Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 09:08

አፕል ኩባንያ ትርፍ፤ ከኢትዮጵያ አመታዊ ምርት ይበልጣል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የአይፖድ፤ የአይፎን፤ የአይፓድ፤ የአይማክ ጌታ 
ሃብት ፈጣሪው ስቲቭ ጆብስ - የዘመናችን ሚዳስ - የነካውን ነገር ወደ ወርቅ የሚቀይር
የአፕል ኩባንያ ፈጠራ የሆነው አይፎን፤ በ2007 አጋማሽ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገበያ የቀረበው። አይፎን፤ ወዲያውኑ አለማቀፍ ዝና ከማግኘቱ የተነሳ፤ በግማሽ አመት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአይፎን ምርቶች ተሽጠዋል። ተወዳጅነቱ የተተኮሰው ግን በቀጣዩ አመት ነው - ከ11 ሚሊዮን በላይ አይፎኖች የተሸጡበት አመት። እንደተለመደው ገበያ የደራለት አፕል ኩባንያ፤ ተጨማሪ አቅም ያላቸውና የተሻሻሉ አይፎኖችን ለማምረት ጊዜ አልወሰደበትም።

እናም በ2009 እንደገና የአይፎን ገበያ በእጥፍ አደገ - 20ሚሊዮን አይፎኖች ተቸበቸቡ። በቀጣዩ አመት ደግሞ 40 ሚሊዮን አይፎን። ዘንድሮስ? አፕል በአመት ውስጥ 72 ሚ. አይፎኖችን በመሸጥ ገበያውን አስፍቷል።
በስቲቭ ጆብስ መሪነት፤ በ60ሺ ሰራተኞች፤ አይፖድና አይፎን በመሳሰሉ ምርጥ ፈጠራዎች አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያገኘው አፕል፤ የስኬት ጫፍ ላይ ደርሷል ሲባል፤ በቀጣዩ አመት እንደገና በተጨማሪ ስኬት ወደ ላይ ሲመነጠቅ የሚታይ አስገራሚ ኩባንያ ነው። ዘንድሮም እንደወትሮው፤ የእድገት ሪከርድ አስመዝግቧል - አመታዊ ሽያጩንና ትርፋነቱን በማስፋት። እናም የአፕል አመታዊ ትርፍ፤ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ አመታዊ ምርት የሚበልጥ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርት፤ በርካታ ሚሊዮን ሰዎች የተሰማሩበት የእርሻና የፋብሪካ ምርት ብቻ ሳይሆን፤ ትምህርትና ጤና፤ እንዲሁም የፖሊስና የፍርድቤት ስራ፤ የግድብና የመንገድ ግንባታም ሁሉ በገንዘብ ተሰልቶ ወደ 30 ቢ ዶላር ገደማ ይሆናል ተብሎ ይገመት የለ? ዘንድሮ የአፕል ትርፍ ደግሞ፤ ከ33ቢ. ዶላር በላይ አልፏል - ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው።
ከአርባ አመት በፊት በሶስት ወጣቶች የተመሰረተው አፕል፤ በኮምፒዩተር ምርት ከሚጠቀሱ ፈርቀዳጅ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው - በተለይም ማኪንቶሽ እና አይማክ በሚሉ ስያሜዎች በሚታወቁ የኮምፒዩተር ምርቶቹ። ኮምፒዩተሮችን ብቻ ሳይሆን፤ መሰረታዊ ፕሮግራሞችንና ሶፍትዌሮችንም ጭምር በማምረት፤ በአርአያነት ይጠቀሳል። ከነስሙም፤ “አፕል ኮምፒዩተርስ” ተብሎ ይጠራ አልነበር? በ2007 ነው ስያሜው የተቀየረው - “አፕል” ተባለ። ለምን?
አፕል፤ ከኮምፒዩተር ምርት በተጨማሪ፤ እነ አይፖድንና አይፎንን በመሳሰሉ ምርቶችም ዝነኛ ለመሆን በቅቷል። ከዚህም በተጨማሪ፤ በአስር አገራት ውስጥ ከ350 በላይ የሽያጭ ሱፐር ማርኬቶች ከፍቷል። በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ የሚያስገኙ የኢንተርኔት ገበያዎችን አስፋፍቷል። ለአራት ተከታታይ አመታትም፤ ብዙ አድናቂዎችን በማፍራት ወደር የለሽ ኩባንያ ተብሎ ተመርጧል።
አፕል እንደዛሬ ሳይሆን፤ አጀማመሩም ሆነ ታሪኩ በአስቸጋሪ ፈተናዎች የተከበበ ነው። አፕልን የመሰረቱት ሶስት ወጣቶች፤ በእጅ እየገጣጠሙ ለገበያ ያቀረቧቸውን ኮምፒዩተሮች ለመሸጥና ለማትረፍ ያደረጉት ጥረት እጅግ ፈታኝ ነበር። ለዚህም ነው ከሶስቱ መስራቾች መካከል አንዱ አንዱ ኩባንያውን ጥሎ ለመውጣት የወሰነው - የራሱን ድርሻ በ800 ዶላር ለቀሪዎቹ ሁለት ወጣቶች በመሸጥ። ያኔ በ800 ዶላር የተሸጠው የአክሲዮን ድርሻ ግን፤ ዛሬ የበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ዋጋ አለው። ሌላው ቀርቶ፤ ዘግይተው የአክሲዮን ድርሻ የገዙ በርካታ ሰዎችም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮነር ለመሆን ችለዋል። በአምስት አመታት ውስጥ ብቻ፤ ከአፕል ባለአክሲዮኖች መካከል 300ዎቹ ሚዮነር ሆነዋል።
በእጅ የተገጣጠሙ ኮምፒዩተሮችን ለገበያ በማቅረብ ቢዝነሱን ሀ ብሎ የጀመረው አፕል፤ በአስር አመታት ውስጥ ከኮምፒዩተር ፈጠራና ዲዛይን እስከ ፋብሪካ ድረስ ራሱን በማጠናከር በገበያው ውስጥ ገናና ሆኗል። ነገር ግን፤ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ገበያ፤ አልጋ ባልጋ አይደለም፤ ፉክክሩ በበርካታ ተወዳዳሪዎች እየተጧጧፈ ነበር። በዚያ ቀውጢ ጊዜ፤ አፕል ውስጥ ውዝግብ መነሳቱ ነው፤ ኩባንያውን ለከባድ አደጋ ያጋለጠው።
በኩባንያው ውስጥ ከቀሩት ሁለት ወጣት መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ስቲቭ ጆብስ፤ በኩባንያው አሰራር ደስተኛ አልነበረም። እንደቀድሞው ሳይሆን፤ የኩባንያውን አቅጣጫ የመምራት አቅሙ በሌሎች ሰዎች እየተሸረሸረ ነበር። የኩባንያው ባለአክሲዮኖች እየበዙ በመጡ ቁጥር፤ የኩባንያው አመራርም ከመስራቾቹ እጅ አምልጧል።
እንዲያም ሆኖ፤ ኩባንያው በኮምፒዩተር ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በተዛማጅ የፈጠራ ስራዎችም ገበያውን ማስፋት አለበት የሚል ሃሳብ የነበረው ስቲብ ጆብስ፤ በዚሁ ሃሳብ የኩባንያውን አቅጣጫ ለመቀየር መጣጣሩ አልቀረም። በአኒሜሽን የፊልም ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሙዚቃ ቴክኖሎጂ የተለያዩ ፈጠራዎችን በማፍለቅ መስራት አለብን በማለት በተደጋጋሚ እቅዶችን አቅርቧል። እቅዶቹ ግን ተቀባይነት አላገኙም። እንዲያውም፤ ወደፊት ሌላ እቅድ ይዞ ከመጣ፤ ተቀባይነት እንዳይኖረው ተወሰነበት። በ1985 ደግሞ፤ ከድርጅቱ ለቅቆ እንዲወጣ ተገደደ።
ስቲቭ ጆብስ ከአፕል ከለቀቀ በኋላ በመሰረተው ኩባንያ፤ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ሃብት ሲያፈራ፤ አፕል ግን በተቃራኒው ቀስ በቀስ በበርካታ ችግሮች ለመተብተብ ጊዜ አልወሰደበትም። ለዚህም ነው፤ ከ12 አመታት በኋላ፤ ስቲቭ ጆብስ ወደ አፕል እንዲመለስ ጥያቄ የቀረበለት። በ1997 ስቲቭ ጆብስ የአፕል ዋና ስራአስኪያጅ ከሆነ ወዲህ፤ ኩባንያው ያለማቋረጥ እያደገ፤ በትርፋማነትና በዝና ቀዳሚነት እየያዘ የመጣው። ከኮምፒዩተር ነክ ፈጠራዎችና ምርቶች በተጨማሪ፤ አዳዲስ የጀመራቸው የፈጠራ ውጤቶችና ምርቶቹም እጅግ ተወዳጅ ሆነውለታል - ከአይፖድ ጀምሮ።
አይፖድ
የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን አሰራርና የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ዘይቤ ወደ አዲስ አቅጣጫ እንደቀየረ የሚነገርለት የአፕል አይፖድ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገበያ የቀረበው በ2001 ነው - በያዝነው ወር አስረኛ አመቱን ደፍኗል። (ስቲቭ ጆብስ የአይፖድን አስረኛ አመት አላከበረም። በህመም የሞተው ከሁለት ወር በፊት በመስረም መጨረሻ ነው)። በመጀመሪያው አመት ወደ አራት መቶ ሺ ገደማ አይፖዶችን ለመሸጥ የቻለው አፕል፤ በቀጣዩ አመት ሽያጩን በእጥፍ በማሳደግ ከዘጠኝ መቶ ሺ በላይ እንዲደርስ አድርጓል።
ግን ገበያው ገና መሟሟቁ ነበር። በሶስተኛው አመት፤ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ አይፖዶች ከተቸበቸቡ በኋላ፤ አፕል አይፖዶቹን ይበልጥ እያሻሻለ፤ በዋጋም ከእጥፍ በላይ በቅናሽ እያቀረበ፤ ገበያውም እየጎረፈለት ሄደ። ከ22 ሚ. በላይ አይፖዶች ተቸብችበዋል በአራተኛው አመት። ቀጥሎም አርባ ሚሊዮን ገደማ። ከፍተኛው አመታዊ ሽያጭ በ2008 የተመዘገበው ነው - ከ54ሚ በላይ አይፖዶች የተሸጡበት አመት። የአይፖድ ምርት አስረኛ አመት ሰሞኑን በአፕል እስከተከበረበት ጊዜ ድረስ፤ ከ320 ሚሊዮን በላይ አይፖዶች ተሽጠዋል፤ ኩባንያውም የቢሊዮን ዶላሮች ትርፍ አግኝቷል።
አይፎን - አይፓድ
ከአይፖድ በመቀጠል፤ እንደገና የሞባይል ቴሌፎን አጠቃቀምን በእጅጉ በሚቀይር የአይፎን ምርት አለምን እያዳረሰ ነው አፕል - በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 150 ሚሊዮን አይፎኖችን በመሸጥ። በተራቀቀ የሞባይል ስልክ (Smart Phone) ዙሪያ፤ አፕል በሶስት አመታት ውስጥ አለማቀፍ ቀዳሚነትን ለማግኘት የቻለው፤ የበርካታ አመታት አንጋፋ የሞባይል ስልክ አምራቾችን በመብለጥ ነው። በዚህም አላቆመም።
አምና፤ አዲስ ፈጠራ ይዞ ብቅ ብሏል - አይፓድን። ደብተር የሚያካክሉ ናቸው። አቅማቸው ግን እንደኮምፒዩተር ነው። ፅሁፎችን ለማቀናበር ወይም የሂሳብና ሌሎች ሰንጠረዦችን ለማቀናበር፤ ምስሎችን ለማስተካከል፤ ቪዲዮ ለማየት፤ ኢንተርኔት ለመጠቀም... የሚያገለግሉ አነስተኛና ጠፍጣፋ መሳሪያዎች ናቸው አይፓዶች። ስፋታቸው 24 በ19 ሳንቲሜትር ገደማ ይሆናል።
ከአይፎንና ከተራቀቁ ሌሎች የሞባይል ስልኮች የሚበልጡ፤ ከላፕቶፕ ኮምፒዩተር ደግሞ አነስ ያሉ፤ ለአያያዝ የሚያመቹ አዲስ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው አይፓዶች - በተች ስክሪን የሚሰሩ። ገበያውስ? አፕል ኩባንያ፤ አይፖድና አይፎን በመሳሰሉ ምርጥ ስራዎቹ አማካኝነት ያፈራው ታአማኒነትና ዝና፤ ለዚህ ጊዜ በጣም ጠቅሞታል።
በመጀመሪያው ቀን ብቻ 300ሺ አይፓዶች የተሽጠዋል። በአመት ደግሞ 15 ሚሊዮን አይፓዶች።
ከሶስቱ የአፕል መስራች ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነውና የኋላ ኋላም ኩባንያውን ከውድቀት አንስቶ ለአለማቀፍ ድንቅ ስኬት ያበቃው ስቲቭ ጆብስ፤ ከ”ሚዳስ” ጋር ተመሳሳይ ነው ቢባል ማጋነን ይሆን? በጥንታዊያኑ ግሪኮች እምነትና አፈታሪክ ውስጥ፤ ሚዳስ ማለት በእጁ የነካውን ነገር ሁሉ ወደ ወርቅ የሚቀይር ሰው ነው - ሃብት ፈጣሪ ልትሉት ትችላላችሁ።
ስቲቭ ጆብስ፤ በአስደናቂ ችሎታውና ታታሪነቱ፤ ለማመን የሚያስቸግር የሃብት መጠን ፈጥሯል። በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችንም ሚሊዮነር አደርጓል። በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ደንበኞችም እርካታንና ደስታን ሰጥቷል። አፕል የውድቀት አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት፤ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 6 ዶላር ነበር። በስቲቭ ጆብስ ስኬታማ መሪነት የአፕል ትርፋማነት በእጥፍና በእጥፍ እያደገ ሲመጣ፤ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 300 ዶላር የደረሰበት ጊዜ ለማየት ተችሏል። ከ20 አመት በፊት በ20ሺ ዶላር የአክሲዮን ድርሻ የገዛ ሰው፤ ዛሬ ሚሊዮን ዶላር ይሆንለታል ማለት ነው።



 

Read 5225 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 09:15