Saturday, 19 October 2013 11:59

የቆላ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ተመረቀ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲና ሄይንሪች ሄይን በተባለ ጀርመናዊ ዩኒቨርስቲ ትብብር በአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ የተሰራው የቆላ በሽታዎች ምርምር ማዕከል ባለፈው ረቡዕ ተመረቀ፡፡
Institute of Research for Tropical Infectious Disease የተባለው የምርምር ማዕከል፤ በጀርመን ዩኒቨርስቲ የገንዘብ ድጋፍ ተሰርቶና ሙሉ የመገልገያ ቁሳቁሶቹ ተሟልተውለት ለምረቃ በቅቷል፡፡
በአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ በተከናወነው የማዕከሉ የምረቃ ስነስርዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የአሰላ ጤና ሳይንሶች ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ዶ/ር ለገሰ ታደሰ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በጀርመናዊው ዩኒቨርስቲ የማቴሪያል፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚንቀሳቀስና ዘመናዊ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚካሄዱበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የህክምና ሙያ በምርምር መታገዝ አለበት ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ደረጃውን በጠበቁ የምርምር መሳሪያዎችና የላብራቶሪ ዕቃዎች የተሟላው ማዕከሉ፤ ዩኒቨርስቲው እየሰጠ ያለውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ለማገዝና በህክምና ሙያ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡
በማዕከሉ በተለይም በቆላ በሽታዎችና (ካላዘር፣ የቆዳ በሽታና ወባ) በጉበት በሽታ ላይ ትኩረት ያደረገ ምርምር የሚካሄድ ሲሆን እንደኤችአይቪ ፣የሳንባ ነቀርሳና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎችን በተመለከተም ምርመራና ጥናት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የአሰላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስር ተቋቁሞ በጤና ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎችን እየተቀበለ የሚያሰለጥን ሲሆን ከመጀመሪያ ዙር ሰልጣኞች መካከል 90 የሚሆኑትን በቅርቡ አስመርቋል። በአሁኑ ወቅት አንድ ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎችን መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ የሚገኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡

Read 2856 times