Saturday, 09 November 2013 11:11

የከተማችን ቆነጃጅትና የወይባ ጢስ!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(15 votes)
  • የወይባ ጢስ የወሲብ ብቃትን ያሻሽላል -
  • የወይባ ጢስ ቤት ባለቤት ተፈጥሮአዊውን የማህፀን ፈሳሽ ስለሚያደርቀው ለኢንፌክሽን ያጋልጣል - የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት

             በወሎና አፋር አካባቢዎች በስፋት የተለመደ ነው፡፡ ለአካባቢው ነዋሪ ሴቶች ውብ ፊትና ጥርት ያለ ቆዳ ምስጢሩ እሱው ነው፡፡ ሴቶቹ ለውበታቸው፤ ለቆዳቸው አብዝተው ይጨነቃሉ፡፡ ወደእነዚህ አካባቢዎች ለሥራም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ብቅ የሚሉ ሁሉ በሴቶቹ ውበት መደነቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ከመደነቅ አልፈው የሴቶቹ ውበት ምስጢር የሆነውን የጢስ እንጨት ይዘው ወደመጡበት ይመለሳሉ፡፡ እንጨቱ በአካባቢው ወይባ፣ ደደሆ፣ ቆቆባና ምስሮች በሚሉ መጠሪያዎች ይታወቃል፡፡ የእንጨቱ ቀለም ወደ ቢጫነት የሚያደላና ዘይትማ ባህርይ ያለው ነው፡፡ እንደተለመዱት የማገዶ እንጨቶች ቦግ ብሎ የመንደድ ባህርይ የለውም። ዝግ እያለ የሚጤስና የጭሱ ሽታ ለአፍንጫ ጥሩ ስሜትን የሚሰጥ አይነት ነው፡፡ ሁሉም እንጨቶች እንደየአይነታቸው የሚሰጡት ጠቀሜታም የተለያየ ነው፡፡ ወይባ እና ቆቆባ የተባሉት የእንጨት አይነቶች ለቆዳ ጥራትና ውበት ተመራጭ ሲሆኑ ደደሆ ደግሞ ጢሱ የቅባትነት ባህርይ ስላለውና በሰውነት ላይ ስለሚጣበቅ ቆዳን በማሣመር የተለየ ውበትና ወዝ ያጐናጽፋል፡፡

ምስሮች የተባለው የእንጨት አይነት ደግሞ ለማህፀን በር ጥበት፣ አላስፈላጊ የሆነ የማህፀን ፈሳሾችን ለማስወገድ የሚጠቅም ከመሆኑም በላይ የወር አበባ ችግሮችን ለማስወገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቃሚዎችና የወይባ ጢስ አገልግሎት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በ80 ሣንቲሜትር ጥልቀት እየተቆፈረ በሚዘጋጀው የወይባ ጢስ ጉድጓድ ውስጥ እንደተጠቃሚዋ ምርጫና ፍላጐት የተዘጋጀው የወይባ እንጨት ይጨመርና ቀስ እያለ እንዲጨስ ይደረጋል፡፡ እንጨቱ በባህርይውም ቀስ እያለ ይጨሳል እንጂ አይነድም፡፡ ሴቶቹ እግራቸውን ግራና ቀኝ በጉድጓዱ ደፍ ላይ በማስቀመጥ ከጉድጓዱ የሚወጣውን ጭስ ይታጠኑታል፡፡ በወይባ ጢስ እጠና ወቅት ታጣኟ አናት ላይ ንፁህ ለጋ ቅቤ ይቀመጣል፡፡ ቅቤው ከጭሱ በሚወጣው ሙቀት እየቀለጠና በጭሱ በተከፋፈተው ገላዋ እየሰረገ ውስጧን ያርሰዋል፤ እንደ ጢስ ባለሙያዎቹ ገለፃ፡፡

የወይባ ጢስ ተጠቃሚዋ እንደምትፈልገው የጭስ አይነትና ሁኔታ ቆይታዋም እንደሚለያይ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህንን የወይባ ጢስ አገልግሎት ዛሬ ዛሬ የከተማችን ቆነጃጅትም በእጅጉ ተላምደውታል፡፡ “ባህላዊ የወይባ ጢስ ቤት” የሚል ታፔላ የለጠፉ በርካታ ጢስ ቤቶችም በራቸውን ለደንበኞቻቸው ክፍት አድርገው የሃያ አራት ሰዓት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በቦሌ፣ በሃያሁለት ማዞሪያ፣ በኮተቤ፣ በጉርድ ሾላ፣ በሣሚት፣ በአያት መንደር፣ በቦሌ መድሃኒያለም፣ በወሎ ሰፈርና ጐተራ አካባቢዎች እጅግ በርካታ ጢስ ቤቶች ተከፍተዋል። እነዚህን ባህላዊ የውበት መጠበቂያ የጢስ ቤቶች የሚጐበኙና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሴቶች ቁጥርም ዕለት ተዕለት እየጨመረ መምጣቱን፣ ወንዶቹም በልዩ ፕሮግራም የጢስ አገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ያነጋገርኳቸው የጢስ ቤቶች ባለሙያዎች ነግረውኛል፡፡ ሰሞኑን በቦሌ መድሃኒያለም አካባቢ ከሚገኙት በርካታ ባህላዊ የወይባ ጢስ ቤቶች መካከል “ዞብል ወይባ ጢስ” የተሰኘውን ቤት ጐብኝቼ ባለሙያዎቹንና ተጠቃሚዎቹን አነጋግሬ ነበር፡፡

ሜሮን ወደዚህ ባህላዊ ጢስ ቤት ከሚመላለሱ ደንበኞች መካከል ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ላለፉት 3 ዓመታት ዕለተ አርብን ሳታሰልስ ወደዚሁ የወይባ ጢስ ቤት ተመላልሳለች፡፡ ምን ትልቅ ጉዳይ ቢገጥማት አሊያም ምን ቢያማት ከዚህ ሣምንታዊ ፕሮግራሟን ተናጥባ አታውቅም፡፡ ለእሷ ከዚህ በላይ አስፈላጊና ወሳኝ የምትለው ጉዳይ የላትም፡፡ የወይባ ጢስን ጠቀሜታ ተናግራ አትጠግብም፡፡ ተራዋ እስኪደርስ በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ተቀምጠን ጥቂት አወጋን፡፡ “የወይባ ጢስ ሱስ ነው፡፡ ከምር እንደሱስ ይሆንብሻል፡፡ መጀመሪያ ወደዚህ የመጣሁት የወር አበባዬ ለወራት ሳይመጣ በመቅረቱ ምክንያት ነበር፡፡ እርግዝና አለመኖሩን በላብራቶሪ ምርመራ ባረጋግጥም የወር አበባዬ ለአራት ወራት ያህል ሳይመጣ ቀረ፡፡ ሁኔታው አሳሰበኝ፤ ጉዳዩን ለአንዲት ጓደኛዬ ሣማክራት ወይባ ጢስ ብትታጠኚ መፍትሔ ታገኛለሽ ብላ ወደዚህ ይዛኝ መጣች፤ መፍትሔ ይሆነኛል ብዬ ባላስብም ሃሳቧን ለመሙላት ተከትያት መጣሁ፡፡ “ውጤቱን ግን ማመን አልቻልኩም፤ ገና በመጀመሪያው ቀን አመሻሹን የወር አበባዬ መጣ።

ቀደም ሲል በወር አበባ መምጫ ወቅት የነበሩኝ ህመሞች ሁሉ አልነበሩም፡፡ በሁኔታው በጣም ተደሰትኩ፡፡ የወይባ ጢሱ የቀረ የወር አበባዬን እንዲመጣ ከማድረጉም ሌላ ጤናማና ደስ የሚል ወሲባዊ ህይወት እንዲኖረኝም አድርጓል፡፡ ስለዚህም ከወይባ ጢስ ጋር ረዘም ያለ ወዳጅነት መስርቼአለሁ፤ ላለፉት 3 ዓመታት የእረፍት ቀኔን ከመጀመሬ በፊት ወደዚህ ሥፍራ እየመጣሁ ምቾትና ውበቴን ስሸምት ቆይቻለሁ፤ ለእኔ በጣም ተስማምቶኛል፡፡” ተራዋ ደርሶ ስሟ ሲጠራ ጨዋታችን ተቋረጠ። የወይባ ጢሱ አስገኘልኝ በምትለው ጥቅምና በሰጣት መፍትሔ እጅግ ደስተኛ መሆኗን ወደጢስ አገልግሎት መስጫው ክፍል እየገባችም ነግራኛለች። በእንግዳ መቀበያው ክፍል ተቀምጠው ተራቸውን ከሚጠባበቁት ደንበኞች በርከት ያሉት በሜሮን ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ የወይባው ጢስ ለወር አበባ ችግሮቻቸው መፍትሔ እንዳስገኘላቸው የነገሩኝ ደንበኞች ብዙ ናቸው፡፡ የወይባ ጢስ ቤቱ ባለቤት ወ/ሮ ህሊና አበጋዝም፤ ይህንኑ የተጠቃሚዎቹን ሃሳብ ታጠናክረዋለች፡፡ “የወይባ ጢስ አገልግሎቱ ከትክክለኛው ሥፍራ በሚገኝ እውነተኛ የወይባ ጢስ እንጨት የሚሰጥ ከሆነ የወር አበባ ችግሮችን ያስወግዳል፡፡

የተዛባ የወር አበባ አመጣጥን ያስተካክላል፣ ለማህፀንና አካባቢው ህመም መፍትሔ ይሰጣል፣ የማህፀንን በር እንዲጠብ ያደርጋል፣ አላስፈላጊ የማህፀን ፈሳሾችን ጠራርጐ በማስወገድ ማህፀን ደረቅ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ “ይህ ደግሞ ወሲባዊ ንቃት እንዲጨምርና ሴቶቹ በወሲባዊ ተራክቦ ወቅት የተሟላ ደስታና እርካታ እንዲያገኙ፤ ወንዱም የተሟላ እርካታ ያለው ወሲብ እንዲፈጽም ያስችለዋል፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ ወንዶች ሴቶቻቸው የወይባ ጢስ እንዲጠቀሙ የሚያበረታቱት፡፡ ብዙ ጊዜ ወደዚህ የወይባ ጢስ ቤት ሚስቶቻቸውን እየያዙ የሚመጡ ወንዶች አሉ፡፡ ጠቀሜታውን ያውቁታልና ሚስቶቻቸውን ወደ እኛ ለማምጣት አይቦዝኑም፡፡” አለችኝ። ሚስቶቻቸውን (ጓደኞቻቸውን) ለማድረስና ለመውሰድ የሚመጡ ወንዶችም፤ በወ/ሮ ህሊና አባባል ይስማማሉ፡፡ ውጭ መኪናቸው ውስጥ ተቀምጠው ሚስቶቻቸውን ከሚጠባበቁ ወንዶች መካከል አቶ ልዑልሰገድ ታምሩ፤ የሁለት ልጆቻቸው እናት ከሆኑት ባለቤታቸው ጋር ለ10 ዓመታት በትዳር ቆይተዋል፡፡

ባለቤታቸው የወይባ ጢስ ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ ወዲህ “የወሲብ ፍላጐታቸው መጨመሩን ነግረውኛል፡፡ የጢስ አገልግሎቱ ስላለው ሣይንሳዊ ጠቀሜታ የማህፀንና የጽንስ ስፔሻሊስት ለሆኑት ለዶክተር ፍቃዱ ወሰንየለህ ጥያቄ አቅርቤላቸው ሲመልሱ፤ “የወይባ ጢስ እየተባለ በየአካባቢው የሚሰጠውን በእንጨት ጢስ የመታጠን አገልግሎት ሳይንሣዊ ጠቀሜታ ለመዘርዘር የእንጨቱ ወይም የጢሱ ኬሚካላዊ ምንነት በጥናት መታወቅና መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩ ጥናት የተደረገበት ባለመሆኑ ጢሱ ጠቀሜታ አለው የለውም ብሎ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን የወር አበባ ችግሮችን ያስወግዳል እየተባለ የሚነገረው ማንኛውም በሴቷ ተፈጥሮአዊ ሥርዓተ ዑደት ውስጥ ያሉ ነገሮች ከአዕምሮዋ ጋር የሚገናኙና አዕምሮዋ በተነገረው ነገር ላይ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ በመሆኑ፣ የወር አበባዋ እንደሚመጣ በማመኗ ብቻ ሊመጣ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ጭሱ በማህፀን ውስጥ ገብቶ የተዘጋ የወር አበባ መምጫን በመክፈት የወር አበባ እንዲፈስ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ “የማህፀን በር ያጠባል፣ የማህፀን ፈሳሾችን ጠራርጐ ያስወግዳል የተባለው ጉዳይም ሳይንሳዊ ድጋፍ የለውም፡፡ ተፈጥሮ በራሷ ጊዜ ያዘጋጀችውና በወሲባዊ ተራክቦ ወቅት የሴቷና የወንዱ ብልት እንደልብ እንዲጫወቱና ፍትጊያው የተለሳለሰ እንዲሁም በእርጥበት የተሞላ እንዲሆን የሚፈጠረውን አስፈላጊ ፈሳሽ ስለሚያደርቀው ተራክቦው ህመምና ቁስለት ያስከትላል፡፡ ይህ ደግሞ በሴቷም ሆነ በወንዱ ላይ ኢንፌክሽን እንዲፈጠርና የብልት መላላጥ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ ኢንፌክሽኑ በወቅቱ ታውቆ ተገቢው ሕክምና ካልተደረገለትም ለማህፀን በር ካንሰርና መሰል ከሆነ ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል። ስለዚህም የወይባ ጢስ የወሲብ ብቃትን ያሻሽላል እየተባለ ሴቶች ማህፀናቸውን እየከፈቱ በጢሱ መታጠናቸው ለሌሎች የጤና እክሎች አሣልፎ ይሰጣቸዋልና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል።

Read 12008 times