Saturday, 26 October 2013 14:25

Medical Abortion …70% ለሚሆኑት ምርጫቸው ሆኖአል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(7 votes)

ሴቶች በአለም ዙሪያ ጽንስን ማቋረጥ የጀመሩት እንዲህ እንደዛሬው በሳይንሳዊው መንገድ ሳይሆን በግላቸው የየራሳቸውን ጥረት በማድረግ እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶች እርስ በእርሳቸው በመረዳዳት አንዱዋ የአንዱዋን ጽንስ ለማቋረጥ ባህላዊ ዘዴዎችን በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ እ.ኤ.አ እስከ 1800/ድረስ እንደቀጠሉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን በጊዜው ጽዳቱ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጽንስን የማቋረጥ ሂደት ብዙ ሴቶችን ለህልፈት ይዳርግ ስለነበር በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች ትኩረትን አግኝቶ ህገወጥ ጽንስን ማቋረጥ እንዲቆም የተቻለውን ያህል ጥረት ተደርጎ አል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደየሀገራቱ አሰራር በተለያየ ጊዜ ቢሆንም በአብዛኛው የአለማችን ክፍሎች ጽንስን ማቋረጥ በህጋዊ መንገድ እንዲሆን ተደርጎአል፡፡ ኢትዮጵያም በ1996 ዓ/ም ጽንስን ማቋረጥ በህግ እንዲደገፍ የራስዋን ድንጋጌ አውጥታለች።
African network for medical abortion የሚባል ድርጅት በአሁኑ ወቅት በጽንስ ማቋረጥ ዙሪያ በአፍሪካ በጋራ ስራ ለመስራት የተቋቋመ ሲሆን የዚህ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪም ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአ.አ. ዩኒቨርሲቲ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ከፍል ትምህርት ክፍል ሀላፊ ናቸው፡፡ ዶ/ር እስክንድር ከበደ የኢሶግ ቦርድ ዋና ጸሐፊና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
African network for medical abortion (ANMA) የሚባለው ድርጅት ምን የሚሰራ ነው?
Medical Abortion ማለት ምን ማለት ነው?
ከሚሉት በመነሳት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዶ/ር እስክንድር ከበደ ማብራሪያቸውን ለዚህ አምድ ሰጥተውል፡፡
ጥ/ Medical Abortion (ሜዲካል አቦርሽን) ሲባል ምንን የሚያመለክት ነው?
መ/ Medical Abortion ሜዲካል አቦርሽን ማለት ውርጃ በህጋዊው መንገድ ጥራቱን እና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ መፈጽም ካለበት ቀደም ባለው ጊዜ በተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ መድሀኒት በመለወጥ ጽንስን ማቋረጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራቅ ካለው ዘመን ጀምሮ መድሀኒትን ለጽንስ ማቋረጫነት መጠቀም የጀመረ ቢሆንም እንኩዋን ውጤታማ በሆነና በተሳካ መንገድ በህክምና ባለሙያዎች በመሰጠት ስራ ላይ የዋለው ከሀያ አምስት አመታት ወዲህ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ የሆነው መድሀኒትም የተገኘው በፈረንሳይ አገር ተመራማሪዎች ሲሆን እሱም እ.ኤ.አ በ1970 እና 80/ዎቹ አካባቢ የተሰራ ነው፡፡ በሕክምናው ዘርፍም የመጀመሪያው ሙከራ የተደረገው በጄኔቭ እ.ኤ.አ በ1981 ዓ/ም ነው፡፡ በ1988 ፈረንሳይ መድሀኒቱን ፈቃድ በመስጠት የመጀመሪያ ሀገር በመሆን ጥቅም ላይ ያዋለች ሲሆን ከዚያም በተለያዩ ሀገራት እየተስፋፋ መጥቶ በኢትዮጵያም በ2008/ ዓ/ም ፈቃድ አግኝቶአል። በአሁኑ ጊዜም ከ40/የሚበልጡ ሀገሮች መድሀኒቱን የሚጠቀሙበት ሲሆን የአለም የጤና ድርጅትም እ.ኤ.አ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ መድሀኒቶቹን ለጽንስ ማቋረጫነት እንዲያገለግሉ ሀሳብ ያጋራል፡፡ መድሀኒቶቹ Misopostol and mifepristone በመባል ይታወቃሉ፡፡
ጥ/ African network for medical abortion … ANMA ምን የሚሰራ ድርጅት ነው?
መ/ African network for medical abortion በምህጻረ ቃሉ ANMA ¾ሚባለው እ.ኤ.አ በ2010/ዓ/ም ሊዝበን ላይ በተደረገ አለምአቀፍ ስብሰባ ጽንስን በማቅዋረጥ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች በተለየ መልኩ የሜዲካልን አቦርሽን በስፋት ስራ ላይ እንዲውል በማስተማር በኩል እንዲሰራ ለተቋቋመው ድርጅት አካል የሆነ በአፍሪካ የተቁዋቁዋመ ድርጅት ነው፡፡ ANMA የመጀመሪያው ስራው ያደረገው በአለም የጤና ድርጅት የተነደፈው መመሪያ ላይ በመሳተፍ ሐኪሞችን በማሰልጠን እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሀገራት ሜዲካል አቦርሽንን እንደአማራጭ እንዲጠቀሙበት ማስተዋወቅና መድሀ ኒቱም ፈቃድ ተሰጥቶት እንዲመዘገብና በየሀገሩም ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡
ጥ/ በኢትዮጵያ በANMA አሰራር ምን ለማድረግ ታስቦአል?
መ/ በኢትዮጵያ አስቀድሞውኑም ጽንስን በማቋረጥ ረገድ ህግን ከማውጣት እና ከመተግበር ጀምሮ ብዙ የተሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጽንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ ይከሰቱ የነበሩ የህይወትም ሆነ የአካል ጉዳቶች በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ ነገር ገን አሁንም ሙሉ በሙሉ ችግሩ ተቀርፎአል ማለት ስለማይቻል በቀጣይነት የሚሰሩ ስራዎች በእቅድ ተይዘዋል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በመቀጠል ለማድረግ የታሰበው የህክምና ባለሙያዎችን በአዲሱ የአለም የጤና ድርጅት መመሪያ ጋይድ መሰረት ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር በመተባበር ማሰልጠን ነው፡፡ በሁለተኛም ደረጃ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት የስራ መደራረብ እንዳይኖር ወይንም አንዱ የሚ ሰራውን ሌላው እንዳይደግመው እና ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንዲኖር ለማስተዋወቅ ታስቦአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሜዲካል አቦርሽን ላይ ያልታዩ ወይንም ያልታወቁ ነገሮች ካሉ ለማሳየት የሚያስችል ጥናት ማድረግ ከእቅዶች መካከል ናቸው፡፡
ጥ/ Medical Abortion ሜዲካል አቦርሽን በሀገራችን ስራ ላይ ውሎአልን?
መ/ Medical Abortion (ሜዲካል አቦርሽን በሀገራችን እ.ኤ.አ ከ2008/ዓ/ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለ አሰራር ነው፡፡ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች በህግ ለተፈቀደ የውርጃ አገልግሎት እንዲሁም በመንግስት የጤና ተቀዋማት ውስጥ በመድሀኒት መጠቀምን ተግ ባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ እንዲያውም በዘርፉ እንደ አንድ አስገራሚ ሁኔታ የታየው ተጠ ቃሚዎች ውርጃን በሕክምና መሳሪያ ከሚሰራላቸው ይልቅ በመድሀኒት እንዲሆን በአብ ዛኛው ምርጫ ቸው በማድረጋቸው ነው። በአለፈው አመት በተደረገው ጥናት እንደተረ ጋገጠው በአሁኑ ሰአት ውርጃ እንዲሰራላቸው ከሚመጡ ሴቶች የምክር አገል ግሎት በሚሰጣቸው ጊዜ በመድ ሀኒቱ መጠቀምን የሚሹት ወደ 70% ደርሰዋል። ስለሆነም ውርጃን በመሳሪያ አማካ ኝነት መስራትን በጣም ቀንሶታል፡፡ በእርግጥ አን ዳንድ ቦታ ዎች የአቅርቦት እጥረት የሚታይ ሲሆን ይህም በጊዜ ሂደት ከሚሻሻሉት መካከል ነው፡፡
ጥ/ በመድሀኒት አማካኝነት ጽንስን ማቋረጥ እስከ ስንተኛው ወር ድረስ ይቻላል?
መ/ መድሀኒቶቹ Misopostol and mifepristone የተባሉ ሁለት መድሀኒቶች ናቸው፡፡ ሁለቱን መድሀኒቶች በአንድ ላይ በምንጠቀምበት ጊዜ እርግዝናው ከመጨረሻው የወር አበባ እስከ 49/ ቀን ወይንም እስከ 7/ ሳምንት ድረስ ከሆነ 95% ለሚሆነ ሴቶች ውጤታማ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህንን መድሀኒት የወሰዱ ሴቶች ወደ ሆስፒታልም ሳይመለሱ ልክ እንደየወር አበባ ቀስ በቀስ እየተቆጣጠሩ ሊወገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን 5% የሚሆኑት ሴቶች ውርጃው በትክክል ሂደቱን ላያሟላና በማህጸን ውስጥ ሊቀር ስለሚችል በተቀ ጠሩበት ቀን ወደ ጤና ባለሙያው በመቅረብ በመሳሪያ የታገዘ አገልግሎትን እንዲያገኙ ግድ ይሆናል፡፡
ጥ/ ከ49/ ቀን ወይንም ከሰባት ሳምንት በሁዋላስ ውርጃው በምን መልክ ይሆናል?
መ/ በሀገራችን ህግ መሰረት ውርጃ የሚባለው እስከ 28ኛው ሳምንት ድረስ ነው፡፡ ነገር ግን ቀኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተጉዋዳኝ ችግሮቹ እየበዙ ስለሚሄዱ ውርጃን ማካሄድ አይመከርም፡፡ ሆኖም ባልታወቁ ምክንያቶች ችግር ደርሶ ከሆነ ፣ወይንም በተፈጥሮአዊ ሁኔታ ውርጃውን ማድረግ ግድ ከሆነ፣ ህጉ እየፈቀደላቸው አገልግሎቱን ሳያገኙ ቀርተው ከሆነ በትልልቅ ሆስፒታሎች እና ስልጠናውን በወሰዱ ሐኪሞች አማካ ኝነት ብቻ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ውጭ የእርግዝናወ ጊዜ ከፍ ያለ ጽንስና ለማቋረጥ በክሊኒኮች ወይንም በጤና ጣቢያዎች አገልግሎቱ ሊሰጥ አይችልም፡፡ በእርግጥ Misopostol and mifepristone የተባሉት መድሀኒቶች በዚህ ደረጃ ላሉ እርግዝናዎች ለጊዜው አገልግሎት ባይ ሰጡም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚገልጹት ግን በመሳሪያ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ነው፡፡ በአጠቃላይም በአፍሪካው ኔትወርክ አማካኝነት ለመስራት የታሰበው በተለያዩ ቦታዎች በተንጠባጠበ እና በተደጋጋሚ የሚሰሩትን ስራ ዎች በተቀናጀ መልክ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በአንድነት በትብብር ለመስራት መድረኩን ለመፍ ጠር ነው፡፡ በዚህም ተጠቃሚው ህብረተሰብ የሰመረ አገልግሎትን ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ፣አላን ጉትማቸር እና አለምአቀፉ የቤተሰብ መምሪያ እኤአ/ በ2009 ዓ/ም ያወጡት መረጃ ጽንስን ማቁዋረጥ በአለማችን ምን ገጽታ እንዳለው ያሳያል፡፡
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በየአመቱ ከሰባ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ የሚደርሱ እናቶች በአለም ይሞታሉ፡፡
ከጠቅላላው የእናቶች ሞት ከ13-20% የሚሆኑት የሚከሰቱት በህገወጥ ጽንስ ማቋረጥ ነው፡፡
በአለም ከሚፈጸሙት ጽንስ ማቋረጦች 1/3ኛው በህገወጥ መንገድ ነው፡፡
በየአመቱ ሀያ ሚሊዮን ህገወጥ ጽንስ ማቋረጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ይፈጸማል፡፡ 90 ሕገወጥ ጽንስ ማቋረጥ የሚተገበረው ባልለሙት አገራት ነው፡፡

Read 9860 times