Monday, 18 November 2013 11:12

ኢትዮጵያ ያቀደችው ይሳካላት ይሆን?

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

           ገና በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜዋ የስምንት ልጆች እናት መሆኗ ሁሌም ያበሣጫታል፡፡ በላይ በላይ እያከታተለች የምትወልዳቸውን ሕፃናት በአግባቡ ተንከባክቦ ማሣደግ ህልም ሆኖባታል፡፡ ባለቤቷ ችግሯን ሊጋራትና ሊደግፋት ፈፅሞ አይፈልግም፡፡ ይልቁንም መተዳደሪያቸው የሆነውን የእርሻ ሥራ ለመሥራት ከቤት በሚወጣበት ጊዜ ሁሉ ባለቤቱ እንድትከተለውና አረሙንም፣ ጉልጓሎውንም፣ ሰብል ስብሰባውንም እንድታግዘው ይፈልጋል፡፡ 
በሆዷና በጀርባዋ ልጆቿን ተሸክማ ማሣው ላይ ደፋ ቀና ስትል ውላ ትመለሳለች፡፡ ከዓመት ዓመት በሽታ እየተጫናትና አቅሟ እየደከመ መምጣቱም ይታወቃታል፡፡ እርግዝናና ወሊድ ተባብረው ጉልበቷን ነጥቀዋታል፡፡ ግን አማራጭ የላትም። ፈጣሪ በቃሽ እስኪላትና ወሊድ የምታቆምበት ተፈጥሯዊ ጊዜዋ እስኪደርስ በየዓመቱ መውለዷ እጣ ፈንታዋ እንደሆነ ታስባለች፡፡ ከዚህ ሥቃይና ችግር ሊገላግላት የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ አምና ተቀብላለች፡፡ ሴቶች ሳይፈልጉ ልጅ መውለድ እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው መድሃኒት መኖሩን የወሬ ወሬ ብትሰማም፣ ነገሩን አምኖ መቀበሉ አልሆነላትም፡፡ የምትኖርበት ገጠራማው የአፈርደባ ቀበሌ፣ ለትራንስፖርት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ህክምናም ሆነ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን እንደልባቸው ለማግኘት አልታደሉም፡፡ በሐረሪ ክልል ሶፌ ወረዳ አፈርደባ ቀበሌ ውስጥ ያገኘኋት ይህቺው የስምንት ልጆች እናት፣ ትዳር ከመሰረተችበት የአስራ ስድስት ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ በየአመቱ እርግዝናና ወሊድን ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡

ባለቤቷ አብዱራህማን ሠይድ፣ የልጆቹ ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረና ኑሮ እየከበደው መምጣቱ ለአፍታም አሣስቦት አያውቅም፡፡ በሰበብ አስባቡ ከሚከሰተው ሞት ተርፈው ለፍሬ የሚበቁት ጥቂቶቹ ናቸውና የልጆቹን ቁጥር በየዓመቱ ለመጨመር እቅድ አለው፡፡ የባለቤቱ በእርግዝናና በወሊድ መጐዳት ለእሱ ትዝ አይለውም። ለሥራ ጉዳይ ወደ አካባቢው በሄድኩበት አንድ አጋጣሚ አግኝቼ ያነጋገርኳት ይህችው ሴት፣ ስለ ወሊድ መከላከያ በግልፅ አስረድቶ እንድትጠቀም ያበረታታት አንድም ሰው አለመኖሩን ነግራኛለች፡፡ በአካባቢያቸው ሴቶች በቡድን በቡድን እየተደራጁ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበትና የሚመክሩበት ሁኔታ እንዳለ ብትሰማም እሷ ወደዚህ ስብሰባና ውይይት እንድትሄድ ባሏ አይፈቅድላትም። እሷ ብቻ ሳትሆን ብዙዎቹ የአካባቢዋ ሴቶች የዚህ ስብሰባና ውይይት ተካፋዮች አይደሉም። እሷንና የእሷ መሰል እድል ያላቸውን ሴቶች ቤት ለቤት በሚደረግ አሠሣ በማግኘት ስለ ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ስለ ቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ፣ ስለ ህፃናት አስተዳደግና መሰል የጤና አገልግሎቶች ለማስተማርና ህብረተሰቡን ለመለወጥ የሚደረግ አንዳችም እንቅስቃሴ አለመኖሩንም ነግራኛለች። በአካባቢው የጤና ኬላና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ስለመኖራቸው እንኳን አታውቅም። የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞቹም ያለ ፍላጐቷ በየዓመቱ የአዳዲስ ህፃናት እናት ለመሆን የተፈረደባት ሴት መኖሯን አያውቁም፡፡
የዓለም አገራት እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ለማሳካት ቃል ከገቡት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል አንዱ የሆነው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአገራችንም መሻሻሎችን እያሣየ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ከነበረበት 15 በመቶ በ2011 ዓ.ም 29 በመቶ የደረሰ ሲሆን በተያዘለት የጊዜ ገደብ 66 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙ እየተነገረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ፈፅሞ የማያውቁ ሚሊዮኖች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በዘርፉ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ34ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ሰልጥነው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሰማሩ ቢደረግም የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች የማይደርሱባቸውና ዛሬም ሳይፈልጉ በየዓመቱ የሚወልዱ እናቶች በርካቶች ናቸው፡፡
ባለሙያዎች ህብረተሰቡን ለማዳረስ እንዲሁም አስተማማኝና በጤናቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትል የማይችል የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመስጠት አሁንም የአቅም ውስንነት ችግር አለባቸው፡፡ የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው ምን አይነት ሴቶች እንደሆኑ፣ መጠቀም የሚገባቸው የትኛውን አይነት የእርግዝና መቆጣጠሪያ ዘዴ እንደሆነ ግልፅ ማብራሪያ በማግኘት ረገድ ችግር እንዳለባቸው ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ፡፡
ሰሞኑን በUSAID የሚደገፈውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለማየት ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተጉዤ ነበር፡፡ አካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት እንደ ልብ የሚገኝበት እንደመሆኑ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉና ሌሎች ጤና ተቋማት የሚመጡ ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን የከተማው አስተዳደር ምክትል ጤና ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ውድነሽ ብሩ ይናገራሉ። በአካባቢው አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ለአምስት መቶ ነዋሪዎች ተመድቦ ይሠራል፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር እንደሆነና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ህብረተሰቡ ውስጥ በመግባት በአግባቡ ለማስተማርና የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት እንቅፋት እንደሚሆን በሥፍራው ያገኘናቸው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የተደረገው የሥነ ህዝብ ጤና ጥናት እንደሚያመለክተው፣ 29 በመቶ የሚሆኑት በመውለጃ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች፣ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የቻሉ ሲሆን ይሄም እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም ከነበረው 15 በመቶ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል 25 በመቶ ያህሉ በመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መጠቀም ቢፈልጉም በተለያዩ ምክንያቶች ዕድሉን ለማግኘት እንዳልቻሉ ይኸው ጥናት ይጠቁማል፡፡
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት ሴቶች መካከልም አብዛኛዎቹ የአጭር ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ይህንን ለማሻሻልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የተለየ ትኩረት በመስጠት፣ ሴቶች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊ ቅስቀሣ ያደርጋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በክንድ ሥር የሚቀበር የወሊድ መከላከያ፣ በ2010 ደግሞ ሉፕ የተባለውን የወሊድ መከላከያ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በስፋት ለማዳረስ ተንቀሳቅሷል፡፡
በጤናው ዘርፍ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ከሆኑት መካከል ያልተሟላ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ፍላጐትን ማሟላት አንዱ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋኑን 66 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዟል፡፡ ሆኖም በምዕተ ዓመቱ ይደረስበታል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው ቁጥር ላይ መድረስ እንደማይቻልና አገሪቱ በዚህ ዘርፍ የተሳካ ዕድገት አለማስመዝገቧ ይነገራል፡፡ መንግስት ለቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ግብአት ለማሟላት የሚያስችል በጀት መድቦ መንቀሳቀስ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ በፊት አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው በአጋር ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ ነበር፡፡
መንግስት እንቅስቃሴ በጀመረበት ዓመት፣ ከአገር ውስጥ ገቢ 910.000 ዶላር፣ ከጋራ ቋት ደግሞ 12 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን ይህም በየዓመቱ እየጨመረ በመሄድ ክልሎችም ለዚሁ አገልግሎት ከራሳቸው በጀት መመደብ ጀምረዋል፡፡
ለዚህ ዕቅድ እውን መሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች፣ የጐሣ መሪዎች፣ ማህበራት፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች ያልተቋረጠ ድጋፍና ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ባለፈው ማክሰኞ ተጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው 3ኛው አለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ጉባኤ ላይ ተገልጿል፡፡ “የተሟላ ምርጫ የተሟላ አቅርቦት” በሚል መሪ ቃል፣ ለአራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ዓለም አቀፋዊ ጉባዔ ላይ ከ3ሺ በላይ ተሳታፊዎች የተካፈሉበት ሲሆን ከ100 በላይ የጥናት ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጐባቸዋል። “አገሪቱ በዘርፉ በምዕተ ዓመቱ ልታሳካው ያቀደችውን ማሳካት ይቻላት ይሆን?” የሚለው ጉዳይ ግን የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

Read 2543 times