Saturday, 02 November 2013 11:55

.....መታከምም መዳንም በሚችል በሽታ መሰቃየት... ..

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

የማህጸን በር የቅድመ ካንሰር ምርመራ አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እየተሰጠ ነው፡፡

የማህጸን በር ካንሰር ማለት ከማህጸኑ በር አካባቢ ያሉ ሴሎች ሲፈጠሩ ከነበራቸው ይዘት ወደ ቅድመ ካንሰርነት ተለውጠው በስተመጨረሻው ካንሰር ሲሆኑ ነው፡፡ 

አንዲት ሴት በማህጸን ካንሰር ለመያዝዋ እንደምልክት የሚሆኑት
የብልት መድማት፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የወር አበባ መፍሰስ፣
የወር አበባ ከተቁዋረጠ በሁዋላ በብልት በኩል ደም መፍሰስ፣
ሽታ ያለው ፈሳሽ ከማህጸን መፍሰስ፣
በወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ሕመም መሰማት አንዳንዶቹ ናቸው ፡፡
ከላይ ያነበባችሁት ስለማህጸን በር ካንሰር ከተለያዩ መረጃዎች ያገኘነውን ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጀመሩን በሚመለከት ወደሆስፒታሉ በማምራት የህክምና ባለሙያዎችን አነጋግረናል። በቀጥታ ስራውን ከሚሰሩት ሲስተር በትረወርቅ ብርሀኑ እንዲሁም ከዶ/ር ማርያማዊት አስፋውን ለዚህ አምድ ጋብዘናቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ከሲ/ር በትረወርቅ ብርሀኑ ያገኘነውን እናስነብባችሁ፡፡ መጀመሪያ ስለ ስራ ድርሻዋ ታብራራለች፡፡
.....እኔ ሲ/ር በትረወርቅ ብርሀኑ እባላለሁ፡፡ ከዛሬ ሁለት አመት ከአምስት ወር ጀምሮ የምሰራው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ የተዘዋወርኩባቸው የስራ ቦታዎችም በድንገተኛ፣ ተመላላሽና ነብሰጡር እናቶች ከሚታዩበት የሰራሁ ሲሆን ከአንድ አመት ወዲህ ግን በማህጸን ተመላላሽ ክፍል እየሰራሁ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ኃላፊ ነርስ ስሆን ከዛ በተረፈም ማንኛውንም ክፍሉን የሚመለከተውን ስራ እሰራለሁም አሰራለሁም፡፡
ጥ/ በማህጸን ክፍል ባለው የስራ ዘመንሽ ህመምተኞችን እንዴት ትገልጪያቸዋለሽ?
መ/ ታማሚዎች የሚመጡበት ሁኔታ እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡ የትኛው የማህጸን በሽታ ይበዛል የትኛው አይበዛም የሚለውን ለይቶ ማወቅ ባይቻልም ብዙዎቹ በማህጸን በር እና በማህጸን በር ካንሰር ያውም ደረጃው ከፍተኛ ከሆነ በሁዋላ ወደ ሆስፒታል ይመጣሉ፡፡ በቀላሉ መከላከልም መዳንም የሚችል ሕመም ሲያሰቃያቸው ይታያል፡፡ ሴቶቹ ለህክምና ሲመጡ ስቃያቸው እጅግ ያሳዝናል፡፡ በህመሙ የተያዙ ሴቶች ከሰው ጋር ቀርበው ለመቀመጥ እንኩዋን በማይችሉበት ሁኔታ በአሰከፊ ጠረን እየሸተቱ ከተበላሹ በሁዋላ ነው ወደ ሆስፒል የሚመጡት፡፡
ጥ/ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አሁን ምን እየተሰራ ነው?
መ/ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአሁኑ ወቅት የማህጸን በርን ቅድመ ካንሰር ምርመራ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በማስታወቂያ ቢነገርም፣ ሆስፒታሉ ውስጥ በየግድግዳው ላይ ቢለጠፍም እስከአሁን ድረስ አመርቂ በሆነ ሁኔታ ህብረተሰቡ እየተገለገለበት አይደለም፡፡ ማንኛዋም ሴት የቅድመ ካንሰር ምርመራ በምታደርግበት ጊዜ የካንሰሩን ምልክት የሚያሳይ ከሆነ በተሟላ ሁኔታ ሕክምናውን ለመስጠት ሆስፒታሉ ዝግጁ ነው፡፡
ጥ/ እስከአሁን ባለው አሰራር ምን ያህል ሴቶች በቀን ተጠቃሚ ይሆናሉ?
መ/ እስከአሁን ባብዛኛው ለምርመራው የሚቀርቡት ለሌላ የማህጸን ሕክምና መጥተው በተጨማሪ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ በሐኪም ሲታዘዝ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ከአሁን ቀደም በአሶሳ ያየነው አንድ ልምድ አለ፡፡ ከአዲስ አበባ በዚህ ስራ ላይ የተሰማራነው የህክምና ባለሙያዎች ምርመራውን ለማድረግ ወደ ስፍራው ስንሄድ ለምርመራ ቀርበው የነበሩ ሴቶች ወደ 105 /አንድ መቶ አምስት/ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ወደ አምስት የሚሆኑት ወደ ካንሰር የሚያመራ ምልክት ታይቶባቸው ሕክምናው ተደርጎላቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው ብለን ብንናገርም ወረቀት ብንለጥፍም ብዙ ሴቶች መቅረብ አልቻሉም፡፡ ሌላው ቢቀር ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ሁሉ አስተዋውቀናል፡፡ ነገር ግን ወደ ምርመራው መቅረብ አልቻሉም፡፡
ጥ/ ምን ይሆን ምክንያቱ?
መ/ ከመስሪያ ቤቱ አንዳንድ ሰራተኞች ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ...ተመርምሬ ካንሰር አለብሽ ከምባል ዝም ብዬ ብቀመጥ ይሻላል የሚል ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን ልክ ከአሁን ቀደም ኤችአይቪን በሚመለከት ተመርምሮ እራስን ማወቅ የሚለው ነገር ሲነገር ብዙዎች እራሳቸውን ከማወቅ ይልቅ ገሸሽ ብለው ችግሩን ማስተናገድን የመረጡበት ሁኔታ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በእርግጥ አሁን ከኤችአይቪ ኤይድስ ጋር በተያያዘ ሲታይ የነበረው ፍርሀትና ጥርጣሬ ተወግዶ ማንኛውም ሰው እራሱን ለማወቅ ከሚወስንበት ደረጃ ተደርሶአል፡፡
የማህጸን በር ካንሰርን አስቀድሞ ከማወቅ ጋር በተያያዘ የሚሰጠው ምክንያት ግን ያንን ጊዜ የሚያስታውሰን ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት መታከምና መዳን ሲቻል ነገር ግን ሕመሙ ስር እስኪሰድ ድረስ በመቆየት ሌላ ችግርን በራስ ላይ መጋበዝ አላዋቂነት ነው፡፡
በመቀጠል ማብራሪያ የምትሰጠን ዶ/ር ማርያማዊት አስፋው ነች፡፡ ዶ/ር ማርያማዊት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሶስተኛ አመት የማህጸንና ጽንስ ክፍል ትምህርት በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡ ለትምህርት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከመምጣትዋ አስቀድሞ የጠቅላላ ሐኪም ሆና በሊሙ ገነት ሆስፒታል ለሁለት አመት አገልግላለች፡፡ ዶ/ር ማርያማዊት ልምድዋን ለአንባቢ ታካፍላለች፡፡
ጥ/ ከማህጸን ካንሰር ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የነበረሽ ልምድ ምን ይመስላል?
መ/ ብዙ ጊዜ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ተይዘው ለሕክምና በሚመጡበት ጊዜ ሕክምናውን በጊዜው ባለማድረጋቸው ሕመሙ ወደሌላው የሰውነት አካላቸው ተሰራጭቶ ይገኝ ነበር። ካንሰሩ ወደ ሽንት ፊኛ ወይንም በአካባቢው ባሉ አካላት ላይ ተሰራጭቶ የሚገኝበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሚፈሳቸው አስከፊ ጠረን ያለው ሽታ ምክንያት ከማህበረሰቡ ተገልለው እንዲኖሩ የሚገደዱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ደም በጣም በሚፈሳቸው ጊዜ በቤተሰብም ይሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀላቅለው ቀደም ሲል ይሰሩት የነበረውን ስራ ለመስራት የሚቸገሩበት ሁኔታም ያጋጥማል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እራስን መጥላት የመሳሰለው ችግር ሁሉ ይኖራል፡፡ ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ማለትም ጉበት በመሳሰለው አካባቢ ስለሚሰራጭ የሰውነት መክሳት ሁሉ ከሚጠቀስ ችግር መካከል ነው፡፡ ስለዚህም በብዛት ይላኩ የነበረው ወደጨረር ሕክምና ነበር፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያለው ሕመም ብዙ ጊዜ በእድሜ በገፉ ሴቶች ላይ የሚከሰት ስለሚሆን ሌሎች የጤና እውክታዎችም ሊኖሩ ስለሚችሉ የጨረር ሕክምናውን መውሰድ የማይችሉበት ሁኔታም ያጋጥማል፡፡ አሁን ግን ምንም እንኩዋን በአብዛኛው ህብረተሰብ ተለምዶአል ባይባልም ሕመሙ ወደከፋ ሁኔታ ሳይለወጥ እና ሊድን በሚችልበት ጊዜ ሕክምና ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ በሆስፒታሉ የቅድመ ካንሰር ምርመራ አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው፡፡
ጥ/ ታካሚዎች በምን ሁኔታ ነው የሚቀርቡት?
መ/ ብዙ ጊዜ ታካሚዎች የሚመጡት ለሌላ የማህጸን ሕክምና ነው፡፡ በዚሁ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ሲነገራቸው ሁሉም ባይሆኑ እንኩዋን አንዳንዶ ሀሳቡን ተቀብለው አገልግሎቱን ተጠቃሚ የሚሆኑ አሉ፡፡ ታድያ ከሚታከሙት መካከል አልፎ አልፎ የካንሰሩ ምልክት በሚገኝት ጊዜ እንደአስፈላጊነቱ በመጠኑም ሆነ በቀዶ ህክምና ደረጃ አስፈላጊው ህክምና ይደረግላቸዋል፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በመጠኑ የተሻሻለ ነገር ቢታይም ነገር ግን አሁንም በአብዛኛው ህብረተሰቡጋ ደርሶ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ከሚያስችል ደረጃ ተደርሶአል ለማለት ገና ብዙ የማስተዋወቅ ስራ መሰራት አለበት፡፡
ጥ/ ለሌላ ሕክምና ከሚመጡት ሴቶች ውጪ በቀጥታ ሕክምናውን ፈልገው የሚመጡ አሉ?
መ/ ብዙ ናቸው ባይባልም አልፎ አልፎ በቀጥታ ለቅድመ ካንሰር ሕክምናው የሚመጡም አሉ፡፡ በሚመጡበት ጊዜ እንዴት እንዳወቁ ሲገልጹ ...ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰማን ...ወይንም ከመገናኛ ብዙሀን ሰማን የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡
ጥ/ ህብረተሰቡ አገልግሎቱ መኖሩን አውቆ ተጠቃሚ እንዲሆን ምን ማድረግ ይመከራል?
መ/ ስራውን በተለያየ መንገድ ማስተዋወቅ አንዱ ሲሆን በሆስፒታሉ ለተለያየ ሕክምና የሚመጡትን ሴቶች አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ መሆኑን እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልእክት ማስተላለፍ ከእኛ ከሰራተኞቹም ይጠበቃል... ደግሞም እያደረግነው ነው፡፡
ከምንም በላይ ግን ሴቶች ስለጤንነታቸው አስቀድመው እንዲያስቡ እና ከህመም በፊት ወደሕክምና ቀርበው ጤንታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ለእራሳቸውም ሆነ ለህብረተሰቡ ማስተማር ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

Read 4493 times