሆናለህ…” አይነት ማን አለብኝነት ኑሮውን የምድር ገሀነም ሲያደርግበት… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ከአንድ ጥግ አንድ ጥግ እንደ ኳስ ሲያጦዙት ከርመው…ሣር የነበረላቸው ነገር ወደ ድርቆሽ መለወጥ ሲጀምር ሽል ሲሉ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
እናላችሁ…እንደ ትናንትና፣ እንደ ትናንት ወዲያ አገር “የባለ አገሯ…” መሆኗ እየቀረ እምነቱ ላይ ሲዘባበቱበት፣ የከበረ ባህሉ ላይ በ‘ግሎባላይዜሽን’ና ‘ወዳጆችን ባለማስቀየም’ ሰበብ ለሚጠየፋቸው ልማዶች እንዲጋለጥ ሲያደርጉት፣ በእሱነቱ ‘ሙድ ሲይዙበት’ (ቂ…ቂ…ቂ…)…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስሙኝማ፣ እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ አለችኝማ!…ምንም እንኳን ወደየምግብ ቤቱ በሩብ ዓመትም ቢሆን ብቅ የሚያደርግ አቅም ከጠፋ ቢከራርምም አልፎ፣ አልፎ እንደ አቅሚቲ ያለውን ተጠግቶም ቢሆን ብቅ ማለት አይቀርም፡፡ ታዲያላችሁ እዛም “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብል ነገር መአት ነው፡፡
ታዲያማ…ሀሳብ አለን፣ አንዳንድ ምግብ ቤት በር ላይ የድንጋይ መፍጫ ማሽን ይቁምልንማ! አሀ…ልክ እኮ ‘ሞቶም ችኮነቱ ያልለቀቀው’ በሬ… “መንጋጋህ ይድከመው እንጂ በቀላሉማ ታፋዬን አታኝካትም…” የሚል ይመስል የሚታኘክ ሳይሆን የሚፈጭ ሥጋ እየቀረበልን ተቸገርና!
እናማ…የድንጋይ መፍጫ ‘ስታንድባይ’ ይሁንልን፡፡ ልክ ነዋ… እንደ ‘ፉድ አምቡላንስ’ ነገር ሆኖ ሊያገለግለን ይችላላ! የምር እኮ…አንዳንድ ጊዜ ከወጡ ውስጥ በመከራ ጠልፋችሁ የጎረሳችሁት ቁራጭ ሥጋ አፋችሁ ውስጥ ሦስት መቶ ስድሳ ዲግሪ አሽከርክራችሁትም ወይ ፍንክች! “ይሄ ሥጋ ከየትኛው እንስሳ እንደተገኘ አንድዬ ይወቀው…” ብትሉ አይፈረድባችሁም፡፡ እኔ የምለው… የሀበሻ በሬዎች እንደ እኛ የሀበሻ ሰዎች ነገራቸው ሁሉ መነቸከ ማለት ነው!
ስሙኝማ…እዚህ አገር “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብል ነገር እንዴት እንደበዛ የምታወቁት ምን የመሰለው ሬስቱራንት ውስጥ የምግባችሁን መቅረብ3 ተከትሎ እግራችሁ ስር የስፔንን ተዋጊ ኮርማዎች የሚያስንቅ ድመት ብቅ ብሎ ይገላምጣችኋል! “እኔ እዚህ ቅንጣቢ የሚጥልልኝ አጥቻለሁ አንተ ገንዘብ አለህና አሮስቶ ስትውጥ የድመት አምላክ አይታዘብህም!” ብሎ የሚዝትባችሁ ነው የሚመስለው፡፡…ነው ወይስ ሼፉ እንዲሰልል ልኮት ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
ታዲያላችሁ… እንግዲህም ጨዋታም አይደል… “ቀን የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል…” የሚለውን አባባል የሚያረጋግጡ፣ “ጌታዋን የተማመነች በቅሎ…” የሚለውን አባባል እውነት የሚያደርጉ፣ ላላስነጠሰው ባለስልጣንና ባለሀብት መሀረብ የሚያቀርቡ እህል እንደሚፈጅ ተምች በዙሪያው እየፈሉ ሲሄዱ… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
በዕውቀትና በ‘ሜሪት’ ስልጣን ሳይሆን…በ‘ድርጎ ስልጣን’ ለዓይንም መከታተል በሚያስቸግር ፍጥነት ወደላይ እየተተኮሱ…የመንግሥተ ሰማያትን ዙፋን የተቆጣጠሩ ይመስል አይደለም ሌላ ሌላውን… የተፈጥሮ መብቶቹን እንኳን ሰጪና ነጣቂ ሲሆኑበት ….ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
“ይህንን ብታደርግ በዚህና በዚህ እናግዝሀለን…” ከማለት ይልቅ…“ይሄን ብታደርግ ውርድ ከራሴ…” አይነት “መች ተዋጋና ገና ነው ገና…” ማለት የሚቃጣቸው ግለሰቦችና ተቋማት ሲበዙበት “መሽናት ክልክል ነው” ከሚል ይልቅ “ትሸናና ትሸነሸናነህ!” የሚሉ ሚጢጢ ጉልበተኞች እየበዙ ሲሄዱ፣ መመሪያዎች፣ ዘጋቢ ፕሮግራሞች ምናምን… “ፈቀድን!” ከሚለው ይልቅ “ከለከልን!” ወደሚለው ትርጉም ሲያዘነብሉ…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስንትና ስንት የሚያኮሩ ልምዶችና እሴቶች እንደ ሌሉት ሁሉ… “ከእከሌ የወሰድነው…” “ከእነ እከሌ የቀዳነው…” እየተባለ የ‘ፈረንጅ ፍርፋሪ’ ለቃሚ ሲያስመስሉት…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
በ‘አፈ ቅቤውም’ በ‘አፈ ኮምጣጤውም’ የዘለፋ ናዳ የሚወርድባቸው የቀድሞ ዘመን ነገሥታት… አለ አይደል… “ሁሉንም ነገር አደረግናላችሁ፣ አፈራችንን ግን ይዛችሁ አትሄዱም…” አይነት ነገር እያሉ ጫማ እያሳጠቡ መርከብ ላይ እዳላሳፈሩ ሁሉ…ዛሬ በየቦታው ‘ቅድሚያ ለነጭ’ አይነት ነገር እየበዛበት፣ ጭርሱን “ለፈረንጅ ጫማውን ብታብጥለትስ ምን አለበት…” ሊባል ምንም ያልቀረን ሲመስል…ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
አንዳንድ ቦታ በችሎታ ሳይሆን በመጠሪያ ስሙ ብቻ ማንነት ‘እየተበጀለት’ ብቁ ለሆነበት ቦታ ሁሉ “ብቁ አይደለህም…” ሲባል፣ በሠለጠነበትና የሥራ ልምድ ባካበተበት ቦታ ሳይሆን…አለ አይደል… በተወለደበት ስፍራ ሲመዘን… ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” እያለ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የስም ነገር የምር አስቸጋሪ ነው። ምን መሰላችሁ…አንዳንድ እዚቹ አገር በሚገኙ ስፍራዎች አገልግሎት ለማግኘት ስም እስከ አያት ድረስ ይጠየቃል የሚባል ነገር አለ፡፡ መቼም ጉዳችን ተወርቶ አያልቅ!
እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝ… አንድ ጊዜ አንድ በ‘ተጨማሪ ሰዓት’ ሊንቀሳቀስ እየተቃረበ የነበረ ወዳጄ የሆነች እንትናዬ ላይ…በትኩሶቹ ቋንቋ… ‘ጆፌ ጥሎ’ ሲያንዣብብ ይከርምና ሊሳካለት ጫፍ ይደርሳል፡፡ ታዲያላችሁ…ይሄን ሁሉ ጊዜ የሚያውቀው ዋናውን ስሟን ሳይሆን ‘ባክአፕ’ መጠሪያዋን ነው፡፡
ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እውነተኛ ስሟ ከሦስተኛ ወገን ይነገረዋል፡፡ መጥቶ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው…“አንተ ያቺ እንትና ስሟ እንትና ነው እንዴ!” አለላችሁና…በቃ የፕሮጀክት ትግበራውን አቆመዋ! እዚህ ደረጃ መድረሳችን በጣም አያሳዝንም!
ሰዋችን ዝም ብሎ እያየ ያለ ድምጽ “ልብ አድርጉልኝ!” የሚያስብሉት ነገሮች የሚቀንሱበትን ዘመን አንድዬ ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3194 times