Saturday, 09 November 2013 12:32

ሞሪሺየስ በመልካም አስተዳደር ትመራለች፤ ሶማሊያ መጨረሻ ናት!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ከ52 የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ 33ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

ከ11 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ደግሞ በ8ኛ ላይ ተቀምጣለች

መልካም አስተዳደር ከ100%

  • ሞሪሺየስ - 80
  • ቦትስዋና - 78
  • ኬፕቨርዴ - 77
  • ሲሸልስ - 78
  • ደቡብ አፍሪካ - 71
  • ሶማሊያ - 8

የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የ2013 የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃን “Ibrahim Index of African Governance (IIAG)” ይፋ ያደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ በመልካም አስተዳደር ምርጥ ተብላ ከአፍሪካ በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠችው ሞሪሺየስ ስትሆን የመጨረሻዋ አገር ሶማሊያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከ52 የአፍሪካ አገራት 33ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የመልካም አስተዳደር ሁኔታ በአራት መስፈርቶች የገመገመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ ባለፉት 10 ዓመታት በሰው ሃብት ልማት ላይ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ገልፆ፤ በዋናነት በጤና እና በትምህርት መስኮች ለውጥ መመዝገቡን አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመልካም አስተዳደር ከ52 የአፍሪካ አገራት 33ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ከ100 ነጥብ 47.6 በማግኘት ሲሆን የአፍሪካ አማካይ ነጥብ 51.6 ነው ይላል ፋውንዴሽኑ፡፡

ኢትዮጵያ ከ11 የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ተወዳድራም በ8ኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠች የጠቆመው የፋውንዴሽኑ መረጃ፤ በዚህ የአፍሪካ ቀጠናም ኢትዮጵያ የሚጠበቀውን የ47.9 አማካይ ነጥብ አለማግኘቷን አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት በመልካም አስተዳደር ያላትን ደረጃ ያሻሻለችው በ5.1 ብቻ ነው ይላል፤ መረጃው፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን “ኢብራሂም ኢንዴክስ ኦፍ አፍሪካን ጋቨርናንስ” ሪፖርት፤ የአፍሪካ አገራት በአጠቃላይ በመልካም አስተዳደር መሻሻል እንዳሳዩ ጠቁሟል፡፡ አገራቱ የተመዘኑት የመልካም አስተዳደር መገለጫ ናቸው ተብለው በሚታወቁት የዜጎች ደህንነት እና የህግ የበላይነት፣ ህዝባዊ ተሳትፎ እና ሰብዓዊ መብት አከባበር እንዲሁም ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎችና በሰው ሃብት ልማት እንደሆነ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከ1 ቢሊዮን በላይ ከሚገመተው የአፍሪካ ህዝብ ውስጥ 94 በመቶ ያህሉ የሚኖሩት በመልካም አስተዳደር መሻሻል ባሳዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እንደሆኑ ታውቋል። ሆኖም በተለይ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ በዲሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብት አከባበር የሚታየው ድክመት፣ ሁሉን ነገር ወደኋላ እየጎተተ ነው ተብሏል፡፡ በመልካም አስተዳደር በአፍሪካ ምርጥ ተብላ በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠችው ሞሪሽዬስ ስትሆን ቦትስዋናና ኬፕ ቨርዴ፤ ሲሸልስ እና ደቡብ አፍሪካ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ወስደዋል፡፡

ባለፉት 13 ዓመታት 52 የአፍሪካ አገራት በጥቅሉ በመልካም አስተዳደር መሻሻል እንዳሳዩ የሚገልፀው ሪፖርቱ፤ በተለይ ጠንካራ መሻሻል የታየው በሰው ሃብት ልማት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ በኢኮኖሚ መስክ ዘላቂ ዕድሎች መፈጠራቸው በመላው አህጉሪቱ የሚታይ አበረታች ክስተት እንደሆነም ይገልፃል። በመላው አፍሪካ ዝቅተኛ መሻሻል እየታየ ያለው በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና በህግ የበላይነት ዙሪያ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ እነዚህ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአሳሳቢ ሁኔታ እያሽቆለቁሉ ናቸው ሲል አስጠንቅቋል፡፡ በህግ የበላይነት ያለው የመንግስታት አፈፃፀም በየጊዜው እየወረደ መምጣቱን በመግለፅም የተሻሉ የሚባሉት ከ54 አገራት 20ዎቹ ብቻ እንደሆኑ ሪፖርቱ ጠቅሷል። አፍሪካ የዜጎቿን ደህንነት በመጠበቅ በኩል ምቹ እንዳልሆነችም ይገልፃል፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የ2013 የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ ይፋ በተደረገበት ወቅት ዶክተር ሞ ኢብራሂም ባደረጉት ንግግር፤ ሽልማቱ ለላቀ የአመራር ብቃት የሚሰጥ ክብር እንጂ መጦርያ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ “ዛሬ አፍሪካ ለራሷ ችግሮች በቂ መፍትሔ እንዳላት እምነቴ ነው” ብለዋል።

“አፍሪካ ፀለምተኛም ሆነ ተስፈኛ መሆኗን ማሰብ ለአህጉሪቷ ዘመናዊ የእድገት እና የለውጥ ዘመን የሚያመጡት አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡ አሁን ዘመኑ የአፍሪካ እውነታን የምንጋፈጥበት ነው፡፡ አህጉራችንን ፊት ለፊት ልንመለከታት ይገባል፡፡ ስኬቶቿን ማድነቅ ተገቢ ነው፤ ጎን ለጎን ግን የወደፊት ፈተናዎቿን ተገንዝቦ ለውጥ በሚያመጣ አቅጣጫ መጓዝ ይገባል” በማለት ዶክተሩ ለአፍሪካ መሪዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በአፍሪካ በብሔራዊ ፀጥታና ደህንነት በኩል መሻሻል እየታየ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ አገራት በአዋሳኝ ድንበሮቻቸው እሰጥ አገባ እና ግጭት መፍጠራቸው እየቀረ መምጣቱ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ለውጥ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ከአፍሪካ ህዝብ ሲሶው ከ25 ዓመት ዕድሜ በታች እንደሆነ በማመልከትም የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ እና በህግ የበላይነት በመገዛት ረገድ አገራት መዳከማቸው በውስጥ ችግሮች የሚታመሱበትን ዕድል ያሰፋዋል ሲል አስጠንቅቋል፡፡ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከ1-8 ባለው ደረጃ ላለፉት 10 ዓመታት መቆየት የቻሉት አገራት፡- ሞሪሽዬስ፣ ቦትስዋና ፤ ኬፕ ቨርዴ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሸልስ፣ ናሚቢያ፣ ቱኒዚያ እና ጋና ናቸው፡፡

ላይቤሪያ፣ አንጐላ፣ ሴራሊዮን፣ ሩዋንዳና ብሩንዲ በግጭት ሲታመሱ ከቆዩበት የመንግስት አስተዳደር ከተላቀቁ በኋላ ባለፉት 10 ዓመታት በመልካም አስተዳደር ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩ የአፍሪካ አገራት መሆናቸውንም ይገልፃል፡፡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን የመሪነት ደረጃ የያዙት አምስት አገራት በመልካም አስተዳደር ከሚሰጠው መቶ ነጥብ ሞሪሽዬስ 83፤ ቦትስዋና 78፤ ኬፕቨርዴ 77፤ ሲሸልስ 75 እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ 71 ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡ በመጨረሻው ደረጃ ላይ የምትገኘው ሶማሊያ ከ100 ያገኘችው ስምንት ነጥብ ብቻ ነው፡፡ በአራቱ የመልካም አስተዳደር መለኪያዎች የሁሉም አፍሪካ አገራት አማካይ ነጥብ 51.6 ከመቶ ነው። የሰው ሃብት ልማት 52፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎች 45፤ በሰብዓዊ መብት 35፤ በዜጐች ደህንነት እና በህግ የበላይነት 20 ነው፡፡ አፍሪካን በአምስት ዞን ከፍለን በመልካም አስተዳደር የተሰጣቸውን ደረጃ ብንመለከት ደቡባዊ የአፍሪካ ቀጠና 59.2 ከመቶ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ሰሜናዊ አፍሪካ 55 ከመቶ፤ ምስራቅ አፍሪካ 52.5 ከመቶ፤ መካከለኛው አፍሪካ 52.5 ከመቶ እንዲሁም መካከለኛው አፍሪካ 40.1 ከመቶ በማስመዝገብ ከሁለተኛ እስከ መጨረሻ ያሉትን ደረጃዎች አግኝተዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር እጦት በመዳከር ላይ እንደሆኑ የተጠቀሱት ደግሞ ዚምባቡዌ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐና ሶማሊያ ናቸው። በሰብዓዊ መብት አከባበር፣ ሃሳብን በመግለጽ ነፃነት፣ በአስከፊ ወንጀሎች፣ በማህበራዊ ቀውሶች እና አለመረጋጋት፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በአገር ውስጥ የእርስበርስ ግጭቶች፤በአወዛጋቢ የስልጣን ሽግግሮች፣ በባንኮች ግልጽ አሰራር እጦት፣ በዜጐች እና በሠራተኞች መብት አከባበር የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የአፍሪካ አገራት በዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንዳይሰሩ ፈተና ሆነው መጋረጣቸውንም ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት የ7 ዓመታት ጉዞ ዶክተር ሞ ኢብራሂም የ67 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ የሱዳንና የእንግሊዝ ጥምር ዜግነት ያላቸው ባለሃብት ናቸው፡፡ ሞ ኢብራሂም፤ በግል ጥረታቸው የቢሊዬነርነት ደረጃ ላይ የደረሱ ስራ ፈጣሪ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ያላቸው ሃብት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ፎርብስ መፅሄት ይጠቁማል፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ በኮሙኒኬሽን ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት፤ በአፍሪካ “ሴልቴል” የተባለ የመጀመርያውን የግል የሞባይል ቀፎ አምራች ኩባንያ የመሰረቱት ሲሆን በ23 የአፍሪካ አገራትና በመካከለኛው ምስራቅ ሰፊ ገበያ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ በ2005 እ.ኤ.አ ይህን ኩባንያቸውን በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽንን በማቋቋም በአፍሪካ አገራት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ፤ የሞ ኢብራሂም የመልካም አስተዳደር ሽልማትን በመስጠት፤ የአፍሪካ አገራትን አመታዊ የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ደረጃ በማውጣት እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ፎረም በመምራት ይንቀሳቀሳል፡፡ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመልካም አስተዳደር ለሚያሳዩት የላቀ ብቃት የሚበረከተው የሞ ኢብራሂም ሽልማት የተጀመረው የዛሬ 7 ዓመት ገደማ ነው፡፡ ሽልማቱ በአፍሪካ በስልጣን ዘመናቸው ለአገራቸው እና በአጠቃላይ ለአህጉሪቱ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ እና የለውጥ ተምሳሌት ለሆኑ የቀድሞ መሪዎች እውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡ ሽልማቱ ገለልተኛ እና ታዋቂ በሆኑ የአፍሪካ ምሁራንና ፖለቲከኞች የተዋቀረ ኮሚቴ በሚያካሂደው ምርጫ መሠረት የሚሰጥ ሲሆን በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ሁለት የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎችም ይገኙበታል፡፡ የኢብራሂም ሽልማት የሚሰጠው በአገራቸው የልማት ጉዞ የላቀ ሚና ለተጫወቱ፣ ህዝቦቻቸውን ከድህነት አረንቋ በማውጣት በዕድገት እና ለውጥ ጐዳና ለተጓዙ፣ ለተሻለ ህይወት እና ብልጽግና የሚያበቃ አመራር ለሰጡ፤ በአህጉር ደረጃ በተምሳሌትነት የሚታይ ብቁ አመራር ላሳዩ የአፍሪካ መሪዎች ብቻ ነው፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊዎች፤ በመንግስት አመራር ላይ ሳሉ የነበራቸውን ብቁ የአመራርነት ሚና ከስልጣናቸው ወርደውም እንዲገፉበት እና ያካበቱትን ልምድ እንዲሰሩበት ያበረታታል፡፡

የሞ ኢብራሂም ሽልማት የሚሰጠው፤ በአገሩ የመንግስት ስርዓት ከፍተኛው ስልጣን ላይ ላገለገለ፤ ከስልጣን ከወረደ ቢያንስ 3 ዓመት ላለፈው፣ በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመመረጥ አገሩን ሲመራ ለቆየ፤ የአገሩን ህገመንግስት አክብሮ በአግባቡ የስልጣን ጊዜውን ላጠናቀቀ እና በስልጣን ቆይታው እንደተምሳሌት ለመታየት የሚያስችል የመሪነት ብቃት እንደነበረው ለተረጋገጠለት መሪ ብቻ ነው፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ ሆኖ ለሚመረጥ መሪ የሚበረከትለት የገንዘብ ሽልማት በዓለም በተመሳሳይ ዘርፍ ከሚሰጠው ከፍተኛው ነው፡፡ አሸናፊው አፍሪካዊ መሪ በ10 ዓመታት ውስጥ 5 ሚሊዮን ዶላር ተከፋፍሎ ይሰጠዋል - በየዓመቱ 500ሺ ዶላር ገደማ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም በህይወት ዘመን ቆይታው በየዓመቱ 200ሺ ዶላር የሚሰጠው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ተሸላሚው በሚያቀርበው የበጐ አድራጐት ፕሮጀክት መሰረት፤ 200ሺ ዶላር ዓመታዊ በጀት ይፈቀድለታል።

የሞ ኢብራሂም ሽልማት የመጀመሪያው አሸናፊ የሞዛምቢኩ ፕሬዚዳንት ጆአኪም ቺሳኖ ነበሩ - በ2007 ዓ.ም፡፡ በቀጣዩ ደግሞ የቦትስዋናው ፕሬዚዳንት ሬስተስ ሁለተኛው ተሸላሚ ሆነዋል። ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ግን ለሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊነት የበቃ አፍሪካዊ መሪ ሳይገኝ ቀረ፡፡ በ2011 ዓ.ም የኬፕ ቨርዴው ፕሬዚዳንት ፔድሮ ፔሬስ፤ ሶስተኛው የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ ለመሆን ሲበቁ፤ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በዚያው ዓመት የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ልዩ የክብር ሽልማትን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም የሞ ኢብራሂም ሽልማትን ያሸነፈ አፍሪካዊ መሪ ለሶስተኛ ጊዜ ሳይገኝ የቀረ ሲሆን ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ለዚሁ ክብር የበቃ መሪ አልተገኘም፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት የመልካም አስተዳደር ዓመታዊ ደረጃ ሪፖርትን ማዘጋጀት የተጀመረው በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የቴክኒክ ድጋፍ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመላው አፍሪካ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በሚደረግ ትብብር ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡

ብዙዎቹ አሃዛዊ መረጃዎች ከአፍሪካ ህዝብ በተለያየ መንገድ (ድምፅ እና አስተያየት) የሚሰበሰቡ እንጂ የየአገራቱ መንግስታት የሚያሰራጩትን ፖሊሲ በመንተራስ የሚሰሩ አይደሉም፡፡ የሞ ኢብራሂም ሽልማት በአፍሪካ አገራት ላለው የመልካም አስተዳደር ስርዓት መዳበር ከሚሰጠው እውቅና ባሻገር በስልጣን ዘመናቸው የላቀ ሚና የነበራቸው የአፍሪካ መሪዎች ከሙስና በፀዳ መንገድ መልካም ስራቸውን እንዲቀጥሉ በማበረታት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ መሪዎች የየአገራቸው ህገመንግስት በሚፈቅደው መሠረት፤ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ለማነሳሳት፣ በብቁ መሪነታቸው ሲያበረክቱ የቆዩትን አስተዋጽኦ በአገራቸውና በአህጉር ደረጃ በመቀጠል ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ለማድረግ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ሞ ኢብራሂም፤ ዓመታዊውን የመልካም አስተዳደር ሪፖርት “ከአፍሪካ ፊት የቆመ መስታወት ነው” ሲሉ ይገልፁታል፡፡

Read 5317 times